‹‹እንደ ዳኛ ሳይሆን እንደ ጳጳስ አስተዳድር››

‹‹እንደ ዳኛ ሳይሆን እንደ ጳጳስ አስተዳድር››

‹‹እንደ ዳኛ ሳይሆን እንደ ጳጳስ አስተዳድር››

ቅዱስ አምብሮስ በቅድስናቸው፣ በተጋድሏቸው ከሚጠቀሱ የምዕራብ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ገና ወደ ክርስትና ከመምጣቱ አስቀድሞ በሰሜን ኢጣልያ የምትገኘው ሜሎና የተባለች ግዛት ተሹሞ ነበር፡፡ ሹመቱን የሰማ ከእርሱ የበላይ አስተዳዳሪ የነበረ ሹም ‹‹እንደ ዳኛ ሳይሆን እንደ ጳጳስ አስተዳድር›› በማለት በመልካም ሁኔታ እንዲያስተዳድር መከረው፡፡ የዚህ ሀገረ ገዥ ምክር ገና ከኢጥሙቃን ወገን የነበረውን የአምብሮስን መጻኢ ዕጣ ፈንታ የተናገረ ትንቢት እንደ ነበር ይነገራል፡፡ እርሱም በተሾመበት ቦታ በሚያስገርም ሁኔታ፣ እጅግ በበዛ ቅንነትና ፍትሐዊነት አስተዳደረ፡፡ በሚላኖ መንበር የነበረው አርዮሳዊ ጳጳስ ሲሞት ተተኪውን በመምረጥ ሂደት በሕዝቡ መካከል ከፍተኛ ረብሻ ተነሣ፡፡ አገረ ገዥው አምብሮስ ሁከቱን ለማብረድ ሕዝቡን በሚያረጋጋበት ጊዜ አንድ ሕፃን ልጅ ድንገት ‹‹አምብሮስ ጳጳስ መሆን አለበት!›› በማለት በጩኸት ተናገረ፡፡ ሕዝቡ ተገርሞ የሕፃኑን ድምፅ የእግዚአብሔር መልእክት አድርጎ ተቀበለው፡፡ ያኔ ንዑሰ ክርስቲያን የነበረው አምብሮስ ግን በእጅጉ ደንግጦ ከአካባቢው ለመሠወር ሞክሮ ነበር፡፡[1]

ከሕዝቡ እስከ ንጉሡ፣ ከካህናቱ እስከ ጳጳሱ አገረ ገዥውን እና ሕፃኑን መንፈስ ቅዱስ እንዳናገራቸው አመኑ፡፡ በሁሉም ዘንድ ፍቅርና አክብሮት ያሰጠው ፍትሐዊ አስተዳደሩም በፈሪሐ እግዚአብሔር የሚኖር ሰው እንደ ሆነ ተጨማሪ ማረጋገጫ ሰጣቸው፡፡ ከፖፑ በተገኘ ልዩ ፈቃድ በተጠመቀ በሳምንቱ ሕዝቡና ካህናቱ የመረጡት አምብሮስ የሚላኖ ጳጳስ ሆኖ ተሾመ፡፡[2]

አስተዋይ ቢገኝ ‹‹እንደ ዳኛ ሳይሆን እንደ ጳጳስ አስተዳድር›› በማለት ምክር የሰጠው የአምብሮስ የበላይ የነበረው አስተዳዳሪ ቃል ብዙ ቁም ነገር ያለው ምክር ነበር፡፡ ዛሬ ጳጳሳትን ‹‹እንደ ጳጳስ አስተዳድሩን›› የሚሉ ተማጽኖዎች በቤተ ክርስቲያናችን በርክተዋል፤ ሰሚ አልባ ጩኸቶች ሆኑ እንጂ፡፡ በእርግጥ እንደ ዳኛም ማስተዳደር ከባድ ነው፡፡ በተለይ አድሏዊነትን አርቆ እኩልነትን፣ ፍርደ ገምድልነትን ወርውሮ ፍትሐዊነትን፣ እበላ ባይነትን ተቆጣጥሮ ሐቀኝነትን የማክበር መሻቱ ላለው መሪ እንደ ዳኛ ማስተዳደርም እጅግ ከባድ ነው፡፡ ዳኝነት ጽድቅን የምትሻ ነፍስ ካለችው ሰው ላይ ካረፈች በጎነት የሚተገበርባት የጽድቅ መንገድ ትሆናለች፡፡ ከራስ ጋር መሟገትን ወይም ከነፍስ ጋር ጦርነትን መክፈት ከማይሰለቸው ፈቃደ ሥጋ ጋር አስቀድሞ መዋጋትና አሸናፊ ሁኖ መውጣት ትጠይቃለች፡፡ በተለይ መሾምን ከኃላፊነት ይልቅ ከተጠቃሚነት ጋር ይበልጥ የማስተሣሠር ባህል ካለው ማኅበረሰብ ለወጣ መሪ እንደ ዳኛም ማስተዳደር ቀላል አይሆንለትም፡፡

በዓለም ያለውን የዳኝነት ኃላፊነት በፈሪሐ እግዚአብሔር ሊከውናት የሚወድድ ሰው እንዲህ ያለ ተጋድሎ የሚጠይቀው ከሆነ መንፈሳዊው ውጊያ የሚበረታባት ጵጵስናማ እንዴት ያለ ጥብዓት ትጠይቅ ይሆን? እንደ ጳጳስ ማስተዳደር መንፈሳዊ ብቃት የሚጠይቅ የነፍስ ጎዳና ነው፤ ሥልጣንን እንደ በትር ሳይሆን እንደ ማሠሪያ ገመድ ማየት የሚጠይቅ የብፁዐን ፍኖት፡፡ በእውነተኞቹ አባቶች ዘንድ ሥልጣን ለበለጠ ጸጋ የሚቀበሏት ኃላፊነት ናት፡፡

የተለየ መንፈሳዊ ትምህርት ይኑረው አይኑረው በግልጽ ያልተነገረለት ይህ ሀገረ ገዥ አምብሮስን ‹‹እንደ ጳጳስ አስተዳድር›› በማለት ምክር ለመስጠት አስቀድሞ ጵጵስናዊ አስተዳደር ውስጥ ያየው ወይም የታዘበው በጎ ነገር እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ የጳጳሳት አስተዳደር መንፈሳዊነትን ማዕከል ያደረገ አስተዳደር ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በቅዳሴው ‹‹በጥላቻ ጎተቱት በፍቅር ተከተላቸው›› እንዳለው የጳጳሳት አመራር መንፈሳዊ አስተዳደር ነውና እንደ ክርስቶስ በክፉ የተነሣባቸውን በፍቅር የሚያስተናግዱበት አስተዳደር ነው፡፡ እግዚአብሔር የሠራው፣ በፍቅር የሚከወን፣ መጋቢውን እግዚአብሔር ያደረገ የሰማያዊው ጉዞ ማሳለጫ መንገድ ነው፡፡ ጳጳሳት ዋጋን በምድር ከሰው እጅ ሳይሆን በሰማይ ከእግዚአብሔር እጅ ለመቀበል ውል ወስደው የተሠማሩ አባቶች ናቸው፡፡

ሰው ደመወዝ የሚቀበለው ጀንበር ከማዘቅዘቋ፣ የጨለማ ግርዶሽ ከመውደቁ በፊት ነው፡፡ አሠሪው የተሠራውን ሥራ በዐይነ ብርሃን ገምግሞ ግምቱን ይከፍላል፡፡ ሰማያዊ ዋጋ ግን እልፍኝ ከተዘጋ በኋላ፣ የጨለማው ግርዶሽ ከከበደ በኋላ፣ የሰው ዐይኖች ከተሸነፉ በኋላም ጭምር የተፈጸመው፣ የተከወነው መንፈሳዊ ተግባር ሁሉ ተቆጥሮ ተሰፍሮ የሚያስደስት ሆኖ ሲገኝ የሚከፈል ክፍያ ነው፡፡ የሰው ዐይኖች የማይደርሱበት የልብ ሐሳብ ጭምር ከተመረመረ በኋላ የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡ ሽልማቱም ክቡርና ዘላለማዊ ነው፡፡ እንደ ጳጳስ ማስተዳደር በዚህ መንሽ በበዛበት መንገድ መጓዝ ነው፡፡ ለድል አክሊል የሚያበቃው የመዓልት ሩጫ ብቻ ሳይሆን የሌሊት ትጋህ ጭምር ነው፡፡ ፀሐይ በሞቀው ስኬትህ ብቻ ሳይሆን ማንም በማያውቀው ባልተነገረው በጎነትህ ጭምር ሽልማትህ ከፍ ይላል፡፡ በተመዘገበ ውጤት ልክ ብቻ ሳይሆን በቅንነት የተነሣሣህው መነሣሣት ሁሉ ተቆጥሮልህ ነው ለክብር የምትታጨው፡፡

የምንኩስና መሥራች አባ እንጦንስ ‹‹የጋለ ብረትን ለመቀጥቀጥ የሚነሣ ሰው አስቀድሞ በብረቱ ምን ለመሥራት እንዳሰበ መወሰን አለበት፤›› ይላል፡፡[3] ጵጵስናም እንዲሁ ነው፤ የጋለ ብረት የተመሰሉ ምእመናንን በሚፈለገው መንገድ ለመቅረጽ ዕድል ያለው አንጥረኛ፡፡ ብረቱን ቢሻው ሰይፍ ቢፈልግ መስቀል አድርጎ ማውጣት ይችላል፡፡ ከጋለ በኋላ ውጤቱ በአንጥረኛው መሻት ጥበብና ትጋት ላይ የተንተራሰ ይሆናል፡፡ መነኮሱም ገና ለኤጲስ ቆጶስነት ሲታጭ አስቀድሞ መክሊቱን እንዴት እንደሚያተርፍበት ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ አድርጎ ማቀድ እና የሚያጠግብ ፍሬ ለማፍራት ልቦናውን ማዘገጀት ግድ ይለዋል፡፡ የአስተዳደር ጅማሬውን በፊቱ ያለውን ሩጫ በትዕግሥት፣ በንጽሕና፣ በመንፈሳዊነት በመሮጥ ይጀምረዋል፡፡ የጽድቅን አክሊል በመቀዳጀት ይፈጽመዋል፡፡ ኤጲስ ቆጶስነት እንደ ዳኝነት በጥሮታ አልያም በበቃኝ የሚቋጩት ሥራ አይደለም፡፡ በድል አክሊል የሚያሳርጉት የዕድሜ ልክ ሩጫ ነው፡፡

አፈራረዱም እንደ ዳኛ መሆን የለበትም፤ መንፈሳዊ አስተዳደር ራስን በፈራጅነት ላይ በማስቀመጥ የሚከናወን አይደለም፡፡ በክርስቲያናዊ ፍቅር ራስን በሌላው ጫማ በማስቀመጥ ስሜቱን መካፈልን (Empathy) ግድ ይላል፡፡ ፍትሕን ብቻ ሳይሆን ርትዕንም ማስፈን ይጠይቃል፡፡ ዳኛው በስም ማጥፋት የተከሰሰውን የጥፋቱን ዋጋ መስጠት ይበቃዋል፡፡ ጳጳሱ ግን አትፍረድ በሚለው አምላካዊ ትእዛዝም የሚገዛ አባት ነው፡፡ ተወቃሹዋን ነፍስ በተወቀሰችበት ጥፋት ምክንያት ሊመጣ ያለባትን መከራ እንድታልፍ መርዳት ይጠበቅበታል፡፡ በሰማይ የሚከፈለውን ዋጋ እያሰበ የዛለችውን ነፍስ ተሸክሞ ረግረጉን የማሻገር፣ ለምለም መስኩ ላይ የማሰማራት የሁል ጊዜ ኃላፊነት አለበት፡፡ ጳጳሱ ምእመናንን ሲያስተዳደር ከሚያማ ሰው ጋር አለመተባበር ብቻ አይደለም የሚጠበቅበት፣ በሐሜተኛውና በሚታማው ሰው መካከል ሚዛን የጠበቀ መስተጋብር እንዲኖረው ይገደዳል፡፡

በግብጽ በርሓ የተጋደለው ኢትዮጵያዊው ጻድቅ ሙሴ ጸሊም ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር ‹‹መነኩሴ ለባልንጀራው መሞት አለበት፤ በምንም መንገድና በምንም ሁኔታ በወንድሙ ላይ መፍረድ የለበትም፤›› ይላል፡፡[4] ለወንድም መዋቲ መሆን ማለት የሌላውን ጥፋት ከቁም ነገር አለመቁጠር ማለት እንደሆነ ያስረዳል፡፡ እንደ ዳኛ ስታስተዳድር በዋናነት አጥፊውን ቀጥተህ ተበዳዩን ክሰህ መገኘት በቂ ሊሆን ይችላል፤ ይህን በተአምኖ ከፈጸምክ ምስጉን ያደርግሃል፡፡ እንደ ጳጳስ ስታስተዳድር ግን ሓላፊነትህ ሁለትዮሽ ነው፡፡ ተበዳዩን አክመህ የበዳዩን (የአጥፊውን) አፉን ለጸሎት ልቡን ለፀፀት በማብቃት ጉዳዩን መዝጋት ይጠበቅብሃል፡፡ ይህን መሰል እንደ ሰማይና ምድር የተራራቁ፣ እንደ ሆድና ጀርባ የማይገናኙ ጉዳዮችን ማቀራረብ ነው ጵጵስናዊ አስተዳደር፡፡

ሙሴ ጸሊም በቀደመ ሕይወቱ ዘራፊ ነበር፡፡ በኃጢአት ደዌ ተይዛ የነበረች ነፍሱን ወደ አምላኳ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ዕቅፍ የመለሳት በግብጽ በርሐ ያየው የመነኮሳት ተጋድሎ የንስሐ ጥሪ ሆኖለት ነው፡፡ ይህ ሙሴ ጸሊም ከላይ ስለመፍረድ ላነሣነው ሐሳብ ማጠናከሪያ የሚሆን ምክር አለው፡፡ ‹‹ከሚያማ ሰው ጋር አትተባበር፤ በሐሜቱም አትደሰት፤›› በማለት በተግባሩ እንዳትተባበር ሲነግርህ ሐሜት አስጸያፊ መሆኑን ይገባሃል፡፡ መለስ ብሉ ደግሞ በዚያው መሥመር ‹‹ወንድሙን የሚያማውን ሰውም አትጸየፈው፤›› ይልሃል፡፡[5] ተግባሩን ረግመህ ከመሰል ተግባር አንድትሸሽ ይነግርህና፣ ተግባሪውን የተሸከሙ የክርስቶስ ትከሻዎች ግን እንዳልዛሉ ያስታውስሃል፡፡ ያኔ የአትፍረድ ትርጉም ይገለጽልሃል፡፡ እንደ ጳጳስ ማስተዳደር ማለት ይኸው ነው፡፡ ከዚህም በላይ ለጳጳስ ለእውነት መቆም የሁልጊዜ የሰርክ መንፈሳዊ ግዴታው ነው፡፡

ወደ ቅዱስ አምብሮስ እንመለስና፤ አምብሮስ ተጠምቆ ጵጵስና ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ ራሱን ለክርስቶስ የሰጠ መንፈሳዊ ዐርበኛ ሆነ፡፡ ዳኛ ሆኖ የጀመረውን እንደ ጳጳስ የማስተዳደር ልምምድ ጳጳስ ሲሆን አጠናክሮ ቀጠለበት፡፡ በአመራርና እና አስተዳደር ችሎታው በሕዝቡ ዘንድ በጣም ተወደደ፡፡ ንብረቱን ሁሉ ለድሆች በመስጠት ለችግረኛ ደራሽ ሆነ፡፡ መንበረ ጵጵስናውን የብሕትውናው በኣት አደረጋት፡፡ ረጅም ጊዜ ወስዶ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጥናት የነገረ መለኮት ሊቅ ለመሆን በቃ፡፡ አስገራሚ የመጽሐፍ ንባብ ልምድ እንደ ነበረው አውግስጢኖስ ደጋግሞ ይመሰክርለታል፡፡ ለተዋሕዶ ሃይማኖት ጥብቅና የቆመ ቅዱስ አባት ስለነበር ‹‹የምዕራቡ አትናቴዎስ›› ተብሎ የሚጠራ የቤተ ክርስቲያን አባት መሆን ቻለ፡፡

የንባብ፣ የብሕትውና የተጋድሎ ሕይወቱ፣ ቅድስናው እና ነገሥታትን የመገሠጽ ጥብዓቱ እጅግ የተዋጣ መንፈሳዊ አስተዳደር እንዲያሰፍን ረድተውታል፡፡ ዛሬም ባለ ሥልጣን ሆኖ እንደ ጳጳስ የሚያስተዳድር መሪ ማግኘት ቢከብድም የክርስቶስ እንደራሴ ሆኖ የተሾመ አባት እንደ ጳጳስ በክርስትና ዕሴቶች ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን በፖለቲካ መርሕ ሲያስተዳድር ማየት የምእመናንን ልብ ይሰብራል፡፡ ስለዚህ ሕዝበ ክርስቲያኑ ብጹዐን ጳጳሳት እንደ ጳጳስ ሲያስተዳድሩ ማየት ይናፍቃል፡፡ በቅዱስ አምብሮስ ፍኖት ሲጓዙበት ማየትና አማን በአማን ብፁዐን መሆናቸውን ማረጋገጥ ይሻል፤ ዛሬም ሕዝቡ ‹‹አባቶቻችን ሆይ እንደ ጳጳስ አስተዳድሩን፤›› እያለ ነው፡፡

ዋቢ መጽሐፍት

  1. ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል (፳፻፭ ዓ.ም.)፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ በምድር ላይ፤ ገጽ ፬፻፳፩፤
  2. ዝኒ ከማሁ
  3. ዲ.ዳንኤል ክብርት(፳፻፬ ዓ.ም.)፤ በበርሐው ጉያ ውስጥ፤ ገጽ ፵፯፤
  4. ዝኒ ከማሁ፤ ገጽ 53፤
  5. ዝኒ ከማሁ