መንፈሳዊ በዓል ለማክበር በወጡ ኦርቶዶክሳውያን ላይ የሚደርስ ጥቃትን አጥብቀን እንቃወማለን
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በአደባባይ ከምታከብራቸው በዓላት መካከል አንዱ የሆነውን የጥምቀት በዓል እና የቃና ዘገሊላ በዓልን በመላ ሃገሪቱ በሚባል ደረጃ በሠላም ለማክበር የተቻለ ሲሆን ለዚህ ደግሞ ቤተክርስቲያኒቱ እና አማኞቿ በጋራ ላሳዩት ኦርቶዶክሳዊ ሥነ ስርዓትና ለጸጥታ ኃይሉ ባሳዩት መልካም ትብብር ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።
ጥር 12 ቀን 2014 ዓ.ም በየሺ ደበሌ አካባቢ በምትገኘው የወይብላ ማርያም ታቦትን አክብረው በሚጓዙ ካህናት ፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና አዛውንት፣ ጎልማሳና ወጣት ምዕመናን ላይ ለጸጥታ ማስከበር ስራ በተሰማራ የጸጥታ አካል ኃይል የተሞላበት ጥቃት ምክንያት የደረሰው ችግር በተደጋጋሚ አንድ አካባቢ ሆነ ተብሎ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን የሚፈጽሙ ክርስቲያኖችን ከማወክ አልፎ ለሞት መዳረጉ በቤተክርስቲያናችን ላይ የሚደርሰውን በደል የሚያሳይ ኢ፟-ሰብአዊ እና ኢ-ፍትሃዊ ድርጊት በመሆኑ የሰንበት ት/ ቤቶች አንድነት በጽኑ ይቃወማል።
ተመሳሳይ ድርጊት ባለፈው ዓመትም የተከናወነ በመሆኑ ካለፈው ተመክሮ በመነሳት ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን እና የጸጥታ አካላት ጋር በዓሉ በሰላም ለማክበር ሰፊ ውይይት በማድረግ ሁሉም ድርሻውን ለመወጣት ኃላፊነት ተወስዶ በዚያ መልኩ እንዲፈጸም ተደርጓል። ነገር ግን ችግሩ በቦታው ዘንድሮም በድጋሚ መፈጠሩ በአጋጣሚ የተፈጠረ ክስተት ሳይሆን የመንግስትን ስልጣን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚያጠቁ አካላት ለመኖራቸው ትልቅ ማሳያ በመሆኑ መንግስት አስቸኳይ ማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ፣ እንዲሁም በድርጊቱ በቀጥታ የተሳተፉና ትዕዛዝ በመስጠት ያስፈጸሙ አካላትን በሕግ አግባብ እንዲጠየቁና ውጤቱን ለህዝቡ ይፋ እንዲያደርግ እያሳሰብን፣በዚህ ሂደት ለተፈጠረው ችግር የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጽን በቀጣይ ሙሉ ሂደቱን እና ቀጣይ ሥራዎችን የምናሳውቅ መሆኑን እንገልጻለን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!!
የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት
ጥር 13 ቀን 2014 ዓ.ም