“ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁ” ገላ. ፪፡፲፬

“ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁ” ገላ. ፪፡፲፬

“ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁ” ገላ. ፪፡፲፬

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የተጠመቅን ሁላችን ክርስቶስን እንደለበስን፣ በክርስቶስ አንድ እንደሆንን፣ ከዚህ አንድነት መውጣት ከክርቶስ አካልነት ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት መለየት መሆኑን ደጋግሞ ነግሮናል። ለዚህም ነው ለገላትያ ክርስቲያኖች “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፤ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፤ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” በማለት የነገራቸው። የክርስቶስ አካልነት በዘር፣ በጎሣ፣ በቋንቋ ወይም በፆታ የሚገኝ ሳይሆን መንፈሳዊ ሰው ለመሆን በመሠራት ገንዘብ የሚደረግ ነው። ቤተ ክርስቲያንም አካለ ክርስቶስ እንደመሆኗ በቋንቋና በዘውግ የምትወሰን አይደለችም። እንዲያውም ቤተ ክርስቲያንን በእነዚህ ምድራዊ አሳቦች መወሰን በመንፈስ ቅዱስ ላይ ትልቅ ጽርፈት ነው። አምላካዊውንም ሕግ በሰብአዊ ሕግ ለመተካት መሞከር ነው። ቅዱስ ዮስጢኖስ ፖፖቪች የተባለ አባት ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር እንዲህ ብሏል።

The church is ecumenical, catholic, God-human, ageless and it is therefore a blasphemy – an unpardonable blasphemy against the Christ and against the Holy Ghost to turn the church into a national institution, to narrow it down to the petty, transient and time-bound aspirations and ways of doing things. Her Purpose is beyond nationality, ecumenical, all-embracing to unite all men in Christ, all without exception to nation or race or social status.[1]

በግርድፉ ሲተርጎም ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፋዊት፣ ኵላዊት፣ ክርስቶሳዊ ሰው (አካለ ክርስቶስ)፣ ብሉየ መዋዕል (በዘመናት የበለጸገች) ናት፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያንን ወደ ምድራዊ (ብሔራዊ) ተቋምነት መቀየር ወይም ቀላል፣ አላፊና በጊዜ የተገደቡ ግቦችንና ተግባራትን የምታከናውን አድርጎ አጥብቦ ማየት በክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ ላይ የሚፈጸም ሥርየት አልባ ተግዳሮት (ስድብ) ነው፡፡ ዓላማዋ በአገር፣ በጎሣና በማኅበራዊ የኑሮ ደረጃ ልዩነት ሳታደርግ በክርስቶስ ሁሉንም አንድ ማድረግ ስለሆነ ከብሔራዊነት ይሻገራል፡፡

ከቤተ ክርስቲያን መገለጫዎች አንደኛው ኵላዊነት ነው። ኵላዊት ማለት ደግሞ ለሁሉም በሁሉም ያለች ማለት ነው። ቤተ ክርስቲያን ለአስተዳደር እንዲመች በሚል በተዘረጋ መዋቅር መንበርን ታሳቢ በማድረግ የኢትዮጵያ፣ የግብፅ፣ የሦርያ እየተባለች ትገለጻለች እንጂ አንድነቷ በቦታና በቋንቋ አይከፋፈልም። አኃት አብያተ ክርስቲያን ስንልም የመንበር እንጂ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በመዘንጋትና ብዙ በማድረግ አይደለም። ከዚህ የነገረ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በመውጣት ቤተ ክርስቲያንን የአንድ ጎሣና ቋንቋ አድርጎ ማሰብ የቀኖና ብቻ ሳይሆን የዶግማም ጥሰት ነው።

“በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ. ፲፮፡፳፬) የሚለውን የጌታ ትእዛዝ ለመፈጸም አስቀድሞ ሰው ከሥጋዊና ከምድራዊ አሳቦች ሁሉ ራሱን ማቀብ ይኖርበታል። በሥጋ ከተወለድንበት ሰውነት መንፈሳዊ ሰው ወደ መሆን መሠራት ይገባናል። ጥምቀት ከሥጋዊ ሰብአዊነት ወደ መንፈሳዊ አካለ ክርስቶስነት የምንለወጥበት ምሥጢር ነው። በዚህ መልኩ የተሠራን ክርስቲያኖች ውሻ ወደ ትፋቱ፣ እሪያም ወደ ጭቃዋ እንደሚመለሱት ወደ ቀደመ አላዋቂነታችን መመለስ የለብንም። ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ቀኖናና ሥርዓት በመጣስ ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመናል ብለው ዐዋጅ ያወጁትም ሆነ ሹመቱን የተቀበሉት አካላት ከዚህ እውነት የወጡ ናቸው። ራሳቸውን ወደ መንፈሳዊነት ከማሳደግ ይልቅ ቤተ ክርስቲያንን በእነርሱ ሥጋዊ ፍላጎትና አሳብ ልክ ለመስፋት ሞክረዋልና። የቤተ ክርስቲያን ዓላማ ሰማያዊ መሆኑን በመዘንጋት ወይም ቸል በማለት ለባህላቸው፣ ለቋንቋቸውና ለሥጋዊ መሻታቸው ሲያደሉ ታይተዋል። ይህ ግን ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ፈጽሞ ያፈነገጠና በሥጋ አሳብ ላይ የተመሠረተ ነው።

ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችው በክርስቶስ ደም የሰፋችውና ያበበችውም በደመ ሰማዕታት ነው። ሰማዕታት የዚህን ዓለም ጣዕም ንቀው፣ መራራ ሞትን በመታገሥ ደማቸውን ያፈሰሱት ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን በማዘከበር፣ ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን በመናፈቅ ነው። ሐዋርያት “እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” (ሐዋ. ፩፡፰) የሚለውን አምላካዊ ቃል መሠረት በማድረግ ዓለምን ዞረው አስተማሩ እንጂ በኢየሩሳሌም ብቻ አልተቀመጡም። ሐዋርያት ዓለሙን ዕጻ በዕጻ ብለው ተከፋፍለው ሲያስተምሩ ወደ ወገኖቻችን ብቻ እንሒድ አላሉም፤ ከኢየሩሳሌም፣ ከይሁዳ፣ ከሰማርያ አልፈው እስከ ዓለም ዳርቻ ሁሉ ድረስ እንጂ። ማንም ለወገኔ ይጠቅማል በሚል በሥጋዊ አሳብ ከቤተ ክርስቲያን የወጣ ባዕድ ትምህርት ወይም እንግዳ ሥርዓት ማምጣት የለበትም። በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ችግርና መከራ ውስጥ ለ፲፮፻ ዓመታት ያህል ከግብፅ ጳጳሳትን ስታስመጣ የቆየችበት መሠረታዊ ዓላማ ሐዋርያዊ ቅብብሎሽን ለማስቀጠልና ነገረ ቤተ ክርስቲያንን በመረዳት እንጂ፣ የሚሾሙ የራሷ ልጆችን አጥታ አይደለም። በእነዚህ ዘመናት ውስጥ ጳጳሳት ሳይላኩ የቆዩባቸው ረጃጅም ጊዜያት አልፈዋል። በፖለቲካዊ ጫና የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ፣ ከሃይማኖት ሕጸጽ እስከ ምግባር ጉድለት ድረስ ችግር ያለባቸው “ጳጳሳት” ተልከዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግን ይህን ሁሉ ታግሣ ሐዋርያዊ ቅብብሎሹን አስቀጠለች እንጂ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ዕውቅና ውጪ ከራሴ ልጆች ጳጳሳትን ሾሜያለሁ ብላ አላወጀችም። ተሹመው ከተላኩት ጳጳሳት ጉድለት እና ከግብፅ መንግሥት ፖለቲካዊ ፍላጎት ይልቅ የእግዚአብሔርን ብድራት ትኩር ብላ በመመልከት ፈተናዎችን ተሻግራለች።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋዶ ቤተ ክርስቲያንን አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን፣ ተሰዓቱ ቅዱሳን፣ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ ዕጨጌ ዕንባቆም ሌሎቹም ቅዱሳንን አስቀድሞ በክብር በመቀበል፣ ሲያልፉም በቅድስና በማዘከር ታከብራቸዋለች። የምታዘክራቸው ትውልዳቸው ኢትዮጵያዊ አለመሆናቸውን በመዘንጋት አይደለም። ቅዱሳን የአገልግሎት ቦታ እንጂ ምድራዊ ርስት የላቸውም የሚለውን በማመን እንጂ። መታወቂያቸው ግብራቸው ነው። የአብዛኛዎቹም ቅዱሳን በቅጽል የሚጠራው ስማቸው የአገልግሎት ቦታቸው እንጂ የትውልድ ስፍራቸው አይደለም። የነገረ ቅዱሳንም ሆነ የነገረ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የሚያስረዳው አገልጋዮች በቋንቋና በጎሣ መስፈርት እንደማይመረጡ ነው። የሚመረጡት ሰዎችን ለሰማያዊ መንግሥት ለማብቃት እንጂ ለምድራዊ ዓላማ ድጋፍ ለማሰባሰብ አይደለምና። አገልጋዮች ለአገልግሎቱ ተመርጠው እንጂ አስገድደው ኃላፊነቱን መውሰድ የለባቸውም። የቤተ ክርስቲያን ሹመት ለግል ጥቅም፣ ዝናና ክብር ሳይሆንም የክርስቶስን መንግሥት ለማስፋት የሚሰጥ መሆኑ በሁሉም ልብ ሊባል ይገባል። ሿሚዎቹም፣ ለአገልግሎቱ የሚገባውን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ መምረጥ፣ ተሿሚዎቹም ለዚህ አገልግሎት አልመጥንም ከእኔ የተሻሉ ስላሉ ለእነርሱ ይገባል በሚል እውነተኛ ትሕትና መቀበል አለባቸው። ከዚህ አካሔድ የወጣ ሁሉ ከቤተ ክርስቲያን የወጣ ነው።

ምእመናን በሚሰሙት ቋንቋ መማር አለባቸው፣ አገልግሎቱ በሚፈለገው መጠን መስፋት አለበት የሚለው ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበት መሠረታዊ ዓላማ ስለሆነ ቸል ሊባል አይገባውም። እንዲያውም እንዲህ ዐይነቱ ጥያቄ በተገልጋዩ ሳይቀርብ አገልግሎቱን በሚመራው መዋቅር ቀድሞ መታሰብ ያለበት ነው። ይህን ለመሰሉ ጥያቄዎች አግባብነት ያለው መልስ በጊዜው አለመሰጠቱ የጥያቄውን ዐውድ እንዲቀየር፣ ጥያቄውም በሌሎች በማይመለከታቸው አካላት ሳይቀር እንዲጠለፍ ዕድል ይፈጥራል። አሁን በገቢር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያየን ያለነውም ይህኑ ነው። በሚሰሙት ቋንቋ መማር የሚገባቸውን የእምነቱ ተከታዮች አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ የቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ግዴታ ነው። ቤተ ክርስቲያንን ማንም በዚህ ቋንቋ አስተምሪ በዚህ አታስተምሪ ብሎ ትእዛዝ ሊሰጣት አይችልም፣ አይገባምም። ቤተ ክርስቲያንም እንዲህ ዐይነት ትእዛዝ ከምድራዊ ባለሥልጣናት ሳትቀበል ለ፳፻ ዘመናት በብዙ ቋንቋዎች ወንጌልን ስትሰብክ ኖራለች። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም አገልግሎቷን በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ማድረግ ኃላፊነቷ መሆኑን በማመን ትሠራለች። በዚህ አግባብ የሚፈጠሩ መዘግየቶችና ክፍተቶች ከአቅም ማነስ እንጂ ከፍላጎት ማጣት መሆን የለባቸውም። ክፍተቱም አገልግሎቱን ሊሸፍኑ በሚችሉ ሰባክያነ ወንጌል በመመደብ እንጂ ኤጲስ ቆጶሳትን በመሾም የሚፈታ እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል። እንዲውም አብዛኛው የቤተ ክርስቲያን ችግር ምንጩ ራሳቸው ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው እየታዩ ባሉበት ወቅት በተለያዩ ቋንቋዎች የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ አንጻር የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ጳጳሳትን በመሾም መፍትሔ ለመስጠት መሞከር ተጨማሪ ችግር ከሚሆን በስተቀር መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም።

በቋንቋ መገልገልና የኤጲስ ቆጶሳት ሢመትም ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው አይደሉም። በቋንቋ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በመሠረታዊነት የሚያስፈልገው ቋንቋውን የሚችሉ መምህራን ማፍራት ነው። መምህራኑም በየአጥቢያው ተመድበው አገልግሎት የሚሰጡ መሆን አለባቸው። ጳጳሳትን ግን ብዙ አጥቢያዎች ባሉባቸው አህጉረ ስብከት የሚመደቡ እንደመሆናቸው አጠቃላይ አመራር ከመስጠት አልፈው ለምእመናን በሰባኬ ወንጌልነት ሊያገለግሉ አይችሉም። በእርግጥ በደረሱበት ደብር አያስተምሩም ማለት አይደለም። ነገር ግን ችግሩን በዘላቂነት ሊፈታ አይችልም። እንዲያውም እንዲህ ዐይነት ቋንቋንና ጎሣን መሠረት ያደረጉ ሢመተ ኤጲስ ቆጰሳት ቤተ ክህነቱ ላይ በቀላሉ ሊስተካከሉ የማይችሉ ችግሮችን ሊደቅኑ ይችላሉ። አድራጎቱ የክርስቶስ አካል የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ወደ አስተዳደራዊ ኩፋሌ ሊመራ ይችላል። የቤተ ክርስቲያንን አሐቲነትና ኵላዊነት ይገዳደራል። ስለሆነም የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት የኤጲስ ቆጰሳት ምርጫ ጸንቶ በቆየው የቤተ ክርስቲያን ቀኖናና ሥርዓት መሠረት ብቻ ከቋንቋና ከጎሣ ተዋጽዖ በራቀ መልኩ መፈጸም አለበት የሚል እምነት አለው።

ዋቢ

  1. http://orthodoxinfo.com/general/inwardmission.aspx