“የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል ያድናቸውማል።” መዝ 33:7
👉 ይህን ኃይለ ቃል የተናገረው ልበ አምላክ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ነው። በግልጽ እንደነገረን የእግዚአብሔር የሆኑት ቅዱሳን መላእክት የሚያድኑ አዳኞች ናቸው። እነርሱን ከሚፈሯቸውና ከሚያምኗቸው ሰዎች አይለዩም። ከሚደርስባቸው መከራ እና ችግር ፈተና ሁሉ ያድኗቸዋል ይታደጓቸዋል። ቅዱሳን መላእክት የሰው ልጆችን የሚያድኑ አዳኞች መሆናቸውን ቅዱስ ያዕቆብ ዮሴፍንና ልጆቹን በባረከ ጊዜም እንዲህ ሲል መስክሯል። “ከታናሽነቴ ጀምሮ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር ከክፉ ነገር ሁሉ #ያዳነኝ_መልአክ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ።” ዘፍ 48:15
👉 እሱም ብቻ አይደለም የሰው ልጅ አምላክ በፈጸመለት የማዳን ተግባር ውስጥ የቅዱሳን መላእክት ሱታፌ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገልገል የሚላኩ የሚያግዙ መናፍስት አይደሉምን?” ብሎ የሰው ልጅ እንዲድን የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት እና እገዛ የግድ እንደሚያስፈልገው ተናግሯል። ዕብ 1:14 እንዲሁም የሰው ልጅ የመዳኑ ነገር ለቅዱሳን መላእክት ታላቅ ደስታ መሆኑን ጌታ በወንጌል እንዲህ በማለት ተናግሯል። “እላችኋለሁ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።” ሉቃ 15: 7
👉 ቅዱሳን መላእክት በተጨነቅን እና በተቸገርን ጊዜ በጸሎት ስንጠራቸው መጥተው ያበረቱናል ያረጋጉናል። ጌታችን በመዋለ ሥጋዌው ለእኛ አርአያ አብነት ይሆነን ዘንድ በምሴተ ሐሙስ መከራን ከመቀበሉ በፊት ሲጸልይ “ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታው መልአክ ታየው።” ይላል። ሉቃ 22:43 የመላእክት ፈጣሪያቸው እርሱ ሆኖ ሳለ የሚያበረታው መልአክ ታየው መባሉ ስለምንድን ነው ቢሉ እናንተም በጨነቃችሁ በጠበባችሁ መከራ ውስጥ በገባችሁ ጊዜ ብትጸልዩ ቅዱሳን መላእክት እናንተን ለማበርታት ይላካሉ ሲለን ነው።
👉 ቅዱሳን መላእክት ስለ ሰው ልጆች ዘወትር በአምላክ ፊት ያማልዳሉ። እግዚአብሔርም ምልጃቸውን ቸል አይልም። ዘካ 1:12–13 “የእግዚአብሔርም መልአክ መልሶ። አቤቱ፥ የሠራዊት ጌታ ሆይ፥ እነዚህ ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው? አለ። እግዚአብሔርም መልሶ ከእኔ ጋር ይነጋገር ለነበረው መልአክ በመልካምና በሚያጽናና ቃል ተናገረው።” እንዲል። መልአኩ እግዚአብሔርን አሳዝነው 70 ዓመት ለተቆጡት እስራኤል ዘሥጋ ከለመነ፤ በቅዱሳን መላእክት ለታመንን እስራኤል ዘነፍስ ለሆንን ለኛ እንደምን አይማልዱም? እነርሱም ዘውትር በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ፣ የእግዚአብሔርንም ፊት ያያሉ። ማቴ 18:10 ኢዮ 1:7 ሉቃ 1:9 “የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና።” እንዲል የቅዱሳን መላእክትንም ምልጃቸውን ይቀበላል። መዝ 33(34):15
በተጨማሪም #ቅዱሳን_መላእክት
👉 አጽናኞቻችን ናቸው። ዳን 10:20
👉 ይረዱናል። ዳን 10:13
👉 ይጠብቁናል። መዝ 90:1
👉 እንሰግድላቸው ዘንድ ይገባል። ኢያ 5:14 ዘፍ 19:1 ራዕ 19:10 ራዕ 22:8
በየዓመቱ ሰኔ 12 ቀን የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል የሚታሰብ ሲሆን በዚህ ዕለት መልአኩ የባሕራንን የሞት ደብዳቤ ወደ ሕይወት የቀየረበትና ቅድስት አፎምያን ከሰይጣን ያዳነበት ዕለት ነው። ከመልአኩ ከቅዱስ ሚካኤል ረድኤት በረከት ያሳትፈን።
ይቆየን።
አዘጋጅ አቤኔዘር ማሙሸት (ወልደ ተክለ ሃይማኖት)