ቤተ ክርስቲያን ምን ዓይነት አመራር ያስፈልጋታል?
ቤተ ክርስቲያን ትውልዱን ለእግዚአብሔር መንግሥት የማዘጋጀት ሰማያዊ ተልእኮዋን በአግባቡ ለመወጣት እና የነገውን ትውልድ ሰብእና በመቅረፅ ረገድ የሰብአዊ ምሕንድስና ሥራዋን ለመፈጸም ዘመኑን የዋጀ አመራርና አሠራር ያስፈልጋታል። ይህም መሻት በብዙ ኦርቶዶክሳውያን ልብ ውስጥ አለ፡፡ ይህ ዕውን ይኾን ዘንድ ዛሬም ኾነ ነገ ቤተ ክርስቲያን ስንዱ እመቤት የሚያሰኛትን የነገረ ሃይማኖት ጥንቃቄ በአስተዳደርና በአመራርም መድገም ስትችል ነው። ቤተ ክርስቲያን በምድር ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ናትና መሠረታዊ መገለጫዎቿ ተጠብቀው ብቻ በምትሰጣቸው የአመራርነት ሚናዋ ተገልጠው ሊታዩ ይገባል። ይህን ዕውን ማድረግም በየዘመኑ የሚነሡ ኖላውያን እና ምእመናን የሁል ጊዜ ሓላፊነት ነው፡፡
በተለይም ቤተ ክርስቲያን ከውጭና ከውስጥ ተገዳዳሪዎች ጋር በተፋጠጠችበት እና እንደ ኢዮብ በፈተና በተከበበችበት በዚህ ዘመን የአሳዳጆቿን በትር መቋቋም የምትችለው በምትሰጠው ውጤታማ አመራር ነው። ፈተናውን ከባድ የሚያደርገው ከውጪው ተጽእኖ በላይ በውስጥ ያለው መንፈሳዊነት መዳከም እና ብልሹ የአስተዳደር ሥርዐት መስፈን ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በጥንቱ መንፈሳዊ ልዕልናዋ ጸንታ እንድትቆም ማስቻል እና በዘመኑ የአስተዳደር ጥበብ የተዋጀ አሠራር የሰፈነባት መንፈሳዊ ተቋም ማድረግ በሁለቱ ተገዳዳሪዎቿ የተሴረባትን ሴራዎች ማምከኛ መንትያ መንገዶች ናቸው፡፡
በማይታበል ሐቅ ቤተ ክርስቲያን ስንዱ እመቤት ናት፡፡ ለእኛ የደረሰችው ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ኾና የተገኘችው ግን ሥራ በፈቱ ጭንቅላቶች፣ ለህልውናዋና ልዕልናዋ ግድ የማይሰጥ ሰብእና ባላቸው አልፎ ሒያጅ የግዴለሽነት ስሜት ባሸነፋቸው መሪዎች እየተመራች አይደለም፡፡ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ነው ብለው፣ ነፍሳቸውን ስለበጎቻቸው በሰጡ መሪዎች ነው። ቀዳምያቱንና መጻዕያቱን በመረዳት፣ ያሉበትን ዘመን በመዋጀት፣ ደሀ ተበደለ ፍረድ ተጓደለ የሚል ቋሚ የፍትሕ ርትዕ ቅርስ ባላቸው አባቶች ነው። የቅርቦቹን እንኳ ብናስታውስ ልጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን ምድራቸውንም በቅኝ እንዳይገዙ በመገዘት የአገራቸውን አሸናፊት በሩቅ ተሳልመው ያለፉት ሰማዕተ ጽድቅ አቡነ ጴጥሮስ አንዱ ናቸው። ሌላው ኮሚኒስታዊው መንግሥት ደርግ ቤተ ክርስቲያን የነበራትን ማኅበረሰባዊ መሠረት በማናጋት ከድህነት አረንቋ ለመጣል በሠራበት ወቅት ሩቅ አልመው ሁሉንም አሳታፊ የሆነ መዋቅር በመዘርጋት ቤተ ክርስቲያንን የታደጉት አቡነ ቴዎፍሎስን መጥቀስ ይቻላል። የቤተ ክርስቲያን ስንዱነት እንዲሁ ተሠርቶ አልቆ እንደ መና ከሰማይ የወረደ ጸጋ ሳይሆን ዋጋ የከፈሉ፣ የተሰጣቸውን መንፈሳዊ ጸጋና የማስተዋል ጥበብ ለሐዋርያዊ ተልእኳቸው ሥምረት የተጠቀሙበት አባቶች ስለነበሯት ነው፡፡ እናም ይህ ሐቅ ቤተ ክርስቲያንን ስንዱ እመቤት አሰኝቷታል፡፡ ይህ የአበውና እማት ብርታት ኢትዮጵያ ከነሐዋርያዊ እምነቷ ለዚህ ዘመን እንድትደርስ አስችሏታል፡፡
አሁን ጥያቄው “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዘመን ከመንፈሳዊ መሠረቷ ሳትናወጽ የማኅበረሰብን እሴት ከመቅረፅ ጀምሮ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የነበራትን በጎ ተጽእኖ ማስቀጠል ወደምትችልበት ቁመና መመለስ የሚቻለው በምን ዐይነት አመራር ነው?›› የሚል ነው፡፡ በቤተ ክህነቱ ውስጥ ነግሠው በሚታዩ መንፈሳዊ ድክመቶችና ከክርስትና መርሕ ጋር በሚጋጭ የዘውገኝነት በሽታ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ በኾኑ አስተዳደራዊ ዝቅጠቶች ምክንያት ቤተ ክርስቲያን በመስቀለኛ መንገድ ላይ አቁመዋታል። በመሆኑም በዚህ ዘመን የተነሡ ጥያቄዎችን፣ ያጋጠሙ ፈተናዎችን እና የተጋረጡ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ወደ ትክክለኛው መንገድ ለመቀጠል የሚያስችል አመራር ያስፈልጋል። የሚሰጡ ግብረ መልሶች ተገቢነት ብቻ ሳይኾን መልሶቹ የሚሰጡበት ፍጥነትም የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና በማስጠበቅ ረገድ ወሳኝነት አለው፡፡
መንፈሳዊ ጉድለቶችን በማስተካከል፣ አስተዳደራዊ ሥርዓትን በማዘመን፣ አሳታፊና ተደራሽ የሆነ አሠራር በመዘርጋት፣ ሕግና ሥርዓትን የተከተለ የሰው ሀብትና የፋይናንስ አስተዳደር ዕውን በማድረግ ያስፈልጋል። በተለይም ወደላይኛው መዓረግ የሚመጡ አባቶች የሚመረጡበት ጥብቅ መስፈርት በማስቀመጥ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት የአሿሿም ሥርዓት፣ የምእመናንን ሱታፌ ያማከለ ጥቆማ እና እግዚአብሔርን ያስቀደመ ምርጫ በማድረግ ይደልዎ የሚባሉ አባቶችን ብቻ መሾም ይገባል። ወደ ነገ ለመሻገር እንደ ጥንቱ አባቶቻችን ዘመናችንን የሚቀድስ አመራር ማግኘት ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ነው፡፡ ይህን ሓላፊነት የሚሸከም አመራር ምን ዓይነት አመራር መሆን ይገባዋል?
- ዘመኑን የዋጀ የአገልግሎት ሥርዓት (የነበረና ያለ እሴትን በዘመናዊ የቴክኖሎጂና የሥርዓት ውጤቶች መደገፍ)
- ከፕትርክና ጀምሮ እስከ ምንኩስና ድረስ ቀኖናዊ ሥርዓቱን የጠበቀ መስፈርት
- አርአያነት ያለው መንፈሳዊ ሕይወትን፣ ሙያንና ሥነ ምግባርን መሠረት ያደረገ የሰው ሀብት ምደባ አስተዳደር ሥርዓት
- የተማከለ የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት
- ምእመናንን፣ ባለድርሻ አካላትን እና ሁሉንም መዋቅሮች የሚያሳትፍ አሠራር
- በኦርቶዶክሳውያን ባለሙያዎች ሙያዊ ምክር የሚመሩ የቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች (ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ)
- በታወቀና በተጻፈ ሕግ የሚመራ ቤተ ክህነት
- የሚያሠራ፣ ፍትሐዊና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሕግ
- የልሕቀት ማእከል የሆኑ ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ዕውን የሚያደርግ አሠራር
- የቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ለሆነው ሐዋርያዊ ተልእኮ እና ለምእመናን ቀኖናዊ ሕይወት ቅድሚያ የሚሰጥ አመራር ሊኖር ይገባል። ይህ ደግሞ ሊሳካ የሚችለው ለዚህ አመራርነት የሚመጥኑ አባቶች በቦታው ሲቀመጡ ነው።