የመንግሥት ጣልቃገብነት ከሕገ ወጡ ቡድን ድጋፍ እስከ ጳጳሳት ምርጫ

የመንግሥት ጣልቃገብነት ከሕገ ወጡ ቡድን ድጋፍ እስከ ጳጳሳት ምርጫ

የመንግሥት ጣልቃገብነት ከሕገ ወጡ ቡድን ድጋፍ እስከ ጳጳሳት ምርጫ

የሃይማኖትና የመንግሥት ግንኙነትን በተመለከተ አገራት የየራሳቸውን ሥርዓት ይከተላሉ። መንግሥት ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮም በተለያዩ ዘመናት ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ የግንኙነት መርሖችን አልፈዋል። ሃይማኖት ከመንግሥት በላይ የሆነበት ጊዜ የነበረውን ያህል መንግሥትም ከሃይማኖት በላይ ተደርጎ የተወሰደበት ዘመን እንደነበር የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ። ባለንበት ዘመን አብዛኛዎቹ አገራት የሚመሩት መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው በሚለው መርሕ ነው። ይህም ሆኖ ዓለማዊ መንግሥት ኖሯቸው፣ አንድን ሃይማኖት ብሔራዊ ሃይማኖት አድርገው ያወጁ አገራት አሉ። እንግሊዝ እና ግብጽ ለዚህ ተጠቃሽ ምሳሌዎች ናቸው።[1] ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ እስከ ፲፱፻፷፮ ዓ.ም ድረስ ኦርቶዶክስ ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ሆኖ ቆይቷል። በተለይም በ፲፱፻፹፯ ዓ.ም የወጣው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ስለ ሃይማኖትና መንግሥት መለያየት ግልጽ ድንጋጌ አስቀምጧል። የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ፲፩ መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ እንደሆኑ፣ መንግሥታዊ ሃይማኖት እንደማይኖርና መንግሥት በሃይማኖት ጉዳዮች፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳዮች ጣልቃ እንደማይገቡ ይደነግጋል። ሆኖም ግን መንግሥት ላወጣው ሕግ ተገዥ ባለመሆን በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጣልቃ ሲገባ ይስተዋላል።

በ፲፱፻፹፫ ዓ.ም ወደ ሥልጣን የመጣው የኢሕአዴግ መንግሥት ርእዮተ ዓለም የተቀረፀው በጎሣ ፖለቲካና በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ነው። የፌደራሉን ሕገ መንግሥት ጨምሮ የሁሉም ክልሎች ሕግጋተ መንግሥት መግቢያ “ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት፣ በሕዝባችን ላይ ሲፈጸም የቆየው ጭቆና” የሚሉ አሳቦችን የያዙ ናቸው። ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውጪ ያሉት የሁሉም ክልሎች ሕግጋተ መንግሥት መግቢያዎች “ለዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየው ጨቋኝ ሥርዓት”፣ “በብሔር ብሔረሰቦች ላይ ሲፈጸም የቆየው አስከፊ ብሔራዊ ጭቆና”፣ “የክልሉ ሕዝብ በወራሪው ሥርዓት የደረሰበት ግፍ”፣ “እንደ ሁለተኛ ዜጋ በመቆጠር ያሳለፍነው የሰቆቃ ኑሮ”፣ ወዘተ የሚሉ አሳቦችን የያዙ ናቸው። በእነዚህ አገላለጾች ውስጥ በአንድ በኩል ጨቋኝ ተብሎ የተሳለ አካል ሲኖር በሌላ በኩል ደግሞ ተጨቋኝ ለሚለው ሕዝብ ራሱን ነጻ አውጪ አድርጎ የሾመ አካል አለ። በቀደሙት ሥርዓተ መንግሥታት ጨቋኝ ተብሎ የተገለጸው አካል ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንዷ ተደርጋ ተገልጻ እናገኛታለን። አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በመመረቂያ ጽሑፋቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሕዝቡ ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የነበራት የተሰሚነት ሚና፣ በሕዝቡና በመንግሥት መካከል እንደ አማካኝ ተቋም ሆና መቆየቷ እና የኢትዮጵያ መሪዎች ቅቡልነት የሚመነጨው ከቤተ ክርስቲያኗ በመሆኑ ምክንያት የተነሣ በሕወሓት እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መካከል የነበረው ግንኙነት መልካም እንዳልነበረ ይገላጻሉ።[2]

ይህን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መልካም ተጽእኖ ለመቀነስ በሕወሓት የተወሰዱ ርምጃዎችን በተመለከተ ሲገልጹ ደግሞ የደርግን የቤተ ክርስቲያኗን መሬት የመውረስ ውሳኔ መቀበል፣ መሠረቱን ቤተ ክርስቲያን አድርጎ የነበረውን የሕዝቡን ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ወደ ሕዝባዊ ምክር ቤቶች ማዞር፣ ቀሳውስቱን በፓርቲው ርእዮተ ዓለም ለመግራት ተከታታይ ሥልጠናዎችን ማዘጋጀትና የትግራይን ቤተ ክርስቲያን ከሰፊው የኢትዮጵያ ክፍል ቤተ ክርስቲያን በመነጠል የትግራይ ብሔርተኝነት ማሳደጊያ ማእከልና የመዋጊያ ዐውድ ማድረግ ነበሩ ይሉናል። ፓርቲው ወደ ሥልጣን ከመጣም በኋላ ቤተ ክርስቲያንን ከማንኛውም አገራዊ እንቅስቃሴ በማግለል፣ የነበራትን ተሰሚነት በመቀነስ፣ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን በመጫን ብዙ ጥፋቶችን ሲፈጸም ቆይቷል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደርግ እና በኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን በብልጽግና መንግሥትም የነበራትን ይዞታና ንብረት ከመነጠቅ ጀምሮ የአምልኮ ነጻነቷን እስከ መጋፋት የሚዘልቁ ፈተናዎችን አስተናግዳለች፤ አሁንም በዚሁ መገፋት ውስጥ ትገኛለች። የብልጽግና መንግሥትም ኦርቶዶክሳዊነትን ለዲሞክራሲና ለብልጽግና የሚመች እንዳልሆነ ለግንዛቤ ማስጨበጫ ባዘጋጀው ሰነድ በግልጽ አስቀምጧል።[3]

በተለይም ከ፳፻፲ ዓ.ም ጀምሮ ኦርቶዶክሳውያን በሃይማኖታቸው ምክንያት በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፤ ቆስለዋል፤ አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል። ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ በግፍ እንዲፈናቀሉ፣ ተገድደው ሃይማኖታቸውን እንዲክዱ፣ ከተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች እንዲባረሩ ተደርገዋል። አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ንዋያተ ቅድሳት ተመዝብረዋል። በ፳፻፲ ዓ.ም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋና አካባቢው፣ በ፳፻፲፩ ዓ.ም በሲዳማ ዞን፣ ጥቅምትና ሰኔ ፳፻፲፪ ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ሰበቦችን ምክንያት በማድረግ ኦርቶዶክሳውያን በሃይማኖታቸው እየተለዩ በግፍ ተገድለዋል፤ ሀብት ንብረታቸው ወድሟል፤ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል። እነዚህ ሁሉ በደሎች እየተፈጸሙ በአጥፊዎች ላይ የተወሰደ ሕጋዊ ርምጃ አለመኖሩ፣ ይባስ ብሎም የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ኦርቶዶክሳውያንን ማሰርና ማዋከብ እንደ ሥርዓት መያዙ መንግሥት የጥፋቱ ተባባሪ እንጂ ተከላካይ እንዳልሆነ ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው። አብዛኛዎቹ ጥቃቶች የተፈጸሙት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ነው። የክልሉ መንግሥት እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችን እንዲያስቆም ተደጋጋሚ ተማጽኖዎች ቀርበውለት ፈቃደኛ ሆኖ ኃላፊነቱን ሲወጣ አልታየም። ጥቃቶቹ የተፈጸሙት በለውጡ ምክንያት እንደሆነ፣ ጥቃቶቹ ሥርዓታዊና መዋቅራዊ ሳይሆኑ ድንገተኛ እንደሆኑ፣ ክልሉ በኦነግ ሸኔ ምክንያት በሁሉም አካባቢዎች ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር ውስንነቶች እንደነበሩበት በመጥቀስ የጥቃቶቹን መፈጸም ካለማመን ጀምሮ የመፍትሔው አካል ለመሆን እስከ መለገም ድረስ የዘለቀ ቸልተኝነት ታይቶበታል። የክልሉ መንግሥት ኦርቶዶክስ ጠል አቋም እንዳለው በብዙ ሁኔታዎች አሳይቷል። ለማሳያ ያህል፡- በግፍ ለተገደሉ ኦርቶዶክሳውያን የሐዘን መግለጫ ለማውጣት ፈቃድ አሳይቶ አያውቅም። በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መዋቅራዊና ሥርዓታዊ መሆናቸውን አይቀበልም። ጥቃት በፈጸሙ አካላት ላይ ምንም ዐይነት ርምጃ አይወስድም። እነዚህ ጥቃቶች ዓላማቸው ኦርቶዶክሳውያንን ማሸማቀቅ፣ ማሳሳት (መቀነስ) እና ከተቻለም ማጥፋት ነው።

ከላይ ከተጠቀሱት በመንግሥት ድጋፍና ቸልተኝነት ከተፈጸሙት ጥቃቶች በላይ ግን ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ሥርዓት በመተላለፍ የተፈጸመው ሕገ ወጥ ሢመት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ገጥሟት የማያውቅ ጠባሳ ነው። በአጠቃላይ ድርጊቱ በሃይማኖት የዶግማና የቀኖና ጥሰት፣ በሞራል ነውር፣ በሕግ ደግሞ ወንጀል ነው። ይህ ድርጊት ሲፈጸም መንግሥት አስቀድሞ መረጃ ያለው መሆኑ በኋላ ከሰጣቸው መግለጫዎች በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ይህም መንግሥት ሕገወጡ ቡድን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያሻውን እንዲያደረግ በስውር በማገዝም ሆነ በዝምታ በማለፍ ተባባሪ እንደሆነ ያሳያል። የፌደራሉ መንግሥት ከዚህ በፊትም በነበረው ቁመና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ለማናገር ፈቃደኛ ካለመሆን ጀምሮ፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸሙ በደሎችንና ችግሮችን ያለመቀበል ችግር ይታይበት ነበር። በዚህ ጉዳይም መንግሥት አስቀድሞ ስለ ጉዳዩ እያወቀ በዝምታ ከማለፍ ጀምሮ፣ ድርጊቱ ከተፈጸመም በኋላ ሕጋዊ ሰውነት ያላትን ቤተ ክርስቲያንን ከመጠበቅ ይልቅ ሕጋዊ ላልሆነ አካል ከለላ የመስጠት ሥራ ሲሠራ ነበር። ጉዳዩን እጅግ መልኩን እንዲቀይር ያደረገው በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥር ፳፫ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የካቢኔ አባላትን ሰብስበው ስለ ጉዳዩ የሰጡት ማብራሪያ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያ አስቀድሞ አቋም የተያዘበት፣ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት በግልጽ የሚያሳይ እና ማስፈራሪያ አዘል ነበር። “ማንም እጁን እንዳያስገባ” በማለት ያስተላለፉት ማስፈራሪያ ጉዳዩ የሃይማኖት ሳይሆን የፖለቲካ ቅርፅ በመስጠት በዓላማ እየተሠራበት እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በኋላም የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት፣ የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኀይል፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ቤተ ክርስቲያንን እንደ ተበዳይ ሳይሆን እንደ አጥፊ በመቁጥር መግለጫዎችን ሲሰጡ ነበር። ጥር ፳፰ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት የሰጠው መግለጫ ቤተ ክርስቲያንን ከዐዲስ ተሿሚዎች ያነሰ ዕውቅና ያላት አድርጎ ያቀረበ ነበር። ቤተ ክርስቲያን መንግሥት ለጥያቄዋ መልስ የማይሰጣት ከሆነ ዓለም አቀዊ ሰልፍ እንደምታደርግ ባሳወቀችበት ወቅት የካቲት ፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በጸጥታና ደኅነንት የጋራ ግብረ ኃይል በኩል ቤተ ክርስቲያን የጠራችውን ሰላማዊ ሰልፍ በአሸባሪ አካላት የተጠራ ሰልፍ በማስመሰል የተሰጠው መግለጫ ተንኳሽ፣ ገፊና አሸማቃቂ ነበር። የፌደራሉ መንግሥት ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ የነነዌን ጾም ጥቁር ልብስ በመልበስ እንዲያሳልፉ ባወጀችበት ወቅት ለክልሎች ምንም እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ትእዛዝ በመስጠት፣ የካቲት ፭ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ምእመናን በአጥቢያቸው ቅዳሴ እንዳያስቀድሱ ከስድስት ኪሎ እስከ መስቀል ዐደባባይ፣ ከመስቀል ዐደባባይ እስከ ልደታ መንገድ በመዝጋት ከሌሊቱ ፲፩ ሰዓት ጀምሮ ወታደራዊ ትርዒት ማሳየት፣ ጥቁር ልብስ ለብሰው ወደ ቢሮ የሔዱ ሠራተኞችን እንዳይገቡ በመከልከል፣ ከሥራ በማገድና በማሰናበት፣ ጥቁር ልብስ የለበሱ ባለጉዳዮችን አገልግሎት እንዳያገኙ በመከልከል፣ ብዙ ኦርቶዶክሳውያንን በገፍ በማሠርና በማንገላታት፣ በሕግ ዋስትና የተፈቀደላቸውን ኦርቶዶክሳውያን የፍርድ ቤት ትእዛዝን ባለማክበር በእስር እንዲቆዩ በማድረግ፣ ወዘተ ብዙ ተንኳሽና ሕዝበ ክርስቲያኑን ለቁጣ የሚያነሣሡ ድርጊቶች ፈጽሟል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በተለያዩ አካባቢዎች ምእመናንን ከቤት ጥቁር ልብስ ለብሰው እንዳይወጡ የሚከለክሉ ፖሊሶችን እንዲመደቡ በማድረግ፣ ቤተ ክርስቲያን በር ላይ ቆመው ጥቁር ልብስ የለበሱ ምእመናን እንዳይገቡ በመከልከል፣ ጥቁር ለብሰው የተገኙ ምእመናንን ከቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ ውስጥ ሳይቀር አፍሶ በመውሰድ በማሠር ብዙ በደሎችን ፈጽሟል። የቤተ ክርስቲያን ጥበቃዎችን ለጥበቃ የተፈቀደና የተመዘገበ መሣሪያ ወስዷል። እነዚህ ሁሉ ድርጊቶች መንግሥት የሿሚዎችንና የተሿሚዎችን እንቅስቃሴ እንደሚደግፍ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን መብቷን ለማስከበር የምትወስዳቸውን ሰላማዊ አካሔዶች ወደ አመጽ ለመቀየር ይሠራ እንደነበር ነው። ይህ ደግሞ የቤተ ክርስቲያንን አገራዊ ውለታ የረሳ፣ ቤተ ክርስቲያንን የመከፋፈልና የማዳከም ግልጽ ተልእኮ ነው።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም እንዲሁ የሹመት ቦታውን ከመምረጥ ጀምሮ፣ ቦታውን በጸጥታ አካላት በማስጠበቅ፣ ለሕገ ወጥ ተሿሚዎች ማረፊያ ቦታ በማዘጋጀት፣ አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት በአጠቃላይ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ጉዳዩን በበላይነት በመምራትና ለተሿሚዎቹ ሕጋዊ ጥበቃና ከለላ በመስጠት ድጋፉን አሳይቷል። ለሕገ ወጥ ተሿሚዎች ከሹመቱ ዕለት ጀምሮ ጠባቂዎችን መድቧል፤ የሕግ ባለሙያዎችን አደራጅቶ ጥብቅና እንዲቆምላቸው አድርጓል፤ በጸጥታ አካላት አጀብ የአህጉረ ስብከትን መንበረ ጵጵስና ሰብረው እንዲገቡ አድርጓል። ቤተ ክርስቲያናቸውን ለመጠበቅ የወጡ ኦርቶዶክሳውያንን ገድሏል፤ አስሯል፤ አንገላቷል። የክልሉ መንግሥት በአቋም ዐዲስ ሲኖዶስ እንዲቋቋም እየሠራ ነበር። ቤተ ክርስቲያን በሕገ ወጥ ሿሚዎችና ተሿሚዎች ላይ ያስተላለፈችውን ውግዘት በመቃወም መግለጫ ማውጣቱ የክልሉ መንግሥት የጉዳዩ ባለቤት መሆኑን ያሳያል። በዚህ እንቅስቃሴ ለደረሰው ጉዳትም ሆነ፣ ለእነዚህ አካላት እንደ ልባቸው መሆን የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ነው። ሕገ ወጥ ሿሚዎችና ተሿሚዎቹ ምሥራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ አርሲ፣ ምዕራብ አርሲና ምዕራብ ሐረርጌ ሲገቡ በአንዳንድ አካባቢዎች በፓትሮል ታጅበው በጸጥታ አካላት እገዛ የአህጉረ ስብከት መንበረ ጵጵስናዎችንና አጥቢያዎችን በመስበር መግባታቸው መንግሥታዊ ድጋፍ እንደነበራቸው የሚያረጋግጥ ነው።

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወደ አህጉረ ስከብታቸው እንዳይሔዱ ሲከለከሉ፤ የሔዱትም ከሀገረ ስብከታቸው እንዲመለሱ ሲደረጉ ሕገወጦቹ ግን ያለ ከልካይ ሲንቀሳቀሱ ነበር። አቡነ እስጢፋኖስ እና አቡነ ሕዝቅኤል ወደ ሀገረ ስብከታቸው እንዳይገቡ ከጅማ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን፣ አቡነ ያሬድ ደግሞ ከሀገረ ስብከታቸው በሌሊት እንዲወጡ ተደርገዋል። ሕገ ወጦቹን በታጠቁ አካላት አጀብ ወደ አህጉረ ስብከት መንበረ ጵጵስና እና አጥቢዎች ለማስገባት በተፈጸመ ጥቃት በሻሸመኔ እና በወለቴ በውል የታወቁ ፲፯ ኦርቶዶክሳውያን በመንግሥት የጸጥታ አካላት ተገድለዋል። የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ እንደሆነ ነገር ግን ብዙዎች አስከሬናቸው ሳይገኝ እንደቀረ በቦታው የነበሩ የዐይን እማኞች ይገልጻሉ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ምእመናን ከፍተኛና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ፈተና ለመሻገር ያወጀችውን ጾምና ጥቁር ልብስ የመልበስ ዐዋጅ ከመፈጸም ጋር በተያያዘ ብዙ አገልጋይ ካህናት፣ የሰበካ ጉባኤ አባላት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የመንፈሳዊ አገልግሎት ማኅበራት አገልጋዮች ከአገልግሎታቸው ተባርረዋል፤ ታስረዋል፤ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ከሥራቸው ተባርረዋል። እነዚህ ሁሉ ጥቃቶች የክልሉ መንግሥት በሕግ ዕውቅና ያላትን ቤተ ክርስቲያን ከመጠበቅና መብቷን ከማስከበር ይልቅ ለሕገወጡ ቡድን የነበረውን ድጋፍ የሚያሳዩ ናቸው።

በክልሉ የሚገኙ የዞንና ወረዳ አመራሮች ደግሞ ለሕገወጦቹ ድጋፍና አቀባበል በማድረግ፣ ሕዝቡን በግድ ወጥቶ እንዲቀበል በመቀስቀስ፣ ያልወጣውን ምእመን በማስፈራራት፣ እንቅስቃሴውን ይቃወማሉ ብለው የሚያስቧቸውን አካላት ሰላይ በመመደብ መውጫ መግቢያ በማሳጣት፣ ያለምንም ጥፋታቸው ኦርቶዶክሳውንን በማፈን፣ በማሰርና በማንገላታት፣ ከሥራ ቦታ እንዲባረሩ በማድረግ፣ አካባቢውን ለቀው ካልወጡ ርምጃ እንደሚወሰድባቸው በመዛትና በማሸማቀቅ፣ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት በሕገወጦቹና በደጋፊዎቻቸው እንዲዘረፍ በማድረግ ተሳትፎ ነበራቸው። እነዚህ የመንግሥት አካላት በተለየ ሁኔታ በራሳቸውም ፈቃድና ፍላጎት ሕገ ወጥ ተሿሚዎችን የሚያግዙ ናቸው። የበላይ አካል ትእዛዝ ሳይጠብቁ በራሳቸው ወሳኝ አካል ሆነው ለሕገ ወጥ ተሿሚዎች የተለየ አቀባበል ከማድረግ ጀምሮ በስቴዴየምና በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች መርሐ ግብር እንዲዘጋጅ እስከ ማድረግ ድረስ የዘለቁ የዞን አስተዳዳሪዎች ነበሩ።

መንግሥት ከዚህ ሁሉ የጣልቃ ገብነት ድርጊቱ በኋላ ደግሞ ራሱን ከከሳሻነት ወደ አሸማጋይነት በመቀየር ውይይት እንዲካሔድ እንዳደረገና ስምምነት እንደተፈጸመ በራሱ ሚዲያዎች ይፋ አደረገ። ሿሚዎቹ ተመልሰናል ብለው ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንዲገቡ ተደረገ። ይህም ከሆነ በኋላ ሕገ ወጥ ተሿሚዎቹ በተለያዩ አህጉረ ስብከት ዘርፈ ብዙ ጥፋቶችን ሲፈጽሙ የሚያስቆማቸው መንግሥታዊ አካል አልነበረም። ሕገወጦቹ የየሀገረ ስብከቱን ቢሮዎች በመስበርና ማኅተም በማውጣት ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ ድረስ ሹምሽር አደረጉ። ሕገወጥ ቡድን በማደራጀት ይቃወሙናል ብለው የሚያስቧቸውን የሰበካ ጉባኤና የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ማስፈራራት፣ ብሎም ማስደብደብ ቀጠሉ። ራሳቸውን እንደ ሕጋዊ አድርገው የአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳትና ሥራ አስኪያጅ ላይ ክስ እስከ መመሥረት ደረሱ። መንግሥት የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት እሠራለሁ ባለው መሠረት በእነዚህ አካላት ላይ ተገቢውን ሕጋዊ ርምጃ ሲወስድ አልታየም።

አሁንም ችግሩ ተዳፈነ እንጂ አልተፈታም። ቃጠሎው ለጊዜው ከመስፋፋት ተገታ እንጅ ፍሕሙ ግን አልጠፋም፡፡ በተለያዩ አህጉረ ስብከት ሕገወጥ ተሿሚዎቹ የባንክ ፈራሚ በመቀየር ገንዘብ እስከ ማውጣት ድረስ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው። በኦሮሚያ ክልል መንግሥት በኩል ሕገወጥ ተሿሚዎቹ በአስመራጭ ኮሚቴው ጥቆማ ለሹመት እንዲቀርቡ ግልጽ ጫና እየተደረገ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነው። በተመሳሳይ በትግራይ ክልልም ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን በወጣ መልኩ ሕገወጥ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ለማከናወን እንቅስቃሴ እንዳለ ይታያል። በትግራይ ክልል ያሉ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጰሳት መንበረ ሰላማ እና የትግራይ ቤተ ክህነት በሚል የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን ዐውዳቸውን በማስፋት በውጪ አህጉረ ስብከት ጳጳስ እስከ መመደብ ድረስ ውሳኔዎችን እያሳለፉ ይገኛሉ። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የጻፉት ደብዳቤ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ በጎ ምላሽ አላገኘም። በቤተ ክህነቱም በኩል ወደ ትግራይ የሚሔዱ ልዑካንን መድቧል የሚሉ መረጃዎችን ከመስማት ባለፈ ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ ምንም ዐይነት ርምጃ አልተወሰደም። እንቅስቃሴው ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት በጅምሩ መቀረፍ ካልቻለ ተመሳሳይ ችግር የሚደቅን እንደሚሆን አያጠራጥርም።

ስለሆነም ከሕገ ወጥ ሹመቱ ጋር በተያያዘ ቤተ ክህነቱ ችግሩን ለመፍታት የያዘበት አግባብ ማስታመምን መሠረት ያደረገ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ ስላልሆነ ጉዳዩን በአግባቡ ሊያጤነው ይገባል። በአንጻሩ መንግሥት የተጣለበትን የሕዝቦችን ሰላምና ደኅንነት የማስከበር፣ መሠረታዊ መብቶችና ነጻነቶችን የመጠበቅና የማስጠበቅ እንዲሁም በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት ግዴታ በአግባቡ መወጣት አለበት። ከዚህ አልፎ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ለሕገወጡ ቡድንም ሆነ ለሌሎች ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ድጋፍ ከመስጠት፣ በቤተ ክርስቲያን የሢመት ሥርዓት ውስጥ እጁን ከማስገባት መቆጠብ አለበት። አሁንም ድረስ በተለያዩ አካባቢዎች ለሕገ ወጥ ቡድኑ የዘለቁ መንግሥታዊ ድጋፎች፣ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ የሕገ ወጡ ሹመት ተሳታፊ የነበሩ አካላት እንዲመረጡ ለማድረግ እየታዩ ያሉ ስውር እጆች መሰብሰብ አለባቸው። ቤተ ክርስቲያንም ከመንግሥት ጋር ያላትንና ሊኖራት የሚገባትን ግንኙነት መርሕን መሠረት ያደረገ ማድረግ አለባት። በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ከመተባበር ያለፈ መንግሥት በቤተ ክርስቲያን የውስጥ ጉዳይ ገብቶ መመሪያ የሚሰጥበትም ሆነ የሚያስገድድበት አግባብ እንዳይኖር ግልጽ ሥርዓት መዘርጋትና ግልጽ አቋም መያዝ ይገባል።

ዋቢ መጽሐፍት

  1. የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ማብራሪያ ያልታተመ
  2. አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)፣ የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ፖለቲካዊ ታሪክ። ፳፻፲፫ ዓ.ም፣ ገጽ ፫፻፹፪-፫፻፹፭
  3. ብልጽግና ፓርቲ፣ የፖለቲካ ብልጽግናን የማረጋገጥ ትልምና ፈተናዎች። ፳፻፲፪ ዓ.ም ገጽ ፻፷፰