ከደቂቀ እስጢፋኖስ እስከ መንበረ ሰላማ

ከደቂቀ እስጢፋኖስ እስከ መንበረ ሰላማ

ከደቂቀ እስጢፋኖስ እስከ መንበረ ሰላማ

አባ እስጢፋኖስን እና ተከታዮቹንበተመለከተ ብዙ ይጻፋል፣ ይነገራል። የእርሱ እና የተከታዮቹ ጉዳይ ማንም እንደፈለገ ለመዘወር የተመቸ ነው። ከትግራይ ክልል የተነሡ ተስፈንጣሪ ፖለቲከኞች ባላንጣችን የሚሉትን ሸዋን ለመተቸት ይጠቅሱታል። በክልሉ ኑፋቄያቸውን ለመዝራት ፈልገው ያልተሳካላቸው ተሐድሶ መናፍቃን በዕውቀቱ አቻ የሌለው፣ በአስተምህሮው እንከን የማይገኝበት አስመስለው ያቀርቡታል። ቤተ ክርስቲያኗን በዘር ለመከፋፈል የሚደክሙ አካላት አርአያነቱን እንከተል በማለት የፈጣራ ድርሰት ጽፈው ያነቡለታል። እንደ አባ እስጢፋኖስ ያለ ምግባረ ብልሹ ራሱን ኮፍሶ ሌላውን ስለሚያናንቅ እንዲህ ያለው ምግባር የመናፍቃንመለያ መሆኑን መረዳት ከተደጋጋሚ ጥፋት ይታደጋል።

አባ እስጢፋኖስ መናፍቃንን ይመስላል ከተባለ ከአስተምህሮው ይልቅ በእቡይነቱ ነው የሚል እምነት አለኝ። ከራሱ በስተቀር ሁሉን የሚንቅ፣ ሁሉን የሚተች፣ ነገሥታት በእግዚአብሔር ፈቃድ የነገሡ በመሆናቸው ማክበር እንደሚገባን የተጻፈውን ዘንግቶ ንጉሥን የሚያንጓጥጥ ሰው ነው። እንዲህ ያለው ምግባረ ብልሹነት የኦርቶዶክሳውያን መገለጫ ሳይሆን የሌሎች መታወቂያ በመሆኑም የሚጮሁለትም እንደ እርሱ እቡይ የሆኑ ወገኖች ናቸው። መታወቅ ያለበት ኦርቶዶክሳውያን መነኰሳት ራሳቸውን አጽድቀው ሌላውን ኃጥእ የማያደርጉ፣ ወንድማቸውን ከፍ አድርገው ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉ መሆናቸው ነው።“እርሱ ከእኔ ይበልጣል፣ እኔ ትቢያ ነኝ”ብለው በመናገር ነው የሚታወቁት። አባ እስጢፋኖስ በዚህ መሥፈርት ሲመዘን ቀልሎ የሚገኝ ሰው ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት የሚሞክሩ መሠረታቸውን ከትግራይ ያደረጉ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች እና ኦርቶዶክስነት አሐቲነት መሆኑ ያልገባቸው ተሐድሶ መናፍቃንአባ እስጢፋኖስን እና ተከታዮቹን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጠበቃ እና የሃይማኖት አለኝታ አስመስለው በማቅረብ ከእነርሱ ወዲያ መነኰሳት ለአሳር ሲሉ ይሰማሉ። እንዲህ የሚሉት በተጋድሏቸው አምነውበት ሳይሆን ማሳካት የሚፈልጉትን እንዳይፈጽሙ ለመናፍቃን መቀጥቀጫ የሆኑ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መግቢያ ቀዳዳ ስላሳጧቸው ነው።

በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ ሊያደርሱ ያሰቡት ጥፋት ያልተሳካላቸው ተሐድሶ መናፍቃን የእምነታቸውን መሠረት አገር በቀል ለማስመሰል መነሻቸውን ከአባ እስጢፋኖስ ለማድረግ ይሞክራሉ። ይህ ድርጊታቸው ለማያውቅሽ ታጠኝ የሚያሰኝ ነው። ከማርቲን ሉተር ቀድሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሐድሶንያመጣ አርቆ አሳቢ አስመስለው በማቅረብ አስተምህሮውን እንደተከተሉ ለማስረዳት መሞከራቸው ውኃ የሚያነሣ ሙከራ አይደለም። አባ እስጢፋኖስ የሚያምነው ከነባሩ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ያፈነገጠ ቢሆንም ከፕሮቴስታንት አስተምህሮ ጋር እንደማይሠምር እርሱን እና ተከታዮቹን በተመለከተ በአማን ነጸረ “ወልታ ጽድቅ” በተሰኘው መጽሐፉ በሚገባ ጽፎታል። ተስፈንጣሪ ፖለቲከኞችን እና ተሐድሶ መናፍቃንን የሚያስማማቸውአባ እስጢፋኖስን እና ተከታዮቹን የሚጠቅሱት አንድም ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃትሁለትምየዋሃንን አሳስተውደጋፊ ለማብዛት ነው። ከነባሩ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ  ለመነጠልም ቢሉ የተመቸ።

እንደ ግብር አባታቸው ራሳቸውን ብቻ አዋቂና ሃይማኖተኛ ማስመሰል የለመደባቸው ተሐድሶ መናፍቃን አባ እስጢፋኖስን እና ተከታዮቹን ንጉሡ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ባያሳድዳቸው ኖሮ ትክክለኛው አስተምህሮ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ተተክሎ ይቀር እንደነበርይናገራሉ። በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ምክንያት ቤተ ክርስቲያንን የትክክለኛው አስተምህሮ እጥፋት እንደገጠማትሲናገሩ ይሰማሉ። እንዲህ ያለው ማስመሰል አባ እስጢፋኖስን ፈረስ አድርጎ ጋልቦ የመጣው ኑፋቄ ቤተ ክርስቲያንን ለምን ሳይበጠብጣት በቀላሉ ተቀጨ የሚል ብስጭት የወለደው መሆኑን መረዳት ይገባል። ሌላው አስነዋሪ ድርጊታቸው ደግሞ ንጉሡ አገረ መንግሥቱን ለማጽናት የፈጸመውን ቅጣት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የፈጸመችው ወይም ለንጉሡ ውክልና ሰጥታ ያስፈጸመችው አስመስለው ማቅረባቸው ነው።

መረዳት የሚገባው ዐፄ ዮሐንስ ፬ኛ አመጸብኝ ያሉትን የጎጃሙን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ለመውጋት ጎጃም በዘመቱበት ወቅት ሠራዊታቸው ክርስቲያን ሊፈጽመው ቀርቶ ሊያስበው የማይፈልገው ግፍ ፈጽሟል። ንጉሡ ያንን ያህል ግፍ ቢፈጽሙም አንድም የጎጃም ሰው ጉዳዩን ከዘር ጋር አገናኝቶ ዐፄ ዮሐንስ ክርስትናን ከጎጃም ለማጥፋት የሄዱ አስመስሎ ሲያቀርበው አልተሰማም። ተስፈንጣሪ ፖለቲከኞች ከእነርሱ ወገን የመሰላቸው የሚያደርገው ሁሉ የተቀደሰ፣ ሌላው ሀገር ለማዳን በማሰብ ቢፈጽመው እንኳ የተወገዘ አስመስለው የሚያቀርቡት ትርክታቸው ውሸት በመሆኑ ነው። ለማንም ሰው የሚፈቀደው  የተፈጸመውን ታሪክ ሳያዛቡ መተረክ እንጂ በመሰለው ጠምዝዞ እየተረጐሙ ሌሎችን ማጥቃትና ማሸማቀቅ አይደለም።

አንባብያን ሊረዱት የሚገባው የተስፈንጣሪዎች ዓላማ ነባሩን የቤተ ክርስቲያን አስተምሮና አገራችን የቆመችባቸውን መሠረቶች በመምታት ኦርቶዶክሳውያንን ከነባሩና ከትክክለኛው አስተምህሮ መለየትነው። በመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን አገራችን ጸንታ እንድትቆም ካደረጓትሦስት ነገሮች አንዱ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የፈጸመው ነው።  ይህን የሚያውቁ ስሑታን በእርሱ አስታከው ቤተ ክርስቲያንን ሊወጉ፣ እርሱ ሀገር ለማጽናት የፈጸመውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዕዳ ከፋይ መሆን አለባት ለማለት ይሞክራሉ።

መናፍቃኑ ከኢትዮጵያውያን አእምሮ ለመፋቅ ይህም ካልተቻለ ለማደብዘዝ የሚሞክሯቸው ሦስት የመካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን አዕማዶች ኢትዮጵያውያን ለድንግል ማርያም ያላቸው ፍቅር፣ ቤተ ክርስቲያን ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት የምትሰጠው ክብር እና ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ አገር ለማጽናት የፈጸመው ተግባር ናቸው።ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን “እነ አባ እስጢፋኖስን ከላይ አንገታቸውን፣ ከታች ባታቸውን ቆርጠህ ከመከራ አሳርፈኝ” ብላ የላከችው አስመስለው የሚያሰሙት ጩኸት ከእውነት የራቀ መሆኑን አንባብያን ሁሉ ሊረዱት ይገባል። ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የሀገር መሪ እንጂ የሃይማኖት አባት አይደለም። በዘመኑ የነበሩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው በመምክር አባ እስጢፋኖስን ቅጣልን አላሉትም። የሀገር መሪ በመሆኑም ሌሎች መሪዎች እንደሚያደርጉት አድርጓል። ጥፋት ከፈጸመ መተቸት የሚኖርበት በአገር መሪነቱ እንጂ እርሱ ፈጸመው ያሉትን ለቤተ ክርስቲያን ሰጥቶ ዕዳውን ክፈይ ማለት በርባንን ፈትቶ ክርስቶስን ማሰር ነው።

የሚገርመው መናፍቃኑ ከሚያነሷቸው ሦስት ጉዳዮች ሁለቱ በዘመናችንየትግራይ ቤተ ክህነትን እንመሠርታለን ብለው በተነሡ ወገኖቻችን እየተቀነቀኑ መሆኑነው። ይህን ድርጊታቸውን አይቶ ከእነዚህ አካላት ጀርባ ማን እንዳለ መገመት አያዳግትም። መገመት ብቻም ሳይሆን ከዓመታት በፊት በትግራይ የሚያገለግሉ አባቶች አግደውት ቅዱስ ሲኖዶስም አውግዞ ለይቶት የነበረው ማኅበረ ሰላማ የሚባለው ቡድን ስሙን ለውጦ፣ የቀበሮ ባሕታዊ መስሎ እንደመጣ መታወቅ አለበት። አባ እስጢፋኖስን እና ተከታዮቹን ለመጀመሪያያሳደዳቸውን እና ቀጥሎ የተከናወነውን ከማየታችን በፊት ተሐድሶ መናፍቃን ለመነቅነቅ ከሚፈታተኗቸው ሦስት አዕማዶች ከአባ እስጢፋኖስ እና በዘመናችን ከተነሡት ተስፈንጣሪ የትግራይ ቤተ ክህነት አቀንቃኞች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸውን ሁለቱን በመጠኑ እንዳስሳለን።

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዲስ ሐዋርያ ብላ የምትጠራውን እና ኢትዮጵያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በወንጌል መረብነት የሰፋትን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ስም ማጠልሸት የፈለጉበትን ምክንያት እና የሄዱበትን ርቀት መዳሰስ ሲሆን ሁለተኛው ከእስጢፋኖሳውያን ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያለው ዐፄ ዘርያ ያዕቆብ የፈጸመውን በመጠኑ በመዳሰስ ወደ ዋናው የእስጢፋኖሳውያን ጉዳይ እንገባለን።

ሚሲዮናውያን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለመቀየር ሲነሡ  እንቅፋት ከሚሆኑባቸው ጉዳዮች አንዱ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የፈጸሙት ሐዋርያዊ ተልእኮ በኦርቶዶክሳውያን ልቡና ውስጥ ተደላድሎ መቀመጡ ነው።የእነርሱ ጉዳይ አስፈጻሚ የሆኑ ተሐድሶ መናፍቃን የአቡነ ተካለ ሃይማኖትን አበርክቶ ከኢትዮጵያውያን ልቡና ፍቀው ለማጥፋት ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልፈጠሩት የሐሰት ታሪክ፣ ያላቀረቡት ማማለያ የለም። አቡነ ተክለ ሃይማኖት ሰላም እንዲሰፍን፣ሃይማኖትም እንዲጸና የከፈሉትን መሥዋዕትነት ስለሚያውቁ አበርክቷቸውን ከትውልዱ ልቡና አጥቦ ለማውጣት ይጠቅመናል ብለው ያሰቡትን ለመፈጸም ቢደክሙም የድካማቸውን ያህል ውጤት አላገኙም። የፈጠራ ድርሰታቸውን በጥናትና ምርምር ሽፋን አቅርበው የትውልዱን አእምሮ ለመበረዝ ሞክረዋል።

ዓላማቸውን ያልተረዱ ክርስቲያኖች የሌሎች መጠቀሚያ በመሆን ለእኩይ ድርጊታቸው ግብዓት እያቀረቡ እንወዳታለን የሚሏትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መውጋታቸው እስከ አሁንአልተገለጠላቸውም። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ መበረዝ የሚያሳስባቸው የተማሩ ክርስቲያኖችም ሆኑ የአገራቸው ታሪክ መቀየጥ የሚያንገበግባቸው የታሪክ ምሁራን በንስር ዓይኖቻቸው መዛግብትን በመመርመር፣ ምርቱን ከገለባው፣ እውነተኛውን ሐሰት ከሆነው፣ የሚያለያየውን ከሚያስታርቀው አንጓለው እየለዩ የተበረዘውን የትውልድ አእምሮ ማስተካከልሃይማኖታዊም፣ ሞራላዊም፣ አገራዊም ግዴታቸውና ኃላፊነታቸው ቢሆንም የሚጠበቅባቸውን ባለማከናወናቸው አንድ ሞኝ የተከለውን ኀምሳ ሊቅ አልነቀለውም።

የሜንዴዝን በማር የተለወሰ የፈጠራ ድርሰትና የኪዳነ ወልድ ክፍሌን የፈጠራ ጽሑፍ ያነበቡ የዘመናችን ምሁር አስተኔዎች የተነገራቸውን ከመቀበል አስቀድመውጉዳዩን መመርመር ይገባቸው ነበር። የሚያደርጉት ግን የተጫኑትን ነገር ወስደው ንጹሕ አእምሮ ባላቸው ወገኖቻቸው ላይ ማራገፍ ነው። አልፎንሱ ሜንዴዝም፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ስማቸውን እንደሚያጠፉት ሳይሆን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን በሰሜን እስከ ታኅታይ ግብፅ፣ በደቡብ እስከ ኬንያ፣ በምዕራብ እስከ ነጭ ዓባይ፣ በምሥራቅ እስከ መቃዲሾ እየዞሩ አሕዛብን በወንጌል መረብነት አያይዘው የክርስቶስ አካል፣ የቤተ ክርስቲያን አባል እንዲሆኑ አድርገዋል።

ተሐድሶዎች እንደሚሉት በዘመኑ በነበረው መንግሥታዊ አስተዳደር ጣልቃ ገብተው የዘውዱ ሥርዓት ከዛጔ ወደ ሰሎሞናውያን እንዲሸጋገር አላደረጉም። የፈጸሙት ማእከላዊውን መንግሥት በተደጋጋሚ ይወጋ የነበረውን የዳሞቱን ንጉሥ ክርስቲያን በማድረግ ሰላምን ማስፈን ነው። አንዱን ከዙፋን አውርደው ሌላውን መተካታቸውን የሚገልጥ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም። እንዲህ ያለውን ተራ ድርጊት የሚፈጽሙት ለሆዳቸው ያደሩ፣ እግዚአብሔር ሳይልካቸው ተልከናል የሚሉ፣ መንፈሳዊ ምሥጢር ሳይገለጥላቸው የተገለጠላቸው የሚመስሉ፣ ሥጋዊ ጥቅም ሲያሳድዱ የሚኖሩ አካላት እንጂ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አይደሉም።

በተደጋጋሚ ማእከላዊውን መንግሥት እየወረረ፣ አብያተ ክርስቲያንን ያቃጥል፣ሊቃውንትን እና ካህናትን ማርኮ ይወስድ፣ ክርስቲያኖችን ይገድል እና የተረፉትንም አሽከር ያደርግ የነበረውን፣መልከ መልካሞችን ሴቶችን ወስዶ ሚስት፣ መልክ የሌላቸውን ገረድ ያደርግ የነበረውን የስለደኔን ልጅ ሞተለሚን አስተምረው ክርስትናን እንዲቀበል ማድረጋቸው እውነት ነው።በዚህም ሰላም እንዲሰፍን፣ የክርስቲያኖች የመኖር ዋስትናም እንዲረጋገጥ አድርገዋል (ገድለ ተክለ ሃይማኖት፣ ገጽ ፻፷፮- ፻፸፬ እና አራቱ ኃያላን፣ ፳፻፮ዓ.ም፣ ገጽ  ፫፴፪- ፫፴፫)።

ስለአቡነ ተክለ ሃይማኖት መግለጽ ያስፈለገው በዘመናችን የተነሡ የትግራይ ቤተ ክህነት አቀንቃኞች የተነጠቀውን መንበራችንን እናስመልሳለን በማለት ሃይማኖትን ፖለቲካ አድርገው በመነሣታቸው ነው። አቡነ ተክለ ሃይማኖት መንበር የነጠቁ አስመስለው የሚናገሩትም ሐሰትነው። የማያውቀውን ለማሳሳት እንዲያመቻቸው መንበረ ተክለ ሃይማኖትን ወደ መንበረ ሰላማ እንመልሳለን ይላሉ። ድርጊታቸው በትግራይየሚኖረውን ክርስቲያን ከጻድቁ በረከት ለመለየት ያለመ ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምታውቀው የአቡነ ተክለ ሃይማኖት መንበር የእጨጌነት እንጂ የፓትርያርክት አለመሆኑን ነው። ለዚህ ማሳያው ለአቡነ ባስልዮስ እጨጌነቱ የተቀጸለላቸው በገዳሙ በእጨጌነት አገልግለው ስለነበር ነው። ለአቡነ ቴዎፍሎስ፣ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት እና አቡነ መርቆሬዎስ እጨጌ የሚለው አልተቀጸለላቸውም። መጠሪያው በዐዋጅ እንዲቀጸል የተደረገው በ፲፱፻፺፩ ዓ.ም   መሆኑ መታወቅ አለበት።ከዚያ ወዲህ ለአቡነ ማትያስም ተቀጽሎላቸዋል። እንዲህ ማድረጉት አባቶች ባይፈልጉትም እንዲህ አስደረግንላችሁ ባዮች ለሹመት ማግኛ ሊያደርጉት ይችላሉ።

ይቆየን