የኢጲስ ቆጶሳት ታሪካችን ክፍል ሁለት

የኤጲስ ቆጶሳት አሿሿም ታሪካችን

የኤጲስ ቆጶሳት አሿሿም ታሪካችን

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኢጲስ ቆጶሳት ሢመት ታሪክ ውስብስብ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ውስብስብ እንዲሆን ያደረገው በአንድ በኩል ግብፆች ሢመቱን ለጊዜያዊ ጥቅም ማግኛ በማድረግ ፓትርያርኮች ከራሳችን መነኰሳት እንድንሾም ቢፈቅዱ እንኳ የእስልምና እምነት ተከታይ መሪዎቻቸው መከልከላቸው ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የአገራችን ነገሥታት በአዎንታዊ መንገድም ቢሆን ጣልቃ መግባታቸው “መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው” በማለት በዐደባባይ ምለው የሚገዘቱ የዘመናችን መሪዎችም በተግባር ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም በእጅጉ “የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ፈጻሚ” ሆነው እንዲታዩ በር የከፈተ በመሆኑ ነው።

የብዙዎቹ ነገሥታት ጣልቃ ገብነት ከተቆርቋሪነት የመነጨ ቢሆንም የአሁኖቹም የጥንቱን ያለ ዐውዱ በመጥቀስ ቤተ ክርስቲያንን አዳክመው ቢቻል ቀስ በቀስ ለማጥፋት ካልቻሉም የራሳቸው ፈቃድ ፈጻሚ ተቋም ለማድረግ አስበው የሚፈጽሙት መሆኑን መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን በግልጽ በተናገሩት ሦስት መንግሥታትም ተጠናክሮ ቀጥሏል። የቀድሞዎቹ አገባብ በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ሲሆን የዘመናችን ደግሞ ተሰሚነቷን ለመቀነስ ካለ ጽኑ ፍላጎት የሚመነጭ ነው። መታወቅ ያለበት ቤተ ክርስቲያን በመንግሥት አሠራር ጣልቃ ገብታ ባታውቅም መንግሥት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በነፃነት እንድትሠራ ከተዋት ሥልጣኑ ውሎ የማያድር እየመሰለው ቤተ ክህነቱን በመቆጣጠር አረዝመዋለሁ ብሎ የሚያልመውን የሥልጣን ዘመን የሚያሳጥር ተግባር እየፈጸመ መሆኑ ነው።

በክፍል አንድ ባቀረብነው ጽሑፍ ከዛጔ ነገሥታት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሐርቤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከራሷ መነኰሳት ኤጲስ ቆጶሳትን እንድትሾም አሳብ አቅርቦ እንደ ነበር ገልጠናል። የቅዱሱን ንጉሥ አበርክቶ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ “ቅዱስ ሐርቤ የመንግሥቱን ስፋትና የሕዝቡን ብዛት ተመልክቶ ከኢትዮጵያውያን መነኰሳት ዐሥር ኤጲስ ቆጶሳት በተጨማሪ ሹም ሲል አባ ሚካኤልን አዘዘው። አባ ሚካኤልም ለእስክንድርያ ፓትርያርክ ሳላሳውቅና ሳላስፈቅድ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም አልችልም አለው። የኢትዮጵያ ንጉሥ ስለዚሁ ነገር ደብዳቤ ጽፎ በዘመኑ ለነበረው የእስክንድርያ ፓትርያርክ ለአባ ገብርኤል ዳግማዊ ቢልክበት አስቀድሞ አሳቡን ተቀብሎት ነበር። በኋላ ግን በቤተ መንግሥቱ የሚያገለግሉ አንዳንድ ግብፃውያን ይህን ነገር ሰምተው ወደ እስላሙ ንጉሥ ገብተው አባ ገብርኤል የኢትዮጵያ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ መፍቀዱ ነው ብለው ነገሩት። እርሱም አባ ገብርኤልን አስጠርቶ የኢትዮጵያ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ መፍቀድህ መልካም አላደረግህም። እንዲህማ ከሆነ ወደ ግብፅ መምጣታቸውና መታዘዛቸው ገጸበረከት ማምጣታቸውም ይቀራል ብሎ መከረው። አባ ገብርኤልም ይህን ምክር ስለተቀበለውና ስለተስማማበት የኢትዮጵያ ኤጲስ ቆጶሳት አትሹም ብሎ ለአባ ሚካኤል ላከበት” በማለት ገልጠውታል (የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ፣ ፳፻፲፩ዓ.ም፣ ገጽ ፫)።

ከዚህ ማብራሪያ የምንረዳው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ሹመት በእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብቻ ሳይሆን በግብፅ ንጉሥ ጭምር ተጽዕኖ ይደርስበት የነበረ መሆኑን ነው። የኢትዮጵያ ነገሥታት በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡ ያስገደዳቸው የግብፅ መንግሥት ድርጊት መሆኑን ከዚህ ገለጣ የምንረዳው ሐቅ ነው። ብላታ መርስዔ ኀዘን እንደገለጡት ፓትርያርኩ ፈቃድ ሊሰጥ ቢፈልግ እንኳ ንጉሡ ጳጰስ ማግኛ መንገዱን እንደ ገቢ ምንጭ በማየቱ ከልክሎታል። የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሠት ጉዳዩን በቀላሉ ስላልተመለከተው ከግብፁ ፓትርያርክ ጋር የከረረ ግጭት ውስጥ ገብቶም ነበር። ግብፆች ራሳቸው ሾመው የሚልኳቸው ጳጳሳትም ቢሆኑ ከኢትዮጵያውያን መነኰሳት ኤጲስ ቆጶሳትን እንዳይሾሙ የሚከለክል ሕግ ያወጡት ከዚህ በኋላ ሊሆን ይችላል። ግብጾች በዚህ ሳይወሰኑ ከራሳችሁ ሊቃውንት ኤጲስ ቆጶሳትን ብትሾሙ መከራ ያገኛችኋል የሚል የሕፃን ማስፈራሪያ ዕለት ዕለት በምንጠቀመው መጽሐፋችን ሥርዋጽ ማስገባታቸው የሚታወቅ ነው።

ግብፆች ከራሳችን ሊቃውንት ጳጳሳትን እንዳንሾም ያስቀመጡት ማስፈራሪያ “የኢትዮጵያ ሰዎች ከራሳቸው መነኰሳት ጳጳሳትን መሾም ስለፈለጉ እግዚአብሔር ተቈጥቶ በአገራቸው ላይ ሦስት ዓመት ሙሉ ዝናም ከልክሎ በድርቅ ቀጣቸው” በማለት ሚያዝያ ፲ ቀን በሚነበበው ስንክሳር ውስጥ ሥርዋጽ ገብቶ የሚገኘው ይጠቀሳል። የግብፅ ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለውን ፈጠራ በስንክሳር ውስጥ ሥርዋጽ ለማስገባት የፈለገችው መጽሐፈ ስንክሳር በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በሙሉ ሳይነበብ ስለማይውል በመላ ክርስቲያኖች ላይ ፍርሃት ለመልቀቅ አስልታ መሆን አለበት። ከመነኰሶቻችሁ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም ካሰባችሁ ትቀሰፋላችሁ የሚለው ማስፈራሪያ በግብፆች ቢቀመጥም አሳቡ በእስልምና እምነት ተከታይ ነገሥታትና በአንዳንድ ጥቅመኛ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች የተሸረበ ተንኮል መሆኑን የተረዱት የኢትዮጵያ ነገሥታት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንን መጠየቃቸውን አላቆሙም።

ከሐርቤና ከበዕደ ማርያም በመቀጠል ዐፄ ዮሐንስ ፬ኛም ጥያቄያቸውን ለእስክንድርያው ፓትርያርክ ማቅረባቸውን ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ “በየጊዜው የተነሡ ነገሥታት ስለጵጵስናው መዓርግ ሲደክሙበት ኖረዋል። የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ አቡነ አትናቴዎስ ካረፉ በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዮሐንስ (፲፰፻፷፬-፲፰፻፹፩ዓ.ም) አንድ ሊቀ ጳጳስና ብዙ የኢትዮጵያ ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙላቸው በዘመኑ ለነበሩት ለእስክንድርያው ፓትርያርክ ለአቡነ ቄርሎስ ፭ኛ ጻፉላቸው። የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ግን በዚህ ጥያቄ የማትስማማ ስለ ሆነች ነገሩን በማሻሻል ግብፃውያን የሆኑ አንድ ሊቀ ጳጳስና ሦስት ኤጲስ ቆጶሳት ተሹመው እንዲላኩላቸው በሲኖዶስ ተወሰነ” በማለት ጽፈዋል (ዝኒ ከማሁ፣ ፳፻፲፩ዓ.ም፣ ገጽ ፬)።

የንጉሠ ነገሥቱ ጥያቄ ከበድ ያለ በመሆኑ የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ፍጹም አላደርገውም እንዳትል ኢትዮጵያውያን ከእኛ ያጡትን ከሌላ ሊያገኙ ይችላሉ በሚል ስጋት ሳይሆን አይቀርም ከእስከ አሁኑ በዛ ያሉ ኤጲስ ቆጶሳትን ሹማ የላከችው። ግብፆች ለተጠየቁት አሳማኝ ምክንያት ማቅረብ ስለማይችሉ ደጋግመው ይጠቅሱት የነበረው የኒቅያ ጉባኤ ከራሳችሁ ሊቃውንት መሾም እንደሌለባችሁ ሥርዓት ሠርቶል የሚል ነበር። እንዲህ ያለው ምክንያት አላስኬድ ሲል ደግሞ ‹‹እናትና ልጅነታችን ይላላል፣ ፍቅራችን ይቀዘቅዛል›› በማለት ሊከለክሉን የሞከሩት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መሆኑን ብላታ መርስዔ ኀዘን በመጽሐፋቸው ጠቅሰውታል።

በዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን በዛ ያሉ ጳጳሳትን ሾማ ከመላክ በተጨማሪም ሀገረ ስብከታቸውን በሢመቱ ዕለት ወስና መላኳ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የተከተለ ድርጊት መሆኑን መመሥከር ይገባል። ከዐፄ ዮሐንስ በመቀጠል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከራሷ መነኰሳት ኤጲስ ቆጶሳትን እንድትሾም ከፍተኛ ተጋድሎ የፈጸሙት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ናቸው። አበርክቷቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ቅዱስ ሲኖዶስ መፈጸም የነበረበትን የሀገረ ስብከት ምደባ እርሳቸው መፈጸማቸው ግን ተገቢ አልነበረም።

ለመጀመሪያ ጊዜ ጵጵስና የተሾሙት ኢትዮጵያውያን የሀገረ ስብከት ምደባ የተከናወነው በቤተ መንግሥቱ ስለመሆኑ ብላታ መርስዔ ኀዘን “ጳጳሳቱ ከሊቀ ጳጳሳቱ ከአቡነ ቄርሎስ ጋር አብረው እየኖሩ አስተዳደር ከለመዱ በኋላ የተመደቡበትን ሀገረ ስብከት የሚያስታውቅ፣ አስተዳደራቸውን የሚያመለክት ደንብ ከንጉሠ ነገሥቱ ጥር ፳፫ ቀን ፲፱፻፳፫ ዓ.ም ወጥቶላቸው ወደየሀገረ ስብከታቸው ሲሔዱ አቡነ አብርሃም ሀገረ ስብከት ምዕራብ ኢትዮጵያ በጌምድር እና ስሜን፣ ጎጃም በመላ የተመደቡ ሲሆን መጠሪያቸውም ‘አቡነ አብርሃም ጳጳስ ዘምዕራበ ኢትዮጵያ ተላዌ አሠሩ ለአቡነ ሐራ ድንግል’ እንደነበረ ገልጸዋል (፳፻፲፩ ዓ.ም ገጽ ፷፬)።

ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል በበኩላቸው “አቡነ አብርሃም ጳጳስ ዘምዕራብ ኢትዮጵያ ሆነው መሾማቸውንና የሹመታቸው ቦታ ራሱ ጎንደር እግሩ መተማ እንግሊዞች ወሰን ድረስ ግንደ ብረት፣ ሰላሌ፣ ደራ፣ ቦረና፣ ሚዳ፣ በጌምድር በመላ፣ ስሜን፣ ቋራ፣ ጎጃም፣ አገው፣ ዳሞት፣ ሜጫ፣ አቸፈር፣ ወንድዬ፣ ይልማና ዴንሳ በማለት በዝርዝር አስቀምጠው ዓባይን ተሻግረው ግንደ ብረት፣ ሰላሌ፣ ደራ፣ ቦረና፣ ሚዳ፣ ቋራ በእርሳቸው ሀገረ ስብከት ሥር ተደልድለው እንደነበር ይነግሩናል። አገልግሎቻቸውን እንዲያከናውኑ ኃላፊነት የተሰጣቸውም መንፈቁን በጌምድር ደብረ ታቦር እና ጎንደር፣ መንፈቁን ጎጃም መርጡለ ማርያም እና ደብረ ማርቆስ እየተቀመጡ እንዲያስተምሩ፣ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ሲዘዋወሩም ከበታቻቸው ሊቀ ካህናት ሆነው ሕግ የሚያስጠብቁላቸው የጣና ቂርቆሱ መምህር፣ የመርጡለ ማርያም መምህር እንዲሆኑላቸው ተደረገ” በማለት ይነግሩናል (ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፣ ዝክረ ነገር፤ ፲፱፻፷፫ ዓ.ም ፣ ገጽ ፭፻፵፪)።

መታወቅ የሚገባው ለአቡነ አብርሃምም ሆነ ለሌሎች አባቶች የተሰጣቸው ኃላፊነት በንጉሠ ነገሥቱ መሆኑ ነው። መሰጠት የነበረበት ከእስክንድርያው ፓትርያርክ ወይም ከሊቀ ጳጳሱ ከአቡነ ቄርሎስ ነበር። በሊቀ ጳጳሱ ሰብሳቢነት አምስቱ ኤጴስ ቆጶሳት ጉባኤ አድርገው ተመካክረው ቢመዳደቡ ደግሞ የተሻለ ይሆን ነበር። በ፲፱፻፳፩ ዓ.ም ከተሾሙት አራት ጳጳሳት እና በዓመቱ ከተጨመሩት አንድ ጳጳስ መካከል ሁለቱ በተለይ አቡነ አብርሃምና አቡነ ሳዊሮስ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ወዳጆች ተደርገው ይታዩ ስለነበር ጳጳሳቱም የልዑል ራስ ተፈሪ እና የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ደጋፊ በመባል በመካከላቸው ክፍፍል እንዲኖር ይደረግ ነበር።

በጥቃቅኑ ሁሉ እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ንጉሠ ነገሥቱ ጣልቃ መግባታቸው ጳጳሳቱ ችግር በገጠማቸው ቍጥር በራሳቸው መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ንጉሠ ነገሥቱን እንዲያማክሩ ምክንያት ሆኗል። መሆን የነበረበት ግን ጳጳሳቱ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን የሚፈቅደውን እየመረመሩ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅመውን መፈጸም ነበር። ጳጳሳቱ የከፋ ችግር ገጥሟቸው ስለማያውቅ በ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ጣሊያን አገራችንን በወረረች ጊዜ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም ጥለው ወደ አገራቸው በሔዱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን እንዴት የመከራውን ዘመን መሻገር እንደሚገባት ሥርዓት ባለመሠራቱ ብፁዕ አቡነ አብርሃም እና ሰባ ሁለት ሊቃውንት አባላት የነበሩት መማክርት የፈጸሙትን ተግባር ግማሾቹ ከሀገር ክሕደት ጋር ሲያያይዙት ሌሎች ደግሞ የመከራውን ዘመን ለማሻገር የተወሰደ አግባብነት የላው ተግባር አድርገው ይመለከቱታል። አቡነ አብርሃምም ሆኑ በዘመኑ የተሾሙ ጳጳሳት በሊቅነታቸው ላይ ጥያቄ የሚያነሣ አካል ባይኖርም አገራችንም፣ ቤተ ክርስቲያናችንም ለችግር በተጋለጡ ጊዜ መከራው ለማለፍ የሚያስችል ግልጽ የሆነ ሥርዓት አለመበጀቱ ግን መዋቅሩ ማንም በፈለገ ጊዜ እጁን እንዲያስገባበት በሩ ክፍት መሆኑን ግን ያሳያል። ይህን መሰል ክፍተቶችን የሚሞሉ አሠራሮች መዘርጋት ከጥያቄም፣ ከተጠያቂነትም፣ ከንጥቂያም ይጠብቃልና ቢታሰብበት እንላለን።

 

ዋቢ መጻሕፍት

የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን፣መጽሐፈ ስንክሳር። ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት፣ ፲፱፻፺፬ ዓ.ም።

ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፣የመጀመሪያው ኢትጵያዊ ፓትርያርክ(፪ኛ ዕትም)። ፳፻፲፩ ዓ.ም።

ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከ፲፱፻፳፪-፲፱፻፳፯ ዓ.ም። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕረስ፣፳፻፱ ዓ.ም

ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፣ ዝክረ ነገር።ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ ፲፱፻፷፫ዓ.ም።