የኤጲስ ቆጶሳት አሿሿም ታሪካችን
ኢትዮጵያውያን ከራሳችን ሊቃውንት ኤጲስ ቆጶሳት ለመሾም ያሰቡትና የጠየቁት ጥንት ነው። ከዛግዌ ነገሥታት አንዱ የሆነው ቅዱስ ሐርቤ ኢትዮጵያውያን ከራሳችን ጳጳሳት እንዲሾሙ አሳብ አቅርቦ ነገሥታት ከትምህርተ ሃይማኖትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር እንዲመረምሩት አድርጎ ነበር። አሳቡ ተግባራዊ እንዲሆን የፈለገውም ጳጳስ ከግብፅ ማስመጣቱን እንደ ቅኝ ግዛት ቈጥሮት ሳይሆን ከአገራቱ ርቀት አንጻር ጳጳስ እንዲሾም የሚጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ለብዙ ዓመታት የሚቆይ በመሆኑ፣ በዚያውም ላይ ባሕሉን የሚያውቀው፣ ቋንቋውን ከሚናገረው ቢሾም ክህነት ከመስጠት በተጨማሪ አስተምሮ ብዙዎችን መመለስ ይችላል ብሎ በማመን ነበር።
በዘመኑ የተፈጸመውን ሥርግው ሐብለ ሥላሴ በአማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት የገለጡት “በዘመኑ ከፈጸማቸው ዋና ዋና ሥራዎች አንዱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ራሷን ለማስቻል ያደረገው ሙከራ ሊጠቀስ ይገባዋል። የግብፅ ተወላጅ ጳጳስ ራሱ ብቻ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የሚያከናውነው ሥራ አጥጋቢ ባለመሆኑ እንዲሁም የአገሩን ቋንቋ ባለመናገሩ ከምእመናንም ሆነ ከካህናት ጋር ለመግባባት የማይቸገር የአገር ተወላጆችን መሾም አስፈላጊ መሆኑ ተሰምቶት ነበር። ስለዚህ በዘመኑ የነበረውን ግብፃዊ ጳጳስ አቡነ ሚካኤልን ጠርቶ ከኢትዮጵያውያን መነኰሳት መካከል ለጵጵስና የሚበቁትን እንዲሾም ጠየቀው። ጳጳሱም እንዲህ ያለ ሥራ ስለማከናወን ሥልጣን ስላልተሰጠው የሚሻለው ለግብፅ ፓትርያርክ ጉዳዩን ማቅረብ እንደሆነ ያመለክተዋል። በዚህ ተነሣሥቶ ዐፄ ሐርቤ መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ይልካል። ነገር ግን መልእክቱ ሳይሳካለት ቀርቷል” በማለት ነው (ቅጽ ፩፣ ፲፱፻፷፱ ዓ.ም፣ ገጽ ፩)።
ከዚህ ጽሑፍ የሚመዘዙ ብዙ ቁም ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው ንጉሡ ቤተ ክርስቲያኗን ራሷን ለማስቻል መሞከሩ ነው። መረዳት የሚገባው ሙከራው በግድ እንዲፈጸም ሳይሆን ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን ማድረጉ ነው። ቀኖናዊነቱ እንዲጠበቅ መፈለጉን የሚያመለክተው ጳጳሱን ጠርቶ ከጠየቃቸው በኋላ የሰጡትን መልስ ተቀብሎ በዚያ መሠረት መመራቱ ነው። ንጉሡ ነውጠኛ ቢሆን ኖሮ ያዘዝኩህን ፈጽም ይላቸው ነበር። ንጉሡ ሐርቤ መንፈሳዊ ስለነበር ቤተ ክርስቲያንም ከሐዋርያዊው ቅብብሎሽ እንድትነጠል ስለማይፈልግ ጳጳሱ አቡነ ሚካኤል ባቀረቡለት አሳብ መሠረት የግብፁ ፓትርያርክ እንዲጠየቁ አድርጓል።
ሌላው ከዚህ ጽሑፍ የምንረዳው ቁም ነገር ጳጳሱ ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሊቃውንቱም ጋር የማይግባቡ በመሆኑ ቋንቋውንም ባህሉንም የሚያውቅ ሊቅ እንዲመረጥ ለማድረግ ማሰቡ ነው። የንጉሡን ጠንቃቃነት የሚገልጠው አንተ የሰው ሀገር ሰው ስለሆንክ አታስፈልገንም አለማለቱ ነው። እንዲያውም የጳጳሱን አሳቡን ተቀብሎ ፓትርያርኩን ለመለመን መልእክተኛ ልኳል። በዚህ አንጻር ከታየ እንዲያውም ንጉሡ በጣም መንፈሳዊ ሲሆን ግብፃውያን ግን የገዥዎቻቸው ተጽዕኖ አስገድዷቸው ነው ካልተባለ በስተቀር ለስብከተ ወንጌል መፋጠን እንቅፋት ሆነዋል።
በፍትሐ ነገሥት “የኢትዮጵያ ሊቃነ ጳጳሳት አለቃ ሊሾሙ አይችሉም ይልቁንም ጳጳሳቸው እስክንድርያ ባለው ፓትርያርክ ይታዘዛል። ይኸውም ጳጳስ በእነርሱ (በኢትዮጵያውያን) እንደ ሊቀ ጳጳስ ይቈጠራል። ጠቅላይ ተብሎም ይጠራል። እርሱ የሊቀ ጳጳሳትን ክብርና ሥልጣን ስለሌለው እንደ ሌሎቹ ሊቃነ ጳጳሳት ሁሉ ጳጳስ ሊሾም አይችልም። ምን አልባትም በሮማውያን ሀገር ጉባኤ የተደረገ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ የሚቀመጠው ከግብጽ ሊቀ ጳጳሳ ቀጥሎ ይሆናል” ይላል (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፬፣ ቍ ፵-፶)። ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን መጠበቅ አንጻር መርምረውት በጉባኤ ኒቅያ ሳያመካኙ ይህን አንቀጽ ግብፃውያን ራሳቸው አርቅቀውት ቢሆን ባላስነቀፈ ነበር። ቀኖናውን እንዲነቀፍ ያደረገው የራሳቸው ምኞት ሆኖ ሳለ በጉባኤ ኒቅያ ማመካኘታቸውና ቀኖናውን የሰጡበት ምክንያት አጥጋቢ አለመሆን ነው። ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ሊቃውንት ኤጲስ ቆጶሳትን አይሹሙ የምትለዋን ማታለያም ይባል ማስፈራሪያ በሥርዋጽ ያስገቡት ቀጣይ ትውልድ የሐርቤን አሳብ ተቀብሎ እንዳይጠይቃቸው እርሱን ያየህ ተቀጣ ለማለት ይመስላል።
ሌላው ንጉሥ ሐርቤ የተናገረው ጠቃሚ ነገር ለጵጵስና የሚገቡትን መነኰሳት መርጠህ ሹምልን ማለቱ ነው። መታወቅ ያለበት ንጉሡ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ ያልገባ እንዲያውም ለሢመቱ የሚመጥኑትን በቤተ ክርስቲያኗ ትውፊትና ሥርዓት መሠረት እንዲያከናውን አሳብ ማቅረቡ ነው። ለጵጵስና የሚመጥኑትን ማለት ነቀፋ የሌለባቸውን፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ አባቶቼ ብሎ የሚቀበላቸውን፣ ሰዎችን ከአምላካቸው የሚያስታርቁትን ምረጥ ማለቱ ነው። እንዲህ ያለው ገለልተኛ አቋም በዘመናችንም ቢኖር ኖሮ ከዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ባልገባን ነበር።
ንጉሥ ሐርቤ ለቤተ ክርስቲያን ያበረከተውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተቀብላ ቅዱስ ብላ የጠራች የሐርቤ አሳብ ወንጌልን ለማስፋፋት ጠቀሜታ ቢኖረውም ሰማያዊውን ሥልጣነ ክህነት በእጅ መንሻ ሰበብ ለገንዘብ መሰብሰቢያ ማድረግ የለመዱት ግብፆች አሳቡን ውድቅ አደረጉት። ይህ አንሷቸው ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ሊቃውንት ጳጳስ እንሹም ማለታቸውን እግዚአብሔር ስላልወደደው በንጉሡ ላይ መቅሠፍት በማውረድ መቀመጫ ከተማውን በእሳት አቃጠለው የሚል ፈጠራ ጽፈው በራሳችን መጻሕፍት ሥርዋጽ አስገብተው እያነበብን በፍርሃት እንድንኖር ብቻ ሳይሆን እነርሱን እየተለማመጥን እንድንኖር የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል።
እግዚአብሔር በሚያውቀው ምክንያት የተፈጠረን ክሥተት ከሌላ ጉዳይ ጋር አያይዞ ማቅረብ የጥቅመኞች መለያ ባሕርይ ቢሆንም የንጉሡ ከተማ ተቃጥሎ ቢሆን እንኳ አንድ ምክንያቱ ከአንድ ንዝህላል ሰው ቤት የተነሣ እሳት ከተማውን አቃጥሎት ሊሆን ይቻላል። ይህ ባይሆን እንኳ የልብ ንጽሕና እንጂ ዘር ማንዘር ለሐዲስ ኪዳን ክህነት መስፈርት እንደማይሆን እየታወቀ እንዲህ ያለ ማታለያ ማቅረቡ ተገቢ አይደለም። እንዲህ ያለውን ተንኮል የፈጸሙት አካላት የግብፅን ቤተ ክርስቲያን ላይወክሉ፣ ለቤተ መንግሥቱም እጅ መንሻ ይላክ ስለነበር ጥቅመኛ አገልጋዮችን ተጠቅሞ ፈጽሞት ቤተ ክርስቲያኗ ስትተች እንድትኖር አድርጎ ሊሆን ይችላል።
አባቶቻችን ግን የግብፆችን ተንኮል እያወቁ ከሐዋርያዊው ትውፊት ላለመውጣትና ሐዋርያዊ ቅብብሎሹን ጠብቀው ለማቆየት በግብፆች ሥር እንድንኖር አድርገዋል። ምንም እንኳ ለደስታችን መግለጫ ብዙ ወቄት ወርቅ እንልክላቸው የነበረ ቢሆን የኢትዮጵያ ነገሥታት ፍጹም ሃይማኖተኞች ስለነበሩ ጉዳዩን ግብፆች በሚያዩበት መንገድ አያዩትም ነበር። አባት ለማስመጣት ለግብፅ ቤተ ክርስቲያን ይሰጡት የነበረው ብቻ ሳይሆን ለተቸገረ ይመጸውቱት የነበረው በረከት ከመጨመር ውጭ ለድህነት ይዳርገናል ብለው አያውቁም ነበር። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ብቅ ብቅ ማለት የጀመረው ቁሳዊነት እያየለ ከመጣበት ከ፲፱ኛው ምእተ ዓመት በኋላ መሆኑን መረዳት ይገባል።
ከኢትዮጵያውያን መካከል አንዳንድ ጽንፍ የረገጡ ግለሰቦች እንደሚሉት ኢትዮጵያውያን ከግብፅ ለአንድ ሺህ ስድስት መቶ ዓመታት ጳጳሳት ስናስመጣ መኖራችንን ከቅኝ ግዛት ጋር ሲያያዙት ይሰማሉ። እንዲህ ያለው አሳብ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ያለውን ጠቀሜታ አለማወቅ የፈጠረው መሆኑን መረዳት ይገባል። በዚያ ላይ ሐዋርያዊ ክትትሉ እንዲቀጥል አባቶቻችንን የፈጸሙትን ተግባር ማቃለል እንደሚሆንም መረዳት ይገባል።
ከቅዱስ ሐርቤ በመቀጠል የእስክንድርያ መንበረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ከራሳችን ሊቃውንት ጳጳሳት እንዲሾሙልን ጥያቄ የቀረበው በዐፄ በዕደ ማርያም ዘመነ መንግሥት፣ አባ መርሐ ክርስቶስ የደብረ ሊባኖስ ዕጨጌ በነበሩበት ዘመን መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። በዘመኑ የተፈጸመውን ሥርግው ሐብለ ሥላሴ “በአማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት” የገለጡት “በዕደ ማርያም በነገሠ በ፱ ዓመቱ ከራሳችን ጳጳስ እንሹም የሚሉ ኢትዮጵያውያን ተነሥተው ነበር። እጨጌው አባ መርሐ ክርስቶስ ግን እንደተለመደው ከግብፅ ይምጣ ብሎ ተከራከረ” በማለት ነው።
፱ኛው የደብረ ሊባኖስ እጨጌ የነበሩት አባ መርሐ ክርስቶስ በጣም መንፈሳዊ አባት ስለነበሩ ይህን ያሉት ምን አልባት አሁን የደረስንበት አስቀድሞ ታይቷቸው ይሆን ብሎ መጠየቅ ይገባል። እንዲህ ያለውን ታሪካችንን መዳሰስ ያስፈለገን እነእገሌ የተሾሙት በዚህ መንገድ ነው እያልን በጥፋት ላይ ጥፋት ከምንደራርብ የማያዳግም መፍትሔ ለመስጠት እንድንችል ነው። በዘመናችን እንደ ጵጵስና ክብሩን የጣለ፣ እንደ ኢትዮጵያውያን መነኰሳት ያለ ለዓለም መሳለቂያ የሆነ የሌለ መስሏል። እንዲህ ያለውን የተበላሸ ነገር ማስተካከል የምንችለው በሚገባ የተማሩትን ብቻ ሳይሆን የምንኵስናን ዓላማ ተረድተው የመነኰሱትን መርጠን ጵጵስና እንድንሾም ያግዘናል።
ዋቢ መጻሕፍት
- ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፣ አማርኛ የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ቅጽ ፩። አዲስ አበባ፣ ፲፱፻፷፱ ዓ.ም።
- ዝኒ ከማሁ፤
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፍትሐ ነገሥት። ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ ፲፱፻፹፱ ዓ.ም።