ሄሮድያዳ ዛሬም የዮሐንስን አንገት ለማስቀላት እየተዋጋች ነው

ሄሮድያዳ ዛሬም የዮሐንስን አንገት ለማስቀላት እየተዋጋች ነው።

ሄሮድያዳ ዛሬም የዮሐንስን አንገት ለማስቀላት እየተዋጋች ነው።

ቍስጥንጥንያ አዲሲቷ ሮም በሚል ስያሜ የምሥራቅ ሮማ ግዛት ዋና ማዕከል ነበረች፡፡ ከአራተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ያለፈቃዱ ቢሆንም ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ፓትርያርክ ሆኖ ተሾሞላታል፡፡ የቅዱሱን ሹመት ተከትሎ የቁስጥንጥንያ መንበረ ፓትርያርክ እና ካህናቱ ከቅምጥል የአኗኗር ዘይቤ ጋር ተለያይተዋል፡፡ መንበረ መንግሥቱ ደግሞ በንጉሠ ነገሥት አርቃድዮስ (አርቃዲዎስ) እጅ ሲሆን ንግሥቲቷ አውዶክስያ ነበረች፡፡

ንግሥት አውዶክስያ ግፍን የማትፈራ መቶ በግ ይዛ አንድ በግ ባለው ደሀ የምትቀና ስስት የተጠናወታት ሴት ነበረች። ንግሥቲቱ መፍቀሪተ ንዋይ ገፋዒተ ነዳይ ነበረችና ዐጸደ መበለት ነጠቀች። ያቺም ደሀ መበለት ወደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቀርባ በደሏን አስረዳች፡፡ ሊቁም ፍርድ ተጓደለ ደሀ ተበደለ የሚል ነውና ንግሥቲቱን መልሽላት ብሎ መልእክት ላከባት፤ መላልሶም መከራት፣ ማለዳትም። ንግሥቲቱ ግን በዙፋኗ በመተማመን በእንቢታዋ ጸናች፡፡ በዚህ ጊዜ መምህር ወመገሥጽ ዘኢያደሉ ለገጽ ነውና ከምእመናን አትገናኚ፣ ከቤተ ክርስቲያን አትግቢ፣ ሥጋ ወደሙን አትቀበዪ ብሎ አውግዞ ከማኅበር ምእመናን ለያት፡፡

ንግሥቲቱ ተደፈርኩ ብላ ቂም ያዘችበት፡፡ ከዚህ ዘመን ጀምሮ አውግዞ ከለያቸው ምግባረ ብልሹ ኤጲስ ቆጶሳት ጋር እየመከረች ስታሳድደው ኖረች፡፡ እርሱም እውነትን ይዞ እግዚአብሔርን አምባና መጠጊያ አድርጎ ከሐኬት ድርጊቷ እንድትታቀብ ፊት ለፊት መገሠጽ ቀጠለ፡፡ ከእስክንድርያው ጳጳስ ቴዎፍሎስ ሰብሳቢነት በተደረገ ጉባኤ በሐሰት ተከስሶ ለግዞት ተዳረገ፡፡

ንግሥቲቷ የደሀዋን መሬት መቀማቷ ሳያንስ የራሷ ምሥል የተቀረጸበት ሐውልት በቅድስት ሶፍያ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት እንዲቆም አደረገች፡፡ ድርጊቷ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን በእጅጉ አሳዘነው፡፡ ድርጊቱም ሕዝቡን ዳግም የነገሥታትን እና የንጉሣውያን ቤተሰቦችን ሐውልት ወደ ማምለክ ጽልመት ለመወርወር የተደረገ ጅማሮ እንደሆነ ተረዳ፡፡[1] “ሰማይ አይታረስ፤ ንጉሥ አይከሰስ” በሚለው ብሒል ተሸብቦ አልተቀመጠም። ይልቁንም መውቀስን፣ እንድትታረም መገሠጽን በማዘውተር መንፈሳዊ ግዴታውን በመወጣቱ ተጋ። የክብር ባለቤት የክርስቶስን መስቀል ከፍ ብሎ ይታይበት ዘንድ በሚገባ ዐደባባይ ላይ የጣዖት ምስል ከፍ ብሎ መታየቱን ተቃወመ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን አምላክ ክብር የሚነካ ተግባር ነውና፡፡ “ሄሮድያዳ እንደገና ተቆጥታለች፡፡ እንደገናም ትቃዣለች፡፡ አሁንም እየዘፈነች ነው፡፡ አሁንም የዮሐንስ አንገት በሣህን እንዲሰጣት እየጠየቀች ነው”[2] በማለት ያለ ፍርሀት ጠንካራ ስብከት ሰበከ፡፡ አውዶክስያ ፈቃዷን የሚፈጽም የጳጳሳት ጉባኤ አዘጋጀችና ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅን እንዲጋዝ አደረገችው፡፡ በሮሙ ንጉሥ አኖሬዎስና በሊቀ ጳጳሱ ዮናክንዲኖስ ደብዳቤ በንጉሥ አርቃዲዎስ ትእዛዝ ቢመለስም ንግሥቲቱ ግን ሌላ ምክንያት ፈልጋ ወደ ግዞቱ መለሰችው። ቅዱሱም ለቆመለት እውነት ወደ ኋላ የማይል ነውና ዳግም ተግዞ ሳለ ሕይወቱ አልፏል፡፡

በእኛ ዘመን ጥቂት የማይባሉ መነኮሳት እንደ አውዶክስያ መፍቀሬ ሢመት ሆነው ይታያሉ። ሢመት ጣዖት ሆኖ ሲፈትናቸው እያየን ነው፡፡ አንዳንዶቹ ጵጵስናቸው ቤተ መቅደስን ሳይሆን ቤተ መንግሥትን ለማገልገል የተቀበሉት ሥልጣን ይመስል በቤተ መቅደስ ተኮፍሰው፣ በቤተ መንግሥት አደግድገው ይታያሉ፡፡ ከእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ክብር በላይ ሢመቱ ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ ፍቅረ ቢጽ፣ ክርስቶሳዊ ትሕትና የተሰበከባት ቤተ ክርስቲያን ፍቅረ ሢመት የሚሠሩትን ያሳጣቸው መነኮሳትን ዕፍረት የለሽ አስረሽ ምችው (ለሹመት መቅበጥበጥ) እንድታስተናግድ ተገዳለች፡፡ አንዱ በሲሞናዊነት ሌላው በዘውገኝነት ቅኝት ዳንኪራ ይረግጣል፡፡ አንዱ የባለሥልጣናትን ፍላጎት፣ ሌላው ወገኔ ያላቸውን ጳጳሳት መሻት በመፈጸም ኤጲስ ቆጶስነትን ሊገበያት ደፋ ቀና ይላል፡፡ የፍቅር ቤት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን የሁከት ቤት እንድትሆን መንግሥትን ተገን በማድረግ ቀን ከሌሊት ይደክማሉ፡፡ አንዳንዶቹ ለሥልጣን ፍትወታቸው ማርኪያ የቤተ ክርስቲያንን አንገት በሳህን አድርገው ከመስጠት የማይመለሱ መሆናቸውን ድርጊታቸው ይመሰክራል፡፡

ፍቅረ ሢመትን ድል ማድረግ መንፈሳዊ ተጋድሎን የሚጠይቅ ከባድ ውጊያ ነው፡፡ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን አበው የኤጲስ ቆጶስነት የከበደ ዕዳው እንጂ ምንዳው አይታያቸውም ነበርና በትሕትና ሲሸሹዋት በፍቅር ስትከተላቸው እንመለከት ነበር፡፡ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ሲገለጥ ደግሞ ፍቅረ ሢመት ብዙ ጊዜ በመነኮሳቱ ቀሚስ ውስጥ ተሸፋፍና ዐይን አፋርነትን ተላብሳ ነበር የምትታየው፡፡ ያኔ ዐዩኝ አላዩኝ በሚል የመሳቀቅ ስሜት ነበር ወደ መንበረ ጵጵስናው የምታማትረው፡፡ አሁን ግን ሽፍንፍኗን ጥላ በግልጽ እየጨፈረች ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ የራቃቸው የመንፈስ ቅዱስን ጥሪ በነውራቸው ያረከሱ የከተማ መነኮሳት ይሉኝታ አልባ የሥልጣን ሽኩቻ አደባባይ ወጥቷል፡፡ ከአንድ መነኮሴ የሚጠበቀው መሠረታዊ ሥነ ምግባር ምን እንደሆነ ከመነኩሴው ይልቅ በምእመናን የኅሊና ሰሌዳ ላይ ተጽፎ ማየት ለቤተ ክርስቲያን ከባድ ዘመን መምጣቱን የሚያመላክት ሁነት ነው፡፡ መነኮሳቱ ሕጉን ሲተላለፉት ምእመናኑ በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ፊት አንገታቸውን ቀና አድርገው መሔድ ይሳናቸዋል፤ የሰቀቀን ከል ይለብሳሉ፡፡ ፆር ሲመጣ እንደ ቀደምት መነኮሳት ከእግዚአብሔር እንዳይለያቸው ከመዋጋት ይልቅ እንደ አመጣጡ ሲያስተናግዱት ይታያሉ፡፡ በዚህም ከእግዚአብሔር ይለያሉ፡፡

የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ አንገት እንዲሰጣት የጠየቀችው ወለተ ሄሮድያዳ ነበረች፡፡ እርሷ ግን ይህ የዮሐንስ አንገት በዘፈኗ ንጉሥን ላስደመመችበት ክህሎት ተመጣጣኝ ዋጋ መሆን አለመሆኑን እንኳ አጣርታ ዐታውቅም፡፡ በልጅነት መቸኮል የበለጠውን ማግኘት ስትችል ከንጉሥ ደጅ ያነሰውን እንዳትጠይቅ ሠግታ አማካሪ ጠየቀች፡፡ ከወለተ ሄሮድያዳ ጥያቄ ጀርባ ያደፈጠች ሌላ ነውረኛ ነፍስ ነበረች፤ እናቷ ሄሮድያዳ፡፡ ወጣቷ ሄሮድያዳ አማካሪ አድርጋ ከመረጠቻት እናቷ አንደበት ነበር ከንጉሥ እጅ ካለው ስጦታ ሁሉ የዮሐንስ አንገት የከበረ ስጦታ እንደሆነ የሰማችው፡፡ እናቷ የሚፈሰውን ንጹሕ ደም ለንግሥትነት አምሮቷ ስኬት የሚቀርብ የመሥዋዕት ደም አድርጋ ቆጠረችው፡፡ የዮሐንስን አንገት እንደ ሐብል እንደማታጠልቀው፣ እንደ አምባር እንደማታጌጥበት አሳምራ ታውቃለች፡፡ ነገር ግን ወደ ሐብሉና አምባሩ ግምጃ ቤት መድረሻ እንደሚሆናት አስልታ ጨርሳለች፡፡ የቅዱሱን ሞት የሩቅ ዓላማዋ ማሳኪያ መሰላል ለማድረግ ፈለገች፡፡ ለዚህ ነው የመሰናክሉን ድንጋይ ከመንገዷ ጠርጋ የምታስወግድበት ስልት ያስፈለጋት፡፡

የነቢዩን ደም ሳታስፈስስ በግዛተ ዐፄው ከፍ ያለ ሥልጣንን ምናልባትም ከዙፋኑ በታች ያለውን ሓላፊነት ማግኘት የምትችልበት ዕድል ነበራት፡፡ መካሪዋ ግን ይህን ናቀች፡፡ ነውረኛ ሥራዋን በዐደባባይ የተቃወማትን የቅዱስ ዮሐንስን አንደበት ዝም ብላ ማየትን እስክትሻ ድረስ በልቧ ቂም አለ፡፡ በዚህ የቂም እርሻ ላይ የበቀል ፍላጎቷ በቀለ፡፡ በእርግጥ ለሄሮድያዳ ቅዱስ ዮሐንስን ማስወገድ የበቀል ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የሄሮድስ ሚስት የመሆን ምኞቷ ላይ የተጋረጠውን ደንቃራ መንቀልም ነው፡፡ ወለተ ሄሮድያዳም የእናቷን ፍላጎት የእርሷ አድርጋ ወስዳ የሰማዕቱን አንገት በወጭት ተቀበለች፡፡ በሽልማቱ ከሽልማቱ ባለቤት ወለተ ሄሮድያዳ ይልቅ በመካሪነት የተመረጠችው ሄሮድያዳ ይበልጥ ደስተኛ እንደምትሆን አያጠራጥርም።

ዛሬም በክርስቶስ ቤት ለምንፈጽመው አገልግሎት በሰማያት አልፎ የሚቆይ ዋጋ እንዳለን ተነግሮናል፡፡ ነገር ግን የሰማያዊ ርስት ባለቤት የሚያደርገውን ታላቅ ስጦታ ንቀው አገልግሎታቸውን ምድራዊ ዕውቅና መጎናጸፊያ መንገድ ለማድረግ የሚጥሩ የመንጋው መሪዎችን እያየን ነው፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከል የሌላ አካል ፍላጎት ተሸካሚ ወለተ ሄሮድያዳዎች ይታያሉ፡፡ ከጀርባቸው ከሹመት ያለፈ መሻት ያላቸው አካላት እንደ ሄሮድያዳ አድፍጠዋል፡፡ ለሰማያዊ ክብር የሚያበቃውን መንገድ ትተው ከደመና በታች ለሚቀር ሽልማት አብዝተው ይሯሯጣሉ፡፡ ከኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ቀኖና በተቃርኖ ቆመዋል፡፡ ሐዋርያዊ ውርስ የሆነውን ክህነት በሲሞናዊነት መንገድ ገንዘብ ሊያደርጉት አሰፍስፈዋል፣ ከገበያ ሊገዙት ይደክማሉ፡፡ አልያም የነገዳዊ ማንነታቸው ድርጎ ተደርጎ እንዲሰጣቸው በፈረስ አንገት በጦር አንደበት እስከ መዋጋት ይደርሳሉ፡፡

ዛሬም ክርስቶሳዊ የሆነን ሁሉ ግሪካዊ፣ አይሁዳዊ ሳይሉ፣ የሥላሴን የእጅ ሥራ ሁሉ ትንሽ ትልቅ፣ ደሀ ሀብታም ሳይሉ እንዲያገለግሉበት የተሰጣቸውን ማዕረገ ጵጵስና የእኛ ከሚሉት ዘውግ የተገኙት ብቻ የሚጠለሉበት ዋርካ ለማድረግ የሚሽቀዳደሙ አባቶች ታይተዋል፡፡ ይህ በጎችን ከጠቦቶች፣ ጠቦቶችን ከግልገሎች ለይቶ በአድልዖ ለማገልገል ከመሻት የተለየ አይደለም፡፡ መንፈሳዊውን አገልግሎትም ለሥጋዊው አስተዳደር እንኳ ሕገ ወጥ እና ኢሞራላዊ በሆነ መንገድ ለማስሔድ መሞከር ነው፡፡ ግልገሎቹን ያልተንከባከበ ኖላዊ ጠቦቶቹን ዐያይም፤ ጠቦቶቹን ያልጠበቀ ኖላዊ በጎቹን አያገኝም፡፡ በጎቹን ያልጠበቀ ኖላዊ የግልገሎቹን ምንጭ ያደርቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መስፋት ከሁሉም ህልውና ጋር እንደ ድርና ማግ የተሣሠረ ነው፡፡ በመንጋው መካከል የሚፈጸም አድልዖ የህልውና መሠረቱን ያናውጣል፡፡ በመጨረሻም የተሾሙለትን መንጋ ያሳድዳል፡፡ ይህም የቤተ ክርስቲያንን አንገት በወጭት ከመስጠት አይለይም፡፡

ከሄሮድያዳ ጥያቄ ጀርባ የተደበቀ ምኞት ነበረ፡፡ ለጽድቅ ቆሞ ከቀድሞ ባሏ ከፊሊጶስ ወንድም ከሄሮድስ ጋር መጋባቷን የተቃወመ ብቸኛ ሰው፣ የእውነት ምስክር የሆነው መጥምቁ ዮሐንስ ነበር (ማቴ. ፲፬፡፫-፲፩)፡፡ የእርሱን መወገድ ከሄሮድስ ጋር ግልጽ ጋብቻ በመፈጸም ንግሥትነትን ያለተቃውሞ የምትቆጣጠርበት አማራጭ አድርጋ ወስዳዋለች፡፡ የቤተ መንግሥት ኑሮዋን ምቹ ያደርግላታል፡፡ አንገቱን በወጭት የመሻቷ የመጨረሻ ግብ ይኸው ነው – ሕግ ፈረሰ፣ ሥርዓት ተጣሰ የሚል አንደበትን መዝጋትና ሕገ ወጥነትን በቤተ መንግሥቱ ያለ ዐሳብ ማንበር፡፡

ዛሬም ሰማያዊ ዜግነትን በምታሰጥ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዘውጋዊ ሲኖዶስን ለማቆም የሚደረገው ሩጫ ግብ ይኸው ነው፡፡ ዛሬም ፈታሔ በጽድቅ የሆነውን አምላክ ለማገልገል የተጠሩ ኤጲስ ቆጶሳትን በዘመድ አዝማድ አልያም በምልጃና በእጅ መንሻ ለመሾም የሚደረገው ሽኩቻ ግብ ቤተ ክርስቲያንን ማዳከም ነው፡፡ የኦርቶዶክሳውያን የቋንቋ ልዩነትን የተሻገረ አንድነት ጠንካራ ሆኖ መገኘት ለአጽራረ ቤተ ክርስቲያን አልተመቻቸውም፡፡ በዘውግ በተከፋፈለች አገር ውስጥ ቤተ ክርስቲያን እስከ አሁን ድረስ የአንድነት ምክንያት ሆና መዝለቋ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል። ዛሬም ኦርቶዶክሳዊነት ቋንቋ ተሻጋሪ ማንነት፣ ሕዝበ ኢትዮጵያን ያስተሣሠረ ጉልበት መሆኑን መቀበል እንደ እሬት ይመርራቸዋል፡፡ እነዚህ አካላት ሄሮድያዳን እያስጨፈሩ ዛሬም የዮሐንስን አንገት በሽልማትነት መቀበል ይፈልጋሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ህልውናን ለመገዳደር የኦርቶዶክሳውያን የአንድነት ገመድ ተቆርጦ ወጭት ላይ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ሞገስ የሚጋርድ፣ የተዋሕዶን ቀንዲል የሚያጨልም ሐውልት በኢትዮጵያ ምድር መትከል ይሻሉ፡፡

ከላይ የተገለጸውን መሻታቸውን ደግሞ በዐደባባይ በሚደረግ ተዋስዖ፣ በዐዋጅ በከፈቱት ጦርነት ሊያሳኩት እንዳልቻሉ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ ስለሆነም ተመሳስለው በመቀሰጥ እና ወቅታዊ ፖለቲካን በመጠቀም መጠምዘዝ አዋጭ ዘመነኛ ስልት ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ለቅሰጣው እንዲመች ቅዱስ ዮሐንሳዊውን የጽድቅ መንፈስ አስቀድሞ ከቤተ ክርስቲያን ጠርጎ ማስወጣት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ተግባር ቀደም ብሎ ምንደኝነቱን እንጂ እረኝነቱን የማይፈልጉትን በመሾም ተጀምሯል፤ አሁን አጠናክሮ ለመቀጠል ጉልበት ተገኝቷል፡፡ የቆሙበትን መሠረት እንዳይናወጽ ለማስጠበቅ ጥብዓት የሌላቸውን ከፈቃደ ሥጋቸው ያልተፋቱትን፣ መፋታት ቢያቅታቸው እንኳ ለመቆጣጠር የማይሞክሩትን ለማሾም ሄሮድያዳውያን ይደክማሉ፡፡ መሻታቸው የሚፈጸምበት አቋራጭ እርሱ ነውና፡፡ ወለተ ሄሮድያዳ ትጨፍራለች ሄሮድያዳ ከጭፈራው ታተርፋለች፡፡

የችግሩ ሥርየት ሩቅ ቢሆንም ዛሬ በመፍትሔው መንገድ መጓዝ ካልተጀመረ መቼም አይደረስበትም፡፡ የዮሐንስን አንገት ለመቁረጥ ዕንቅልፍ ካጡት ራሳችንን መለየት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ሄሮድያዳዊ ሴራዎችን ባለማስተዋል ለወለተ ሄሮድያዳ አጨፋፈር በአድናቆት ማጨብጨብ ማቆም አለብን፡፡ ለመንጋውና ለራሳቸው በሚጠነቀቁ፣ ለእውነት በሚቆሙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ላይ እንደፈቀደ እጁን የሚያነሣውን ሄሮድስን ያለ ፍርሀት መቃወም ይገባል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊ ነጻነት ለማስጠበቅ ንቁ ኦርቶዶክሳዊ ሆኖ መገኘት ግዴታችን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ለጳጳሳት መተው የዛሬዋን ቤተ ክርስቲያን በምእመናን ሱታፌ ጠንክራ ከወጣችው ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መነጠል ነው፡፡ ከትውፊቷና ከቃሉ የተነጠለች ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ከክርስቶስ ትነጠላለችና ሁላችንም ድርሻችንን ልንወጣ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

ዋቢ መጽሐፍት

  1. ዲ. ያረጋል አበጋዝ፣ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕይወቱና ትምህርቱ። ፲፱፻፺፱ ዓ.ም.፣ ገጽ ፷
  2. ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በምድር ላይ። ፳፻፭ ዓ.ም.፤ ገጽ ፬፻፫