ከእግዚአብሔር ጋር መታገል

ከእግዚአብሔር ጋር መታገል

ከእግዚአብሔር ጋር መታገል

ንስሐ ገብተህ ኃጢያትን ለማስወገድ ትፈልጋለህ? አንድ ነገር አስታውስ። ኃጥያትን ለማሸነፍ የሚደረገው ትግል በሰው ጉልበት ብቻ ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ኃጥያት ጠንካራ በመሆኗ “ወግታ የጣለቻቸው ብዙዎች ናቸው። እርሷም የገደለቻቸው ብዙዎች ናቸው” ምሳሌ(7፥26) ተብሎ ተጽፏል።

 

ይህ አዳምን፣ ሶምሶምን፣ ዳዊትና ሰለሞንን ወግቶ የጣለ ኃጢያት ያለ እግዚአሔር አጋዥነት አንተ ብቻዬን እወጣዋለው ብለህ ታስባለህ? አስቀድመህ የወደቅህበት ኃጢያት ያለ እግዚአብሔር እርዳታና ድጋፍ አንተን እንደሚቆጣጠርህ አትጠራጠር። ውጊያው ውጫዊ የሆነ ጦርነት ብቻ አይደለም። በተለይ የኃጢያት ዝንባሌ የምታሳይ ከሆነ ውጊያው እጥፍ ነው የሚሆነው። የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ እንዲህ ይላል። “እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል”(መዝሙር 127፥1)። ጌታ እራሱ “ያለ እኔ አንዳች ነገር ማድረግ አይቻላችሁም”(የሐዋ 15፥5) ይላል። እግዚአብሔርን ሳትይዝ የምታደርገው ትግል ፍጻሜው ውድቀት መሆኑን አትጠራጠር። ውጊያውን ማሸነፍ ቢቻልህ እንኳን በከንቱ ውዳሴ ተጠልፈህ መውደቅ መቻልህን አትዘንጋ። ምክንያቱም በራስህ ኃይል ታግለህ እንዳሸነፍከው ይሰማኻልና።

 

ትሕትና ሰይጣንን ልናሸንፍበት የምንችለው መሣሪያ መሆኑ ተደጋግሞ ተገልጿል። ቅዱስ እንጦስ በትሕትና ሰይጣንን እንዲህ አለው፤ “ከአንተ ከትንሹ የባስኩኝ ደካማ ነኝ።” ወደ እግዚአብሄርም አዘውትሮ እንዲህ በማለት ይጸልይ ነበር፤ “ጌታ ሆይ አንዳች ነገር የሌለኝን እኔን እንደባለጸጋ አድርጎ ከሚቆጥረኝ ከጠላቴ ሰይጣን ወጥመድ ጠብቀኝ።”

 

ምን ያህል ጊዜ ለመነሣት ሞከርክ? ምንስ ያህል ጊዜ ሳይሳካልህ ቀረህ? ቅዱሳን መጽሐፍት የሚመክሩንህ ይሕንን ነው፤ “ንስሐ ለመግባት ቃል እገባልኻለው” ብለህ ለአምላክህ ከመናዘዝ ይልቅ “አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና መልሰኝ እኔም እመለሳሁ”(ኤር 31፥18) በለው። ንስሐን ከእግዚአብሔር የምትቀበለው በጎ ሥጦታ አድርገህ ለምን። እርሱ ራሱ እንዲህ ይልኻል፤ “መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፣ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉታላችሁም”(ሕዝ 36፥27) ከቃልኪዳኑ ጋር ተጣበቅ ይህንን ንስሐ ይሰጥህ ዘንድ ለምነው። ቅድስት ቤተክርስቲያን የምታስተምረን ይኼንን ነው።

 

“በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለሁ፤ እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ”(መዝ 51፥7)። ነጭ እንድትሆን የሚያጥብህ እግዚአብሔር እንጂ አንተ ራስህን አጥበህ ነጭ ማድረግ አይቻልህም። በሦስተኛው ሰዓት ጸሎታችን እንዲህ እንላለን፤ “ከሥጋና ከነፍስ እድፍ አንጻን። ጽድቅህን እንከተል ዘንድ በመንፈሳዊ ሕይወት መንገድ ምራን።” ስለዚህ ከቤተክርስቲያችን አስተምህሮ የምንማረው ንስሐና ንጹህ መሆን የእኛ ጉልበት ውጤት ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጠይቀን የምንቀበለው ጸጋ  መሆኑን ነው። ሰው፤ “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ እኔ ራሴን ማንጻት አልቻልኩም” ሊል ይገባዋል። አንተም፤ “እንደ ቃልኪዳንህ ተነሣና ሕይወቴ ድኅነት የሚያገኝበት ስጦታህን ፈጽም” በለው።

 

በዚህ ሥፍራ ወደ ንሥሐ ለመድረስ የጸሎት አስፈላጊነት ጎልቶ ወጥቷል። ቅዱስ ይስሐቅ እንዲህ ይላል፤ ”ከጸሎት ውጭ ወደ ንስሐ የሚመራ መንገድ አለ ብሎ የሚያስብ ወገን እርሱ በሰይጣን ተታሏል። እናንተን በተመለከተ የምናገረውን ነገር ይህ ነው። በተጋድሎአችሁ ሁሉ በራሳችሁ ጥንካሬ አትተማመኑ፤በራሳችሁም ማስተዋልና በጥንካሬያቸሁ አትደግፉ። ያለ እግዚአብሔር እርዳታ ወደ ንስሐ መድረስ አይቻላችሁም።” እንደዚህ ከሆነ ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፤ በእኔ የሚያድር ኃጢያት ነው እንጂ በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና ፈቃድ አለኝና መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም”(ሮም 7፥17-19)። ጌታ ሆይ አንተ እንዲህ ያልክ አይደለህምን?” እኔ ራሴ በጎቼን አስማራለሁ፣የባዘነውም እመልሳለሁ፣የተሰበረውንም እጠግናለሁ፣የደከመውንም አጸናለሁ፣ የወፈረውንና ተበረታውን አጠፋለሁ”(ሕዝ 34፥15-16)። ጌታ ሆይ እኔ የጠፋሁ፣የተሰበርኩ የባዘንኩና የታመንኩ በግህ ነኝ በሉት።

 

የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷል።(ሉቃ 19፥10) እኔ ድኅነትን ከሚፈልጉ ባሪያዎችህ መካከል አንዱ ነኝ። ድኀነትን የምፈልገው ከዘላለማዊ ፍርድህ ብቻ ሳይሆን በእኔ ላይ  ከነገሠ ኃጢያትም ነው። ሥምህ ኢየሱስ ነው፤ መድኃኒትና አዳኝ። ምክንያቱም ሕዝብህን ከኃጢአታቸው አድነካቸዋልና፤ ስለዚህ እኔንም ከኃጢያት አድነኝ።

 

ወንድሜ ሆይ ለንስሐ እንዲያበቃህ ከእግዚአብሔር ጋር የምትታገልበትን ጥበብ ተማር። በመስጠም ላይ እንዳለ በአቅራቢያው ባለው ጀልባ ላይ ለመውጣት እንደሚታገል ሰው ኃጢያትን ታገል። “ካልባረከኝ አለቅህም”(ዘፍ 32፥26) በለው። ጌታን እንዲህ በለው፤ “ድካሜንና ውድቀቴን አውቃልሁ፣ በራሴ መንገድ ኃጢያትን ለመተው ሞክሬአለሁ፣ አሁን በሕይወቴ አንተ ጣልቃ ትገባ ዘንድ ያስፈልጋል፣ እኔ በራሴ ኃይል ኃጢያትን መተው አልቻልኩምና።”

 

ትእዛዝህን እጠብቅ ዘንድ፣ ሕይወትም ይሆኑኝ ዘንድ፣ ትእዛዝህንና ሕግህን የምጠብቅበት ጥንካሬን ስጠኝ።የኃጢያት ፍቅር ቆርጬ የምጥልበትን ፍቅርህን በልቡናዬ ውስጥ አሳድር። በጸሎት ጠንክር። ይህ መንገድ ወደ ንስሐ መርቶ የሚያደርስህ አስተማማኝ መንገድ ነውና። ጠንካራና ጸሎትን ገንዘብ ያደረገ በውጊያው እግዚያብሔርን ርዳታ የሚጠይቅ ተዋጊ ፈጽሞ ሊሸነፍ አይችልምና።

 

ስለዚህ እግዚአብሔር አስቀድመህ ታገል ከርሱም ኃጢያትን ድል የምታደርግበት ኃይል ውሰድ።የምትዋጋበትን  መንፈሳዊ መሣሪያ በእምነት ጠይቅ። ከእርሱ መለኮታዊ ቃልኪዳንን ገንዘብ አድርግ። እርሱም አዲስ ልብና ንጹሕ መንፈስን ነው። የምትዋጋበትን እምነት ገንዘብ አድርግ። በውጊያውም በአሸናፊነት እንደምትወጣ ታመን። ከእግዚአብሔር ጋር ሆነህ በምታደርገው ተጋድሎ ውጤታማ ከሆንክ በዚህ ምድር ላይ ሊዋጋህ ሊያሸንፍህም የሚችል ኃይል አይኖርህም። ነገር ግን ጌታ ለነብዩ ኤርሚያስ የገባውን ቃልኪዳን በሕይወትህ ተፈጻሚ ሲሆን ትመልከተዋልህ። እርሱም እንዲህ የሚል ነው፤ “ከአንተ ጋር እዋጋለሁ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ  ጋር ነኝ፣ ድል አይነሡህም “(ኤር1፥19)

 

በውስጥም በውጭም የምታደርገውን ጦርነት እግዚአብሔር ከአንተ ጋር በመቆም አብሮህ ይዋጋል። ውጊያው በአእምሮህም በልብህም ውስጥ ከሚመላለስ ዓለማዊ አሳብ ጋር ሁሉ ነው፡። ስለዚህ በመንፈሳዊ ጦርነትህ ሁሉ፤ “ሰልፉ የእግዚአብሔር  ነው”(1ኛሳሙ 17፥47) በል። እግዚአብሔር በብዙም በጥቂቱም ለማዳን የሚከለከለው አንዳች ነገር የለም። እስራኤል ከአማሌቃውያን ጋር በተዋጉ ጊዜ ውጊያው የተዋጋው ያሸነፈውም እግዚአብሔር ነው።(ዘጸ17፥16) በተመሳሳይ ሁኔታ እግዚአብሔር ከጠራኸው በልብህ ውስጥ ተገቢውን ሥፍራ ከሰጠኸው በአንተ ውስጥ ነግሠው ዙፋናቸውን ከዘረጉ ኃጢአቶችን ጋር ይዋጋል። ይገለባብጣቸዋልም። ኃጢያትን እናሸንፈዋለን፤ “አይዞአችሁ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”(ዮሐ 16፥35)። ይህን ያለው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ አንተ አይደለህም። በፈጣሪያችንና በአምላካችን ድጋፍ ካልሆነ በስተቀር ወደ ንስሐ መምጣት ኃጢያትንም ማሸነፍ አይቻልህም።

 

እርሱ ለእኛ ባለው እውነተኛ ፍቅር ምክንያት ከውድቀታችን ሁሉ ያነሣናል። በክርስቶስም አሸናፊ የምንሆንበትም ጸጋ ያለብሰናል(2ቆሮ2፥14)። ከመምህራችን ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር በመሆን እንዲህ ማለትም ይቻለናል፤ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ”(ፊል 4፥15)።

 

ያለ ክርስቶስ ምንም ነገር ማድረግ አይቻልህም። ከኃጢያት ጋር ከመታገልህ አስቀድመህ ከጌታህ ጋር ታገል። ያዕቆብ ወንድሙን ኤሳውን ከመገናኘቱም አስቀድሞ ከእግዚአብሔር ጋር እንደታገለ አስብ። እግዚአብሔርን ታግሎ ማሸነፍ ሲቻለው ነገሮችን ቀላል ሆኑለት። ከኃጥያት ጾር ጋር ለመታገልህ በፊት መጀመሪያ ከማን ጋር መታገል እንዳለብም ማውቅ ይኖርብናል።

 

ያዕቆብም እንዲህ በማለት ይመልስልሃል፤ “ይህንን ሰው ማሸነፍ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው” ይልሃል። ስለዚህ፤ “አስቀድሜ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ እሄዳለሁ ኤሳውን ለመገናኘት  ስወጣ እግዚአብሔር ጋር እሄዳለሁ።” ኃጢአትም ለማሸነፍ ተመሳሳይን ነገር አድርግ።

 

አንዳንድ ጊዜ የንስሐ ፍላጎት እንኳን በውስጥህ ላይነሳሳ ይችላል። እንዴት መዋጋት እንዳለብህ  አታውቅም። የጠላትህን ፈተና ልትቋቋም አትችልም። በአጭሩ እንዴት ንስሐ መግባት እንዳለብህ ሊጠፋህ ይችላል። አንድ ጊዜ ብታሸንፍ እንኳን ብዙ ጊዜ ድል ትሆናለሁ። እግዚአብሔር በጸሎት ከእርሱ ጋር የሚደረግን ትግል ይወደዋል። ምክንያቱንም ከእርሱ ጋር የሚታገሉ ወገኖች ኃይል-መንፈሳዊን ገንዘብ ማድረግ ይቻላቸዋልና።

 

ሰው፤ “ብዙ እጸልያለሁ ነገር ግን ወደ ንስሐ መመለስ አልተቻለኝም” ሊል ይችላል። ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የሚስማማ ማንኛውም ጸሎት መልስ ሊያገኝ ይገባዋል። ለንስሐ የሚደረግ ጸሎት ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ይስማማል። ነገር ግን ምናልባት ጸሎትህን  ከልብህ-ጥልቅ የሚነሳ ላይሆን ይችላል። ከእውነተኛ  የንስሐ ልብ የማይነሳና ከእግዚአብሔር ጋር ለመታገልም ተነሳሽነት የጎደለው ሊሆን ይችላል። ጸልየህ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በጸሎትህ ያለማወላወልና ያለማቋረጥ መቀጠል ተስኖህ ሊሆን ይችላል። በጸሎትህም አለመሰልቸትን ገንዘብ አላደረግህ ይሆናል። በእምነት ጌታ የምትጠባበቅበት ጸሎት ያስፈልግሀል። ጸሎትህ በተጋድሎ፣ በእምነት በጽናት ይሁን።

 

ኤሊያስ ሰማይ ዝናብ እንዳያዘንብ ጠየቀ ጸሎቱን ደጋገመ በሰባተኛው ጊዜ መልስ እስኪመጣለት ድረስ ከመጸለይ አላቋረጠም(1ነገ 18፥44)። ከጌታ ጋር የታገለውን ያዕቆብን ተመልከተው፤ “እስኪነጋ ድረስ ታገለው።” (ዘፍ 32፥24) ለሊቱን በሙሉ ሲታገል መልስ እስኪያገኝ ተስፋ አልቆረጠም።

 

ጸሎትህ በፍጹም ንስሐና በተሰበረ ልብ ካልሆነም መልስ ልታገኝ አትችልም። ምናልባት እግዚአብሔር ፈጥኖ የሚሰጠውን መልስ ያዘገየብህ ዋጋውን እንድታውቀው ፈልጎ ይሆናል። ምክኒያቱም፤ በቀላሉ የተቀበልነውን ነገር ቶሎ የመልቀቅ እድላችን ሰፊ ነውና። አንዳንድ ጊዜ፤ ኃጢያት ሲሰለጥንብህ እግዚአብሔር ዝም ብሎ የሚመለከተው ኃጢአትን የመተውና በንስሐ የመመለስን ጥቅም ገንዘብ ታደርግ ዘንድ ነው። ባለህ ጥንካሬህ ሁሉ ትጠብቃታለህ፤ ምክንያቱም የተቀበልከው በታላቅ ድካም እንደሆነ ትገነዘባለህና። በንስሐ ጠንቃቃ ትሆናለህ። ፈሪና ጠንቃቃ ትሆናለህ። አንዳንድ ጊዜ በጸሎትህ ውስጥ እያለህ ወደ ንስሐ ለመመለስ ያለህን ቁርጠኝነት እስከሚመለከት ነው።

 

የጸሎትህ መልስ ለመዘግየቱ ምክንያቱ አንተ የምትሆንበትም ጊዜ አለ። በእውነት አፍህ ይጠይቃል ልብህ ግን ብዙም አይፈልገውም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል፤ “ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉት።” (ዕብ 3፥7) እግዚአብሔር በአንተ ውስጥ ሆኖ የሚዋጋው ጦርነት አንተ ሰነፍ እንድትሆን የሚጋብዝ ሳይሆን ውጊያውን በብቃትና ያለማሰላሰል እንድትዋጋ የሚያደርግ መንፈሳዊ ኃይል ነው።

 

እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንድትሠራ ያደርጋል። ድጋፍ ያደርግልሃል። ነገር ግን፤ በፈቃድህ እንቅፋትህን ወደ ውስጥህ አታስገባ። ከመንፈስ  ቅዱስ ጋር አብረህ የምትሠራ ሁን። አስቀድመህ ፍላጎትህንና መነሳሳትህ ግለጽ።

 

እግዚአብሔር በራሳቸው አንዳች ነገር ማድረግ የማይቻላቸውን ብዙዎችን አድኗል። ለምሳሌ ከቤቱ ጣራ በታች የነበረውን ሽባ (ማር 2፥4)፣ በሕይወትና በሞት መካከል የነበረው የተጎዳው ሰው ደጉ ሳምራዊ መልካም ነገርን ያደረገለት(ሉቃ 10፥40)፣ ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ የነበረው በሽተኛ(ዮሐ 5፥5)። የማይድን በሽታ የነበረባቸውን ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያዳናቸውን ብዙዎችን ልንዘረዝር እንችላለን። እነዚህም ወገኖች በራሳቸው ምን ማድረግ ይቻላቸው ነበር? አንዳችንም ነገር ማድረግ አይቻላቸውም። ጌታችን ከሙታን መካከል እንዲነሡ ያደረጋቸውን ወገኖች ዕጣ ፈንታም ተመሳሳይ ነው። የሞቱ ሰዎች ከወገኖቻቸው መካከል እንዲነሡ የሚያደርግ የተለየ ኃይል በውስጣቸው የለም። ያለ ምንም ጥርጥር በኃጥያት ጨለማ ውስጥ ያለ ሰው በራሱ የሞተ ነው። (ኤፌ 2፥5)

 

“ሥራህን አውቃለሁ ሕያው እንደ መሆንህም ሥም አለህ ሞተህማል።”(ራዕ 3፥1) በራሱ ምንም ማደረግ ካልቻለ እግዚአብሔር ያሥነሳዋል። አስቀድመን ያነሣናቸው ምሳሌዎች ሁሉ የሚያስረዱን፤ እግዚአብሔር ኃጢያተኞችን ለማንሳት የራሱ የሆነ መንገድ ያለው መሆኑን ነው። ወደ ንስሐ መምጣት የተቻላቸው ወገኖች አሉ። ያልተቻላቸውም ወገኖችም አሉ። ወደ ንስሐ መመጣት የተቻለው፤ የጠፋው ልጅ ምሳሌ ነው። ወደ አባቱ ቤት ለመመለስ ተችሎታል። ወደ አባቱ ቤት ለመመለስ ያልተቻለው በጠፋው በግና በጠፋው ጌጥ አማካኝነት የተሰጠው ምሳሌ ነው። ሦስቱም በአንድ ምዕራፍ በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል ውስጥ የተጥቀሱ ናቸው።

 

ያለ እነርሱ ጥያቄ እግዚአብሔር ያዳናችው  ወገኖችን ስንመልከት፤ አብርሃም ከሰዶም አገር ውጭ እንዲኖር አድርጎታል። ሎጥንም ሳይጠይቅ ከኃጢያተኞች ለይቶ ከሰዶምና የገሞራ ሰዎች ጥፋት ጠብቆታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤ “ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን፤ ተነሣ ሚስትህንና  ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፤ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፉ እያሉ ያስቸኩሉት ነበር። እርሱም በዘገየ ጊዜ እግዚአብሔር ስላዘነለትና እነዚያ ሰዎች የእርሱን እጅ የሚስቱንም እጅ የሁለቱን የሴቶች እጅ ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት”(ዘፍ 19፥15-16)። “እግዚአብሔር ስላዘነለት” የሚለው  ሐረግ ያለጥርጥር በእርሱ ላይ ያለውን ትኩረት ያሳየ ነው። ለሌሎች ሰዎች ርሕራሔን ያደረገ አምላክ በአንተም ሕይወት ርሕራሔውን ይገልፃል።

 

 

ንስሃን ገንዘብ አድርግ በዕርሷም መንገድ ተጓዝ። “እግዚአሔር  ድንጋይ ልብህን አውጥቶ አዲስ ልብን ይሰጥሀል(ሕዝ 36፥21)። ሰውም  በንሰሀ  የሚረዳ፣ የሚመልስ እንዲድንም የሚያደርግ እግዚአብሔር የተመሰገነ  ነው።

 

ምስጋና ይሁን  አንድ አምላክ ለሚሆን ለአብ ወልድ ለመንፈስ ቅዱስ አሜን!