የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ዮናታን እስር

የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ዮናታን እስር

የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ዮናታን እስር

ሊቀ ጳጳስ ዮናታን በዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተልኪና ብራስላቭ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው። የሀገሪቱ መንግሥት ዩክሬን የምትመራበትን ወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 109፣ 110፣ 161 እና 436 (2) በመጥቀስ በአራት ወንጀሎች ጠርጥሬያቸዋለሁ በማለት ክስ ይመሠርትባቸዋል። ጉዳዩን በአግባቡ ለመረዳት ሊቀ ጳጳሱ የተከሰሱባቸው የወንጀል ሕጉ ድንጋጌዎች ምን ምን እንደሚሉ አስቀድመን እንመለከታለን።

  • አንቀጽ 109 በዐመጽ ለውጥ ለማምጣት ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማስወገድ ወይም በኃይል ሥልጣን ለመያዝ የሚፈጸሙ ተግባራት
  • አንቀጽ 110 – የዩክሬንን ሉዓላዊ የግዛት ወሰን ማለፍ ወይም ዳር ድንበሯን ለመለወጥ አስቦ መሥራት
  • አንቀጽ 161 – ዘርን፣ ሃይማኖትን እና ዜግነትን መሠረት በማድረግ ልዩነት መፍጠር
  • አንቀጽ 463 (2) – የጦርነት ፕሮፖጋንዳ መንዛት (ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን የኃይል ወረራ አይቀበሉም፣ ለሕጋዊነቱ ዕውቅና ሰጥተዋል፤ የሩሲያ ወታደሮችን አድንቀዋል) የሚሉ ናቸው።

ለክሱ መነሻ የሆነው በራሪ ወረቀቶችን በማሰራጨት የዐመጽ ጥሪ አድርገዋል የሚል ነው። ነገር ግን ለአስረጅነት የቀረቡት በራሪ ወረቀቶች በማንና መቼ እንደ ተዘጋጁ ዐቃቤ ሕግ በማስረጃ ያረጋገጠው ነገር የለም። ይህም ሆኖ ግን የቪኒሺያ ከተማ ፍርድ ቤት ነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ሊቀ ጳጳስ ዮናታን የአምስት ዐመት እስር እንዲፈጸምባቸው እና ንብረታቸው እንዲወረስ ውሳኔ አስተላልፏል።

ከውሳኔው በኋላ የዩክሬን ቤተ ክርስቲያን ሕግ መምሪያ የሊቀ ጳጳሱ መታሰር የዩክሬን ሕገ መንግሥት፣ የወንጀል ሕጉን እና ሥነ ሥርዓት በመጣስ የተፈጸመ መሆኑን ገልጿል። ስለ ሕገ ወጥነቱም ሲያብራራ ብዙ መረጃዎች የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓቱን ባልተከተለ መንገድ እንደተካተቱ ይህም ከዩክሬን የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት አንቀጽ 291 እና ከዩክሬን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 62 ጋር የሚቃረን መሆኑን ገልጿል። ዐቃቤ ሕግ በሌለው ሥልጣን በመጥሪያ ወረቀቱ ላይ መፈረሙ፣ ሊቀ ጳጳሱን እንደ መንግሥት ባለሥልጣን መቁጠሩ፣ ዐቃቤ ሕግ ሙከራ አድርገዋል ካለ በኋላ ወንጀሉን እንደፈጸሙ አድርጎ ክስ ማቅረቡ እርስ በርሱ የሚጣረስ መሆኑ፣ ለክሱ መነሻ የሆኑት በራሪ ወረቀቶች ቤታቸው በተበረበረበት ወቅት የተገኙ ናቸው ተብለው ቢቀርቡም በወቅቱ ስለመገኘታቸው መርማሪዎቹም ሆኑ ምስክሮች ያላስረዱና በቀረጻውም ወቅት ያልታዩ መሆናቸው፣ መቼና በማን የተዘጋጁ እንደሆነ ባልተረጋገጡ ወረቀቶች ላይ መመሥረቱ እና ያለ ምንም ማስረጃ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 161 መጥቀሱ ሌሎች የክሱን ሒደት አግባብነት የሌለው የሚያደርጉ ማሳያዎች መሆናቸውን ይጠቅሳል።

የዩክሬን መንግሥት ከየካቲት 2014 ዓ.ም ጀምሮ በዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ላይ 65 ክሶች መሥርቷል። 19 ካህናት ደግሞ የዩክሬን ዜግነታቸውን ተነጥቀዋል። ከእነዚህም መካከል ሊቀ ጳጳስ ዮናታን አንዱ ናቸው። ሊቀ ጳጳሱ በትውልድ የዩክሬን፣ የሩሲያና የቤላሩስ ዝርያ ያላቸው ሲሆን ከ1991 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ጀምሮ የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መለየት የለባትም በሚል አሳብ አቅርበው ነበር። በዚህም ምክንያቱ በወቅቱ የኬቭና መላው ዩክሬን ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ፊላሬት (በአሁኑ ሰዓት ከሩሲያ የተገነጠለው የዩክሬን ቤተ ክርስቲያን መሪ) ጋር በመጋጨታቸው ከአገልግሎት ታግደው ቆይተዋል። በ1992 ዓ.ም ሊቀ ጳጳስ ፊላሬት ተወግዘው በምትካቸው ሊቀ ጳጳስ ቭላድሚር የኬቭና መላው ዩክሬን ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሲሾሙ እገዳቸው ቀኖናዊ እና ሕጋዊ ሆኖ ስላልተገኘ ተሽሯል።

ከ2022 ጀምሮ እየተካሄደ በሚገኘው የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ሊቀ ጳጳስ ዮናታን ቀድሞ በነበራቸው አቋም ብዙ ግፎች ሲፈጸምባቸው ቆይቷል። ሊቀ ጳጳሱ የ74 ዐመት አዛውንት ከመሆናቸውም በላይ በተደጋጋሚ የቀዶ ጥገና ሕክምና የተደረጉላቸው የኢንሱሊን ተጠቃሚ ናቸው። ዜግነታቸውን በመነጠቃቸው ምክንያት የጤና መድኅን መብት እና ሕጋዊ ከለላ ተነፍጓቸዋል። ዜግነታቸው እንዲነጠቅ የተደረገው በዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ዜለንስኪ ቀትተኛ ትእዛዝ ነው። ስለሆነም ክሳቸው የሕግ መተላለፍን መሠረት ያደረገ ሳይሆን ፖለቲካዊ ጫና ያጠላበት መሆኑን መረዳት ይገባል። ይህም በዐለም አቀፍ ደረጃ ኦርቶዶክሳውያን ላይ የተከፈተው ጥቃት አንዱ ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ነው። በእኛ ሀገር በኦርቶዶክሳውያን ላይ የሚፈጸመውም የዚህ ተመሳሳይ ነው።

የሊቀ ጳጳሱን እስር ተከትሎ በጉዳዩ መልእክት ያስተላለፉት የሩሲያው ፓትርያርክ ቄርሎስ “በሊቀ ጳጳስ ዮናታን ላይ የተላለፈው እስር ሊቀ ጳጳሱ ለቤተ ክርስቲያን እና ለክርስቶስ ታማኝ በመሆናቸው ጫና ውስጥ ለመክተት ታስቦ የተደረገ ነው” ብለዋል። አክለውም ሊቀ ጳጳስ ዮናታን እንደ ማንኛውም የቤተ ክርስቲያን አባት ስለ ሰላም የሚጸልዩ፣ የሩሲያን መንፈሳዊ  አንድነት የሚናፍቁ፣ መከፋፈልን የሚጸየፉ እና የዩክሬንን ቤተ ክርስቲያን ጥቅምና መብት ለማስከበር የሚተጉ ናቸው” ብለዋል። ከዚህ የምንረዳው በፖለቲካ ግፊት የዩክሬንን ቤተ ክርስቲያን ከሩሲያ ቤተ ክርስቲያን ለመገንጠል በሚደረገው ሒደት ሊቀ ጳጳሱ ዮናታን “እንቅፋት” ሆነው የተገኙ መሆናቸውን ነው። ሊቀ ጳጳሱ በአገልግሎታቸውና በመንፈሳዊ አባትነታቸው በመልካም አርአያነት የሚጠቀሱ ቢሆንም ያለ በቂ ምክንያት ለእስር መዳረጋቸው ዓለም የጸና እምነት ያላቸውን ኦርቶዶክሳውያን እያሳደደች ለመሆኑ አንድ ማሳያ ነው።