የተወገዙት በዕጩነት እንዳይቀርቡ ቤተ ክርስቲያን የምትቃወምባቸው መሠረታዊ ምክንያቶች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦት ፳፻፲፭ ዓ.ም በነበረው የርክበ ካህናት መደበኛ ጉባኤው ዘጠኝ አዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙ ይታወቃል። አስመራጭ ኮሚቴውም አዲስ ኤጲስ ቆጶሳት በሚመደብባቸው ዘጠኝ አህጉረ ስብከት ተሿሚዎችን በመምረጥ የመጨረሻዎቹን ፲፰ ዕጩዎችን በመለየት አቅርቦ ዘጠኙ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠው ለሹመት በመዘጋጀት ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ ዕጩዎች ውስጥም ሦስቱ ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት የተሳተፉ መሆናቸው ይታወቃል። ነገር ግን በዕጩነት የሚያቀርባቸው ምንም ምክንያት የለም። በዕጩነት ቢቀርቡም ቅዱስ ሲኖዶስ መቀበል አልነበረበትም። ምክንያቱም የፈጸሙት ተግባር በያዙት የክህነት መዓርግ ስንኳ ለመቀጠል የሚያስችላቸው ባለመሆኑ ነው። ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር ውጉዛኑ በዕጩነት መቅረብ የለባቸውም የምንልባቸው ምክንያቶችም የሚከተሉት ናቸው።
፩. ለእረኝነት ስለማይመጥኑ
የቤተ ክርስቲያን የቀኖና መጻሕፍት ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ የያዟቸው አናቅጽ ኤጲስ ቆጶሳት ለመንጋው የሚራሩ፣ ስለ ሕዝቡ ኀጢአት የሚያዝኑ፣ እንደ ልጅ የሚወዱና ከእግዚአብሔር በታች የሁሉም አባት መሆን እንዳለባቸው ያዝዛሉ። እነዚህ አካላት ግን ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች፣ ስለ ሕዝቡ ኀጢአት የማይገዳቸው ክፉዎች፣ ሕዝብን እንደ ልጅ ሳይሆን እንደ ዕቃ የሚቆጥሩ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው። አባትነታቸውም ለሕዝቡ ሁሉ ሳይሆን ለአንድ ሰፈር እንደ ሆነ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ መሾማቸው ሳያንስ በባለሥልጣናት ድጋፍ ወደ አህጉረ ስብከት መናብርተ ጵጵስና እና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ለመግባት የብዙ ምእመናን ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆነዋል። ምእመናንን አስተምረው ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ የመመለስ ኀላፊነት ያለባቸው ቢሆንም እነርሱ ግን የሞት ምክንያት ሆነዋል። ይህም በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፭ የተጠቀሰውን “ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾም ሰው ነውር ነቀፋ የሌለበት ይሁን” የሚለውን መስፈርት የሚያሟሉ አለመሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው። ስለሆነም በዕጩነት ሊቀርቡና ሊሾሙ አይገባቸውም።
፪. ኤጲስ ቆጶስነትን በባለሥልጣናት ድጋፍ ለማግኘት ስለሞከሩ
ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፭ “በዚህ ዓለም መኳንንት ኀይል ተረድቶ የተሾመ ኤጲስ ቆጶስ ቢኖር ከሹመቱ ይሻር” ይላል። እነዚህ አካላት በቅዱስ ሲኖዶስ የተቀወገዙበት ምክንያት ኤጲስ ቆጶስነትን በራሳቸው ለራሳቸው ለመውሰድ መሞከራቸው ነው። ይህንም ሲፈጽሙ ከጀርባቸው የተማመኑት መንግሥትን ነው። የተሾሙበት ቦታ በመንግሥት የጸጥታ አካላት ይጠበቅ ነበር። ወደተለያዩ አህጉረ ስብከት ሲገቡ የነበረው በጸጥታ አካላት ታጅበው ነበር። ሹመታቸውን ማንም እንደማይወስድባቸው ደጋግመው ሲናገሩ ታይተዋል። ቅዱስ ሲኖዶስ በሕገወጥ ሹመት በመሳተፋቸው ተጸጽተው የሚመለሱ ከሆነ እንደሚቀበላቸው በመግለጽ የሰጠውን የንስሐ በር በእልህና በትዕቢት ሲገፉ የነበሩ ናቸው። ይህም እልህና ትዕቢት ምንጩ በሹማምንት መታመን ነው። በኋላም ተመልሰናል የሚል ደብዳቤ እንደሚጽፉ ሲጠበቅ የመንግሥትን ጣልቃገብነት በሚጋብዝ መልኩ ተስማምተናል የሚል ደብዳቤ የጻፉ ናቸው። ሹመቱ እንዲጸናላቸው እንጂ ውግዘቱ እንደሚነሣላቸው ጥያቄ አልነበራቸውም። ይህም ከሰማዊ አምላክ ይልቅ ለምድራዊ ክብር የሚጓጉ፣ ኤጲስ ቆጶስነትን በማስፈራራት ገንዘብ ለማድረግ የሚተጉ መሆናቸውን የሚያጠይቅ ነው።
፫. በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና ስለማያምኑ
እነዚህ አካላት (ሕገወጥ ሿሚዎቹም ሆኑ ተሿሚዎቹ) ስለ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ስለ ቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና የሚገዳቸው አይደሉም። በእርግጥ ያለመረዳት ፍላጎት ይሁን ወይም አለማወቅ ባታወቅም የተፈጸመው ድርጊት ቀኖናዊ መሆኑን ለማስረዳት ብዙ ደክመዋል። ከሁለም የከፋው ግን የቤተ ክርስቲያንን አሐቲነትና ሐዋርያዊነት የሚፈታተን ተግባር እየፈጸሙ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም እንዳደረጉት ለማስረዳት ሲጥሩ መታየታቸው ነበር። ድርጊታቸው ሕጋዊ እንደሆነና ምንም የጣሱት ቀኖና እንደሌለ ማብራሪያዎችን ሲሰጡ ነበር። ይህ ድፍረታቸውም ከተወገዙም በኋላ ቀድሞ በነበራቸው ክህነት ብቻ ሳይሆን በሌላቸው የኤጲስ ቆጶስነት ሥልጣንም “ሲያገለግሉ” ነበር። ሥርዓተ ጽዮን ቁጥር ፳፯ “በታወቀ በደል በትክክል የተሻረ ኤጲስ ቆጶስ ቢኖርና ቀድሞ በተሰጠው ሥልጣን ለመሥራት ቢደፋፈር እስከ ዘለዓለሙ ድረስ ከቤተ ክርስቲያን ይሻር” ይላል። በተመሳሳይ መልኩ አብጥሊስ ፳፯ “በፈጸመው በደል ከሥልጣኑ የተሻረ ኤጲስ ቆጶስ ቢኖር፣ ከተሻረ በኋላ ከመሻሩ በፊት የሠራው የነበረውን የክህነት ሥራ ሲሠራ ቢገኝ እስከ መጨረሻው ከቤተ ክርስቲያን ይሰናበት” በማለት ደንግጓል። በተጨማሪም “ባደረሰው በደል ምክንያት ሥልጣኑ ተይዞ ከቤተ ክርስቲያን የተባረረ ኤጲስ ቆጶስ ከተወገዘ በኋላ ውግዘቱን አቃልሎ በክህነት ቢገለገል እስከ መጨረሻው ከቤተ ክርስቲያን ይሰናበት” (ቀሌምንጦስ ቀኖና ፳፯) የሚል ቀኖና ተሠርቷል። ውጉዛኑ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በማቃለልና የቅዱስ ሲኖዶስን ልዕልና ባለመቀበል ከተወገዙ በኋላ ሥልጣነ ክህነት ከመስጠት ጀምሮ ሌሎች የክህነት አገልግሎቶችን ሲሰጡ ነበር። ስለሆነም በእነዚህ ቀኖናዎች መሠረት ከተሻሩ በኋላ በክህነት ሲገለገሉ የነበሩ በመሆናቸው ከቤተ ክርስቲያን ሊሰናበቱ እንጂ ፈጽሞ በዕጩነት ሊቀርቡ አይገባቸውም።
፬. በምእመናን ተቀባይነት ያላገኙ ስለሆኑ
ፍትሐ ነገሥት ፭፡፴፮ “ኤጲስ ቆጶስ በሚሾምባቸው ሕዝብ ፈቃድና በሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ ይሾም” ይላል። በዚህ ሒደት ውስጥ ሐዋርያትም በአብጥሊሳቸው “ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ሊሾም የቀረበ ሰው በሀገረ ስብከቱ ባሉ ሰዎች ሁሉ ስምምነት ይሁን” ብለዋል። ሊቀ ጳጰሱና ምእመናን የወደዱት በኤጲስ ቆጶስነት እንዲሾም፣ ያለ ሊቀ ጳጳሱና ያለ ሕዝቡ ፈቃድ ደግሞ እንዳይሾም በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መጻሕፍት ታዝዟል። እነዚህ አካላት ደግሞ በሕገ ወጥ መንገድ ተሹመናል ብለው ወደ ተለያዩ አህጉረ ስብከት በሔዱበት ወቅት ምእመናን እስከ ሕይወት ህቅታ በሚደርስ ተቃውሞ አንቀበላችሁም ያሏቸው ናቸው። እነርሱም ምእመናን ካልተቀበሉን ሹመቱበ ይቅርብን ከማለት ይልቅ ምእመናን በግድ እንዲቀበሏቸው ኃይልን ያማከለ ጥቃት እንዲፈጸም አድርገዋል። አሁንም ቢሾሙ ሊያስተናግዱት የሚችሉት ተቃውሞ ከቀድሞው የከፋ እንጂ የሚሻል አይሆንም። “የተሾመ ኤጲስ ቆጶስ የተሾመባቸውን ሀገረ ስብከት ሕዝብ ፈቃድ ካላገኘ እስከሚቀበሉት ድረስ ታግዶ ይቆይ” (ሥርዓተ ጽዮን ቁጥር ፴፭) የሚለው ቀኖና የሚያስረዳው ምእመናን ያለፈቃዳቸው የተሾመን ኤጲስ ቆጶስ ያለመቀበል ሙሉ ሥልጣን ያላቸው መሆኑን ነው። የክብር ኤጲስ ቆጶስነት ደግሞ የለም። ኤጲስ ቆጶስ ከተሾመ በኋላ ባያስተምር፣ ማስተዳደር ባይችል፣ የተቸገሩትን የማይረዳ ሆኖ ቢገኝ እንዳስፈላጊነቱ ሊሻር ወይም ከሕዝቡ ሊለይ እንደሚችል ቀኖና መጻሕፍት ይናገራሉ። ኤጲስ ቆጶስ የሚሾመው ለሕዝብ ጥቅም በሕዝብ ፈቃድ እንደመሆኑ መጠን ውጉዛኑ ደግሞ በምእመናን ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ስላልሆኑ በዕጩነት ሊቀርቡ አይገባም።
፭. የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ርስት ስላደረጉ
ኤጲስ ቆጶስ ሹመት ሲሰጥ ለልጁ ወይም ለወንድሙ ወይም ለዘመዶቹ ሊሆን አይገባውም። ኤጲስ ቆጶስነትን በውርስ ያስተላልፍ ዘንድ አይቻለውም። ሥልጣኑ የእግዚአብሔር እንጂ የኤጲስ ቆጶሱ አይደለምና። የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ርስት ደርግ ዘንድ ተገቢ አይደለም። ይህን አድርጎ ቢገኝ የእርሱም የተሾመውም ሹመት ይታገድ (ሥርዓተ ጽዮን ቁጥር ፸፪) ይላል። እነዚህ አካላት ግን ፈጽሞ ከዚህ ቀኖና በተቃራኒ የእኛ ዘር፣ የእኛ ጎሣና የእኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነ ሊሾም ይገባዋል በማለት ነው የተሿሿሙት። በመንፈስ ቅዱስ የሚመራውን ቅዱስ ሲኖዶስ የአንድ አካበቢ ስብስብ እንደሆነ በመንቀፍ “በቋንቋና በሃይማኖት ራስን መቻል” በሚል ፈሊጥ የራሳችን የሚሏቸውን ሰዎች በመምረጥ ሕገወጥ ሹመት ፈጽመዋል። በወቅቱ የተሾሙት አካላትም ይህ ተግባር ትክክል አይደለም፤ ፈጽሞ ሊደረግ አይገባውም ብለው አልተቃወሙም። በተቃራኒው በሕገወጥ መንገድ ለመሾም ሌላም ቀኖና ጥሰዋል። ይህን ሕገወጥ ሹመት ለማግኘት መደለያ ከፍለዋል። ቤተ ክርስቲያንን የአንድ አካል ርስት በማድረግ በዘውግና በቋንቋ ተሰባስበው ተሿሹመውባታል። እነዚህ አካላት በቤተ ክርስቲያን የቀኖና መጻሕፍት መሠረት ተገቢው ቀኖና እንጂ ሹመት ሊሰጣቸው አይገባም። ኤጲስ ቆጶስነት ለሚገባው እንጂ ለወደደውና ለፈለገው ሁሉ የሚሰጥ አይደለም። እንዲያውም ኤጲስ ቆጶስነት ለመሾም የወደደ ሊከለከል እንደሚገባው፣ በማስፈራራት ተሾሞ ቢገኝ ከሹመቱ እንዲሻር ቀኖና መጻሕፍት ያዝዛሉ። ስለሆነም ውጉዛኑ ፈጽሞ በዕጩነት ሊቀርቡም ሆነ የቀረቡትም ሹመቱ ሊፈጸምላቸው አይገባቸውም።