የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ልዩ ልዩ ብዙኃን መገናኛዎች
በያዝነው ዓመት ሊደረግ የታሰበው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የእምነቱን ተከታዮች በሁለት ከፍሎ ደጋፊና ተቃዋሚ አድርጎ እያነታረከ ነው። ጉዳዮን ማኅበራዊና ብዙኃን መገናኛዎች እየዘገቡት ያለው በሚከተለው መልኩ ነው።
ግዮን መጽሔት የዘገበው በጥብቅ ምሥጠር የተያዘው የዕጩ ኤጲስ ቆጶስ ተጠቋሚ መነኰሳትስም ይፋ እንዲደረግ መጠየቁን አስመልክቶ የዘገበው “የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ፣ ከ18 እስከ 20 ተጠቋሚዎችን መለየቱን፣ ከ25ቱ በኢቀኖናዊ ሢመት ተሳታፊዎች መካከል ስድስቱ የተጠቆሙ ሲሆን ሦስቱ ለሹመት እንደሚቀርቡ፣ ኮሚቴው ኀሙስ ሰኔ 22 የሚያደርገው ስብሰባተጠቋሚዎችን ይፋ እንደሚያደርግ፣ ካህናት እና ምእመናን ያልመሰከሩለት ተሿሚ፣ አባታዊ ቅቡልነትን ማግኘቱ አጠጣሪ መሆኑን፣… አስመራጭ ኮሚቴው፣ ጥቆማ የመቀበሉንና የምልመላ ሥራውን እንዳጠናቀቀ፣ ባለፈው ሰኔ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ለቋሚ ሲኖዶስ ሪፖርት ማቅረቡን ተከትሎ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ብፁዓን ሊቃነጳጳሳት፥ ለእሑድ ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እንዲገኙ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የስብሰባ ጥሪ ተላልፏል” ብሏል ፡፡
ከጊዮን መጽሔት ዘገባ መረዳት የሚቻለው አስመራጭ ኮሚቴው አሁን ከደረሰበት ደረጃ አስቀድሞ ምንም መረጃ አለመልቀቁን ነው። የመጽሔቱ ቅድመ ትንበያ ወደ እውነቱ የሚጠጋ መሆኑን የምናረጋግጠው ሊመረጡ ለታሰቡት 9 ኤጰስ ቆጶሳት 18 አባቶች ቀርበው በጉባኤው 9 መለየታቸውን ስለተረዳን ነው። ከዚህ በተጨማሪም በኢቀኖናዊ ሢመት ተካትተው ከነበሩት አባቶች በእጩነት 6 ቀርበው ሦስቱ ማለፋቸው የሚታወቅ ነው።
መጽሔቱ ከዘገበው ውስጥ“ለአስመራጭ ኮሚቴው ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ በግንባር ያቀረቡት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራሮቹ፥ ካህናት፣ ምእመናንና ወጣቶች፣ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ካላቸው የጸና የአስፈጻሚነት ድርሻ አንጻር፣ በዕጩዎች ሕይወት፣ ትምህርት፣ የአስተዳደር እና የአገልግሎት ብቃት፣ እንዲሁም ሥነ ምግባር ላይ፣ አስተያየት የመስጠት መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም እንዳለባቸው አመልክተዋል። ግልጽ በኾነ መስፈርት እና የጥቆማ ሒደት መከናወን የሚገባው የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምልመላ፣ ቀኖናዊ አሠራሩ ተጥሶ እና የተቀደሰው ትውፊት ተገፍቶ፣ ከሊቃነ ጳጳሳት በተሰበሰበ ጥቆማ ብቻ ለመጨረሻው የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ከቀረበ፣ ከፍተኛውን የኖላዊነት ሥልጣን ‘ይደልዎ’ የሚል ምስክርነት እንደሚያሳጣውና በሲሞናዊ መንገድ ለግላዊ ጥቅም የተሸቀጠ ሥጋዊ ሹመት እንደሚያደርገው አስገንዝቧል” የሚለው ቁልፍ ጉዳይ ነው።
መጽሔቱ የዘገበው ይህ ጉዳይ ትኩረት የሚሹ ነጥቦችን የያዘው አንድን ሀገረ ስብከት ለማስተዳደር የሚመረጥ አባት በምእመናን ቅቡልነት ካናገኘ የኖላዊነት ተግባሩን ለማከናወን ስለሚቸገር ነው።
አደባባይ ሚዲያ በሰኔ 26 ቀን 2015 ዓ.ም ዘገባው “ተጠቋሚዎቹን በይፋ ሳያሳውቅ፣ ነገ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አቅርቦ ያስመርጣል፤‘በሸክም የሚገቡ ሰካሮች እና ሕዝብ በአደባባይ ያበረራቸው አማሳኞች አሉበት’።የዕጬ ኤጲስ ቆጶሳት ጥቆማን ድብቅነት የተቃወሙት ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን በአስመራጭ ኮሚቴው ተከሠሡ። ነገ፣ ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ለዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ እንደሚቀመጥ የሚጠበቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በድብቅ እና ሕገ ወጥ አካሔድ የተጠቆሙ ቆሞሳትን በዕጩነት እንዳይቀበል በመጠየቅ ግልጽ ተቃውሞ ያሰሙት፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ በላይ መኰንን፣ በአስመራጭ ኮሚቴው የክስ አቤቱታ ቀርቦባቸዋል” በማለት ነው። በዚህ ዘገባ ውስት ምክትል ሥራ አስኪያጁ “ነገ፣ ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ለዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ እንደሚቀመጥ የሚጠበቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በድብቅ እና ሕገ ወጥ አካሔድ የተጠቆሙ ቆሞሳትን በዕጩነት እንዳይቀበል በመጠየቅ ግልጽ ተቃውሞ ማሰማታቸው ተገልጧል። ርጫው በድብቅ መካሔዱ ኢቀኖናዊ መሆኑን የሚያስገነዝብ ሲሆን በሕገ ወጥ አካሔድ የተጠቆሙ ቆሞሳት በዕጩነት እንዳይቀርቡ መገለጡ ሌላ አጀንዳ ከሌላው ተስተቀር የቤተ ክርስቲያን ድምፅ መሆኑን መረዳት ይገባል።
“ለምን በድብቅ ይጠቆማል? ለምእመናን አይደለም ወይ የሚሾመው?” በማለት መጠየቃቸውን አደባባይ ሚዲያ የዘገበው “የካህናት እና የምእመናን ተሳትፎ፥ ትክክለኞቹን አባቶች ከፍ ወዳለው መዓርግ ለማምጣት ከማገዙም በላይ፣ ለዚህመዓርግ የማይበቁትን ለመለየትም እንደሚጠቅም አስረድተዋል። ለአብነትም፤ ከሰካርነታቸው የተነሣ በየሜዳው ወድቀው በሰው ትክሻ ወደ ቤት የሚገቡ፤ በአስተዳደር በደላቸው ሕዝብ ከኃላፊነት ያባረራቸውና የመሳሰሉት በጥቆማው ስለመካተታቸው መረጃው እንዳላቸው፣ ለአስረጅነት ጠቅሰዋል” ይላል ። እንዲህ ያሉ አባቶች ተካትተው ከሆነ የቀረበው ማሳሰቢያ ጉዳዩን ደግሞ ማየት እንደሚገባ እንጂ ሥራውን አጠናቀናል ተብሎ የሚታረፍበት አለመሆኑን የሚያስገነዝብ ነው።
“የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ዛሬ ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሚያካሔደው የዘጠኝ አዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ፣ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙት ሰባት አህጉረ ስብከት ለመመደብ፣ በአስመራጭ ኮሚቴው የቀረቡት 14 ተጠቋሚ ቆሞሳት ዝርዝር እንደደረሰው አደባባይ ሚዲያ ገልጦ በአንድ ሀገረ ስብከት ሁለት አባቶች እንደሚወዳደሩ ጨምሮ ገልጧል። በእጩነት ከቀረቡት አባቶች መካከል “ለቡኖ በደሌ፣ ድሬዳዋ እና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ አህጉረ ስብከት የቀረቡት ስድስት ተጠቋሚ ቆሞሳት፣ እንዲሁም ለምሥራቅ ሐረርጌ ከቀረቡት ውስጥ አባ ተክለ ማርያም ስሜ የተባሉት፣ ባለፈው ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ – ወሊሶ ሀገረ ስብከት ሀሮ ዳጬ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሞ ከነበረው ሕገ ወጥ የኤጰስ ቆጶሳት ሢመት የተመለሱ ናቸው” ይላል። ይህ ዘገባ በኢቀኖናዊ ሢመት ተካትተው ከነበሩ አባቶች መካከል የታጩ መኖራቸውን የሚያስገነዝብ ነው፡፡
ዐደባባይ በሌላ ዘገባው “ጥያቄዎች የበዙበት የቅዱስ ሲኖዶስ የአዳዲስ ኤጲስ ቆጰሳት ምርጫ ጉባኤ ከጅምሩ በውዝግብ እና በግልግል አረፈደ፤ አምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አቋርጠው ወጡ ።ለስብሰባው የተገኙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቁጥር ከሚጠበቀው በታች እንደኾነና ምልአተ ጉባኤ ሆኗል ለማለት እንደማይቻል ተገልጿል። በጥር 14ቱ ሕገ ወጥ ሢመት የተሳተፉት፣ የብፁዕ አባ ኤዎስጣቴዎስ እና የብፁዕ አባ ዜና ማርቆስ በጉባኤው አለመገኘት እያነጋገረ ነው። አስመራጭ ኮሚቴው፣ ከጉባኤው አባላት ለቀረቡለት የቅድመ ምርጫ ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ በአፋጣኝ ምርጫውን ማስፈጸም ላይ ትኩረት ሰጥቷል፤ዛሬ ማክሰኞ፣ ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠዋት፣ ለዐዲስ ኤጲስ ቆጰሳት ምርጫ የተሠየመው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የቀትር በፊት ውሎ፣ በውዝግብ መቋጨቱ” ገልጧል።
ዐደባባይ ሚዲያ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤን በተመለከተየዘገበው “ከውጭ ይልቅ የሀገር ውስጥ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት፣ በአንጻራዊ ብዛት የተገኙበት ነው፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ የስብሰባ ሥነ ሥርዐት መሠረት፣ ቀኖናዊ ለኾነው የሢመተ ኤጰስ ቆጰሳት አጀንዳ፣ ከጠቅላላ አባላቱ (53+)፣ ቢያንስ 75 በመቶ ማለትም ከ38 ያላነሱ አባላት መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ኾኖም፣ የተገኙት አባላት ከ30 ያልበለጡ እንደኾኑና ተፈላጊው የምልአተ ጉባኤ ቁጥር ባለመሟላቱ፣ ስብሰባውን ለመቀጠል አዳጋች እንደሆነበት፣ ከሹመት ይልቅ እርቁን እናስቀድም። የምንሾምለት ሕዝብ ጥቁር ልበስ ስንለው ጥቁር የለበሰ፣ ሱባኤ ግባ ስንለው ሥራውንና ጥቅሙን ሠውቶ ሱባኤ የገባ፣ ሙት ስንለው የሞተ እንደኾነ ያስታወሱት ብፁዕነታቸው፣ ለሕዝብ በቁዔት የማይሆን ሢመተ ኤጲስ ቆጶስ መልሶ እንዳይጎዳን መጠንቀቅ እንደሚገባ፡ አሳብ ያቀረቡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መኖራቸውንም ገልጧል።
ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል የዘገበው ደግሞ “የተሰየሙት አስመራጭ ብፁዓን አበው ሊቃነጳጳሳት ቋሚ ሲኖዶስ አስቀድሞ ባወጣው የእጩ ኤጲስ ቆጶሳት መመልመያ መስፈርት መሠረት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በጥቆማ ከቀረቡላቸው 75 ቆሞሳት መካከል በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በአሠረ ምንኲስናቸው፣ በቋንቋ ችሎታቸውና መንፈሳዊ አገልግሎታቸው መስፈርቱን አሟልተው የተገኙትን 18 እጩ ቆሞሳትን ከነሕይወት ታሪካቸው የተሟላ ሪፖርት ሰኔ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ለቋሚ ሲኖዶስ አቅርበዋል። ቋሚ ሲኖዶስም የቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ በቀረቡት እጩ ቆሞሳት ላይ ምርጫ እንዲደረግ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ባስተላለፈው የስብሰባ ጥሪ መሠረት ከሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባደረገው የ2 ቀን ስብሰባ በሁለት ዓበይት አጀንዳዎች ማለትም በእጩ ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫና በትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት ወቅታዊ ችግር ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል” የሚለው ይገኝበታል።