የተማረ ግብረ ገብ ይሾም
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ እየተነሡ ያሉ ጉዳዮች አሉ። አንደኛውና ዋናው ከእኛ ዘር፣ ጎሣና ቋንቋ ተናጋሪ በኤጲስ ቆጶስነት አልተሾሙም የሚል ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ቅዱስ ሲኖዶስን የአንድ አካባቢ አባቶች የተሰበሰቡበት ነው የሚል ነው። ይህም ቅዱስ ሲኖዶስን በመንፈስ ቅዱስ እንደሚመራ የቤተ ክርስቲያን አካል ሳይሆን የዘር ውክልና ያለበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አድርጎ የመውሰድ የተሳሳተ አረዳድ ወይም ክፉ አሳብ ነው። ብዙ ጊዜ ይህን አሳብ የሚያራምዱት ግን ምእመናን ሳይሆኑ በአቋራጭ ጳጳስ እንሆናለን ብለው የሚያስቡ አካላትና ደጋፊዎቻቸው ናቸው። ጥያቄውም ከመንፈሳዊነት ይልቅ ወደ ፖለቲካዊነት ያጋደለ ነው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ትንቢት ከቶ ከሰው ፍላጎት እንዳልመጣ ባስተማረበት መልእክቱ “ይህን መጀመሪያ ዕወቁ” (፪ኛ ጴጥ. ፩፡፳፩) ይላል። ስለ ኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ስናስብም መጀመሪያ ማወቅ የሚገባን ጌታ በወንጌል “ከእናንተ ታላቅ መሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን” (ማቴ. ፳፡፳፮) በማለት ያስተማረውን ነው። ኤጲስ ቆጰስነት ዝቅ በማለት የሚያገኙት እንጂ በፍለጋና በመሻት ገንዘብ የሚያደርጉት ሥልጣን አይደለም። ክርስቶስም ወደዚህ ምድር የመጣው ሊያገለግልና እና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አይደለም (ማቴ. ፳፡፳፰)። ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በእግርም በሕይወትም ሁሉን ትተው የተከተሉት ሐዋርያት፣ ከእነርሱ በኋላ የተነሡት ሐዋርያውያን አበው፣ ዐቃብያነ እምነት እንዲሁም ሊቃውንት ሢመትን የተቀበሉበት መሠረታዊ ምክንያት የቤተ ክርስቲያንን ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ የመስበክ ኃላፊነት ለማስፈጸም ብቻ ነው።
የቀደሙት አባቶች ኤጲስ ቆጶስነት ከክብሩ ይልቅ ሸክሙ የከበደ መሆኑን በመገንዘብ ሲሸሹት እንጂ ሲሹት አይታዩም። አይደለም ገንዘብ ከፍለው እና ከእኛ ወገን በውክልና አስገቡን ብለው ሹመት ሊፋረዱ ይቅርና፣ ተሹሙ ሲባሉ ስንኳን ይጠፉና ይደበቁ ነበር። ኤጲስ ቆጶስነት በራስ ኀጢአት ብቻ ሳይሆን በሕዝቡም ኀጢአት ለመጠየቅ ራስን ቤዛ አድርጎ መስጠት ነው። ኤጲስ ቆጶስነት የማሠርና የመፍታት ሰማያዊ ሥልጣን፣ በሌሎች መንፈሳዊ ሕይወት ላይ የመወሰን መንፈሳዊ ሥልጣን፣ በእግዚአብሔር ቤት የሚያገለግሉ ካህናትንና ዲያቆናትን የመምረጥና የመሾም ሐዋርያዊ ሥልጣን፣ በክርስቶስ ደም የተዋጀችዋን የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን የመጠበቅ፣ ለራስና ለመንጋው የመጠንቀቅ አምላካዊ ትእዛዝ ነው። ይህን ጸጋ በቅተው ሊያገኙት፣ ጸጋውም የበቁ ሆነው ሊያገኛቸው ይገባል።
በቅርብ ጊዜያት እየተለመዱ የመጡት አሠራሮች ግን የኤጲስ ቆጶስነትን ክብር ዝቅ የሚያደርጉ ናቸው። ሹመቱም መንፈሳዊ ጸጋ፣ ሰማያዊ ዋጋ ለማግኘት ሳይሆን ለምድራዊ ስም፣ ክብር እና ዝና በሚመስል መልኩ በፍላጎትና በንጥቂያ ሲሆን ይታያል። ኤጲስ ቆጶስነትን ምድራዊ ሀብት ለማካበት እንደ አንድ መንገድ በመቁጠር ሹሙኝ ብሎ ደጅ ጥናትና መማለጃ ማቅረብ እንዳለ በዐደባባይ የምንሰማው ሐቅ ሆኗል። ለእንዲህ ዐይነት ሁኔታ አሳልፈው የሰጡን ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም የጳጳሳት ገደብ አልባ ሥልጣንና ከገዳማዊ ሕይወት የራቀ አኗኗር ግን ኤጲስ ቆጶስነትን ሁሉም እንዲመኘው አድርጎታል። የተመኘው ሁሉ የሚያገኘው መሆኑ፣ በመንፈሳዊ ዕውቀት፣ በክርስቲያናዊ ሕይወት ሐሜት ያለባቸው አባቶች ኤጲስ ቆጶስ ሆነው መሾማቸው ደግሞ ምእመናን ለጵጵስና የነበራቸውንና ያላቸውን ክብር እንዲቀንስ አድርጎታል። ለኤጲስ ቆጶስነት የሚታጩ አባቶች በትምህርትና በሕይወት የተሻሉ መሆን አለባቸው እንጂ ከምእመናን እንደ አንዱ መሆን የለባቸውም። ይህ ካልሆነ የኤጲስ ቆጶስነት ብልጫው ምንድን ነው የሚል ጥያቄ የሚያስነሣ ይሆናል።
ሐዋርያትም በጥንተ ስብከት “የተማረ ግብረ ገብ ይሾም” የሚል ሥርዓት ሠርተው ነበር። ሁለቱን አስተባብሮ የያዘ ባይገኝ የተማረ ይሾም፤ መናፍቃንን በትምህርቱ ተከራክሮ ይረታቸዋል፤ በጎ ምግባሩን ውሎ አድሮ ይሠራዋልና ብለዋል። የተማረ ቢታጣ ደግሞ በጎ ሥነ ምግባር ያለው ይሾም። በበጎ ትሩፋቱ ምእመናንን ያስተምራል፤ በጸሎቱ ይጠብቃል፤ ትምህርቱን ግን ውሎ አድሮ ይማረዋልና ብለዋል። ሐዋርያት ሁለቱንም የሚያሟሉት እንዲሾሙ ካዘዙ በኋላ ሁለቱን አስተባብሮ ማግኘት ካልተቻለ የተማረውን ማስቀደም እንደሚገባ አዝዘዋል። ይህም ይታወቅ ዘንድ ቤተ ክርስቲያንን በዓላማ ከተዋጓት አካላት ባልተናነሰ ወይም በከፋ ሁኔታ የጎዷት በመንበሩ ላይ የተቀመጡ አላዋቂዎች ናቸው። ሐዋርያት አንዱን ብቻ ያሟላውን ሰው እንዲሾም ሲያዝዙ ሌላኛው በሒደት ይፈጽመው አሉ እንጂ ሌላኛውን መስፈርት ፈጽሞ ይቅር አላሉም። ትምህርትም በጎ ምግባርም የሌለው ከሆነ ግን ኤጲስ ቆጶስነት ሊሾም አይገባውም፤ ከሐዋርያት ትእዛዝ ውጪ ነው። ሐዋርያት ከትምህርትና ከመንፈሳዊ ትሩፋት ውጪ ሌላ መስፈርት አላስቀመጡም።
ሐዋርያት የተማረና መንፈሳዊ የሆነ እንዲሾም ቀኖና የሠሩት የኤጲስ ቆጶሳት ዋናው አገልግሎታቸው ምእመናንን በአፍም በመጣፍም ከኑፋቄ መጠበቅ፣ በሕይወትና በቃል ማስተማርና ማጽናት ስለሆነ ነው። ይህ መስፈርት መዘንጋቱ ቤተ ክርስቲያንን በእጅጉ ዋጋ እያስከፈላት ነው። ከታችኛው መዓርግ ጀምሮ የክህነት አሰጣጡ ትምህርትን እና ሥነ ምግባርን መሠረት ያደረገ አለመሆኑ ወደ ከፍተኛው የክህነት መዓርግ ወደ ኤጲስ ቆጶስነት የሚመጡት ተሻሚዎች ተጠቃሾቹን መስፍርቶች ያላሟሉ እንዲሆኑ ያደርጋሉ። ያልተማሩ፣ ሥነ ምግባር የጎደላቸው፣ ከጎጠኝነት ያልተላለቀቁ፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ወዘተ ሰዎች የሚሾሙት ወጥ የሆነ የሥልጣነ ክህነት አሰጣጥ ሥርዓት ተግባራዊ አለመሆን ነው። የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መንፈሳዊ እንደመሆኑ መጠን ለአገልግሎቱ የሚያስፈልጉት መንፈሳዊ ዕውቀትና ሕይወት ያላቸው ብቻ ናቸው።
ቅዱስ ሲኖዶስ በያዝነው ዓመት የርክበ ካህናት ጉባኤው ከውጪ በመጡ ጫናዎች ምክንያት ምእመናንን በሚሰሙት ቋንቋ ከማስተማር ጋር በተያያዘ ቋንቋ መቻልን እንደ አንድ መስፈርት በመጠቀም ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ ወስኖ፤ ዘጠኝ እጩ ኢጲስ ቆጶሳትን መርጧል። በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ አባቶችን መሾም በመርሕ ደረጃ አግባብነት ያለው መሆኑ ቢታመንም ውሎ አድሮ የሚያመጣው ችግር ግን ቀላል አይሆንም። ማንም ሰው በሚሰማው ቋንቋ ወንጌልን መማር አለበት። በሚሰማው ቋንቋ ወንጌልን ለማስተማር ደግሞ ከቋንቋው በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት የተማሩ ሊቃውንት ያስፈልጋሉ። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ወንጌል እንጂ ቋንቋ አይደለም። የሚሾሙት ኤጲስ ቆጶሳት ምንም እንኳን ክህነት ከመስጠትና ከመባረክ ያለፈ ሚና ባይኖራቸውም በደረሱበት አጥቢያ የተሾሙበትን ሕዝብ በሚሰማው ቋንቋ ለማስተማር ቋንቋውን መቻላቸው ተገቢ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በላይ ግን በመንፈሳዊ ዕውቀታቸው፣ በሕይወታቸው እና በንጽሕናቸው የተመሰከረላቸው መሆን አለባቸው። ስለሆነም ቋንቋውን ብቻ ሳይሆን ለኤጲስ ቆጶስነት የሚያበቁ ከትምህርትና ከቅድስና ሕይወት ጋር የተያያዙ መስፈርቶችንም አሟልተው የተገኙ ብቻ ሊሾሙ ይገባል። ለሁሉም ቋንቋ ተናጋሪዎች ይህን መስፈርት የሚያሟሉ አባቶችን ማግኘት ትልቁ ፈተና ነው። ሌላው በዚህ መልኩ የሚሾሙ አባቶችም የሁሉም አባቶች ሳይሆኑ የተሾሙለት ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ አባት ብቻ የሚያስመስልና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚፈታተን ነው።
ቋንቋውን መቻላቸው ብቻ ለኤጲስ ቆጶስነት ምርጫ ሊያበቃቸው አይገባም። ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው የክርስቶስን ወንጌል እንጂ የቋንቋ ልማት አይደለም። ስለሆነም በእነዚህ አካላትም ላይ ሐዋርያት ያዘዙት የተማረ ግብረ ገብ ይሾም፤ ከታጣ ግን አንዱን የሚያሟላው ይሾም፤ የጎደለውን በሒደት ያሟላዋል የሚለው ትእዛዝ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል። ኤጲስ ቆጰስ ሆነው የሚሾሙት የሚመደቡበትን ሀገረ ስብከት ወክለው የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ለመሆን ሳይሆን ለመንጋው መጠበቅ ሰማያዊ ኀላፊነት ተጥሎባቸው ነው። ተሿሚዎቹ ይህን ኀላፊነት ሊወጡ የማይችሉ ከሆነ ምእመናን ቋንቋቸውንና ባህላቸውን የሚያውቅ አባት በመሾሙ የሚያገኙት ቅንጣት ትርፍ የለም። የኤጲስ ቆጶሳቱ መሾም የቤተ ክርስቲያንን መሠረታዊ ዓላማ ከማሳካት አንጻር እንጂ ከፖለቲከኞችን ወይም ከሹመት ፈላጊዎችንና ደጋፊዎቻቸውን ፍላጎት አንጻር መመዘን የለበትም። እነዚህ በቅንነት የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በመጠምዘዝ መልስ አልባ ጥያቄዎቻቸውን ከማጉረፍ ውጪ ቤተ ክርስቲያን የምትሰፋበት አግባብ የሚገዳቸው ስላልሆኑ ተመለሰልን የሚሉት ነገር አይኖርም። ስለሆነም ጉዳዩን በትዕግሥትና በጥበብ መያዝ ያስፈልጋል እንጂ ጥያቄ የማቅረብ መብት የሌላቸው አካላት በሚቀዱት የስሕተት ቦይ መፍሰስ አይገባም።
ሌላው ለሕገወጥ ተሿሚዎችና ሹመት ፈላጊዎች በር የከፈተላቸው የቤተ ክርስቲያን የውስጥ ችግር ነው። ከዚህ በፊት የተሾሙት አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳትም በዚሁ አግባብ የተሾሙ መሆናቸው፣ በትምህርትና በንጽሕና የሚታሙ አባቶች መኖራቸው እኔ ከእገሌ አንሳለሁ ለሚሉ ደፋሮች የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል። የመዋቅሩ ለሚጠየቁ ጥያቄዎች አግባብነት ያለው ወቅታዊ ምላሽ አለመስጠት ያለ ቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅና እንኳን ኤጲስ ቆጶስ ለመሾም ወደኋላ የማይሉ አካላትን ፈጥሯል። ይህ አካሔድ እጅግ አደገኛ ነው። የአደገኛነቱን ያህል ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት በአግባቡ ሊፈታ የሚችልበት አግባብ አለመታየቱ፣ ብሎም በሻሚዎችና በተሿሚዎች ላይ የተወሰደ ርምጃ አለመኖሩ ደግሞ አሁንም ማንም ተነሥቶ ኤጲስ ቆጶሳትን እሾማለሁ እንዲል በር ከፍቷል። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ለወለደው ልጁ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክቱ “ሌሎቹ ደግሞ እንዲፈሩ፣ ኀጢአት የሚሠሩትን በሁሉ ፊት ገሥጻቸው” (፩ኛ ጢሞ. ፭፡፳) እንዳለ ሁሉንም የሚያስተምር ቀኖናዊ ርምጃ አለመወሰዱ ሌሎች አጥፊዎችን የሚያነሣሣ ነው።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩ አድሏዊ አሠራሮች መኖር፣ ሙሰኝነት፣ ሌብነት፣ ወጥነት የሌለው፣ ፍትሐዊነት የጎደለው እና ለምዝበራ የተጋለጠየሰው ሀብት፤ የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር መኖር ሹመት ፈላጊዎች እነዚህ ችግሮች በመጠቃቀስ ደጋፊ ለማብዛትና በቤተ ክህነቱና በምእመናን መካከል ግንብ ለመሥራት ይጠቀሙበታል። ቅጥር የሚፈጸመው በመንፈሳዊ ሕይወት፣ በዕውቀትና በሥራ ልምድ ሳይሆን በገንዘብ መሆኑ የዐደባባይ ምሥጢር ከሆነ ሰነባብቷል። ይህም የአገልግሎት ተደራሽነት ችግርን፤ የአገልጋዮች የእረኝነት ሚና መድከምን፣ ቤተ ክርስቲያንን የማያውቁ ሰዎች ከውስጥ መገኘትን እና ፟የምእመናን መንፈሳዊ ሕይወት ድክመትን አስከትሏል። አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳት ሀገረ ስብከታቸውን ጥለው አዲስ አበባ መቆየታቸው በምእመናን ዘንድ ቅሬታ፣ በአስተዳደር ላይ ክፍተት ይፈጥራል። የሥልጣን ጥመኞች ደግሞ ይህን ቅሬታ መነሻ በማድረግ ግላዊ የጥቅምና የሥልጣን ፍላጎት በሕዝብና በማኅበረሰብ ጥያቄ ስም ለማቅረብ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
ስለሆነም ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት አግባብነት ያላቸውን ጥያቄዎች አግባብነት ከሌላቸው ጥያቄዎች በመለየት፣ የምእመናንን ጥያቄዎች ከፖለቲከኞች ፍላጎትና መሻት በመነጠል ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ምላሽ በመስጠት ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአገልጋዮችና በምእመናን የተጠየቁ እና በውጫዊ ተጽእኖዎች ምክንያት መልስ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ተገቢና ፈጣን የሆነ ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባል። ለጥያቄዎቹ ትኩረት አለመስጠትና በወቅቱ ተገቢውን መልስ አለመመለስ ጥያቄዎቹ በማይመለከታቸው አከላት እንዲጠለፉና እንዲወሳሰቡ በር ይከፍታል። ቤተ ክርስቲያንም ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም እንደገጠማት ዐይነት የልጆቿን ሕይወት የሚያስገብር ችግር ይዞ ይመጣል። በተለይም በቤተ ክርስቲያን ላይ ለሚነሡ ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊና ወቅታዊ ጥያቄዎች የማያዳግም ምላሽ መስጠት የቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ዓላማዋና የአባቶች ዋና የእረኝነት ሚና መሆን ይገባዋል። የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎቶችን በቋንቋ ተደራሽ እንዲሆኑ ከማድረግ አንጻር የሚጠየቁ ጥያቄዎች፣ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ ሰባክያንን በማፍራት ረገድ፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በአገልጋይ እጥረትና በንዋያተ ቅድሳት አለመሟላት ሲዘጉና አገልግሎት ሲጓደል ከሚሰጣቸው ትኩረት አንጻር ክፍተቶች አሉ። እነዚህ ችግሮች ዘላቂነት ባለው መልኩ ባልተፈቱ መጠን ሕገወጥ ተሿሚዎች መፍትሔው መፈንቅለ ሲኖዶስ ማካሔድ ነው ብለው እንደኒሡ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል። ከኢትዮጵያ አልፋ ለአፍሪካ ወንጌልን ትሰብካለች ተብላ የምትጠበቅ ቤተ ክርስቲያን ለራሷ ሳትሆን ከመቅረት በላይ ተጠያቂነት ሊኖር አይችልም። ስለሆነም ያልተማሩትና ግብረ ገብነት የሌላቸውን አካላት ወደ ሢመት እንዳመጡ ማድረግ የሚቻለው በአቋራጭ ለመሾም የሚጠቅሙባቸውን ከቋንቋ አገልግሎትና ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግሮች አንጻር የሚያነሧቸውን ክፍተቶች በመሙላትና ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ነው።