“የመንበረ ሰላማ” እና “የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት” ጉዳይ
በትግራይ ክልል የሚገኙ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተከሠተው ጦርነት ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የአስተዳደር ክፍተት በማስተካከል ግንኙነቱ እንዲቀጥል በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ለተጻፉ ደብዳቤዎችም ሆነ በአካል በመሔድ ያቀረቡትን የሰላም ጥያቄ በመግፋት ክልላዊ ሲኖዶስ ለማቋቋም የሚያደርጉትን ሒደት አጠናክረው ቀጥለዋል። መንበረ ሰላማ የሚባል መንበር፣ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት ጉባኤ ጽ/ቤት የተሰኘ መዋቅር እንደፈጠሩ በደብዳቤዎቻቸውና በመግለጫዎቻቸው አሳውቀዋል። ከዚህም አልፈው ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለአገር ውስጥ አምስት ለውጪ አምስት አህጉረ ስብከት በአጠቃላይ አሥር “ኤጲስ ቆጶሳትን” እንደመረጡ አሳውቀዋል። ጳጳሳቱ በዚህ ሳይገቱ ሐምሌ ፲፮ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም መረጥናቸው ካሏቸው ውስጥ ስድስቱን ሾመዋል። የተፈጸመው ድርጊት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆነ፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚፈታተን፣ ሐዋርያዊነቷን የሚያቃልል፣ ቅድስትነቷን የማይቀበል፣ ኵላዊነቷን በጎጥ የከፋፈለ ድርጊት በመሆኑ የማያዳግም መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል። በዚህ ጽሑፍ በመጠኑ መዳሰስ የምንፈልገው የትግራይ ቤተ ክህነትን የትመጣ፣ ለጉዳዩ እንደ ገና መቀስቀስ ገፊ ምክንያቶች፣ የእንቅስቃሴው መሪዎችና ግባቸውን በተመለከተ ነው።
የትግራይ ቤተ ክህነት የት መጣ፡– የትግራይ ቤተ ክህነት አንቅስቃሴ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተደጋግሞ የሚሰማ ቢሆንም እንቅስቃሴው ግን የቆየና ከደርግ ዘመነ መንግሥት የጀመረ መሆኑ የታወቀ ነው። ከሕወሐት መሥራቾች አንዱ የሆኑት ዶክተር አረጋዊ በርሔ “የሕወሐት ታሪክ” በሚል ርእስ ለሦስተና ድግሪ ባዘጋጁት የመመረቂያ ጽሑፋቸው ጉዳዩን በተደጋጋሚ ገልጠውታል። ሕወሐት ከሥሪቱ ጀምሮ የቀድሞውን ዘውዳዊ ሥርዓት በመተቸትና በመንቀፍ የሚታወቅ ከመሆኑ አንጻር የኢትዮጵያ መሪዎች ቅቡልነት የሚመነጨው ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን በመሆኑ ምክንያት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበረው ግንኙነት የተበላሸ ነበር። ስለሆነም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የነበራትን ተሰሚነት ለማጉደፍ ብዙ ደክሟል። ግእዝ ተናጋሪ ካድሬዎችን ወደ ቤተ ክርስቲያን አስርጎ በማስገባት፣ በአባቶች መካከል መለያየት እንዲፈጠር በማድረግ ምእመናንን ከአባቶች የመነጠል፣ በሕዝብና በመንግሥት መካከል እንደ አማካኝ ተቋም ሆና እንዳትታይ የማድረግ ተግባር ሲያከናውን ኖሯል። አባቶች በምእመናን ላይ የነበራቸው ቅቡልነት እንዲቀንስ የፈጸመው ድርጊትም ውጤቱ በተግባር እየታየ ነው።[1]
የቤተ ክርስቲያንን ተጽዕኖ ለመቀነስ ሕወሐት ከወሰዳቸው ርምጃዎች አንዱና ዋናው ቀሳውስትን የድርጅቱ ርእዮተ ዓለም አስፈጻሚ ለማድረግ በተከታታይ ሥልጠናዎችን ይሰጥ እንደ ነበር ዶ/ር አረጋዊ ገልጠዋል። የሥልጠናው ዓላማም የትግራይን ቤተ ክርስቲያን ከዋናው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ነጥሎ ከፓርቲው ስትራቴጂካዊ ግብ ማስማማት ነበር። ይህም የትግራይ ብሔርተኝነትን ኮትኩቶ ለማሳደግ ተጠቅሞበታል። ለካህናቱ ሥልጠና ይሰጡ የነበሩ ካድሬዎችን፣ የቤተ ክርስቲያንን እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ደኅንነቶችንና ተመሳስለው የገቡ ሰላዮችን በመጠቀም በፓርቲው መሪዎች የሚንቀሳቀሱ ጽ/ቤቶች እስከ ማቋቋም ተደርሶ ነበር። የፓርቲው መሥራች ከነበሩት ግለሰብ ጽሑፍ የምንረዳው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የመክፈልና ለማዳከም ስልት ተነድፎለትና ሥርዓት ተዘርግቶለት የሚሠራ የፓርቲው አንድ ፕሮግራም እንደ ነበር ነው። ለዚህም መነሻው በፓርቲው የሚቀነቀነው የዘውግ ፖለቲካ ነው።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን በውስጥ ኩፋሌ መንበር ገጥሟት የቆየ ሲሆን ቀድሞ የነበራትን ተሰሚነት፣ ክብርና ልዕልና ለማሳጣትም ብዙ ውጪያዊ ተግዳሮቶች ተፈራርቀውባታል። ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ጉዳዮች ሳይቀር ምክንያት በማድረግ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥቃት መፈጸም፣ ኦርቶዶክሳውያንን ስልታዊ በሆነ መንገድ ከሥልጣንና ከመንግሥት ኃላፊነት ማግለል፣ አስተምህሮዋን ለማጠልሸት የሚሠሩ ተሐድሶ መናፍቃንን በእጅ አዙር መደገፍ ድርጅቱ ሲፈጽማቸው የኖራቸው የጥፋት ተግባራት ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በተለይም በያዝነው ዓመት የጎሣ ቤተ ክህነትና የጎሣ ሲኖዶስ ማቋቋም በዐዲስ መልክ እንደ አትራፊ ንግድ በብዙዎች እየተተገበረ ያለ አጀንዳ ሆኗል። እነ አባ ሳዊሮስ “የኦሮሚያ ቤተ ክህነት” እና “የኦሮሚያና ብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ” በሚል ከቅዱስ ሲኖዶስና ዕውቅና እና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ “ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመናል” ብለው እንደነበር በተመሳሳይ በትግራይ ክልል የሚገኙ አራት ጳጳሳትም “መንበረ ሰላማ የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት” እና “የጳጳሳት ጉባኤ” አቋቁመናል፤ “ኤጲስ ቆጶሳትን መርጠናል፤ ሾመናል” በማለት በሕገ ወጥ ድርጊት ብቅ ብለዋል።
ጳጳሳቱ ድርጊቱን ሲፈጽሙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን የሰጠችው ክብር አንሶ ለመጨመር አለመሆኑ መታወቅ አለበት። ለዘመናት ጸንቶ የኖረውን ጉዳይ ግለሰቦች ተነሥተው “አጥሯል እናስረዝመው፣ ረዝሟል እናሳጥረው” ማለት እንደማይችሉም የሚታወቅ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የኖረችው በመንበረ ማርቆስ ቢሆንም ከዘመናት በኋላ ራሷን ስትችል መንበሯ በኢትዮጵያዊው አዲስ ሐዋርያ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ሥም ተሰይሟል።
ተልእኮዋ ሰማያዊ የሆነውን ቤተ ክርስቲያን ራሳቸው ከፈጠሩት ከዘመን አመጣሽ የዘውግ ፖለቲካ ጋር በማገናኘት ከመንበረ ተክለ ሃይማኖት ወደ መንበረ ሰላማ ለመመለስ አስመስለው የሚያቀርቡት ማታለያ መሆኑን መረዳት ይገባል። የተወሰደ መንበር ያለ አስመስሎ በተንኮል የዋሀንን በማሳሳት ደጋፊ አድርጎ ቤተ ክርስቲያንን ለመክፈል መሞከር የሚጎዳው ራሳቸውን መሆኑን መረዳት ይገባል። “ማርቆስ አባቴ፣ እስክንድርያ እናቴ” ስትል ለኖረችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአቡነ ሰላማም ሆነ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት የሚባል መንበር ኖሯት አያውቅም። የአቡነ ተክለ ሃይማኖት መንበር የዕጨጌነት እንጂ የፕትርክና አለመሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል።
ስለሆነም በምንም መንገድ ከሐዋርያዊው ቅብብሎሽ ያፈነገጠ ተግባር እየፈጸሙ ሥሙን ማሽሞንሞን የቅዱስ ጴጥሮስን ትምህርት ትታ በመንበሩ ስትመካ የኖረችውን ካቶሊክን በተግባር መምሰል መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊነት የሚገለጸው በዋናነት ከሐዋርያት ጀምሮ ሳይቋረጥ በመጣ የክህነት ክትትል ነው። የክህነት ክትትል ከሐዋርያት የሚጀመር ነው። መናብርት ሁሉ መሠረታቸው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከዋለበት ውለው፣ ካደረበት አድረው በእግርና በሕይወት የተከተሉት ቅዱሳን ሐዋርያትና አርድዕት ናቸው። ከእነርሱ መሠረትነት ውጪ ሌላ ለመመሥረት እየሞከሩ የተወሰደ ለመመለስ የተነሱ አስመስለው ማቅረባቸው አታላይነት መሆኑን አንባብያን ሁሉ ሊገነዘቡት ይገባል። ስለሆነም በትግራይ ክልል የሚገኙ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት የሚቀነቀነው የትግራይ ቤተ ክህነት እና የመንበረ ሰላማ ጉዳይ፣ እንዲሁም ፈጸምን የሚሉት “የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት” ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ያፈነገጠና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የጣሰ በመሆኑ ሳያውቁ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል። ጳጳሳቱ ከፈጸሙት ስሕተት በንስሓ በመመለስ የራሳቸውንም ግራ ሲያጋቡት የከረሙትን ምእመን ሕይወትም ማስተካከል ይኖርባቸዋል። በንስሓ ካልተመለሱ ግን ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚለዩ፣ በታሪክም ሲወቀሱ የሚኖሩ መሆናቸውን መረዳት ይኖርባቸዋል።
ዋቢ መጽሐፍት
- አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)፣ የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ፖለቲካዊ ታሪክ። ፳፻፲፫ ዓ.ም፣ ገጽ ፫፻፹፪-፫፻፹፭