ፍኖተ-ጎርጎርዮስ

ፍኖተ-ጎርጎርዮስ

የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አባቶች የኤጲስ ቆጶስነት መንበሩ የሚጠይቀው መንፈሳዊ ሕይወትና የትምህርት ዝግጅት እያላቸው፣ ትእምርታዊ ገድል እየተጋደሉ፣ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ተልእኮ በፍጹም ፍቅር እየፈጸሙ እና በተግባር እየኖሩት ሹመቱን ግን እንደ ጦር ሲፈሩት ኖረዋል፡፡ ሽሽታቸው አፍአዊ እንዳልነበረ ለዚህ ዘመን የሚተርፍ ጥብዓታቸውን በዚህ ጽሑፋችን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ወሳኝ የታሪክ አንጓዎች ላይ እየተከሠቱ በቃልና በኑሯቸው በተራራ ላይ እንዳለች መብራት ሲያበሩ የኖሩት አበው ከሢመት የመሸሻቸው ምክንያቱ ከልብ የመነጨ ትሕትና ነበር፡፡ በልብ ‹‹ምን አማራጭ አላቸው ዙረው ዙረው እኔው እግር ላይ ተደፍተው መለመናቸው አይቀርም፤›› ከሚል ራስን የትምክህት ማማ ላይ ሰቅሎ በአፍኣዊ ግን ትሑት መምሰልን ከመሻት የሚቀዳ ሽሽት አልነበረም፡፡ የራስን ዐቅም በትሑት ሰብእና መዝኖ፣ በማንኛውም ሥጋ ለባሽ ልብ ውስጥ ቦታ ያለውን ከፍ ያለ ሥልጣን የማግኘት መሻትን ተዋግቶ በመግራት የሚደረስበት ውሳኔ ነው፡፡

ከሢመት የሸሹት አበው በእርግጥም ፍቅረ ሢመትን ከውስጣቸው አውጥተው የጣሉ መሆናቸውን የሚያስረግጡልን መንፈሳዊና ታሪካዊ ድርሳናት ብዙ ናቸው፡፡ ሕዝቡ ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋር ተመካክሮ ሊያሾማቸው ወደ በዓታቸው ሲመጣ ከሹመት ይልቅ አካላቸውን በማጉደል በምነና መኖር ቁርጥ ውሳኔያቸው መሆኑን አሳይተዋል። ከሹመት ለመራቅ ጆሯቸውን እስከ መቁረጥ የደረሱ አሉ፡፡ ምላሳቸውን እስከ መዘልዘል እንደሚጨክኑ ቁርጠኛ አቋማቸውን በማሳወቅ ከኤጲስ ቆጶስነት በታች ባሉ መዓርጋት እያገለገሉ ለመኖር ያላቸውን ቁርጠኛ መሻት መራጮቹም ሿሚዎቹም ዐውቀው እንዲተውአቸው አድርገዋል፡፡ ተገድዶ የወጣበትን ጵጵስና ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ሥምረት አብዝቶ የተጠቀመበትና ኋላም ሢመትን በውዴታ የተሰናበታትን ነባቤ መለኮት ቅዱስ ጎርጎርዮስን ለአብነት እናንሣ፡፡

ሕዝበ ክርስቲያኑ የቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙን ትምህርቱን ሰምተው ግብሩን ዐይተው ሲወዱት ኖረዋል፡፡ ወላጆቹን በተለይ በእርግና ዘመን ላይ የነበረ አባቱን ጠይቆ ለመመለስ ወደ ወላጆቹ በሔደበት አጋጣሚ በሕዝቡ ግፊት ሥልጣነ ክህነት እንዲቀበል ተደረገ፡፡ እርሱ ግን ገዳማዊ ሕይወትን እጅግ ወድዶ ነበርና ጠፍቶ ከልብ ባልንጀራው ባስልዮስ ዘቂሣሪያ ጋር በብሕትውና ወደሚኖርበት ገዳም ሔዶ ተደበቀ፡፡ የቃልም የሕይወትም መምህር ነበር፤ በአንዲት በዓት ረጅም ጊዜ በጾም በጸሎት በመወሰን የሚታወቅ ገዳማዊ አባት፡፡ በትምህርትም ዓለማዊውን ትምህርት ከቂሣሪያ እስከ አቴና በመጓዝ በግሪክ ፍልስፍና የተራቀቀ፣ በመንፈሳዊው ትምህርትም ከሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በኋላ ነባቤ መለኮት (ታኦሎጎስ) እስከ መባል የደረሰ የነገረ መለኮት ሊቅ ነበር፡፡

በኋላ ግን የእንዚናዙ ሀገረ ስብከት ማኅበረ ምእመናን፣ የአባቱና በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ጥሪ ስለበዛበት ተመልሶ በክህነት አገልግሎት አባቱን ሲራዳ ቆየ፡፡ በኋላም የልብ ባልንጀራው ቅዱስ ባስልዮስ ታላቁ የሳሲማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አድርጎ ሾመው፡፡ እርሱ ግን የእንዚናዙ ሀገረ ስብከት ኤጲስ ቆጶስ የነበረው አባቱ ጎርጎሪዮስ (Gregory the Elder) በጣም ሸምግሎ ስለነበር እርሱን በአገልግሎት መርዳት ሲል ወደ ተሾመበት ሀገረ ስብከት ሳይሔድ በእንዚናዙ ቆየ፡፡

ቤተ ክርስቲያን በቁስጥንጥንያ በአርዮሳውያን ቁጥጥር ሥር ልትገባ አደጋ ላይ መሆኗን ከሚገልጽ መልእክት ጋር ቁስጥንጥንያን እንዲታደግ ለቅዱስ ጎርጎሪዮስ ከቁስጥንጥንያ ሲኖዶስ ጥሪ ቀረበለት፡፡ ጥሪውን ተቀብሎ ወደ ቁስጥንጥንያ በማምራት አርዮሳውያንን በጥብዓት ተዋጋ፡፡ ብዙዎችን በቀናች ሃይማኖት አጸና፤ በማጥመቅ ላይ እያለ በድንጋይ እስኪ ወግሩት ድረስ መከራን ተቀበለ፡፡ ከዚህ ሁሉ ተጋድሎ በኋላ ለቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ እንዲሆን የእግዚአብሔር ጥሪ መጣለት፡፡ አሁንም በማኅበረ ምእመናንና ጳጳሳት የበዛ ተማጽኖ ሀገረ ስብከቱን በመተው የምሥራቅ ሮም ማእከል ወደ ነበረችው ቁስጥንጥንያ ሔዶ የፕትርክና መንበሩን ተረከበ፡፡ የቁስጥንጥንያ ፓትርያርክ ሆነ፡፡

በ፫፻፹፩ ዓ.ም. በቁስጥንጥንያ የተካሔደውን ሁለተኛውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ በሊቀ መንበርነት እንዲመራ የተመረጠው እርሱ ነበር፡፡[1] ጉባኤውን ከፍቶ ለተወሰኑ ቀናት በርእሰ መንበርነት መርቷል፡፡ በኋላ ግን ዘግይተው የደረሱት የግብጽ እና የመቄዶንያ ጳጳሳት ቅዱስ ጎርጎርዮስን ሀገረ ስብከቱን ለቅቆ በሌላ መንበር ላይ መሾሙን ከኒቂያ ቀኖና ጠቅሰው ተቃወሙ፡፡ ምንም እንኳ ክሱ አግባብነት ባይኖረውም ቅዱስ ጎርጎሪዮስ ግን ለታላቅ ዓላማ የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከእርሱ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጊዜ ማጥፋት እንደሌለበት ያመነ ይመስላል፡፡ ተቃውሟቸውን ትክክል እንደሆነ በመቀበል ፓትርያርክነቱን በፈቃዱ ለቀቀ፡፡[2] አቡነ ጎርጎሪዮስ ከጉባኤው ሊቀ መንበርነት መልቀቁን ተናግረው ከቁስጥንጥንያ ፓትርያርክነቱ ስለ መልቀቁ ግን ምንም አያነሡም፡፡[3]

በዚህ ዘመን ከዚህ መልካም የትሕትና ፍኖት የሚጓዙ ኖላውያን ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ይደልዎ ተብሎላቸው የተሾሙ ነገር ግን ፍቅረ ሥልጣን ፍትወት ሆናባቸው፣ ከቀደመ ሰብእናቸው ጋር በሚቃረን አዲስ ማንነት የተገለጹ አባቶችን ማየት ተለምዷል፡፡ ከዓላማቸው ፈቀቅ፣ ከተልእኳቸው ገሽሽ ሲሉ፣ ይሠራሉ ሲባል ሲያፈርሱ፣ ያርማሉ ሲባል ሲያበላሹ የታዩ ብዙ ናቸው፡፡ ወደ ልባቸው እንዲመለሱ ‹‹ኧረ በሥላሴ›› የሚል ተምጽኖ ሲመጣ እዛ ቦታ ላይ ያስቀመጣቸውን አምላክ እንደረሱ የሚያሳብቅ ትምክህት የተጫነው መልስ የሚሰጡም አልታጡም፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ግን ከእነርሱ እንደ አንዱ አልሆነም፡፡ ልቡን እልከኛ አድርጎ(ዕብ. ፫፥፲፫) አምነውበት፣ ለምነው ለሹመት ያስገደዱትን ምእመናንን ተስፋ አላስቆረጠም፤ በእነርሱ አድሮ የመረጠውን መንፈስ ቅዱስ አላሳዘነም፡፡

ቅዱሱ ድሮም ሥልጣንን በእሺታ የተቀበለው እግዚአብሔርን ለማገልገል እና ሥልጣኑን ተጠቅሞ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ተልእኮ ለማስፈጸም ከነበረው ቀና ሐሳብ የተነሣ ብቻ ነበር፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያን መረጋጋት፣ ሰላም እና ፍቅር ሲል መንበሩን ለመልቀቅ ወሰነ፡፡ በመሰናበቻ ንግግሩ ራሱን ከነብዩ ዮናስ ጋር በማነጻጸር ለመርከቧ(ለቤተ ክርስቲያን) ሲል ራሱን ወደ ባሕር ለመጣል ዝግጁ መሆኑን በይፋ ገለጸ፡፡ ባሕሩ ውስጥ መልካም ዓሣ አንበሪ እንደሚቀበለው ተስፋው ጽኑ መሆኑን ተናግሮ፣ ጉባኤተኞች ለቤተ ክርስቲያን የሚበጀውን እንዲያደርጉ አደራ ብሎ ሊቀ መንበርነቱን ለቀቀ፡፡ ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላም ወደ ቀድሞ የብሕትውና ሕይወቱ ተመለሰ፡፡[4]

የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያንም ቅዱስ ጎርጎርዮስን መሰል አባት አጥብቃ ትፈልጋለች፡፡ ለሰላሟ ሲል ራሱን ወደ ባሕሩ የሚወረውር(ሥልጣኑን የሚለቅ፤)፣ ለመንፈሳዊ ተልእኮዋ ስኬት ዕንቅፋቱን የሚያነሣላት፣ ዕንቅፋቱ እኔ ነኝ ብሎ ካሰበ ራሱ ላይ ለመፍረድ ወደ ኋላ የማይል አባት ትፈልጋለች፡፡ የያዘው ሥልጣን የእግዚአብሔር መሆኑን የማይረሳ፣ የተጠራበት ተልእኮ የሚጠይቀውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅቶ የሚኖር፣ ፍኖተ ጎርጎርዮስን ፍኖቱ ያደረገ አባት ትፈልጋለች፡፡

ሰዋዊ ባሕርያችን ስኬታችን እንጂ እንከናችን አይነገር ባዮች እንድንሆን ገፊ ምክንያት ነው፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ በሓላፊነት ወንበር ላይ የተቀመጡት ብቻ ሳይሆኑ ከልሒቅ እስከ ደቂቅ ስሕተትን በሌላ ስሕተት ማረም አዋጭ ስልት ተደርጎ ተይዟል፡፡ ይህ ሥጋዊ ጠባይ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የተዋቀረበትን መንፈሳዊ መርሕ ጥሶ ገብቷል፡፡ በፈሪሐ እግዚአብሔር ላይ የተመሠረተውን ሥነ ምግባር አንቆ ይዞ አስጨንቆታል፡፡ ዋጋን በሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ እቀበላለሁ የማለትን ተስፋ አመንምኖታል፡፡ እንደ ቅዱስ ጎርጎሪዮስ እነርሱ ሊከሰሱበት በማይገባ ጉዳይ ይቅርና ፀሐይ የሞቀው፣ ሀገር ያወቀው ጥፋታቸው በቤተ ክርስቲያን ላይ ለፈጠረው ሁከት እንኳን የመፀፀት ምልክት የማይታይባቸው እረኞች በዝተዋል፡፡ በምእመናን ሐዘንና ዕንባ በኩል የእግዚአብሔርን ድምፅ ሰምተው እንደ ቅዱስ ጎርጎሪዮስ በፀፀት ራሳቸውን ወደ ባሕር የሚወረውሩ አባቶችን አልተመለከትንም፡፡ ይህ ሐቅ ነው ፍኖተ ጎርጎርዮስ በዚህ ዘመን እጅግ ከባድ ግን ደግሞ አስፈላጊ ዕሴት መሆኑን የምንገነዘበው፡፡

በዚህ በእኛ ዘመን በቅዱስ ጎርጎርዮስ መንገድ የሚሔድ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ዋና ምክንያቱም እንደ ክርስቶስ ሎሌዎችና የእግዚአብሔር ምሥጢር መጋቢዎች አድርጎ በተቀበላቸው ሕዝብ ፊት ለተጠሩበት የታመኑ አገልጋይ አባቶችን ማግኘት እየከበደ ስለመጣ ነው(፩ኛ ቆሮ. ፬፥፪፤ ዕብ. ፫፥፭)፡፡ የቅዱስ ጎርጎርዮስ መንገድ ራስን መግዛት ይጠይቃል፤ የቅዱስ ጎርጎርዮስ ፍኖት ኤጲስ ቆጶስነትን እንደ ሥልጣን ሳይሆን እንደ ሓላፊነት የሚመለከት ሥነ ልቡና ያለው አባት ሆኖ መገኘትን ይጠይቃል፤ ፍኖተ ጎርጎርዮስ መንፈሳዊ ሹመቱን በፍጹም የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ ምንጭ አድርጎ የማያይ መረዳት ያለውን አባት ይሻል፡፡ ሥልጣን የሚወልደውን ተአብዮ በትሕትና ሰይፍ የቀላ አባት ሆኖ መገኘትን ይፈልጋል-ፍኖተ ጎርጎርዮስ፡፡

ኤጲስ ቆጶስነት ከፍ ያለ ሰማያዊ ሽልማት የሚያስገኝ የአገልግሎት ቀንበርን መሸከም እንጂ የመደብ ደረጃን ከፍ የሚደረግበት መዓርግ አይደለም፡፡ ዕለት ዕለት በደሙ የዋጃት ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ፣ ያለመታከት ለተሾሙለት ለመንጋው ሁሉ እና ለራስ የጽድቅ ሕይወት የሚጠነቀቁበት ሕይወት ነው፡፡ ይህን አብዝቶ የተገነዘበው ቅዱስ ጎርጎርዮስ የእርሱ ሥልጣን፣ የነገ ዕጣ ፈንታው አላሳሰበውም፡፡ ለጽድቅ ከተረከበው ሓላፊነት ጉያ ሥር የተተቸበትን ጉዳይ ለመመከት የሚረዳው ጋሻደብቆ አልተገኘም፡፡ በእልኸኝነት ጽድቅን የተራበች ነፍሱን ያጎሳቁላት ዘንድ አልወደደምና የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ሰላም አስቀደመ፡፡

ዛሬም ምእመናን አባቶቻቸው ጳጳሳትና ለኤጲስ ቆጶስነት የሚመረጡት መነኮሳት በዚህ የቅዱስ ጎርጎርዮስ መንገድ ሲሔዱ ማየት ይሻሉ፡፡ እንኳን ጵጵስናቸው ይቅርና ሕይወታቸውም የእግዚአብሔር እንደ ሆነች ዕለት ዕለት እያስታወሱ ቅድሚያ ለሰማያዊው ጉዳይ የሚሰጡ አባቶች እንዲሾሙ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ ይፈልጋሉ፡፡ የእውነት ዐርበኞች ሁነው ልናገኛቸው፣ የእግራቸውን ትቢያ ስመን ልናከብራቸው እንጓጓለን፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን አባቶች ግን ጵጵስናን ከገበያ ሊገዙ ወይም በዘውግ መረብ ሊያጠምዱ ከሚደክሙት መካከል በፍጹም አናገኛቸውም፡፡

የቤተ ክርስቲያንን ሰማያዊ አገልግሎትየሚያውክ፣ የሰላም አምላክን የምትሰብከውን ቤተ ክርስቲያን ሰላም አልባ ያደረገ አሠራር ተዘርግቶ ከሆነ መመርመር ይገባል፡፡ ትሑት ሆኖ ራሱን ወደ ባሕሩ የሚወረውር ቅዱስ ጎርጎርዮስን ያጣች ቤተ ክርስቲያን ጅራፍ የያዘ አምላኳን የማስተናገድ ግዴታ ይወድቅባታል፡፡ የትኛው አሠራር ቤተ ክርስቲያን ከውስጥ ያለዕረፍት እንድትታመስ ያደረጋትን ብልሹ አስተዳደራዊ ሥርዐት እንዳሰፈነ ተለይቶ መታወቅ አለበት፡፡ የተበላሸው አሠራር ጠበቃዎች እነማን እንደሆኑ ሰከን ተብሎ መመርመር ግድ የሆነበት ሰዓት ላይ ተደርሷል፡፡ ይህን ሐቅ መመርመርና ማረም ካልተቻለ ማለባበሱ ቤተ ክርስቲያንን ከመንፈሳዊ ተልእኮዋ ያሰናክላታል እንጂ የሚበጃት ፍኖት አይሆንም፡፡

ቅድሚያ የሚሰጡት የግል ጉዳያቸው ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ የመሰናክል ድንጋይ የሆነባቸው የበዙበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ቢችል እንደ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ራሱን ወደ ባሕር የሚጥል (ስለ ሰላሟ ሥልጣን የሚለቅ) ካልቻለ ቢያንስ እንደ ዮናስ ‹‹ማዕበሉ በእኔ ምክንያት መጥቷልና እኔን ጣሉኝ፤›› የሚል ለመርከቧ ደኅንነት የሚቆረቆር አባት ያስፈልገናል፡፡ እንዲህ ዓይነት አበው ሲበዙ አርአያነታቸው ለትውልድ ይተርፋል፡፡ የጵጵስና መንፈሳዊ ልዕልና ይጠበቃል፡፡ የጠመመውን ለማቅናት፣ የፈረሰውን ለመጠገን ዕድል ይገኛል፡፡ ፍኖተ ጎርጎርዮስ አብዝተው የሚያተርፉበት የቅድስና ፍኖት ነው፡፡

የአባቶቻችን ጥርጥር የሌለባት እምነታቸው፣ ክህደት የሌለባት ሃይማኖታቸው፣ የከበረች በረከታቸው፣ ድል የማትነሣ ረድኤታቸው ከእኛ ጋር ትሁን፡፡

ዋቢ መጽሐፍት

[1]ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑዔል (2005 ዓ.ም.)፤ ጠቅላላ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ(አንደኛ መጽሐፍ)፤ ገጽ 404)

[2]ዝኒ ከማሁ

[3]አባ ጎርጎሪዮስ(፲፱፻፸፰ ዓ.ም.)፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፤ ገጽ ፻፳፰

[4]ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል (2005 ዓ.ም.)፤ ገጽ 404)