እንኳን ደስ አለዎ ወይስ እግዚአብሔር ያስችልዎ?

እንኳን ደስ አለዎ ወይስ እግዚአብሔር ያስችልዎ?

እንኳን ደስ አለዎ ወይስ እግዚአብሔር ያስችልዎ?

ኤጲስ ቆጶስነት ምቾትን አብዝቶ ለሚሻው፣ አድልኦንና ወገንተኝነት ለሚስማማው ለሥጋ ጠባይ የሚመች ሓላፊነት አይደለም፡፡ ሰዋዊ ባሕርይን ገርተው የነፍስ ባሕርይን ገንዘብ ወደሚያደርጉበት ማዕርግ የሚሰግሩበት ራስን በመካድ መሠረት ላይ የቆመ የእግዚአብሔር ጥሪ ነው፡፡ ክህነት ትሑት ሰብዕናን የሚሻ የአገልግሎት ሥልጣን ነው፡፡ አንዱን ከሌላው አስበልጠው ለመጥቀም፣ ያልተደሰቱበትን ደግሞ ከሌላው በታች አድርገው ለመጉዳት ለቂም መወጫነት ዐስበው የሚሹት በትረ ሥልጣን አይደለም፡፡ የቂም በትር ወይም የድሎት መወጣጫ እርካብ ላድርግህ ቢሉት ባለቤቱ እውነተኛው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ (ዕብ. ፯፥፳፰) መክሊቱን የጠየቀ ዕለት መሸሸጊያ ጥግ ይጠፋል፡፡ እናም ኤጲስ ቆጶሳት አገልግሎታቸውን የሚፈጽሙት እውነተኛ ዳኝነት የባሕርይው በሆነ በእግዚአብሔር ፊት መሆኑን ለአፍታ መዘንጋት እንደሌለባቸው ቤተ ክርስቲያን አበክራ ታስገነዝባለች፡፡

አገልግሎቱ ብርቱ ሰልፍ ከመሆኑ የተነሣ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት ለዚህ አገልግሎት የተሾመን አባት ‹‹እግዚአብሔር ያስችልዎ፤›› እንጂ ‹‹እንኳን ደስ አለዎ፤›› አይሉትም፡፡ እንኳን ደስ አለዎ፣ እንኳን ለዚህ አበቃዎ በማለት ከደስታው የሚካፈሉት በኋላ ነው፤ በአገልግሎቱ ለጽድቅ አክሊል የሚያበቃ ፍሬ አፍርቶ ሲገኝ፡፡ ያኔ ሰውም መላእክትም ያሸበሽቡለታል፡፡ የተጋድሎው ታሪክ በአፍ ለመጭው ትውልድ እየተነገረ፣ በመጽሐፍ ተጽፎ ዝክረ ስሙ እየተወሳ ገድሉ ዐዲስ መንፈሳዊ ዐርበኛ የሚያፈራ ለም መሬት ይሆናል፡፡

በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በርካታ ቅዱሳን አበው ለኤጲስ ቆጰስነት ሢመት የተገባን አይደለንም ብለው ሥልጣንን አምርረው ሲሸሹ በተደጋጋሚ ታይተዋል፡፡ የእስክንድርያው ፓትርያርክ ቅዱስ አትናቴዎስ ከአራተኛው ክፍለ ዘመን የቤተ ክርስቲያን ፈርጦች ውስጥ ከቀዳሚዎቹ የሚመደብ ነው፡፡ ትምህርቱ፣ መንፈሳዊ ቅንዓቱ፣ ተጋድሎው እና አጠቃላይ አባትነቱ ሐዋርያዊ የሚል ቅጽል አጎናጽፎታል፡፡ ገና በወጣትነቱ ፓትርያርኩን እለ እስክንድሮስን ተከትሎ በኒቂያ ጉባኤ በመገኘት በጥልቅ የነገረ መለኮት ዕውቀቱ አርዮስን ተከራክሮ የረታው፣ አትናቴዎስ በተባሕትዎ አኗኗሩም ይታወቃል፡፡ ዛሬ ድረስ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚቀበሉትን እና የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ዋና መግለጫ የሆነውን ጸሎተ ሃይማኖት ለኒቂያ ጉባኤ አርቅቆ ያቀረበ ሊቅ ነው፡፡ ዕውቀት ከሕይወት ስምም ያሉለት ባሕታዊው ሊቅ አትናቴዎስ ፓትርያርክነት አይገባኝም ብሎ ሸሽቶ ተደበቀ፡፡ እለ እስክንድሮስም በሞት አፋፍ ሆኖ ‹‹አትናቴዎስ ሆይ አንተ ልትሸሽ ትፈልጋለህ፤ ሸክሙ ግን ከአናት ትከሻ አይወርድም›› ብሎ አንቀላፋ፡፡[1]

የቀጰዶቅያ አባቶች (Capadocian Fathers) ኦርቶዶክሳዊውን የምሥጢረ ሥላሴን ትምህርት አስፍተው በማስተማር ይታወቃሉ፡፡ስለ አንድነት እና ሦስትነት ትምህርት ጠንካራ መሠረት ያስቀመጡ ዐቃብያነ እምነት ናቸው፡፡ እነዚህም ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ እና ሁለቱ ወንድማማቾች ባስልዮስ ዘቂሣርያ እና ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ናቸው፡፡ ጥልቅ የነገረ መለኮት እና የፍልስፍና ዕውቀታቸው፣ ነቀፋ የሌለበት ክርስቲያናዊ አኗኗራቸው አስገራሚ ነበር፡፡ እነዚህ ቀደምት አበው ቅድስናን፣ ሊቅነትንና በትጋት ለወንጌል አገልግሎት መገዛትን ብቻ አይደለም የሚጋሩት፡፡ ሁሉም ሢመተ ጵጵስናን ሸሽተው የመደበቅ የጋራ ታሪክም አላቸው፡፡ ከሸሹበት ተፈልገው፣ በሕዝበ ክርስቲያኑ እና በካህናቱ ፈቃድ ይደልዎ ተብለው በግዴታ ለኤጲስ ቆጶስነት ተሹመዋል፡፡ ተገደው የተቀበሏትን ሢመት ደግሞ ከፍ ባለ መሥዋዕትነትና በውዴታ ሲያገለግሉባት፣ አገልግለውም በእጅጉ እንዳተረፉባት የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይመሰክርላቸዋል፡፡[2]

ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ ከአይሁድና አረማውያን የሚወረወሩ የኑፋቄ ቀስቶችን ጋሻ ሁነው የሚመክቱ በሺሕ የሚቆጠሩ የዕቅበተ እምነት መጻሕፍትን፣ የዝማሬና የምስጋና ድርሰቶችን በመጻፍ ዕድሜ ዘመኑን ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግል ኖሯል፡፡ በዚህ አገልግሎቱ ብቻ ሳይሆን ጵጵስናን ሲሽሽ በመኖርም ይታወቃል፡፡ ቀደምት አበው ለጳጳስም ብቻ ከተሰጠው ምሥጢራት በስተቀር ቆላ ወርደው፣ ደጋ ወጥተው የጳጳሱን ሥራ እየሠሩ፣ አፍ ከጸሎት ልብ ከጸጸት ሳይለያዩ በመንፈሳዊ ተጋድሎ አብነት የሚሆን አኗኗር ነበራቸው፡፡ ሢመቱን ግን ለሌላው አሳልፈው ይሰጡ ነበር፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ለጵጵስና እንዲሾም ሁለት ጳጳሳት ተልከው ወደ ቂሣሪያ ሊወስዱት መጡ፡፡ በጳጳሳቱ ፊት አእምሮውን እንደሳተ፣ የሚሠራውን እንደማያውቅ ሕመምተኛ መስሎ ታዬ፡፡ እነርሱም በእርሱ ዘንድ ለጵጵስና የሚያበቃ ጤነኛነት አጥተው ተመለሱ፡፡

አበው ሽሽት መታዘዝን ከመጥላት አይደለም፡፡ ነቀፋ ታይቶባቸው ወይም ለቦታው የሚመጥን ትምህርት ጎድሏቸውም አልነበረም፡፡ የሽሽታቸው አመክንዮ ከእኔ ይልቅ ወንድሜ ቢሾም የበለጠ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ሥራ ይሠራል ከሚል ክርስቲያናዊ ትሕትና ነው፡፡ ጵጵስና ጸጋቸውን፣ ትምህርታቸውን እና ክህሎታቸውን ተጠቅመው ከፍ ባለ ደረጃ እግዚአብሔርን ለማገልገል እንደሚረዳቸው ያውቃሉ፡፡ ሓላፊነት ይህን ለማድረግ የሚያስችል ዕድልን ይሰጣልና፡፡ ነገር ግን በመንበሩ ላይ ተቀምጠን ሐዋርያት በሔዱበት ፍኖት ለመሔድ የሚያበቃ ጸጋ ባይኖረን እግዚአብሔርን እናሳዝናለን ከሚል ፍርሐት ይሸሹታል፡፡ ሐዋርያውያን አበው የተጋደሉትን ገድል መጋደል ባንችልና ነቀፋ ቢገኝብን በመስቀል ላይ ስድባችንን የተሰደበው አምላክ ዳግም በእኛ ምክንያት ሊሰደብ አይገባም በሚል ምክንያት ሹመትን ይርቁታል፡፡ መንበሩ መከራን ይጠራል፤ መከራውን በአኮቴት የምንቀበልበት ትዕግሥትና ጽናት አጥተን ቀራንዮ ላይ ክርስቶስን አላውቀውም ከሚሉት መካከል መገኘትን ይጠላሉ፡፡ በእኛ ስንፍና ሐሳዊ ምእመንነት ምክንያት እውነተኛው አምላካችን ይናቅብናል ከሚል ትሕትና እና ሥጋት ሹመትን ይፈሩታል፡፡ ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ በትሑት ልብ ለክብረ ክህነት የሚመጥን ሕይወት የለኝም ብሎ ራሱን ዝቅ በማድረግ ከሥልጣነ ክህነት ይሸሽ ነበር፡፡ አስገድደው ቅስና ሰጡት፡፡ በ፫፻፸ ዓ.ም. የቂሣርያ ጳጳስ እና የመላው ቀጵዶቅያ ሊቀ ጳጰስ ሆኖ የተሾመውም በልብ ወዳጁ በቅዱስ ጎርጎሪዮስ ዘእንዚናዙ እና በአባቱ ከፍተኛ ግፊትና ተግሣጽ ነበር፡፡[3]

እነኛ ደጋግ አበው ጵጵስና በደጅ ቆማ ደጋግማ በራቸውን ታንኳኳላቸው ነበር፡፡ እነርሱ ግን መልስ አይሰጧትም፡፡ አኗኗራቸው ቅድስና በሚያሰጥ ልዕልና ላይ ነበር የሚገኘው፡፡ ጳጳስ የሚቀበለውን ተልእኮ ተሸክመው አኗኗሩን ተላብሰው በማስተማር ረገድ ከቆላ ደጋ ወጥተው ወርደው፣ መናፍቃንን በአፍ በመጣፍ እየረቱ መኖር የለመዱት ነበር፡፡ ምሥጢራትን ከመፈጸም በስተቀር ጳጳስ የሚሠራውን የወንጌል አገልግሎት ሥራ እየሠሩ ሹመትን ግን አጥብቀው ይሸሿት ነበር፡፡

በታሪክ ገጾች ወደ ኋላ ተመልሰን የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ከመናፍቃኑ ትምህርትና ኑፋቄ፣ ከነገሥታቱ ጣልቃ ገብነት ጠብቀው ያቆይዋትን አባቶች የአገልግሎት ጥብአት እንደ አብነት ተመለከትን፡፡ በዚህ በእኛ ዘመንም በቀደሙት አበው አሠረ ፍኖት ተጉዘው ኤጲስ ቆጶስነትን ሲሸሹዋት የታዩ አባቶች አሉ፡፡ ነገር ግን በሚያስወግዝ ሲሞናዊው ፍኖት ተጉዘው ሢመትንሊቃርሟት የሚተጉትበዝተው ብዙ ክርስቲያኖችን ድንጋጤ ላይ ጥለዋል፡፡ ድግስ ደግሰው፣ አስኬማ ገዝተውና አርዌ ብርትአሠርተው ከፍ ባለ የፍቅረ ሢመት መንፈስ ሲታዩ በእርግጥም ያስደነግጣል፡፡ ሰማያዊ ዜግነታቸው ባገኙበት የጥምቀት ልጅነታቸው ላይ ካላቸው ትምክህት ይልቅ በምድራዊ ዘውጋቸው የተደገፉ መነኮሳት ለሹመት ከፊት ተሰልፈው ሲታዩ መደንገጥ ትንሹ ነው፡፡ ከፈጣሪያቸው ፈቃድ ይልቅ በባለ ሥልጣናት እጅ የተጻፈ ጦማርን ተማምነው ለሹመት የተሰለፉት በዝተው እውነተኞቹን ሸፈኗቸው፡፡ ይሁንና ያን ዘመን ብቻ በታሪክ እየተረክን እንዳንኖር በዘመናችን ህያው አብነት ሊሰጠን የወደደ የቤተ ክርስቲያን አምላክ እግዚአብሔር ሹመትን ሸሽተው በየበኣታቸው የተሠወሩ አባቶችን በዚህ በእኛ ዘመንም ዐሳይቶን ተስፋችንን ሲያለመልም ምስክር ሆነናል፡፡

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት የሚኖሩት አባ ገብረ ሥላሴ ተስፋ አንዱ ህያው አብነት ናቸው፡፡ አባ ገብረ ሥላሴ በቅዱስ ፓትርያርኩ ነው የተጠቆሙት፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት ፲ ቀን በ፳፻፱ ዓ.ም. ባደረገው ምርጫ ለኤጲስ ቆጶስነት ከመረጣቸው 16 ዕጩዎች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ እርሳቸው ግን ‹‹የጀመርኩት ሥራ አለብኝ፤ ከዚህ በላይ ሓላፊነት ለመጨመር ብቁ አይደለሁም፡፡ በተሰጠኝ የክህነት ሥልጣን ከሠራሁበት ይበቃል፤›› በማለት ሹመቱን ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡ ይህ የሆነው ገና ትናንት ነው፤ ታሪኩ የተከተበበት ቀለም እንኳ በቅጡ አልደረቀም፡፡ አፍቃሪያነ ሢመት በበዙበት ዘመን መናንያነ ሢመት የሆኑ አበውን በማግኘታችን ተደንቀን ነበር፡፡ ነገር ግን እርሳቸው ይህን በመሰለ መንፈሳዊ ትሕትና ከሢመት በሸሹበት ዓመት ተቃራኒውንም መታዘባችንን አንረሳም፡፡ በደጅ ጥናት ያስጻፉትን የባለሥልጣን ጦማር እንደ አሕዛብ ሰይፍ እያወዛወዙ ያስፈራሩ በነበሩ መነኮሳት ድርጊት ኦርቶዶክሳውያን አዝነዋል፡፡ ጣራ የነካ ፍቅረ ሢመት ከሌላ አታወዳድሩኝ ሲያስብላቸው ተመልክተናል፡፡ የፍትሕን አምላክ ለማገልገል ለተዘጋጁት የሚሰጠውን ሀብተ ክህነት ያለ ፍትሕ ሲወስዷት ለታሪክ ተጽፏል፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሚገለጥበትን ዕጣም እኔ ጋ እንዳይሞከር በማለት መለኮታዊ ጣልቃ ገብነትን ሲቃወሙ ዐይተን ተሸማቅቀናል፡፡

አንዱ የሸሻትን የኤጲስ ቆጶስ ሢመት ሌላው ሊጨብጣት ሲያሳድዳት ታዝበን በተቃርኖው ተገርመናል፡፡ በፍቅረ ሢመት የነደዱ አንዳንድ መነኮሳት ላገለግለው እወዳለሁ በሚሉት አምላክ ፊት ፈቃዱን ለመጠየቅ አደግድገው ሳይሆን እንኳን ደስ አለዎ ለመባል ድግስ ደግሰው ታዩ፡፡ ጥሞና ወስደው፣ ‹‹ለዚህ አገልግሎት የመረጥከኝ ባሪያህ ሆኜ ብገኝ እነሆኝ እኔን ላከኝ፤›› ማለት በሚገባቸውና በጸሎት መጠመድ በሚገባቸው ሰዓት ድግስ ደግሰው እንኳን ደስ አለዎ የሚል ታዳሚ ጠርተው የተሰለፉትን ልብ ያለ ስለ ቤተ ክርስቲያን ማልቀሱ አይቀርም፡፡

አሁንም በሒደት ላይ ባለው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የሕዝበ ክርስቲያኑን ቋንቋ እና ሥነ ልቡና የሚያውቁ አበውን መርጦ መሾም ለሰማያዊው ተልእኮ አስፈላጊ እና እንደ መቅድም ነው፡፡ ነገር ግን ከትምህርትና ከመንፈሳዊነት ጉድለት የተነሣ በሕዝቡ ፊት የቤተ ክርስቲያን ልሳን መሆን የማይችሉ ጦማረ ነገሥትን እያውለበለቡ ወይም በሲሞን መዶሻ ደጀ ሰላሙን ሰብረው እንዳይገቡ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኗ ዋነኛ ተልእኮ የእግዚአብሔርን መንግሥት መስበክና ለሰማያዊ ዜግነት ማዘጋጀት ነውና፡፡ ትውልዱ በሚያውቀው ቋንቋ የሚሰብኩለትን ብቻ ሳይሆን የሰበኩትን ኑረው የሚያሳዩት ራሳቸውን የተግባራዊ ክርስትና ቤተ ሙከራ ያደረጉ ለባውያን መምህራን እንዲኖሩት ይፈልጋል፡፡ በሥልጣን ጥማት የተቸገሩ ከአገልግሎት ጥብአት ጋር የተላለፉ ሲሾሙ ሲኖዶስም ልዕልናውን ማስጠበቅ ቤተ ክርስቲያንም ተልእኮዋን ማሳካት ዳገት እንደሚሆንባቸው ማስታወስ ይገባል፡፡

የቤተ ክርስቲያን አምላክ ‹‹እንኳን ደስ አለዎ፤›› ለመባል ሳይሆን ‹‹እንዲያስችለኝ  ጸልዩልኝ›› የሚሉ ብቁ ኤጲስ ቆጶሳትን እንዲሰጠን እንጸልይ፡፡

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!

ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም.

 

ዋቢ መጻሕፍት

[1]ዲ. ያረጋል አበጋዝ (2000 ዓ.ም.)፤ ቅዱስ አትናቴዎስና ሐዋርያዊ ሕይወቱና ትምህርቱ፤ ገጽ 26፤

[2]ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል(2005 ዓ.ም.)፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በምድር ላይ፤ አንደኛ መጽሐፍ፤ ገጽ 397፣ 402፣403፤

[3]ዝኒ ከማሁ