የብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽሕፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ በዓል አስመልክተው ለመላው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን
ሞተ ወኬዶ ለሞት
ለእለ ውስተ መቃብር
ወሀበ ሕይወተ ዘለዓለም ዕረፍተ

“ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሳ ሞቶ ሞትን አጠፋው፣ በመቃብር ለአሉም የዘላለም ዕረፍት የሚሆን ሕይወትን ሰጠ”። ይህ ቃል በዕለተ ትንሳኤ የኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ምእመናን በያሉበት ቤተክርስቲያን ወንድ፣ ሴት፣ ህፃን፣ ሽማግሌ ሳይለይ በአንድነት የሚዘምሩት የደስታ /የምስራች/ ቃል ነው፡፡

ትንሳኤ የሚለው ቃል በሕዝበ ክርስቲየኑ ዘንድ ልዩ ትርጉምና ስሜት አለው ምክንያቱ ደግሞ ከበዓላት ሁሉ የተለየ የአከባበር ሥርዓትና መልክ ስላለው ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ፋሲካ ይባላል፣ ፋሲካ ማለት ደስታ /ሐሴት/ ማለት ነው ስለሆነም ይህ ዕለት ጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም የመጣበትን ተግባር በድል አድራጊነት የፈፀመበት ዕለት ስለሆነ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በደስታ ታከብራለች፡፡

ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም

እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሳ፣ በኋላውም ጠላቶቹን ገደለ ሲል ነብዬ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት እንደተናገረ አይሁድ በቅንዓት ከሰቀሉት በኋላ እንደሚነሳ ህሊናቸው ይረዳ ስለነበረ ወደ ጲላጦስ ሔደው መቃብሩን በፅኑ ቁልፍ እንዲያስቆልፍ ሀሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ነገር ግን አምላካችን ከነሱ ሀሳብ በላይ በሆነ መንገድ በግርማ መለኮት ተነስቷል ፤ እሱ ራሱ የሰውን ልጅ ይገድሉታል፣ ይሰቅሉታል፣ በሶስተኛው ቀን ይነሳል እያለ ለደቀ መዝሙራቱ ያስተምራቸው ነበር ፤ በዚህ መልክ ጌታ በሥልጣኑ ተነሳ፡፡

በሌላ መንገድ ይህ በዓል የነፃነት በዓል ይባላል ፤የአንድ ሀገር የነፃነት ቀን በዓል በታላቅ ሥነ ሥርዓት ይከበራል ፤ መላው የሰው የሰው ዘር ሥጋዊ ነፃነት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ነፃነትና ዘላለማዊ የሆነ ፍፁም ህይወት ያገኘበት በመሆኑ በበለጠና ከፍ ባለ ልዕልና ሊከበር ይገባዋል፡፡ ምክንየቱም ከዛሬይቱ ዕለት በፊት የነበሩት የሰው ልጆች በሰይጣን ባርነት ውስጥ ግዞተኛ ሆነው በሞትና ፍርሀት ውስጥ ይኑሩ ነበርና ነው፡፡ ለ5500 ዘመን ነፃነታቸውን አጥተው የነበሩ ነፍሳት አምላካችን ራሱ ትንሳኤም ሕይወትም እኔ ነኝ ብሎ ባስተማረው መሰረት የሰው ልጅ የትንሳሌ ሕይወት በጌታ ትንሳኤ ተረጋግጧል፡፡ /ዮሐ11÷25/

ስለሆነም የሰው ልጆች ሁሉ ይህንን ሰይጣን የተሸነፈበትን፣ ሰላም የነገሰበትን፣ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጸብ ግድግዳ የፈረሰበት ፣ በመስቀሉ ሰላም የታወጀበት ዕለትም ነው። /ኤፌ 2÷14/

በዓሉን ስናከብር በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ችግር ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንን መርዳት ክርስቲየናዊ ግዴታችን ስለሆነ የአቅማችንን ስናግዝ ነው የትንሳኤው በዓል ትርጉም ሊኖረው የሚችለው፡፡

በተለይም አባቶቻችን በደምና በአጥንት በሀይማኖትና በታሪክ በነፃነት እንድንኖርባት መስዋዕትነት በመክፈል ያስረከቡንን ሃገራችንን እኛም በተራችን በተለያዩ አካባቢዎች በአሁኑ ሰዓት የሚታዩትን ከኢትዮጵያዊያን ባህል ውጭ የሆኑ መፈናቀሎችን ምእመናንና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በመተባበርና የችግሩን መንስኤ ከስሩ በማንጠፍ ሰላሟ የበዛ ፣ያልተበረዘና ያልተከለሰ ዕሴቷን የጠበቀች ታላቋን ኢትዮጵያ ለቀጣዩ ትውልድ እንድናስረክብ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ።

በመጨረሻም የፍቅር ባለቤት የሰላም አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ሀገራችንን በቸርነቱ ይጠብቅልን ለሕዝቦቿም ሰላሙን ፍቅሩን አንድነቱን ይስጥልን በዓሉንም የመተሳሰብ የአንድነት የፍቅር ያድርግልን።