ኤጲስ ቆጶስ ለመሾም የሚያገለግለው መስፈርት

ኤጲስ ቆጶስ ለመሾም የሚያገለግለው መስፈርት

ኤጲስ ቆጶስ ለመሾም የሚያገለግለው መስፈርት

ኤጲስ ቆጶሳት የአህጉረ ስብከታቸውን ክርስቲያኖች በአባትነት የሚጠብቁ፣ በመምከር ችግራቸውን የሚያቃልሉ፣ በማንኛውም ነገር አርአያ የሚሆኑ ናቸው። በዓመት ሁለት ጊዜ በሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በመሳተፍ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ውሳኔዎች እንዲተላለፉም የድርሻውን ይወጣሉ። ይህም የአገልግሎቱን ከባድነት ሲያመለክት ለከባድ አገልግሎት የሚታጨው አባትም ኃላፊነቱን በመደንብ መወጣት የሚችል መሆኑን ይገባዋል።

አባቶችን ለኤጲስ ቆጰስነት ለማጨት ሲታሰብ ሃይማኖት ከምግባር የሠመረላቸው መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባም አይደለም። ዕውቀት፣ ጥብዓትና ርኅራኄ ያላቸው መሆንም ይገባቸዋል። እነዚህን መስፈርቶች ያሟሉ አባቶች ከተመረጡ ለሀገረ ስብከታቸውም ለምእመናንም ኖላዊ መሆናቸውን ተረድተው መንጋውን ለመጠበቅ ይተጋሉ። የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል የሚባለውም ኃላፊነቱ ከባድ በመሆኑ ነው። የተጣለበትን ኃላፊነት ያልተረዳ ግዴለሽ ሰዎች ከተሾሙ በራሳቸው ኃጢአት ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ኃጢአት እንደሚጠየቁ መረዳት ይገባል። አባቶችን ለኤጲስ ቆጶስነት ለማጨት መስፈርት ባወጡት መስፈርት መሠረት ለሢመት የሚገቡትን መፈለግ፣ ጣልቃ የሚገቡትን አካላት ድርጊት በማስቆም ለቤተ ክርስቲያን የሚሆኑትን ብቻ ለመሾም ያበቃል።

ለኤጲስ ቆጶስነት የሚመረጡ አባቶች ማሟላት ከሚገባቸው መስፈርቶች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።

ሀ. በሌሎች ኃጢአት የሚጠየቁ መሆኑንን የተረዱ፡- አንድ ወንድ ልጅ የነበራት ጠንካራ ክርስቲያን እንደ ነበረች መጽሐፈ ስንክሳር ያስነብበናል። ሴቲቱ ልጇን መንፈሳዊ ትምህርት እንዲማር ስላደረገችው ተምሮ መነኰሰ። መንኵሶ ገዳም መግባቱን ስትሰማ ተደሰተች። የመንፈሳዊ ሕይወቱን ጥንካሬ የተመለከቱ የሀገሩ ክርስቲያኖች ኤጲስ ቆጶስነት እንዲሾም አደረጉ።

የልጇን ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ መሾም ስትሰማ እናት በጣም አዘነች። ሌሎቹ እየሔዱ እንኳን ደስ አለህ ሲሉት እርሷ ሳትሔድ ቀረች። ተሿሚውም አባት እናቱ ሔዳ ባለመጠየቋ በጣም ተገረመ። በአንድ ወቅት ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወጥቶ ወደ መንበረ ጵጵስናው ሲመለስ እናቱ ባለችበት አካባቢ ማለፍ ግድ ሆነበት። በዚህ ካለፍኩ ላይቀር እናቴን ልጠይቃት ብሎ ወደ ቤቷ ሔደ። ሰዎች ቀድመው ሔደው ልጅሽ ሊጠይቅሽ መጣ ብለው ቢነግሯትም ልትቀበለው አልወጣችም። እርሱም ከቤቷ ደርሶ ሰላምታ ቢያቀርብላትም ከተቀመጠችበት ተነሥታ ሰላምታ ሳትሰጠው ቀረች።

በእናቱ እንግዳ ጠባይ የተገረመው አባት “እናቴ እኔ እኮ ልጅሽ እገሌ ነኝ፤ አላወቅሽኝምን?” ቢላት እርሷም “አውቄሃለሁ” ብላ መለሰችለት። “ጵጵስና መሾሜ አላስደሰተሽምን?” ቢላት እርሷም “እንዲህ ሆነህ ከማይህ ሞትህን ቢነግሩኝ እመርጥ ነበር” አለችው። እርሱም “እናቴ ለምን እንዲህ አልሽ?” ብሎ ጠየቃት። እርሷም “እስከ አሁን ትጠየቅ የነበረው በራስህ ኃጢአት ብቻ ነበር፤ ከእንግዲህ የምትጠየቀው ግን በአገሩ ሰው ሁሉ ኃጢአት ጭምር ነው” አለችው። መጽሐፍ ከተማረው ይልቅ ያልተማረችው እናቱ በመብለጧ ተገርሞ በቃሏ ራሱን ሲገሥጽ ኖሯል። እንዲህ ያለው ድርጊት በምሳሌነት የሚጠቀሰውም  ሁሉም እየፈራ የኢጲስ ቆጶስ ሹመቱን አይቻለኝም እንዲል ሳይሆን ማንም ዘው ብሎ የሚገባበት እንዳልሆነ ለማሳየት ነው።

ለ. አዲስ ተጠማቂ ያልሆነ፡- ለኤጲስ ቆጶስነት የሚታጭ አባት አዲስ ተጠማቂ መሆን እንደሌለበት በመጽሐፈ ሲኖዶስ ዘሐዋርያት “አዲስ የተጠመቀ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ አይሾም” ተብሎ ተገላጧል (ገጽ ፻፭)። አዲስ ተጠማቂዎች ኤጲስ ቆጶስ ሆነው መሾም እንደሌለባቸው አባቶች ሥርዓት የሠሩት የቤተ ክርስቲያኗን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓት በሚገባ ስለማይረዱና ፈተና ያልለመዱ በመሆናቸው ነው። መከራ ያልለመዱ በመሆናቸው ችግር ሲጠናባቸው እንደ ዴማስ ተሰሎንቄ እንዳትናፍቀው በማሰብ ነው። ምክንያቱንም “ያልተፈተነ ሰው ለሌሎች ሰዎች መምህር ሊሆን አይገባውም” በማለት ይገልጠዋል።

ሐ. ቸልተኛ ያልሆነ፡- ቸልተኝነት እንኳን በእግዚአብሔር በሰውም የሚያስጠይቅ ድርጊት በመሆኑ መንጋውን ለመጠበቅ የተሾመ አባት ሁሉንም ክርስቲያን በትጋት መጠበቅ  ይገባዋል። ቸልተኝነት ነፍሳትን ለአውሬ ለማስበላት ምክንያት ስለሚሆን ሲያስነቅፍ ትጉ መሆን ደግሞ ለአባትነት ያስመርጣል። ሁለቱ ሰዎች ቸል ብለውት የነበረውን ሰው ደጉ ሳምራዊ ቀርቦ በቁስሉ ላይ ዘይት ያፈሰሰለት መንፈሳዊ አባት አርአያውን እንዲከተል ነው። እንዲህ  ያለው ርኅራኄ ብዙዎችን ለድኅነት ያበቃል።

መ. በአይሁድ ሥርዓት የማይተባበርና ከመናፍቃን ጋር አብሮ የማይጸለይ፡- ከአይሁድ ጋር መተባበር የክርስቶስ ሰቃያን የሆኑትን ድርጊት መደገፍ ማለት ነው።  ከመናፍቃን ጋር መጸለይም ክርስቶስን አምላክም፣ አማላጅም እያሉ ማምታታት ነው። በመጽሐፈ ሲኖዶስ “አይሁድን የሚወድ፣ እንደ አስቆሮታዊው ይሁዳም ወዳጃቸው የሚሆን፣ ጣዖት የሚያመልኩ ጠንቋዮችንም የሚያፈቅር በሹመትና በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ አይሁን” በማለት ሥርዓት ተሠርቷል (ገጽ፵፯)። በሌላም ቦታ “ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ከመናፍቃን ጋር ቢጸልዩ ይታገዱ” ይላል (ገጽ ፻፳፯-፻፳፰)። ይህ ሁሉ የሚያሳየው ለኤጲስ ቆጶስነት የሚታጩት አባቶች ከእንዲህ ያለው ጉድለት ነጻ መሆን ስለሚገባቸው ነው። ኤጲስ ቆጶስ በኮከብ ቈጠራ የማይታማ መሆን እንደሚገባው ሥርዓት የተሠራውም የእግዚአብሔር አገልጋይ እንጂ የሰይጣን ባለሟል መሆን ስለማይገባው ነው።

ሠ. መንፈሳዊውን ሹመት በመማለጃ የማይቀበል፡- ሌላው ለኤጲስ ቆጶስነት የሚያስመርጠው መስፈርት መንፈሳዊውን ሹመት በመማለጃ ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ እየተቻለው አይቻለኝም የሚል አባት ሲሆን ነው። ሰማያዊውንና መንፈሳዊውን ሹመት በገንዘብ ለማግኘት የሚሞክር ሰው እግዚአብሔር ሳይመርጠው ራሱን የመረጠ መሆኑን መረዳት ይገባል። ለእንዲህ ያለው ሰው መንፈሳዊው ሥልጣን ሊሰጠው ይቅርና በስሕተት ከተሾመም ይታገዳል ማለት ነው። “ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ካለችው የክህነት መዓርግ ሌላ ማንኛውንም ክህነት በዋጋ ቢገዛ፣ መማለጃም ቢሰጥ ወይም በክርክርና በተንኮል ይሾም ዘንድ መማለጃ ለመስጠት ተስፋ ቢሰጥ ስለእርሱ ሹመቱን አይቀበሉት” በማለት ቅዱሳን ሐዋርያት ሥርዓት የሠሩትም ለዚህ ነው(ገጽ ፻፷፩)።

ረ. ዓለማዊውን ሹመት ከክህነት የማይቀላቅል፡- ኤጲስ ቆጶስነት መሾም የሚገባው አባት ዓለማዊውን ሹመት መንፈሳዊ ከሆነው ከክህነት የማይቀላቅል መሆን ይገባዋል። የዚህን ዓለም ሥራ የሚሠራን ሰው በእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ላይ ሹም አያድርጉት የተባለውም አንድ ሰው ለሁለት ጌቶች መገዛት ስለማይገባው ነው። “ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ዓለማዊ ሹመትንና ክህነትን ሁለቱን ለመሥራት ወታደር ሆኖ ማገልገል ቢፈልግ ይሻር” በማለት አባቶቻችን ሥርዓት የሠሩት ሰማያዊው ሹመት ራሳቸውን ለአምላካቸው በሰጡ አባቶች ላይ ማረፍ እንደሚገባው የሚያስገነዝብ ነው (ገጽ ፵፱፤፻፭)።

ሰ. የሚገሥጽ፡- ኤጲስ ቆጶስ ያጠፋውን የሚገሥጸው፣ መልካም የሠራውን ደግሞ በመልካም ሥራው እንዲገፋበት የሚያበረታታ፣ ገጽ አይቶ የማያደላ ፍጹም የእግዚአብሔር ሰው ነው። “ሕዝብን የሚያዝዝ፤ በመስቀልም የሚገሥጽ ይሁን” የተባለው ለዚህ ነው (ገጽ፶፫)።

ሸ. የሚሾምበት ሀገረ ስብከት ምእመናን የተቀበሉት፡- ኤጲስ ቆጰስነት የተሾመን አባት የሚሾምበት ሀገረ ስብከት ምእመናን አምነው የተቀበሉት መሆን እንዳለበት ሥርዓት የተሠራውም ለሚሾምበት ሀገረ ስብከት ምእምናን ሁሉ ነገራቸው በመሆኑ ነው። አልተቀበሉትም ማለት መንፈሳዊ አባት በመሆኑ ላይ ጥያቄ አላቸው ማለትም ነው።  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ምእመናን እንዲሳተፉ ሥርዓት የሠራችውም አባት ይሆነናል ብለው ከመረጡት ሲያዛቸው ለመፈጸም፣ ችግር ሲገጥማቸው ቀርበው ለማማከር፣ ቀድሶ ቢያቈርባቸው በአባትነቱ ላይ ጥርጣሬ ስለማያድርባቸው ነው።  አንድን አባት የሀገረ ስብከቱ ምእመናን ሳይፈልጉት በግድ መጫን እንደማይገባ በመጽሐፈ ሲኖዶስ “ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ሊሾም የቀረበ ሰው ካለ ይህ በሀገረ ስብከቱ ሰዎች ሁሉ ስምምነት መሆን አለበት” ተብሎ ሥርዓት ተሠርቷል (ገጽ ፻፵፭)። እንዲህ ያለው መስፈርት አስፈላጊ የሚሆነው የሚሾመው አባት ለክርስቲያኖች ነፍስ መዳን የሚጨነቅ፣ ሀገረ ስብከቱንም በሚገባ የሚያስተዳድር መሆን ስለሚኖርበት ነው።

ቀ. በዝሙት፣ በመሓላ፣ በሌብነት ያልወደቀ፡- በእነዚህ ኃጢአቶች ያልወደቀ አባት  እንዲሾም ሥርዓት ተሠራ ማለት በእነዚህ የወደቀው እንዳይሾም ይከለከላል ማለት ነው። “የሐሰት መሐላን እና የሐሰት ምስክርነትን የሚደፍር፣ ለሰዎችም እንቅፋት የሚሆን፣ ባላደረጉትም ሰዎችን የሚያማ፣ በሰዎች መካከል ለመፍረድ የቤተ ክርስቲያን መልእክተኛነትንና ሥጋዊ ሹመትን ይከልክሉት” የተባለው ለዚህ ነው( ገጽ ፵፭)። ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ከእነርሱ በመዓርግ የሚያንስ በዝሙት ወድቆ ቢገኝ ወይም በሐሰት መሓላ ወይም በሌብነት ቢገኝ ከክህነት ይሻር” በማለት በሌላ ቦታ የሚያጸናውም ኃላፊነቱ ከባድ በመሆኑ ነው (ገጽ ፻፶፱)።

በ. ሥርዓትን የማያቃልል፡- አንድ ክርስቲያን አባቶች የሠሩትን ሥርዓት የማክበር መንፈሳዊ ግዴታ አለበት። አባቶቹ ያስቀመጡትን ሥርዓት ካፈረሰ በማንኛውም ሥርዓት በሐዋርያዊ ቅብብሎሽ አያምንም ማለት ነው። ክርስትና እንዳይዳከም፣ ቀድሶ የሚያቆርብ አባት እንዳይጠፋ በመጨነቅ መከራ ዘመን ሊቀ ጳጳስ ባይኖር ሁለት ወይም ሦስት ኤጲስ ቆጶሳት በተጓደሉ መናብርት ላይ አባቶችን እንዲሾሙ ለጭንቅ ቀን ብለው በተለየ መልኩ እንዲሠራበት የሠሩትን ሥርዓት ለሁል ጊዜና በማንኛውም ሁኔታ መጠቀም የሚገባ አስመስሎ ማቅረብም አባቶች የሠሩትን ሥርዓት ማፍረስ ነው። ሐዋርያት አባቶቻችን “በሕግ የማያምን በክርስቲያኖች ላይ አይሾም፤ የሚሠራባት እንጂ። ሕግና ሥርዓት የማያውቅ አያዝዛቸውምና” በማለት ሥርዓት የሠሩት ቀኖናውን እንጂ ዶግማውን አላፈረስንም በማለት በጥፋት ላይ ጥፋት የሚፈጽሙትን ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለማሳሰብም ጭምር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ( ገጽ ፵፭)።