በሰማይ የሀሉ ልብክሙ – ልቡናችሁ በሰማይ ይኑር ቅዳሴ እግዚእ
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ በአኃት አብያተ ክርስቲያን ጸሎተ ቅዳሴ የሚጀመረው ካህኑ ከምእመናን ጋር በሚያደርገው ተዋሥዖ (ምልልስ) ነው፡፡ ብሔራውያን ሊቃውንት ከመጽሐፈ ኪዳን የወሰዱትን አኮቴተ ቁርባን ቅዳሴ እግዚእ (የጌታ ቅዳሴ) ብለው ሰይመውታል፡፡[1] የዚህ ቅዳሴ አውስኦ የሚጀምረው በዲያቆኑ ‹‹በሰማይ የሀሉ ልብክሙ-ልባችሁ በሰማይ ይኑር›› በሚል ቃል ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ከሐዋርያት ጋር ለዐርባ ቀናት ያህል ሲቆይ ያስተማራቸው እና ከሰባቱ ኪዳናት አንዱ ነው፡፡ ሊቃውንቱ ይህ ቃል ጌታ አስቀድሞ በጸሎተ ሐሙስ ሕብስቱን ያከበረበት በለሆሳስ የደገመው ቃል መሆኑን ይነግሩናል፡፡ ይህንኑ ቃል ከትንሣኤው በኋላ ለሐዋርያት እንዳስተማራቸውም ያስረዳሉ፡፡[2]
ጸሎተ ቅዳሴ በዚህ ምድር ያለችው ቤተ ክርስቲያን ከሰማያውያን መላእክት ጋር ኅብረት የምትፈጥርበት ሥርዓት፣ እግዚአብሔር በአንድያ ልጁ ሞት ለገለጸልን ታላቅ ፍቅር የምስጋና መሥዋዕት የምታቀርብበት የአምልኮዋ ማዕከል ነው፡፡ ልባችሁ በሰማይ ይኑር የሚለው አምላካዊ መልእክት ወደ ፊት በመንግሥተ እግዚአብሔር ከሰማያውን መላእክት ጋር የምንፈጽመውን አምልኮ በምድር ሆነን መለማመድ ወደሚያስችለን ሕይወት የሚመራን አምላካዊ ትእዛዝ ነው፡፡
ምእመናንም ‹‹አዎን ልቡናችን በሰማይ ይኑር፡፡ ስለ ስምህ አጽናን፤ ጌታችን እና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የተዘጋጀንም አድርገን›› በማለት ልቡናን በሰማይ ማኖር ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ እንደማይቻል ያመኑትን ምስክርነት ይሰጣሉ፡፡ እንዲያስችላቸውም ሁሉን የሚያስችል ኃያል ስሙን ጠርተው ይማጸናሉ፡፡
ጌታችን ‹‹ልቡናችሁ በሰማይ ይሁን፤›› ማለቱ ትንሣኤ ልቡናን ሲያስተምራቸው እንደሆነ ሊቃውንቱ ያስረዳሉ፡፡ ሰው ትንሣኤ ልቡና ካላገኘ ነፍስ ከምድር ጋር ካጣበቃት ጊዜያዊ ሐሳብ ተላቅቃ፣ የዲያብሎስን አሽከላ ሰብራ ነጻ መውጣት ይሳናታል፡፡ የእያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ትንሣኤ ልቡና በምእመናን እና በቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዘንድ እየተዳከመ የመጣው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እና መንፈሳዊነት ትንሣኤ እንዲያገኝ መሠረት ነው፡፡ መልካም እረኞች በማነሳቸው ምክንያት የተቀዛቀዘው በምድር ላይ የእግዚአብሔር መንግሥት የሆነችው ቤተ ክርስቲያን የተሰማራችበት ተልእኮ መንፈሳዊ ሙቀት ያገኛል፡፡
ይህ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ልባቸውን በሰማይ የሚያኖሩ ምእመናንን፣ ካህናትንና ጳጳሳትን በባትሪ የምታፈላልግበት ዘመን ነው፡፡ ልባቸውን በሰማይ ያኖሩ፣ ኅሊናቸውን በሰማይ የሆነላቸው በክርስቶስ ኢየሱስ ካገኙት ዘላለማዊ ጸጋ ተካፋዮች ናቸው፡፡ ልባቸውን አጭርና አላፊ ከሆነ ምድራዊ ኑሯቸው ሸክም አላቀው ኆኅተ ሰማይን በሚያስከፍት መንፈሳዊ ተግባር ላይ ያሰማሩ ናቸው፡፡ ስለዚህም ያለንበት ጊዜ ልባችንን በሰማይ የምናኖርበት ጸጋ እንዲሰጠን ደጅ የምንጠናበት፣ ልባቸውን በሰማይ ያኖሩ አባቶች እንዲሰጠን አብዝተን ልንማጸንበት የሚገባ ጊዜ ነው፡፡ ምክንያቱም ልባቸውን በላይ በሰማይ ያኖሩ አበው መልካም እረኝነትን ገንዘብ ያደርጋሉ፤ በበጎቹ፣ በጠቦቶቹ እና በግልገሎቹ መካከል ልዩነት ሳያደርጉ ለሁሉም ነፍስ እኩል ይጠነቀቃሉ፡፡
በእርግጥ ‹‹ልባችሁን በሰማይ አኑሩ፤›› ብሎ የሚመክር የቤተ ክርስቲያን አባት ድምፅ እዚህም እዚያም ይሰማል፡፡ የምእመናን ነፍስ እየተፈተነች ያለችው ደግሞ ይህን መንፈሳዊ መልእክት ለምእመናኑ ሲነግሩ ኖረው እነርሱ ግን ልባቸውን በሰማይ አኑረው የሕይወት መምህር መሆን ባልቻሉ ‹‹አባቶች›› ነው፡፡ ልባቸውን በሰማይ አላኖሩምና ‹‹አኑሩ›› የሚል መልእክታቸው የምእመናንን የልቡና ደጅ ማስከፈት አልቻለም፡፡ በሰማይ በምድር ለሚኖር እግዚአብሔር ሲገዙ አልታዩምና ጵጵስና በክብር ከተጻፈበት የምእመናን የኅሊና ሰሌዳ መፋቅ ጀመረ፡፡ የእግዚአብሔር ጥሪ ሳይደርሳቸው ራሳቸውን ለሹመት አጭተው ሹመት ባለበት በዚያ ሲገፋፉ ያዩ ምእመናን በልባቸው ላይ ለአባቶች የሰጡት ዙፋን ተገረሰሰባቸው፡፡ ኖላውያን ተብለዋል ልባቸውን ግን ለዘውጋቸው፣ ልባቸውን ለገነነ ፍቅረ ነዋያቸው፣ ልባቸውን ለመንደርተኝነታቸው አስረክበዋል፡፡ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ ለሚገኘው ሰማያዊ በረከት የቀረ ቦታ ልባቸው ውስጥ መኖሩ ያጠራጥራል፡፡
ለአገልግሎት የተቀበለውን ሥልጣነ ክህነት የምድር ሕይወቱን ሊያቀናበት የሚሻ ሰው ልቡን ገንዘቡን ባስቀመጠበት በዚህ በምድር እንጂ የነፍስ ፍስሐን ፍለጋ በሰማይ ማኖር ይከብደዋል፡፡ ገንዘብህ ባለበትልብህበዚያደግሞይኖራል። ከምድራዊነት መላቀቅ አይችልም፡፡ ልባቸውን በሰማይ ያደረጉ እውነተኛ አበው ግን መንፈሳቸው ለሰማያዊው ክብር ከመሸነፉ የተነሣ ለቁመተ ሥጋ ያህል የሚመገቡትን መቁኑን እንኳ ጨርሰው ሲረሱት እንመለከታለን፡፡ አንድ ማሳያ ታሪክ አንስተን እንቋጨው፤
አንድ አረጋዊ ሌላውን በተጋድሎ ላይ ያለ አረጋዊ አባትን ሊጎበኝ ወደ በዓቱ ሔዱ፡፡ አስተናጋጁ አረጋዊውም ረድዑን ትንሽ የሚቀመስ እንዲያዘጋጅ አደራ አለው፡፡ ረድዑ በሰዓቱ አዘጋጅቶ አቀረበ፡፡ እነርሱ ግን ስለ መንፈሳዊ ነገር እየተነጋገሩ እስከሚቀጥለው እኩለ ቀን ድረስ ቆዩ፡፡ ልባቸው በሰማይ ነውና የምድሩን ረሱት፡፡ አስተናጋጁ አባትም ረድዑን እንደ አዲስ ‹‹ልጄ ሆይ ትንሽ ነገር አዘጋጅልን›› አለው፡፡ እርሱም ከአንድ ቀን በፊት ያዘጋጀውን አቀረበላቸውና ያን ጊዜ በሉ፡፡[3] አባቶች በእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲህ ሲገናኙ ከለመዱት መንፈሳዊ ተጋድሎ ዐረፍ ብለው ቃለ እግዚአብሔርን እየተነጋገሩ መሽቶ ሲነጋ፣ ቀን ሔዶ ቀን ሲተካ አይታወቃቸውም፡፡ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ ከአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጋር በተገናኙ ጊዜ፣ እንዲሁም ሌሎች ቅዱሳን ስለመገናኘታቸው በተዘገበባቸው ድርሳናት ተመሳሳይ ነገር መፈጸሙ ተከተቧል፡፡ በሚነጋገሩት መንፈሳዊ ቃል ተመስጠው የሥጋ ረለብ፣ የአካል ድካም አይሰማቸውም፤ ልባቸውን በሰማይ አኑረዋልና፡፡
ዋቢ መጽሐፍት
- ቀሲስ ዶ/ር መብራቱ ኪሮስ (፳፻፲፪ ዓ.ም.)፤ አኮቴተ ቁርባን፤ ገጽ ፻፵፬፤ ፪፻፹፯፤
- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ (፳፻፲ ዓ.ም.)፤ እረኛ ወይስ ምንደኛ፣ ገጽ ፺፤
- ዲ. ያረጋል አበጋዝ (፳፻፰ ዓ.ም.)፤ ከበርሐውያን ሕይወትና አንደበት፤ ገጽ ፵፫