የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ታሪካችን – ክፍል ሦስት

የኤጲስ ቆጶሳት አሿሿም ታሪካችን

የኤጲስ ቆጶሳት አሿሿም ታሪካችን

 

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጽሑፎች የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ታሪካችን በፈተና የተከበበ መሆኑን አንሥተናል። ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ቅድስት ቤተክርስቲያን ከራሷ መነኰሳት ጳጳሳትን እንድትሾም ያደረጉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ ቢሆንም በራሳቸው ወርድ ለመስፋት ያደርጉት የነበረው ጣልቃ ገብነት ደግሞ አሁን ለደረስንበት ችግር እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችል ነው።  ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት እንዲሾሙ ያደረጉት ተጋድሎ በሌላ በኩል አባቶች መንግሥት ካከልን ብለው እንዲዘናጉ ሳያደርግ አልቀረም። በ፲፱፻፳፩ዓ.ም ከራሳችን መነኰሳት ኤጲስ ቆጶሳት እንደተሾሙ ሊቀጳጳሱና ኤጲስ ቆጶሳቱ ጉባኤ አድርገው በመምከር ሊያደርጉት የሚገባውን የሀገረ ስብከት ምደባ ንጉሠ ነገሥቱ መፈጸማቸው ለጉዳዩ ትኩረት ለመስጠት ጠቅሟል የሚል አካል ቢኖርም በየዘመናቱ ለተነሡ ባለሥልጣናት መንገድ ቀይሰዋል።

 

አባቶቻችን በጵጵስና መንበር ላይ ሆነው አገር የመምራት ልምድ ስላልነበራቸው ንጉሠ ነገሥቱ ማገዛቸው በዘመኑ ተገቢ ቢሆንም ቤተክርስቲያን የሚገጥማትን ችግር በራሷ ከመፍታት ይልቅ በቤተ መንግሥቱ እንድትተማመን አድርጓል። ይህ ማለት ግን ሊቃውንቱ ክርስትና ባልተስፋፋባቸው አካባቢዎች ገብተው በማስተማር ለቤተመንግሥቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን መዘንጋት አይደለም።  የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ሊያስከትል የሚችለውን ችግር አርቆ በማየት የማያዳግም መፍትሔ የመስጠት አቅሟን አሟጣ ተጠቅማለች ማለት አይቻልም። ይህ ቢሆን ኖሮ ሐዋርያዊ የክህነት ቅብብሎሽን ከማያምኑ ሰዎች ዘንድ ባልደረስን ነበር። የቀኖና መጻሕፍትን መሠረት በማድረግ ግልጽ የሆነ የአሿሿም ሥርዓት በመሥራት በዚያ መመራት አለመቻሉ በኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ፖለቲከኞች ገብተው የሚያዙበት፣ እገሌን ሹሙ እገሌን አትሹሙ እስከማለት እንዲደርሱ ዕድል ሰጥቷል።

ሳይበቁ የበቁ የሚመስሉ ሰዎች ሢመት እየተቀበሉ ቤተክርስቲያንን በቀኖናዋ መሠረት መምራት ሲሳናቸው የራሳቸውን ፍላጎት የቤተክርስቲያን ሕግ አስመስለው አዲስና አንግዳ ሥርዓት ሲፈጥሩ ይታያሉ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኤጲስ ቆጶሳት አመራረጥ ችግር እንዲገጥመው ያደረገው ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ እንዲጠናከርና ሐዋርያዊው የወንጌል አገልግሎት እንዲስፋፋ ከመሥራት ይልቅ መንፈሳዊውን ሥልጣን ለጊዜያዊ ጥቅም ማግኛ አድርገው የሚያስቡ “አባቶች” ከፍ ወዳለው የሢመት መዓርግ መምጣታቸው ነው። ሌላው ችግር ደግሞ ለሢመት የሚመረጡ አባቶች ለመንፈሳዊው ሥልጣን የማይመጥኑ መሆናቸው ነው።

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ በሚለው መጽሐፍ መቅድም ላይ በጻፉት ጽሑፍ ቤተክርስቲያን ላይ ፈተና እና ችግር እንዲፈጠር ካደረጉት ጉዳዮች መካከል ዋናዋናዎቹ ሁለት መሆናቸውን ይገልጻሉ። የመጀመሪያው የመናብርት ክብርና ደረጃ ያመጣው ጣጣ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሮማ ግዛት ሥር ክብሩ የተሰጣቸው መናብርት በሥራቸው ለነበሩ ሀገራት አስፈላጊ እየሆነ እንኳ ራሳቸውን ችለው ወንጌለ መንግሥትን እንዲያስፋፉ መፍቀድ አለመቻላቸው ነበር” ይላሉ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን የገጠማት ሁለተኛው አይነት ችግር ነው።  ኢትዮጵያ ሰፊ አገር መሆኗን ግብፆች ቢያውቁም ራሳችንን እንድንች ልማድረግ ይቅርና ከራሳቸው መነኰሳት እንኳ በዛ ያሉ አባቶችን ሾመው ለመላክ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ችግር ሲፈጥርብን ኖሯል። በአንድ ጊዜ በዛ ያሉ አባቶች ቢሾሙ የሚኖረው ጠቀሜታ ብዙ ነው።  አንዱ አባት በደዌም ይሁን በእርግና ቶሎ ቢያርፍ ወይም አገልግሎቱን በሚፈለገው አግባብ መስጠት ባይችል ሌላኛው አገልግሎቱን የመሸፈን ዕድል ስለሚኖረው ቢያንስ ክህነት የሚሰጥ አባት አይጠፋም ነበር። ይህም ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ሚቀመጡበት ርእሰ ከተማ ክህነት ለመቀበል ሲሔዱ ለብዙ ድካም፣ ውጣ ውረድና ሞት የሚዳረጉትን ይታደግ ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ ከኢትዮጵያውያን መካከል ሊቅነት ከምንኵስና የሠመረላቸው መነኰሳት ለኤጲስ ቆጶስነት ሲታጩ ቤተ መንግሥቱ እጁ ረጅም ነበር። በ፲፱፻፳፩ ዓ.ም ከተሾሙ አባቶች መካከል እጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስና መምህር ደስታ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እንጂ በራስ ተፈሪ የማይፈለጉ ሊቃውንት ነበሩ። በኋላም ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የነበራቸው ግንኙነት የሻከረ ነበር። የንጉሠ ነገሥቱ ወዳጅ የነበሩት መምህር ኃይለ ማርያም ነበሩ። እንዲህ ያለው ልዩነት ከዓመታት በኋላ ፋሽስት ኢጣሊያ አገራችንን በወረረች ጊዜ የአሰላለፍ ለውጥ እንዲመጣ የራሱ የሆነ ምክንያት ሆኗል የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱ አሳማኝ ይሁንም አይሁንም ቤተመንግሥቱም ሆነ ሌላ ተጽዕኖ ፈጣሪ አካል በምርጫ ሂደቱ ላይ ጣልቃ ሲገባ እንዲህ ያለ አሉታዊ ነገር ማስከተሉን መረዳት ይገባል።

ለሁለተኛ ጊዜ በዛ ያሉ ኢትዮጵያውያን ኤጲስ ቆጶስነት ተሹመው አገልግሎት ሲሰጡ ከቆዩ በኋላ የሊቀጳጳሱን የአቡነ ቄርሎስን ዕረፍት ተከትሎ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ ይባሉ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ሊቀጳጳስ ተሾሙ። ከግብፅ ቤተክርስቲያን ጋር ያለን ግንኙነት እንዳይሻክር ቀኖና ቤተክርስቲያን በሚፈቅደው ብቻ ጥያቄው እንዲቀርብ መጻሕፍት አገላብጠው፣  በየዘመናቱ የተሰጡ ቀኖናዎችን መርምረው የመፍትሔ ሐሳብ ያመጡት ከየክፍላተ ሀገሩ ተወክለው ወደ አዲስ አበባ የመጡ ሊቃውንት ቢሆኑም የቤተመንግሥቱ ተጽዕኖ ቀላል አልነበረም።  ችግር ሲገጥም ቤተመንግሥቱ ጣልቃ መግባቱ ቤተክርስቲያን ለተፈጠረ ችግር መፍትሔ ለመስጠት ያላትን አቅም እንዳትጠቀም አሉታዊ አስተዋጽዖ አድርጓል።  እንዲህ ያለው ድጋፍም  ይባል ተጽዕኖ ቅድስት ቤተክርስቲያን ችግር ሲገጥማት ራሷ ከመፍታት ይልቅ ችግሩ እየተወሳሰ በዘመናትን እንዲሻገር አድርጓል።

ፋሽስት ኢጣሊያ አገራችንን በወረረችበት ወቅት የብፁዕ አቡነ ቄርሎስን ወደ አገራቸው መመለስ ተከትሎ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በዘመኑ ተቋቁሞ በነበረው የሊቃውንት መማክርት ሊቀጳጳስነት መሾማቸው ይታወቃል። በዚያን ጊዜ በሕይወት የተረፉት ሁለት ጳጳሳት ብቻ ስለነበሩ ሊቀጳጳሱ ከመነኰሳት መርጠው ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመው ነበር።  ነጻነት ከተመለሰ በኋላ ሾመዋቸው ከነበሩ መነኰሳት መካከል አንዳንዶቹ ተከልሰው ዳግም ሲሾሙ ሌሎች ሳይሾሙ ቀርተዋል። የተከለሱትንም ሆነ ሳይከለሱ የቀሩትን በተመለከተ ካለማንም ጣልቃ ገብነት ቅድስት ቤተክርስቲያን ቀኖናዋ በሚፈቅደው መንገድ ፈጽማው ከነበረም ምእመናን ጉዳዩን እንዲያውቁት ተደርጎ በዘመናችን ለገጠመን ችግር በመፍትሔነት እንደመነሻ መታየት ነበረበት። የተፈጸመው የሢመት ክለሳ ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጭ ከነበረም እንዳይደገም መጠንቀቅ ይገባ ነበር።  የጣሊያን ወረራን የመሰለ መጥፎ ዘመን ሲገጥማት ምን ማድረግ እንደሚገባም ግለጽ የሆነ ሥርዓት መቀመጥ ነበረባት። የሢመት ክለሳ ሲደግም በምን መልኩ መከናወን እንዳለበት ከአኃት አብያተ ክርስቲያንና ከኦርቶዶክሳዊ ትውፊት በመነሣት ዝርዝር አሠራር ሊኖር ይገባዋል። እንዲህ ያለው ድርጊት ቀኖና ቤተክርስቲያንን በሚገባ የማያውቁ የዋህ ምእመናንን እንዳይጎዳ በአብዝኆ ጥንቃቄ መፈጸም የሚገባው ተግባር ነው።

በዚያ ዘመን ለተፈጠረውም ሆነ ፓትርያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዐርፈው በመንበሩ የሚተካ ፓትርያርክ ለመምረጥ ሲታሰብ ሀገረ ስብከት ያላቸው አባቶች ከምርጫው ውስጥ እንዳይካተቱ የሚል አሳብ ተነሥቶ የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ ሳይደረግ ቀርቷል። ለእንደዚህ ያለው ችግር መፍትሔው ማንኛውንም አካል ጣልቃ ከመግባት የሚከለክል ሥርዓት አዘጋጅቶ ያለማወላወል ተግባራዊ በማድረግ ነው። አንዱ ወገን ሲጥሰው ትክክል የሚሆንበት፣ ሌላው ሲጥሰው ስሕተት የሚሆንበት የቤተክርስቲያን ቀኖና ባለመኖሩ ሁሉም ጳጳሳት ቀኖናውን የማክበር ኃላፊነት አለባቸው።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በሕይወት እያሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ ሆነው የተሾሙበት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በሕይወት እያሉ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ የሆኑበት መንገድ ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጭ መሆኑ ቢታወቅም አሁንም “እነ እገሌስ ፈጽመውት የለም እንዴ” እየተባለ በጥፋት ላይ ጥፋት ሲፈጸም እንጂ የማያዳግም መፍትሔ ሲሰጥ አይታይም። የሚበጀው ግን የማያዳግም ሥርዓት መሥራት ነው።  የማያዳግም ተግባር ለመፈጸም ደግሞ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ከተፈጸመው ሢመት ጀምሮ በየጊዜው የተከሠተውን ችግር በተመለከተ በአግባቡ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል።  የሚጠናውም የነበረውን ሁኔታ በሚገባ ለመገንዘብ እንደመሆኑ መጠን ከግላዊ ፍላጎትና መሻት በመውጣት የጥናት ስልቶችን ተከትሎ ሊሠራ ይገባል።

በየዘመናቱ የነበሩትን አስገዳጅ ሁኔታዎች መለየት፣  አባቶች ከዚያ ውሳኔ ላይ ያደረሳቸውን ምክንያት መረዳት፣  ውሳኔያቸው ከቀኖና ቤተክርስቲያን አንጻር ሲመዘን ምን እንደሚመስል ማስገንዘብ መሠራት ካለባቸው ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ከድርጊቱ ምን አተረፍን፣  ምንስ አጎደልን፣ መደረግ ሲገባው ሳይከናወን የቀረ፣  ከድርጊቱ የተማርነው እና ሳንማር የቀረነው ጉዳይ ተለይቶ ከቀረበ በኋላ ወደፊት ተመሳሳይ ችግር ቢገጥመን እንዴት እንደምናልፈው የመፍትሔ አሳብ ማቅረብ ይገባዋል። ከዚህ በመነሣት የፍትሐ ነገሥት ሊቃውንት፣  የታሪክ ምሁራን፣  የቀኖና ቤተክርስቲያን መምህራን የመፍትሔ አሳብ እንዲያቀርቡ ከተደረገ በኋላ ቅዱስ ሲኖዶስ ያንን መነሻ አድርጎ ውሳኔ ከሰጠ የኤጲስ ቆጶሳትንም ሆነ የፓትርያርክ ምርጫን በተመለከተ ማንም ጥያቄ አያነሣም፣  ማንም ተነሥቶ ጣልቃ አይገባም። በዘመናችን ለተከሠተው ችግር መፍትሔ መስጠት የሚቻለውም በዚህ አግባብ መሆኑን አለበት የሚል እምነት አለን።