ከደቂቀ እስጢፋኖስ እስከ መንበረ ሰላማ
የተከበራችሁ አንባብያን የዚህን ጽሑፍ የመጀመሪያ የሆነውን እና አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በተመለከተ ተሐድሶ መናፍቃን እና ተስፈንጣሪ ፖለቲከኞች የሚያነሷቸውን የፈጠራ ድርሰቶች መነሻ ምክንያት የሚያስነብበውን ጽሑፍ ለንባብ ማብቃታችን የሚታወቅ ነው። ቀጣዩን ክፍል ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባብ፡-
ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ
በመካከለኛው ዘመን ለቤተ ክርስቲያን መልካም ካደረጉ ነገሥታት አንዱ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ነው። ንጉሡ አገሪቱን ለሁለት ሊከፍል ጫፍ ደርሶ የነበረውን የቤተ ተክለ ሃይማኖት እና የቤተ ኤዎስጣቴዎስ ጉዳይ መፍትሔ በመስጠት ሰላም እንዲወርድ አድርጓል። ጉዳዩ እንዲህ ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን በሐዋርያዊ አገልግሎታቸው የሚታወቁት የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም መነኰሳት እና የአባ ኤዎስጣቴዎስ ተከታዮች ልዩነት ፈጥረው ነበር። የልዩነቱ ምክንያት ቤተ ተክለ ሃይማኖቶች መከበር የሚገባት ሰንበተ ክርስቲያን እንጂ ሰንበተ አይሁድ መከበር የለባትም ሲሉ ኤዎስጣቴዎሳውያን ደግሞ ቅዳሜም፣ እሑድም መከበር አለባቸው የሚል አቋም ያዙ። በዘመኑ የነበሩ ነገሥታት አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ያከበርን መስሏቸው የእርሳቸውን ገዳም መነኰሳት አሳብ ደግፈው ቤተ ኤዎስጣቴዎሳውያንን መግፋት በመጀመራቸው ልዩነቱ እየሰፋ ሄደ።
ጉዳዩ ሲንከባለል ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ሲደርስ ንጉሡ የተማረ ስለነበር ሁለትም ዓይናማ ሊቃውንትን በማማከር “በ፲፬፻፵፪ ዓ.ም ደብረ ምጥማቅ ላይ በተደረገ ጉባኤ ሁለቱም ሰንበታት እኩል እንዲከበሩ” (በአማን ነጸረ፣ ፳፻፱፣ ገጽ ፲) በማድረጉ በቤተ ተክለ ሃይማኖት እና በቤተ ኤዎስጣቴዎስ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ልዩነት ተወግዶ ሰላም ወረደ። ሰንበተ አይሁድ ወይም ቅዳሚት ሰንበት መከበር አለባት የሚሉ ወገኖች ያቀርቡ የነበረው ምክንያት ለሰንበተ ክርስቲያን ምሳሌዋ መሆኗን፣ ምሳሌውን ማጥፋት አማናዊውን ለመርሳት ምክንያት እንደሚሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቀዳሚት ሰንበት ካላለፉ የብሉይ ኪዳን ሕግጋት በመሆኗን በመጥቀስ ነበር።
ንጉሡ ችግሩን በሰላም በመፍታቱ ሊቃውንቱን ምክንያት አድርጎ ሀገሪቱንም ለሁለት ሊከፍላት ይችል የነበረውን ችግር አስቀርቶታል። የንጉሡ መልካም ተግባር አገራችን ተበታትና ማየት ለሚፈልጉ ምዕራባውያን እና የእነርሱ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ዓላማቸውን ከንቱ ስላደረገባቸው የንጉሡን አበርክቶ ከኢትዮጵያውያን አእምሮ ፍቀው ለማጥፋት እንቅልፍ አሳጣቸው። ደቂቀ እስጢፋኖስ ላይ ፈጸመ የሚሉት ክስም የዚያ አንዱ ማሳያ መሆኑን መረዳት ይገባል።
ሁለተኛው የንጉሡ አበርክቶ የእስጢፋኖሳውንን ድርጊት ማስቆሙ ነው። አባ እስጢፋኖስ እና ተከታዮቹ በመጀመሪያ የተሳደዱት ትግራይ ውስጥ ከሚገኘው ደብረ ቆየጻ ገዳም መሆኑ ይታወቃል። ንጉሡ በአባ እስጢፋኖስ እና ተከታዮቹ ላይ ቅጣት የፈረደባቸው ለእመቤታችንም፣ ለመስቀልም አንሰድግም ከማለታቸውም በተጨማሪ በሚሰጡት መረን የረቀቀ መልስ መሆኑን ከንግግራቸው መረዳት ይቻላል። አባ እስጢፋኖስን የምንኵስና ውኃ ልክ አድርገው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚተቹ አካላት መነኵሴው ለእመቤታችን እና ለመስቀል ይሰግድ እንደ ነበር አስረጅ ማቅረብ አይችሉም።
በእመቤታችን ላይ ድርድር የማያውቀው ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ መነኵሴውን ከእነተከታዮቹ መቅጣቱ ቢታወቅም ንጉሡን መነኵሴው እና ተከታዮቹ በማንጓጠጣቸው ቅጣቱ መጠንከሩን ከገድላቸው አንብበን የምናገኘው ነው። ራሱን ብቻ ጻድቅ የሚያደርገው ተመጻዳቂው አባ እስጢፋኖስ በትዕቢት ተወጥሮ ንጉሡን በማንጓጠጡ ቅጣት ተፈጽሞበታል። አባ እስጢፋኖስ ነገሥታትን እጅ መንሣትን እንደ አምልኮ ስግደት ቆጥሮ የሚሰጠው መልስ በዘመኑ በነበረው ንጉሣዊ ሥርዓት አግባብነት የሌለው ነበር።
አባ እስጢፋኖስ የመነኰሰው ሕንጻ መነኰሳትን ተምሮ ከሆነ ነገሥታትን አክብሮ እጅ መንሣትን እና የአምላኮ ስግደትን ይቀላቅላል ተብሎ አይታሰብም። ንጉሡን እጅ መንሣት ለአምላክ የሚቀርበውን ስግደት ለፍጡር እንደ መስጠት ስለቆጠረው ከንጉሡ ችሎት ሲቀርብ እንኳ እንደ ጅብራ ተገትሮ ነበር። በዚህ ምክንያት ቅጣቱ ጠንክሮበት ሊሆን ቢችልም ንጉሡ በፈጸመው ቅጣት ቤተ ክርስቲያን ተጠያቂ የምትሆንበት ምንም ምክንያት የለም።
ንጉሡ አባ እስጢፋኖስን ከእነተከታዮቹ የቤተ ክርስቲያኗን ሥርዓት እንዲያከብሩ የሰጣቸውን ዕድል ባለመጠቀማቸው እና ከያዝነው አቋም ንቅንቅ አንልም በማለታቸው ቀጥቷቸዋል። ጥፋተኞችን በመቅጣቱ ሊቃውንትን እና መነኰሳትን ለሁለት ከፍሎ በተራዛሚው የአገር እና የቤተ ክርስቲያን ሳንክ ሊሆን ይችል የነበረውን አሳብ አምክኖታል። ከጥፋታቸው የተመለሱት ቀኖና ተሰጥቷቸው ከምእመናን አንድነት ሲጨመሩ በጥፋታቸው የቀጠሉት ተለይተው በመውጣታቸው አገራችን ከመበጥበጥ፣ ቤተ ክርስቲያንም ከመከፈል ድናለች።
በሌላ በኩል ማእከላዊው መንግሥት አባ እስጢፋኖስን ደግፎ ቢሆን ኖሮ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተለየ አስተምህሮ የሚከተለውን አባ እስጢፋኖስን ከገዳሙ አስወጥተው የሰደዱት ንጹሐን የደብረ ቆየጻ መነኰሳት በተሰጠው የተንጋደደ ፍርድ ምክንያት ይቀየሙ ነበር። ፈጸመ በሚሉት ድርጊት ንጉሡን ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን የሚተቹ የዘመናችን ተሐድሶ መናፍቃን እና ተስፈንጣሪ ፖለቲከኞችም አባ እስጢፋኖስን ደግፎ ንጹሐንን አሳደደ ብለው መተቸታቸው አይቀርም ነበር። ንጉሡን የሚተቹት የተንጋደደ ፍርድ በመስጠቱ ለእውነት ጠበቃ ሆነው ሳይሆን ኢትዮጵያውያንን ድር እና ማግ አድርጋ በማስተሳሰር ለዘመናት የዘለቀችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳትበጠበጥ በቀላሉ መፍትሔ በመስጠቱ ተበሳጭተው ነው።
የእስጢፋኖሳውያን ስደት
አባ እስጢፋኖስ እና ተከታዮቹ በያዙት የተሳሳተ አቋም ምክንያት ከነበሩበት ገዳም የወጡት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዙፋን ላይ ከመውጣቱ አስቀድሞ ነው። አባ እስጢፋኖስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከገዳሙ የተባረረው ነባሩን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንደ ሰባልዮስ ኑፋቄ በመቁጠሩ እና ራሱን የትክክለኛው አስተምህሮ ጠበቃ በማድረጉ ምክንያት መሆኑን የሚጠቁም ፍንጭ በገድሉ ገጽ ፸፫ ላይ እናገኛለን። ለመባረር ያበቃው እና ንጉሡ ሲጠይቀው ለእርሱ የሚሆን መምህር እንደ ሌለ መልስ የሰጠው የራሱን ያፈነገጠ አስተምህሮ የሚቀበለው በማጣቱ ነው። የሚገርመው ነባሩን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከሰባልዮሳውያን (እግዚአብሔርን አንድ ገጽ ባዮች ) አመሳስሎ የራሱን የተንጋደደ ግላዊ አመለካከት ያልተቀበሉትን ሁሉ የሚተቸውን ነው የሃይማኖት አባት ብለው የሚያወድሱት።
ከገዳሙ የወጣበትን ምክንያት ገድሉ “የደብሩ ሰዎች በቅዱሱ እና ከእርሱ በሚማሩት ላይ ተቆጡ፤ ግን የሚያደርጉትን አጡ። በአንዳች ነገር ላይ ሲከራከሩት እነርሱው ተመልሰው ይረታሉ። በዚያ ላይ ራሷ ትምህርቱ ሥራቸውን ነቃፊ ሆነች። ከቅዱሱ የሚማሩትን ከቍርባን እና ከገበታቸው ያገሏቸው ጀምር። በሁሉም ስም የሚናገሩት ጠበቆቻቸው ተነሥተው ቅዱሱን እንዲህ ሲሉ በእግዚአብሔር ስም ተናገሩት። ከደብራችን እንድትወጣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ይዘንሃል። ቅዱሱ ከደብሩ ሰዎች የመጣበትን ስደት ሲሰማ አበምኔቱ ከእነርሱ ጋራ ተስማምቶ እንደ ሆነ ወይም ይፈርድለት እንደ ሆነ ሊጠይቀው ወደ እርሱ ሄደ። እርሱም የማደሪያውን በር ዘግቶ እንዳይገባ ከለከለው” በማለት ያስነብባል (ደቂቀ እስጢፋኖስ፣ ፳፻፪፣ ፸፫)።
የአባ እስጢፋኖስ የመጀመሪያው ጥፋቱ ነባሩን አስተምህሮ የሚከተሉትን መነኰሳት ሰባልዮሳውያን ብሎ መጥራቱ ነው። በዚህ ብቻ ሳይወሰን አስተምህሮውን ያልተቀበሉትን መነኰሳት “የገዳም ሰዎች” (በእርሱ አገላለጽ የምንኵስናን መስፈርት የማያሟሉ ለማለት ነው) ብሎ መጥራቱ ትዕቢተኛነቱን እንጂ በገድል ተቀጥቅጦ ትሕትናን ገንዘብ ማድረጉን አያሳይም። እርሱ “የገዳም ሰዎች፣ ሰይጣኖች፣ አጋንንቶች” የሚላቸው መነኰሳት በተቃራኒው ገዳማቸውን እንዲለቅ የሚያማጽኑት በአምላካቸው ስም እንጂ እንደ እርሱ በመሳደብ አልነበረም። ኑፋቄውን በመረዳታቸውም ከእርሱ እና ከተከታዮቹ ጋር መገናኘት አቆሙ። ይህ የሆነው በዐፄ ይስሐቅ ዘመነ መንግሥት በ፲፬፻፳፩ ዓ.ም አካባቢ ነው።
ከነባሩ የቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ የተለየ ነገር ሲገጥማቸው ተከራከሩት። አልሰማ ሲላቸው ገዳማችንን ልቀቅ አሉት። ይህንም ያደረጉት የአምላካቸውን ስም በመጥራት እንጂ በጉልበት አለመሆኑን ከራሱ ገድል አንብበን እንረዳለን። ስለሆነም መነኰሳቱ ያደረጉት ትክክል ነው። በአንጻሩ እርሱ እና ተከታዮቹ የገዳም መነኰሳትን “የገዳም ሰዎች፣ አጋንንት፣ ሰይጣን” በማለት ሲጠሯቸው ንጉሡን ደግሞ “ድብ ጸር” ይሉታል። የዘመናችን ተስፈንጣሪ ፖለቲከኞችና ተሐድሶ መናፍቃን የሚጮኹት እንዲህ ያሉት እቡዮች ለምን በተጋድሎ ከሚኖሩ መነኰሳት ተለይተው ወጡ ብለው ነው። ኑፋቄ የተገኘበት ሰው ተመክሮ እንዲመለስ ዕድል ሲሰጠው ካልተመለሰ ቢወገዝም አካላዊ ቅጣት መፈጸም የቤተ ክርስቲያን ተግባር አይደለም። ሰዎች የንጉሡን ድርጊት መተቸት ካማራቸው ጉዳዩን ከቤተ ክርስቲያን ጋር ሳያያይዙ መተቸት መብታቸው ነው። በእርግጥ ከዘርዐ ያዕቆብ የከፋ ጥፋት እየፈጸሙ ዘርዐ ያዕቆብን ለመንቀፍ ማሰብም ሰይጣንን እየረገሙ የሰይጣንን ግብር መፈጸም ስለሆነ ሃይማኖተኛ አያሰኝም።
እነ አባ እስጢፋኖስ ከገዳም የተባረሩት ከነባሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አስተምህሮ በመለየታቸው እንጂ ደጋፊዎቻቸው እንደሚሉት ተጋድሏቸው ጾር አስነሥቶባቸው አይደለም። ለስደታቸው የመጀመሪያው ምክንያት ለእመቤታችን እና ለቅዱስ መስቀል አንሰግድም ማለታቸው ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ተመጻዳቂዎች በመሆናቸው ነው። ስለሆነም ከገዳሙ ያስወጣቸው የራሳቸው አፈንጋጭነት እና እቡይነት እንጂ መነኰሳቱ አይደሉም። የመነኰሳቱን ድርጊት በተመለከተ በአማን ነጸረ ወልታ ጽድቅ በተሰኘው መጽሐፉ “ገድሎቻቸውን ያነበበ ሁሉ ደቂቀ እስጢፋኖስ ለእመቤታችን ያላቸውን ፍቅር እና አክብሮት እንዲሁም በአማላጅነቷ ማመናቸውን ለማረጋገጥ አይቸግረውም። ለእመቤታችን እና ለመስቀል የጸጋ ስግደት ማድረግን በሚመለከት ግን መጀመሪያ አካባቢ በራሳቸው ተነሣሽነት ሲያከናውኑት ማግኘት ከባድ ሲሆን በተለይም በገድለ እስጢፋኖስ ውስጥ አንድም ቦታ ለእመቤታችንና ለመስቀል ሲሰግዱ አናገኘቸውም” በማለት ገልጦታል (፳፻፱፣ ፳፱)።
ከበአማን ነጸረ ጽሑፍ መረዳት የሚቻለው ሰዎቹ ግራ የሚያጋቡ መሆናቸውን ነው። በአንድ በኩል ለእመቤታችን ልዩ ፍቅር እና አክብሮት እንዳላቸው ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ለእመቤታችንም፣ ለመስቀልም ሲሰግዱ አይታዩም – በተለይም አባ እስጢፋኖስ። ለእመቤታችን ፍቅር እና አክብሮት ካላቸው የጸጋ ስግደት ማቅረብ የተናነቃቸው ለምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ይገባል። የየገድሎቹ ጸሐፊዎች ጽፈው ያስነበቡን ከዘመናት በኋላ የተደረሰውን ስምምነት መሠረት በማድረግ እንጂ አስቀድሞ የነበራቸውን አቋማቸውን በመግለጥ አይደለም። ምክንያቱም ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ወደ ነባሩ አስተምህሮ የተመለሱት በአባ ዕዝራ አማካኝነት ነውና።
የደቂቀ እስጢፋኖስ ደጋፊዎች የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን ድርጊት ያብጠልጥሉ እንጂ አባ እስጢፋኖስ የቤተ ክርስቲያኗ አማኝ ነኝ እያለ ለእመቤታችን እና ለመስቀል አለመስገዱን ዕውቅና ሰጥተው ለእመቤታችን መስገድ እንደሚገባ የጻፈው ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ እንጂ ከነባሩ አስተምህሮ ያልነበረ ለማስመሰል የሄዱበት ርቀት ለትችት የሚዳርግ ነው። ጉዳዩንም በአማን ነጸረ “መምህር ካሕሳይ በበኩላቸው ንጉሡን በአምባገነንነትና ስግደት ፈላጊነት በዝሙት በሃይማኖት ሕጸጽ ይከሱታል። ጠንካራ ጎኑን ገፍቶ ለመናገር ዳተኛ ይሆናሉ። ደቂቀ እስጢፋኖስን ለመከላከል ግን የአንድ ወገን መረጃ ብቻ በመያዝ እስከ ጥግ ይሄዳሉ። እንቅስቃሴው ሲጀመር ሰጊድን እንደማይቀበሉ በቂ ፍንጮች እያሉ የጅማሬውን የእነ አባ እስጢፋኖስን እምቢታ በኋለኞቹ የእነ አባ ዕዝራ እሺታ (ሰጊድ) ሸፍነው ለማለፍ ብርቱ ጥረት ያደርጋሉ። ቅድመ ሥዕል መስገድ የጸና ኦርቶዶክሳዊ ትውፊት መሆኑ እየታወቀ እስጢፋኖሳውያን ‘ወቅድመ ሥዕላ ስግዱ’ ማለትን ያልተቀበሉት በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ የመጣ አዲስ ብሂል ስለሆነ ብቻ አስመስሎ ማለፍ እንደ ኦርቶዶክሳዊ ተገቢ ሆኖ አልታየኝም” በማለት ገልጦታል (ገጽ ፳፯)። በአማን እንዲህ የጻፈው በቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ የነበረው መምህር ካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔር ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ይልቅ ለእነ አባ እስጢፋኖስ ጠበቃ በመሆኑ ነው።
የመምህር ካሕሳይን የመሰለ አቋም ያለው ሰው በቤተ ክርስቲያኗ ከፍተኛ የኃላፊነት ደረጃ ላይ መቀመጡ የሚያስገርም ከመሆኑም በላይ ክርስቲያን ነኝ ብሎ እያመነ ለእመቤታችንም፣ ለሥዕሏም መስገድን ጀማሪው ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ነው ማለት በጣም ያስነቅፋል። እንዲህ በማለት የሚጽፉ ሰዎች ክርስትናቸው ጥያቄ የሚያስነሣ ነው። ታሪክ ለመጻፍ የሚነሣ ሰው በሚመስለው መረጃውን ሞርዶ ራሱ የሚያምንበትን እንዲናገርለት ሳይሆን በዚያ ጉዳይ ላይ የተጻፉትን ማስረጃዎች ሁሉ አሟጦ በመጠቀም እስከ አሁን ይዞት ከነበረው አቋም የተለየ ድምዳሜ ላይ ቢደርስ እንኳ መቀበል ነው።
ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን መውደድም፣ መጥላትም መብት ነው። ታሪክ ለመጻፍ የተነሣ ምሁር ግን ጥላቻንውም ሆነ ፍቅሩን ወደ ጎን አድርጎ ማስረጃ ላይ ብቻ መመርኮዝ ይገባዋል። የዘርዐ ያዕቆብን ድክመትም ሆነ ጥንካሬ ያለ አድሎ በማስረጃ መሞገት ተገቢም፣ አስተምሪም ተግባር ነው። ንጉሡን ስለጠላ ብቻ ለእመቤታችን ስገዱ ሲባሉ “ለልጇ ስንሰግድ በዚያ በኩል እናገኛታለን” የሚል የተንሸዋረረ መልስ ለሚሰጡ እቡዮች ጠበቃ የሚሆን ጸሐፊ አምንበታለሁ ለሚለው ሃይማኖቱ ከግለሰቦች ያነሰ ፍቅር ማሳየቱ ስለሆነ ሊስተካከል ይገባዋል።
የደቂቀ እስጢፋኖስ ደጋፊዎች “ከዚያ መልእክተኞቹ በሉ ለንጉሡ ስገዱ አሏቸው። እነርሱም እኛስ ለእግዚአብሔር በቀር ለሰው አንሰግድም አሉ። በሉ ለእግዚአብሔር ስገዱ አሏቸው ጥሩ አሏቸው። ይህንም ለንጉሡ ነገሩት። ንጉሡ ወዶ ነው ለእግዚአብሔር የሚሰግደው በግድ አይደለምን ለማርያም ስገዱ በላቸው አለ። ለማርያም ስገዱ ቢሏቸው ለልጇ ስንሰግድ እዚያ እናገኛታለን አሉ። ይኽን ለነጉሡ ነገሩት ። ጤጠይ በምትባለው ጅራፍ እንዲገርፏቸው በቁጣ አዘዘ። አጋድመው ብዙ ገረፏቸው” የሚለውን ከገድላቸው ማንበብ አይፈልጉም (ደቂቀ እስጢፋኖስ በሕግ አምላክ፣ ፳፻፪፣ ፻፵፮)። ከገድሉ በተቀነጨበው በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ብዙ ቁም ነገሮች ተካትተውበታል። የመጀመሪያው ንጉሡ ወደ አባ እስጢፋኖስ እና ወደ ተከታዮቹ ተደጋጋሚ መልእክተኛ በመላክ እምነታቸውን መረዳቱ ነው። ከመካከላቸው አንዱን ኤርምያስ የሚባለውን አስቀርቦ ለምን ከአድባራቱ ሥርዓት ወጣህ ብሎ ሲጠይቀው በመጽሐፈ ሲኖዶስ እንደሚመራ መልስ ሲሰጠው ንጉሡ የተሸጋገረው ወደ ሌላ ጥያቄ ነበር። ኤርምያስ የሚባለው መነኵሴ ከወጣ በኋላ በመቀጠል መልክእተኞች ሄደው ለአባ እስጢፋኖስ ተከታዮች “ለንጉሡ ስገዱ” ሲሏቸው መልሳቸው “እኛ የምንሰግደው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው” የሚል መሆኑ ንጉሥን ማክበር በኅሊናቸው የሌለ መሆኑን ያሳያል።
መልእክተኞች ለንጉሡ ስገዱ ሲሉ ንጉሡን እጅ ንሡት ማለታቸው እንጂ አምልኩት እያሉዋቸው አለመሆኑ መታወቅ አለበት። የመነኰሳቱ መልስ ግን እጅ መንሣትን እና የአምልኮ ስግደትን በማምታታት እኛ የምንሰግደው ለአምላካችን ብቻ ነው ብለዋል። ንጉሡን አምልኩት የተባሉ አስመስለው እንዴት ሆኖ ለንጉሥ እንሰግዳለን ማለታቸው የሚያስገርም ቢሆንም በዚህም ንጉሡ ታግሷቸዋል። በመቀጠል የላከባቸው ለእግዚአብሔር ስገዱ በማለት ነበር። በዚህ የንጕሡ አሳብ መነኰሳቱ ተስማምተዋል። ለእግዚአብሔር መስገድን ከተቀበሉ ለእመቤታችን ስገዱ ብሎ ሲልክባቸው መልሳቸው ፍጹም እቡይነትን የሚያንጸባርቅ ነበር። “ለልጇ ስንሰግድ እዚያው እናገኛታለን” ብለው መልስ መስጠታቸው ንጉሡን በጣም ስላበሳጨው በጅራፍ አስገርፏቸዋል።
በገድላቱ ተጽፎ ከምናነበው ንጉሡ የገረፋቸው ካልሰገዳችሁልኝ ብሎ ሳይሆን በመልስ አሰጣጣቸው ተበሳጭቶ ነው። አስቀድመን እንደገለጥነው መምህር ካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔር በሃይማኖት ሕጸጽ የሚከሰው ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ እንዲህ ያለ እምነትም አቋምም ያለው ነው። በተለይም ጉዳዩን በዘመን አመጣሹ የዘውግ ፖለቲካ መነጽር የሚመለከቱት ፖለቲከኞች እና የዘውግ ፖለቲካ አራማጆች ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብን የሚከሱት የእኛን ወገን አሳድዷል በሚል ነው። ማንጸሪያቸው ዘውግ እንጂ ሃይማኖት ወይም ታሪክ አይደለም። አባ እስጢፋኖስን የሚደግፉትም ትክክል ስለሆነ ሳይሆን ከእኛ ወገን ውጪ በሆነ አካል ተጠቅቷል በሚል ነው። መታወቅ ያለበት ንጉሡ እነርሱ የሚጠሉት ቋንቋ ተወካይ፣ ደቂቀ እስጢፋኖሳውያንም የትግራይ ተወካይ አለመሆናቸውን ነው። መጀመሪያ ከገዳም ያባረሩት የትግራይ ገዳማት መነኰሳት ሆነው ሳለ የገዳሙን መነኰሳት ጥፋተኛ ናቸው ብለው ሲወቅሷቸው አይሰሙም። ከዚህ የምንረዳው የሚከሱት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ከትግራይ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ያለ ውርጅብኝ የማይደርስበት መሆኑ ነው። ታሪክ የሚጻፈው ወገን እና ጠላት ለመለየት ሳይሆን የመረጃ ክፍተትን በመሙላት ሰውን ከስሕተት ለመታደግ ቢሆንም ተስፈንጣሪዎች የሚጽፉት ራሳቸውን እንከን የሌላቸው አድርገው ሌሎችን ለማንቋሸሽ ነው።
የደቂቀ እስጢፋኖስ ደጋፊዎችም ሆኑ ነቃፊዎች እንዲሁም የንጉሡ ነቃፊዎችም ሆኑ ደጋፊዎች ከስሜታዊነት ወጥተው ትችታቸውንም ውዳሴያቸውንም በሚያገኙት ማስረጃ መሠረት መሆን ይገባዋል። ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘውዳዊውን ሥርዓት በማናናቃቸው መነኰሳቱን መቅጣት ቢኖርበትም ቅጣቱ ከመጠን ማለፍ አልነበረበትም። በሌላ በኩል ንጉሡ ያሳለፈውን ቅጣት መበየን የሚኖርብን በዛሬ መነጽር እያየን ሳይሆን ከዘመኑ ንቃተ ሕሊና አንጻር መሆን ይገባዋል። የዘርዐ ያዕቆብን ድርጊት እየተቸን ከእርሱ የከፋ ጥፋት ለመፈጸም መዘጋጀት ሰዎች ለጥፋታቸው ምክንያት እየፈለጉ እንጂ ከስሕተት እየተማሩ ላለመሆኑ ማሳያ ነው።
መምህር ካሕሳይም ሆነ ሌሎች የዘመናችን የደቂቀ እስጢፋኖስ ደጋፊዎች ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ላይ ቢረባረቡም የእነ አባ እስጢፋኖስ ጉዳይ ከትግራይ ገዳማት ተነሥቶ ከንጉሡ ችሎት እስከሚደርስ የነበረውን እያንዳንዱን ሁነት ለማለፍ መሞከራቸው ለትዝብት የሚዳርግ ነው። መታወቅ የሚገባው ግን አባ እስጢፋኖስ እና ተከታዩቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳደዱት በ፲፬፻፳፩ ዓመተ ምሕረት ትግራይ ከሚገኘው ከደብረ ቆየጻ ገዳም መሆኑ ነው (በአማን፣ ፳፻፱፣ ፲)። ይህ ዘመን የዐፄ ይስሐቅ ዘመነ ንግሥና ነው። ከዚህ የምንረዳውም ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት አስቀድሞ ሲያስቸግሩ የነበሩ መሆናቸውን ነው።
በአባ እስጢፋኖስ እና በተከታዮቹ ላይ የተፈጸመውን ቅጣት በሃይማኖት ምክንያት ከተፈጸመ ተጋድሎ ጋር ከማያያዝ ይልቅ ምግባረ ብልሹነት ያስከተለው ቅጣት መሆኑን መቀበል ወደ እውነቱ ይጠጋል። ለዚህ አስረጅ የምናቀርበውም ከራሱ ከአባ እስጢፋኖስ ገድል “ለእነዚህ መነኰሳትም እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት የእግዚአብሔርን ልጅ ለመከተል ወንጌልን በመሸከም የምትገኝ የሥርዓት ብርሃን ውበት ተሰጣቸው። ከዚያ በኋላ ኪዳናቸውን ትተው እነሆ ወደ ዓለም ተመልሰዋል። እኔም ጋኔን እንዳልሆን ልተባበራቸው አልፈልግም…ንጉሡ ቅዱሱን ለመሆኑ መምህርህ ማን ነው አለው። ቅዱሱ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አለ። ንጉሡ ከዚያስ ቀጥሎ አለው። ብፁዓን ነቢያትና ሐዋርያት አለው። ንጉሡም ከእነርሱ በኋላስ አለው። ቅዱሱ በነቢያትና በሐዋርያት ሥርዓት የሚሄደውን ሁሉ ትልቅም ሆነ ትንሽ አለይም ሁሉም መምህሮቼ ናቸው አለው። ንጉሡ ከዚያ በኋላስ አለው። ብፁዑ እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ ከዚያ በኋላማ ሌላ የለኝም ምክንያቱም ሁሉም የሰይጣን ሠራዊት፣ የአጋንንት ማኅበር ናቸው” የሚለውን በመጥቀስ ነው (ደቂቀ እስጢፋኖስ በሕግ አምላክ፣ ፳፻፪፣ ፺፫-፺፭)። እንዲህ ያለው መልስ አሰጣጥም ሆነ ራስን አጽድቆ ሌላውን ሰይጣን ማድረግ ከሃይማኖት አባት የሚጠበቅ አለመሆኑን መግለጥ ይገባል።
በአጠቃላይ በዘመኑ በነበረው ንጉሣዊ ሥርዓት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ለአገሬ እና ለመንግሥቴ ይበጃል ብሎ ያምነበትን ማድርግ ይችላል። አገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ እና መንግሥቱን ለማጽናት በእርሱ ላይ በመገዳደር የሚነሡትን የመቅጣት ሥልጣን አለው። ይህን የሚያደርገው ግን በንጉሥነቱ እንጂ ቤተ ክርስቲያን ወክላው አይደለም። የዘመኑ የዘውግ ፖለቲካ አራማጆች እንደሚሉት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ “የቤተ ክርስቲያን መሪ ወይም የአንድ ጎሣ ተወካይ” ሳይሆን የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ነበር። ስለሆነም ያልተጻፈ በማንበብ በሕዝብ እና በክርስቲያኖች መካከል ልዩነትን መዝራት የተንሸዋረረ የታሪክ አረዳድ የፈጠረው ነው። በወቅቱ ከገዳማቸው ያባረሩት የትግራይ መነኰሳትም በአባ እስጢፋኖስ ላይ በተፈጸመው ቅጣት ተቃውሞ አልነበራቸውም። ይህም የአባ እስጢፋኖስ ግብር ሊያስቀጣ የሚችል መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው።
ስለሆነም የዘውግ ፖለቲካ አራማጆች እና ተሐድሶ መናፍቃን ለዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ እና ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ካላቸው ጥላቻ የተነሣ እንጂ ቤተ ክርስቲያን አባ እስጢፋኖስን በማሳደድም ሆነ መንበር በማፋለስ የምትከሰስበት ምክንያት የለም። በቤተ ክርስቲያን ታሪክም መንበረ ሰላማ የሚባል መንበር ኖሮ አያውቅም። የነበራት ቢሆን ስንኳ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የአባታቸውን መንበር የነጠቁ አስመስሎ ማቅረብ የጤንነት አይደለም። ስለሆነም “የተወሰደውን መንበረ ሰላማን እናስመልሳለን” በማለት የተነሡ አካላት ድርጊትም የዋሃንን ለማሳሳት እና በዘውግ በመጥለፍ የራሳቸውን ዓላማ ለማሳካት እንጂ እውነተኛ ታሪካዊ መሠረት ኖሯቸው አይደለም። አሳቡ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃንን ባልዋሉበት የሚያውል ከመሆኑም በላይ ፖለቲካዊ እንጂ መንፈሳዊ አለመሆኑን አስረግጦ መናገር ይገባል። የዚህ ሁሉ ዳር ዳርታ መዳረሻው ምክንያት ፈልጎ የዋሃንን ከእናት ቤተ ክርስቲያናቸው ለመነጠል መሆኑን ክርስቲያኖች ሁሉ ሊረዱት ይገባል።
ማጣቀሻ መጻሕፍት
በአማን ነጸረ። ወልታ ጽድቅ። አዲስ አበባ፣ ፋር ኢስት ትሬዲንግ ፣ ፳፻፱ ዓ.ም።
ደብረ ሊባኖስ ገዳም። ገድለ ተክለ ሃይማኖት።
ጌታቸው ኃይሌ (ተርጓሚ)። ደቂቀ እስጢፋኖስ በሕግ አምላክ። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕረስ። አአዩ ማተመያ ቤት፣ ፳፻፪ ዓ.ም