‹‹በበጎነት ላይ ዕውቀትን ጨምሩ›› ፪ኛ ጴጥ. ፩፥፭-፯
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምነው ከተከተሉት መካከል ጥቂቶችን መረጦ ሐዋርያትን ሾመ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በእረኛውና በመንጋው መካከል ላለው መስተጋብር መሠረት አስቀመጠ፡፡ የዛሬዎቹ አበው ጳጳሳት እና ካህናት የዚህ ሐዋርያዊ ውርስ ተቀባዮች ናቸው፡፡ በሐዋርያነት የተሾሙት ለተጠሩበት ሐዋርያዊ አገልግሎት ስኬት የሚያስፈልጋቸውን ሥነ ምግባርና ዕውቀት ከጌታ በነቢብም በገቢርም ተምረዋል፡፡ ዛሬም ድረስ ለተጠሩበት አገልግሎት የሚመጥን ሥነ ምግባር እና ትምህርት (ዕውቀት) የሢመተ ጵጵስና ሁለት ምሰሶዎች ናቸው፡፡
ሥነ ምግባር፡- የክርስትና የሥነ ምግባር መሠረት እግዚአብሔርን በመፍራት ላይ የቆመ ነው፡፡ በፈሪሐ እግዚአብሔር የተገራች ነፍስ ከክርስትና ዕሴት ጋር የማይጋጭን የትኛውንም ሕግና ሥርዐት ለማክበር አትቸገርም፡፡ በዚህ የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ መሠረት ላይ ጸንቶ የቆመ አባት በጎቹን በትክክለኛው ፍኖት መምራት አይሳነውም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ለኤጲስ ቆጶስነት የተገባ ሰብእና ምን ዓይነት መሆን እንዲገባው በዝርዝር የገለጻቸውን ጠባያት (፩ኛ ጢሞ. ፫፥፩) የሚያሟላ ሆኖ ይገኛል፡፡ ምእመናኑም ‹‹ይገባዋል ይገባዋል›› ብለው አባትነቱን በደስታ ይቀበላሉ፡፡ ሊቀ ጳጰሳቱም ተቀመጥ በወንበሬ ተናገር በከንፈሬ በማለት በደሙ የተዋጀችውን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዲጠብቅ ኤጲስ ቆጶስ አድርገው ይሾሙታል፡፡ መምህርነቱ የቃል ብቻ ሳይሆን የሕይወትም ነውና፡፡ በቀንም በጨለማም፣ በቤትም በደጅም በሕግና በሥርዐት እየኖረ ማኖር የሚያስችለውን ትልቁን ዕሴት ገንዘብ አድርጎ አግኝተውታልና፡፡ ይህ እረኞች በኑሮ ፍሬያቸው በጎቻቸውን ወደ ለመለመ መስክ፣ ወደ ዕረፍት ውኃ የሚያሰማሩበት የሕይወት መምህርነት እንደ ሥዕል ነው፡፡ ከብዙ የቃል ትምህርት ይልቅ እጅግ አትራፊ ነውና፡፡
ጠቢቡ ‹‹መኮንን ሐሰተኛ ነገርን ቢያዳምጥ ከእርሱ በታች ያሉት ሁሉ ዓመፀኞች ይሆናሉ›› (ምሳ. ፳፱፥፲፪) እንዳለ እረኛው ኤጲስ ቆጶሱ ከአሿሿሙ ጀምሮ አርአያሆኖ ባይገኝ በሚመራው መንጋ ላይ የሚፈጠረውን አጠቃላይ ቀውስ መረዳት አይከብድም፡፡ ፈሪሐ እግዚአብሔርን የሚያስተምሩ እግዚአብሔርን ባለመፍራት ውስጥ ሆነው ሲገኙ ቀውሱ ከባድ ነው፡፡ የማስታረቅ አገልግሎት በእነርሱ ላይ ያኖረባቸው አበው እርስ በእርስ ለመታረቅ ሽማግሌ ሲያስፈልጋቸው ካየን የኑሯቸው ፍሬ መምረር ጀምሯል ማለት ነው፡፡ መለኮታዊውን ሥልጣነ ክህነት በመለካዊ መሥመር ሔደው ገንዘብ ሊያደርጉት ሲደክሙ ከተመለከትን የሰብእና መታመም እንዳለ እንረዳለን፡፡
በበጎነት ላይ ዕውቀትን ጨምሩ፡- ሥልጣነ ክህነት ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ሰጭውም እርሱ ነው፡፡ ይህ ሰማያዊና መለኮታዊ ሥልጣን የሚገባቸው ደግሞ ተገቢው ትምህርትና ክህሎት ያላቸው አገልጋዮች ናቸው፡፡ ሐዋርያት ከተጠሩበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ድረስ ከጌታ ሳይለዩ ከአንደበቱ፣ ከተአምራቱና ከተግባሩ ተምረዋል፡፡ እንዲያውም ከጌታ ደቀ መዛሙርት ብዙዎቹ ከመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት ጀምሮ ቃሉን ሲማሩ የቆዩ ናቸው፡፡ በኋላም የመምህራቸውን ምስክርነት ተቀብለው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተከተሉ፡፡ በጌታ መምህርነት ከተማሩ በኋላ ነው በዓለም ሁሉ ምስክሮቹ ይሆኑ ዘንድ በሐዋርያነት የተሠማሩት፡፡
‹‹ሕዝቤ ዕውቀትን ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷልና…›› (ሆሴዕ ፬፥፮) እንደተባለ ዓለም በመስቀል ላይ የተከፈለለትን ዋጋ፣ የፈሰሰለትን ደም ባለማወቅ እየኖረ ነው፡፡ የምሥራቹን ያወቀውም ባወቀውና በተማረው መጽናት ተስኖት በምግባር ጠፍቷል፡፡ ይህ በነብዩ ሆሴዕ የተነገረው ተግሣጽ እግዚአብሔር አገልጋዮቹ ካህናት ምን ዓይነት ሰብእና እንደሚጠበቅባቸው በግልጽ የተናገረበት ነው፡፡ ቃሉን ያለማወቅና በቃሉ ያለመኖር ድካምን ከሕዝቡ ያስወግዱ ዘንድ፣ ከጥፋትም ይታደጉት ዘንድ ወደ ዓለም የሚልካቸው መልእክተኞቹ የእርሱን ዕቃ ጦር የታጠቁ እንዲሆኑ እንደሚሻ ጠንከር ባለ ቃል ተናግሯል፡፡
እዚህ ላይ ዕውቀት ሲባል ተናግሮ አመሥጥሮ፣ መክሮና ገሥጾ ማስተማሩን ብቻ ማለቱ አይደለም፡፡ ካህኑ በትምህርት ላሳመናቸው ልጆቹ በሕይወትም አርአያ ሆኖ፣ ከሥነ ምግባር ርካብ ሳይወርዱ ወደ ሰማያዊ ርስት መምራት የሚችልበትን ዕውቀትና ክህሎትም እንዲኖረው ይፈለጋል፡፡ ይህን ዕውቀት፣ ይህን ምግባር፣ ይህን ክህሎት ንቀሃልና ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ ይላል እግዚአብሔር፡፡ እነዚህን ሀብቶች ገንዘብ ልታደርግ ካልወደድህ እኔም ግልገሎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን አሰማራ ብዬ አደራዬን ባንተ ላይ ላስቀምጥ አልወደድሁም አለ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በጠቢቡ ‹‹ጥበብን የወደደ ሰው አባቱን ደስ ያሰኛል፤›› (ምሳሌ ፳፱፥፫) እንደተባለ ለተዘጋጀበት ሢመት የሚመጥን ጥበብ መንፈሳዊን፣ ጥበብ ሥጋዌን ይዞ የተገኘ ደግሞ ባለቤቷ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆነላት ሥልጣነ ክህነት ማረፊያ አግኝታለችና ጥበብን ወድዶ በፈለጋት ካህን ደስ ይሰኝበታል፡፡
ዛሬ በእኛ ዘመን ይህችን የኤጲስ ቆጶስነት ማዕርግ ደጅ የሚጠኗት መነኮሳት በዝተው እናያለን፡፡ እኛም ‹‹ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል፤›› (፩ኛ ጢሞ. ፫፥፪) ተብሏልና ያለ ነቀፋ ለበለጠ አገልግሎት ራሱን ያዘጋጀ ካለ እንቃወመው ዘንድ አይቻለንም፡፡ ነገር ግን ከእነርሱ መካከል በቃሉም በሕይወቱም ለምእመናን መምህር የሆነ፣ እግዚአብሔር እንዳይንቀው፣ ምእመናን እምነት እንዳያጡበት ሁኖ የተዘጋጀ አባት እርሱ ማን ነው? ብለን እንጠይቃለን፡፡ ምክንያቱም የዕውቀትም የሕይወትም መምህርነት ጸጋ ነው፡፡ ያለ እነዚህ ጸጋዎች በኤጲስ ቆጶስነት ሥልጣን የሚሾሙ ቢኖሩ ስሕተታቸው ቤተ ክርስቲያንን ዋጋ የሚያስከፍል፤ ስንፍናቸው የቤተ ክርስቲያንን ዕድገት ያደናቅፋል፡፡
ምእመናን ሕግጋተ እግዚአብሔርን የሚማሩት በዋናነት ከኤጲስ ቆጶሱ፣ ከካህኑ ከናፍር ነው፤ የእግዚአብሔር እንደራሴ ነውና፡፡ እርሱም የተማረ፣ ያወቀ፣ መጻሕፍትን ባልንጀራው ያደረገ መሆን አለበት፡፡ በዕውቀቱ የታመመች ነፍስን የሚፈውስበት መድኃኒት ከቃለ እግዚአብሔር ይቀምማል፡፡ እየመጠነ ለግልገሎቹ፣ ለጠቦቶቹና ለበጎቹ ይሰጣል፡፡ ኤጲስ ቆጶስ ዘወትር በትጋት ከመጻሕፍት ምዕራፍና ቁጥሩን እየጠቀሰ፣ አንቀጹን እየተረጎመ ምእመናንን የሚያስተምር መሆን እንዳለበት ፍትሕ መንፈሳዊ ይደነግጋል (አንቀጽ ፭)፡፡ በኤጲስ ቆጶስነት ሊያገለግለው ወድዶ ነገር ግን እንደተገለጸው ዐውቆ ልቆ ያልተገኘን አገልጋይ እግዚአብሔር እንዲህ ይለዋል፤ ‹‹ዕውቀትን ጠልተሃልና እኔም ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤›› (ሆሴዕ ፬፥፮)
ኤጲስ ቆጶሱ ከአፉ በሚወጣ ቃል ብቻም አይደለም፤ ዕለት ዕለት እግዚአብሔርን በመምሰል እየኖረ በተግባራዊ ክርስትና ‹‹እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ፤›› (፩ኛ ቆሮ. ፲፩፥፩) የሚል የሕይወት ትምህርት ያስተምራል፡፡ እንዲህ ያለ በቃልና በሕይወት (በምግባር) የማስተማር ዕውቀትና ጸጋ የሌለው ማንም ቢሆን በመሻቱ ብቻ ኤጲስ ቆጶስነትን ሊያገኛት የተገባ አይደለም፡፡ ቢያገኛትም መለኮታዊውን ሥልጣን መለካዊ አድርጓታልና የነፍስ ዋጋ የምታስገኝ አትሆንለትም፡፡
እግዚአብሔር ሕዝቡን ይመሩ ዘንድ የወደዳቸውን ኖሎት አንድም በሕዝበ ክርስቲያኑ በኩል ይደልዎ ይደልዎ አስብሎ አልያም እንደ ድሜጥሮስ ድንግል በተኣምራት ክብራቸውን ገልጦ ይሾማቸዋል፡፡ በሁለቱም የአመራረጥ መንገዶች ማዕከላዊው ጉዳይ ሕዝቡ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ያለው በጎቹን በበጎነት እና በዕውቀት ወደ ለምለም መስክ በሚያሰማሩለት እረኞች ላይ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ትውፊት ለኤጲስ ቆጶስነት የሚሾመው ሰው ዕውቀት ከምግባር ስምም ያሉለት መሆን እንዳለበት አብዝቶ የሚታመነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ምእመናንን ‹‹ይደልዎ፣ ይደልዎ… ይገባዋል፣ ይገባዋል›› የሚያስብላቸው እነዚህን ዕሴቶች ከመነኮሴው ዘንድ ማግኘታቸው ነው፡፡
አንዳንዴ በበጎነት ላይ ዕውቀትን የጨመረ፣ ያለነቀፋ የሚኖር አባት ማግኘት ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ ዓለማዊነት ገዝፎ፣ ሥነ ምግባር ደቅቆ በታየበት ዘመን በጎላ ነገር ሁለቱን አስተባብሮ የያዘ አባት ተፈልጎ ሊታጣ ይችላል፡፡ ያኔ ምግባር ኖሮት ዕውቀት የጎደለውን ግዴለም ትምህርቱን ይማረዋል፣ ይሁን ብለው ለኤጲስ ቆጶስነት ይሾሙታል፡፡ በጸሎቱና በረድኤቱ የጎሰቆለውን የምእመናን ሕይወት ያክማል፡፡ መናፍቃን ጎልብተው አማናዊቷን መርከብ በኑፋቄ ትምህርታቸው በሚያውኩበት ዘመን ላይ ምግባር ቢጎድለው በዕውቀቱ መናፍቃኑን ተከራክሮ ይረታልናል ብለው ይሾሙታል፡፡ ይህ ሹመት በዕውቀት ላይ ራስን መግዛት እየጨመረ ወደ ዋናው የሥነ ምግባር ዓላማ እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ይደርሳል በሚል ተስፋ የሚሰጥ ሹመት ነው፡፡
ይህ ይትባህል ለኤጲስ ቆጶስነት ማዕርግ ምግባር እና ዕውቀት መሠረት መሆኑን ያሠምርበታል፡፡ ሹመቱም የተሿሚውን ፍቅረ ሹመት ሳይሆን የሚሾምላቸውን ክርስቲያኖች ፍላጎትና ሁኔታ ያገናዘበ መሆን እንደሚገባው በግልጽ ያስረዳል፡፡ ከዚህ ተነሥተን የዘመናችንን ሢመተ ጵጵስና አካሔድን ስንመዝን ብዙ ጊዜ ማዕከሉ ራስን በሹመት ወንበር ላይ የማስቀመጥ ፍላጎት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ መሻት ውስጥ ደግሞ በፈሪሐ እግዚአብሔር ላይ የቆመ ሥነ-ምግባርንም ሆነ ቤተ ክርስቲያኗን የመረዳት ዕውቀትና የአስተዳደር ክህሎትን አናገኘውም፡፡ ይህ ሲባል ግን በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያናችን ለኤጲስ ቆጶስነት የተገባ ልጅ ከመውለድ መክናለች ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ምግባር ከዕውቀትና ክህሎት ጋር የተስማማላቸውን አባቶች እጅ መንሻ ይዘው ለሹመት ከተሰለፉት መካከል ማግኘት መቻሉ በጣም ያጠራጥራል፡፡ የነገሥታትን ማዘዣ ደብዳቤ ይዘው ሹመትን እያሳደዷት ካሉት መካከል በመንጋውና በካህናቱ ይገባቸዋል የሚባልላቸውንማግኘት ያስቸግራል፡፡
ሹመቱን ይፈልጉታል፤ አገልግሎቱ የሚጠይቀውን መስፈርት ለሟሟላት ግን መድከም አይፈልጉም፡፡ ቢያንስ እንኳ አንዱን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምረው ለማስመስከር ጊዜ የላቸውም፡፡ ታዲያ ዋነኛ ተግባሩ ማስተማር የሆነውን የኤጲስ ቆጶስነት ሥልጣን አብዝተው የሚፈልጉት ምን ሊያስተምሩት ነው?መማር የሚጠይቀውን ውጣ ውረድ ለመሸከም ጽናት ይጎድላቸዋል፤ ታዲያ በሰይፍ ስለት ላይ እንደ መራመድ የሚከብደውን ሐዋርያዊውን ተልእኮ እንዴት ሊፈጽሙት ይሆን?ይህ ለትምህርትም ለትሩፋትም ታካች የሆነ ልብ ኤጲስ ቆጶስነትን በዝምድና፣ በገንዘብ፣ በብሔረሰባዊ ማንነት ተከልሎ በአቋራጭ ሊቆጣጠራት ሲያደባ ይታያል፡፡ በዕውቀትም በገቢርም መምህር መሆን ያልቻሉ መነኮሳት፣ የተጠሩበትን ሰማያዊ ተልእኮ ከረሱ ጥቂት ጳጳሳት ጋር ሆነው ኢቀኖናዊነትን ማንገሥ መንፈሳዊነትን ማራከስ ተያይዘውታል፡፡ ይህን የሕዳጣኑን ድርጊት በግዴለሽነት የሚመለከቱ አባቶችም ሆኑ ምእመናን በእግዚአብሔርም ሆነ በታሪክ ፊት ተጠያቂና ተወቃሽ መሆን አይቀርላቸውም፡፡
የእስክንድርያው ፓትርያርክ እለ እስክንድሮስ ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፈ፡፡ ምእመናን እና ማኅበረ ካህናቱም በግብረ ገብነቱ፣ በቅድስናውና በዕውቀቱ የተመሰከረለትን ወጣቱን መነኮስ ሊቀ ዲያቆን አትናቴዎስን ተተኪ ፓትርያርክ አድርገው መረጡት፡፡ ከተደበቀበት አውጥተው አስገድደው ሾሙት፡፡ እርሱም ዕድሜ ዘመኑን ለተሰጠው ታላቅ ሓላፊነት ሲጋደል ኖረ፡፡ ምእመናንም ነገሥታቱ ሲያሳድዱት በማንም ሳይተኩት፣ መንበሩን እየጠበቁ፣ ሲመለስ በዕልልታና በደስታ ተቀብለው መንበሩን ያስረክቡት ነበር፡፡ መልካም ሰብእናህን፣ ዕውቀትህንና ቅድስናህን ያወቀ ሕዝብ የሹመትን ዕዳ ሊያሸክምህ ብቻ አይደለም የሚፈልግህ፣ ይታዘዝሃል፤ በመከራህ ቀንም አብሮህ ይቆማል፡፡
ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!