በሕገ ወጥ ሹመት የተሳተፉ አባቶችን ዕጩ አድርጎ ማቅረብ ያለው ዳፋ

በሕገ ወጥ ሹመት የተሳተፉ አባቶችን ዕጩ አድርጎ ማቅረብ ያለው ዳፋ

በሕገ ወጥ ሹመት የተሳተፉ አባቶችን ዕጩ አድርጎ ማቅረብ ያለው ዳፋ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦት ፳፻፲፭ ዓ.ም በነበረው የርክበ ካህናት መደበኛ ጉባኤው አዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም አስመራጭ ኮሚቴ መሠየሙ ይታወቃል።ኮሚቴው ዕጩ ኤጲስ ቆጶሳትን እንዲያቀርብ ከመሠየም ውጪ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዩን በምሥጢር እንዲያከናውን የሰጠው ትእዛዝ የለም። የተሠየመው አስመራጭ ኮሚቴ ግን ሥራውን በድብቅ ሠርቶ ለቋሚ ሰኖዶስ ሪፖርት አድርጓል። ቋሚ ሲኖዶሱም የሥራውን መጠናቀቅ በመግለጽ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እንዲገኙ ጥሪ አስተላልፏል። የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤም ኮሚቴው በዘጠኙ አህጉረ ስብከት የሚመደቡ ዘጠኝ ተሿሚዎችን ለመለየት የመጨረሻዎቹን ፲፰ ዕጩዎች ማቅረቡን በመግለጽ ሪፖርት ሲያደርግ በምርጫ ዘጠኙን በመለየት ሹመታቸው ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም እንደሚፈጸም ውሳኔውን ይፋ አድርጓል። ኮሚቴው ካቀረባቸው ዕጩዎች ውስጥ ሰባቱ ጥር ፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በሕገ ወጡ ሢመት ተሳታፊ የነበሩ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠዋል። የእነዚህ አካላት በዕጩነት መቅረብ እጅግ ብዙ ውስብስብ ችግሮችን የሚፈጥር መሆኑ አያጠራጥርም። ለማሳያ ያህል የተወሰኑትን እንመልከት።

፩. የምእመናንን ሰማዕትነት ከንቱ ማስቀረት ነው

ጥር ፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በተፈጸመው ሕገ ወጥ ሢመት ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን መግለጫ እና ያወጀችውን ዐዋጅ ተከትሎ ምእመናን በጾም፣ በጸሎት፣ በሐዘን፣ ሕወታቸውን ሳይቀር አሳልፎ በመስጠት ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ምን ያህል ቁርጠኞች መሆናቸውን አሳይተዋል። ታስረዋል፤ ተንገላተዋል፣ ተደብድበዋል፤ ከሥራ ተፈናቅለዋል፤ ቀላልና ከባድ አካል ጉዳት አስተናግደዋል፤ ሰማዕትነት ተቀብለዋል። ይህ ሁሉ የሆነው ቤተ ክርስቲያኔን አላስደፍርም፤ ቀኖና እና ሥርዓቷ አይጣስም በሚል ነው። ይህ ሁሉ መሥዋዕትነት የተከፈለበትን ጉዳይ ያለ ምእመናን ፈቃድና ይሁንታ ለዚህ ሁሉ ችግር ምክንያት የሆኑ ተሿሚዎችን ለሹመት ዕጩ አድርጎ ማቅረብ ዳፋው ቀላል አይደለም። ምእመናን በአባቶች ላይ ያላቸውን እምነት ይሸረሽራል። ለቤተ ክርስቲያን መሞት፣ ለቀኖናዋ መቆርቆር፣ ለሥርዓቷ ዘብ መቆም ትርጉም አልባ እንዲሆንባቸው ያደርጋል። ያስገደሏቸውን ሰዎች በአባትነት እንዲቀበሉ መደረጋቸው ደም የተከፈለበት ባርነት ውስጥ ማስገባት ይሆናል። በአጠቃላይ ይህ ውሳኔ ምእመናን አባቶቻቸው ሲጠሯቸው የማይሰሙበት ጊዜ እንዲቀርብ የሚያደርግ ስለሆነ ቆም ተብሎ ሊታሰብበት ይገባል።

፪. መርሕ አልባ ሹመትን የሚያለማምድ ነው

በዕጩነት ከቀረቡት ውስጥ የተካተቱት በሕገ ወጥ ሢመቱ የተሳተፉት ሦስቱ መነኮሳት በዕጩነት ለመቅረብ ያበቃቸው ብቸኛው ምክንያት በሕገ ወጡ ሢመት መሳተፋቸው ነው። ይህ ደግሞ ነገ ሌላውም ተነሥቶ ተሾሜያለሁ እያለ በማወክ ሹመቱ እንዲጸድቅለት እንዲጠይቅ የሚያበረታታ ነው። መንፈሳዊ ሹመት የጸና ዓለም አቀፋዊና ሐዋርያዊ ቀኖናና ሥርዓት አለው። ቤተ ክርስቲያን ያላት የሹመት ሥርዓት ለብዙ ዘመናት ጸንቶ የቆየና በቀኖናና በግዝት የታጠረ ነው። ማንም እንዳሻው የሚዘርፈው አይደለም። ለሚገባው እንጂ ላሻው ሁሉ አይሰጥም። “ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን” እንዳለው ሐዋርያው ከሕግና ከሥርዓት ውጪ የሆነ አካሔድ ሁሉ ውሎ አድሮ ለራስም ለሌላውም ዳፋ ይዞ መምጣቱ አይቀሬ ነው። በሕገ ወጡ ሢመት ላይ የተሳተፉት ሦስቱ ዕጩዎች መርሕ አልባ ሹመትን ለመፍቀድ ማሳያዎች ከመሆናቸው በዘለለ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እነዚህን የሚመርጡበት የተለየ ምክንያት የለም።

፫. አጥፊዎችን ከጥፋታቸው ተጠቃሚ የሚደርግ ነው

በዓለማዊ የሕግ መርሕ ማንም ሰው ከራሱ ጥፋት ተጠቃሚ ሊሆን አይገባም የሚል መርሕ አለ። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ለወራሽነት ያልተገባ መሆን የሚለው የሕግ ፅንሰ ሐሳብ ነው። አንድ ልጅ የአባቱ ወራሽ ለመሆን በሕይወት መኖር አለበት ይላል ሕጉ። በሕይወት ኖሮም ግን ላይወርስ የሚችልበት ሌላም ምክንያት አለ። እርሱም ለወራሽነት ያልተገባ መሆን ነው። በሟቹ ላይ የግድያ ወንጀል ወይም የመግደል ሙከራ ቢኖርና ይህ ቢታወቅ ከጥፋቱ ተጠቃሚ ሊሆን አይገባውም ተብሎ ከውርሱ ይገለላል። አባቱን የገደለ ሰው የገደለውን አባቱን ሀብት ሊወርስ አይገባውም። እነዚህ አካላትም ንቀው የገደሏትን ክህነትን እንደገና ሊያገኟት አይገባም። እንዲህ ማድረግ ከጥፋታቸው እንዲመለሱ ወይም እንዲጸጸቱ ሳይሆን በጥፋታቸው እንዲቀጥሉ ሽልማት መስጠት ነው። እነርሱ በሕገ ወጥ መንገድ ተሾመናል ብለው በመንግሥት የጸጥታ አካላት ድጋፍ በፓትሮል ታጅበው መናብርተ ጵጵስናና አብያተ ክርስቲያን እየሰበሩ የገቡ፣ የምእመናን ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት የሆኑ ናቸው። ይህ ድርጊት ከነበሩበት የክህነት መዓርግ የሚያሽራቸው እንጂ ኤጲስ ቆጶስነት የሚያሾማቸው ሊሆን አይገባም።

፬. የጵጵስናን ክብር ማቃለል ነው

ሴሰኞች፣ አመንዝሮችና ነፍሰ ገዳዮች ጵጵስና የሚሾሙ ከሆነ ምእመናን ለጵጵስና ያላቸውን ክብር፣ ለክህነት የሚሰጡትን ቦታ ዝቅ የሚደርግ ነው። እነዚህ አካላት ሢመትን በፈረስ አንገት በጦር አንደበት በቅሚያ ለመውሰድ የታገሉ ሴሰኞች ናቸው። የራሳቸውን የክህነት መዓርግ በመናቅ የማይገባቸውን ኤጲስ ቆጶስነት በአቋራጭ ለማግኘት የቀላወጡ አመንዝሮች ናቸው። በሕገ ወጥ መንገድ ያገኙትን ሹመት ለማስጠበቅ የምእመናንን ደም ያፈሰሱ፣ ቤተ ክርስቲያንን ማቅ ያስለበሱ፣ ክርስቲያኖችን ደም እንባ ያስለቀሱ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው። እነዚህን በዕጩነት ማቅረብ ክብረ ክህነትን ማቃለል ነው። የተከሰተውን ችግር ለመፍታት የግድ እነዚህ በሕገ ወጥ ሢመት የተሳተፉት መሾም የለባቸውም። በቋንቋ ከመገልገል ጋር ተያይዞ የሚቀርብ ጥያቄንም መረቁን ከምርቁ ለይቶ መመለስ ይገባል። የሕዝበ ክርስቲያኑን ባህልና ቋንቋ የሚችል ሰው መሾም ቢያስፈልግ እንኳን ለኤጰስ ቆጶስነት የሚያበቁ በቀኖና መጻሕፍት የተቀመጡ መስፈርቶችን መሠረት በማድረግ መሾም እንጂ ከፖለቲካዊ ጥያቄዎች ጋር በማዳበል የክህነትን ክብር ዝቅ ማድረግ አይገባም።

፭. ሿሚዎችን ያስነቅፋል  

ካህናት አዕይንተ እግዚአብሔር ናቸው። አንድ የሩሲያ ሊቀ ጳጳስ ከፕሮፌሰሮች ጋር ተሰብስበው ሲወያዩ ‘እስከ ግድግዳው ድረስ ከእናንተ ጋር እኩል፣ ከግድግዳው ጀርባ ግን ብቻችንን እናያለን” እንዳሉት ካህናት የማያዩት የለም። የእግዚአብሔር ዐይኖች ሁሉን እንደሚያዩ ዐይኖቹ የሆኑ ካህናትም ሁሉን የሚያዩና የሚያስተውሉ ናቸው። የካህን ዐይን የማያየው ነገር ሊኖር አይገባም። ፍካሬው ካህን የማያውቀው ነገር ሊኖር አይገባም ማለት ነው። በዚህ ልክ የሚታሰቡ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሰው ሳይጠፋ፣ በሕገ ወጥ መልኩ የተሾሙበት ማኅተም ሳይደርቅ ሕገወጦቹን በዕጩነት ማቅረባቸው በእጅጉ የሚያስነቅፍ ይሆናል። በእነዚህ ሕገወጦች ድርጊት ልጆቻቸውን ያጡ እናቶች፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆች፣ ባሎቻቸውን ያጡ ሚስቶች፣ በአጠቃላይ የሥጋ ዘመዶቻቸውን ያጡ ክርስቲያኖች እነዚህ ሰዎች ተሾመው ወደ ሀገረ ስብከታቸው ሲሔዱ ምን እንደሚሰማቸው ማሰብ አለመቻል የሚያስነቅፈው ሿሚዎቹን ነው። ምእመናን ገዳዮቻችንን በአባትነት ተቀበሉ ልንባል አይገባንም ብለው ቢቃወሙ ዕጩዎቹ ምን ሆነው ሊቀጥሉ ነው የሚለው ሊታሰብበት ይገባል።

በአጠቃላይ በሕገ ወጡ ሢመት ላይ የተሳተፉት አካላት ለዚህ መዓርግ የሚያበቃቸው የትምህርትም ሆነ የግብረ ገብነት ውኃልክ ላይ የሚገኙ አይደሉም። ስለሆነም በቀጣይ የሚያስከትለውን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት ጉዳዩን በድጋሜ ማጤን ያስፈልጋል እንላለን።