የኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ ያከናወናቸው ተግባራትና ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገባቸው ጉዳዮች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦት ፳፻፲፭ ዓ.ም በነበረው የርክበ ካህናት መደበኛ ጉባኤው ዘጠኝ አዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም ሰባት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ያሉበት አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙ ይታወቃል። አዲስ ኤጲስ ቆጶሳት የሚመደብባቸው ዘጠኙ አህጉረ ስብከትም ምዕራብ ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ምዕራብ አርሲ (ሻሸመኔ)፣ ድሬ ዳዋ፣ ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ቡኖ በደሌ፣ ጌዴኦ፣ ቡርጂና አማሮ እንዲሁም ዳውሮ ኮንታ አህጉረ ስብከት ናቸው። የአስመራጭ ኮሚቴው አባላት ደግሞ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፣ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስና ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል ሲሆኑ አስመራጭ ኮሚቴው ግንቦት ፳፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ሥራውን በይፋ የጀመረ መሆኑን የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሕዝብ ግንኙነት አገልግሎት አሳውቋል።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ምልመላውን ለማከናወን የሚያስችለውን ጉዳይ በተመለከተ ሲመክር ቆይቶ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጥቆማዎችን ተቀብሏል። ኮሚቴው የተሰጠውን ሥራ እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጾ ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ሪፖርት ማቅረቡን በመጥቀስ ቋሚ ሲኖዶስ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ከሰኔ ፳፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ጀምሮ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እንዲገኙ ጥሪ አስተላልፏል። በዚህ ጉባኤ ኮሚቴው በዘጠኙ አህጉረ ስብከት የሚመደቡ ዘጠኝ ተሿሚዎችን ለመለየት የመጨረሻዎቹን ፲፰ ዕጩዎች (ለአንድ ሀገረ ስብከት በድምፅ ብልጫ የሚለዩ ሁለት ዕጩዎችን) እንደሚያቀርብ ታውቋል። ዕጩዎቹም ለሕዝበ ክርስቲያኑ ይፋ ተደርገው አስተያየት ይሰጥባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ ሒደት ውስጥ እስካሁን ድረስ በዕጩነት ስለተጠቆሙት አባቶችም አስመራጭ ኮሚቴው ከደረሱት ጥቆማዎች ውስጥ እያጣራ ስለሚያሳልፍበት መስፈርት የተገለጸ ነገር የለም። አስመራጭ ኮሚቴው የኤጲስ ቆጶሳትን ምርጫ ምሥጢራዊ ማድረጉ የሚበረታታ ተግባር አይደለም። ዕጩዎቹ ይፋ ሲደረጉ ሁሉንም ምእመን በሚያስማማ መልኩ ይደልዎ የሚባሉ አባቶች ከፍ ወዳለው መዓርግ እንዲመጡ ትኩረት እንዲሰጠው እንሻለን። ሢመቱ ምድራዊ ክብር ፈልገው የሚቀበሉት ሳይሆን ምእመናንን ለመጠበቅ የሚሰጥ ሰማያዊ ሥልጣን ነው። የሚመረጡት አባቶች ምእመናንን ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኙ እንጂ ጊዜያዊ ጥምቅ ለማግኘት የሚቀበሉት አለመሆኑን መረዳት ይገባል። ምንም እንኳን ወደ ምርጫ የተገባው በፖለቲካ ጫና ጭምር በመሆኑ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው ቢታወቅም የሚሾሙት አባቶች የአካባቢውን ባህልና ቋንቋ የሚያውቁ መታጨት ያለባቸው መሆኑ ቢታመንበትም ወደ ደምና አጥንት ቆጠራ ገብቶ ቤተ ክርስቲያንን ለፈተና አሳልፎ የሚሰጥ ተግባር እንዳይፈጸም ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። የሚመረጡት አባቶች ሃይማኖት ከምግባር የተስማማላቸው፣ የተማሩ፣ በገዳማዊ ሕይወት የተፈተኑ፣ መንጋውን በመንፈሳዊ ዕውቀት የሚያጸኑና ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ሊሆኑ ይገባል። ይህ ማለት ሃይማኖት ከምግባር የሠመረላቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ የአስተዳደር ችሎታ ያላቸው መሆን ይገባቸዋል ማለት ነው።
ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ. ፲፮፡፳፬ ማር. ፰፡፴፬ ሉቃ. ፱፡፳፫) በማለት እንዳስተማረው እርሱን ለመከተል የተጠሩ ናቸውና ሊከተሉት የሚወዱ፣ ራሳቸውን የካዱና መስቀሉን ለመሸከም የፈቀዱ መሆን አለባቸው። ራስን መካድ ማለት ከምድራዊ አምሮት መራቅ፣ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ምኞቱ ጋር መስቀል (ገላ. ፭፡፳፬) ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች የሥጋ ሥራ ብሎ ከዘረዘራቸው ክፉ ተግባራት በመራቅ የመንፈስ ፍሬዎችን ያፈሩ፣ ምእመናንም እነዚህን የመንፈስ ፍሬዎች እንዲያፈሩ በቃል በሕይወት የሚመክሩ አባቶች መሆን አለባቸው።
እንዲህ ዐይነት አባቶች በቀላሉ የሚገኙ አይደሉም። ቢገኙም አይገባንም ብለው ይሸሻሉ እንጂ ሹሙን ብለው የሿሚዎችን ደጅ አያጣብቡም። የጽድቅ ሕይወታቸው የተገለጠ ቢሆንም በብዙኀኑ እንዳይታወቅባቸው ራሳቸውን ስለሚሰውሩ ታዋቂዎች አይደሉም። ስለሆነም ከጥቆማ ጀምሮ እስከ ምርጫ ድረስ ገዳማውያን አባቶች፣ ጉባኤ ዘርግተው የሚያስተምሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ማኅበረ ምእመናን እና ሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ሊጠየቁና ሊሳተፉበት ይገባቸዋል። ይህም ደጋግ አባቶችን ከፍ ወዳለው መዓርግ ለማምጣት ከማገዙም በላይ በተቃራኒው ለዚህ መዓርግ የማይበቁትን ለመለየትም ይጠቅማል። በተለይም የሚታወቅ ነውርና ነቀፋ ያለባቸውን፣ ላሉበት የክህነት መዓርግ ተገቢ አይደሉም ተብለው በሃይማኖት፣ በምግባርና በዕውቀት የሚነቀፉት፣ ሹመት ለማግኘት ጉቦና መደለያ የሚሰጡትን በዕጩነት ማቅረብ ቤተ ክርስቲያንን መበደል መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለበትም። ቋንቋና ዘርን መሠረት በማድረግ ለኮታ ማሟያ ለመግባት የሚቋምጡ ሹመት ፈላጊዎች፣ በጎጥና በሰፈር አሳብ የእኔ የሚሉትን ለማስመረጥ የሚደክሙ አባቶች እንዳሉ እየሰማን ነው። ይህ ፈጽሞ ከአባትነት የማይጠበቅ ግብር ነው።
አስመራጭ ኮሚቴው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚሰፋበትን አግባብ ብቻ መሠረት በማድረግ ለአገልግሎቱ የሚመጥኑ መነኮሳትን በዕጩነት ከማቅረብ በዘለለ በጎጥ እሳቤ፣ በፖለቲካ ጫና ለመንበሩ የማይመጥኑ አባቶች በዕጩነት እንዲቀርቡ በአንድም በሌላም የሚታዩ ግፊቶችን ተቋቁሞ ሥራውን ሊሠራ ይገባል። ኮሚቴው ሥራውን አጠናቅቆ ለቅዱስ ሲኖዶስ ከማቅረቡ በፊት በኮሚቴው የተሠሩ ሥራዎች፣ ለኮሚቴው የደረሱ ጥቆማዎች፣ ተጠቋሚዎቹን ያጠራበትን መስፈርት፣ የቀሩ ሥራዎችንና ከምእመናንና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የሚሻቸውን ድጋፎች ግልጽ ማድረግ ይገባዋል እንላለን። ጳጳሳት የሚሾሙት ለምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ጥቅም እንደመሆኑ መጠን ከጥቆማ ጀምሮ በተጠቋሚዎቹ ላይ የሕዝበ ክርስቲያኑን አሳብ መቀበል መታለፍ የሌለበት የጸና የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው።