የአዲስ አበባ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት በ2015 ዓ.ም በ4 በ6ና በ10ኛ ክፍል ያስተማራቸውን ከ4500 በላይ ተማሪዎች አስመረቀ

ጥቅምት 04 2016 ዓ.ም (የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት)

የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በ2015 ዓ.ም በ4 በ6 እና በ10ኛ ክፍል በተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርት ያስተማራቸውን ተማሪዎች በዛሬው ዕለት በደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም እና ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ካቴድራል አስመረቀ። በመርሐ ግብሩ ላይም ብጹዕ አቡነ አብርሃም የባህርዳር ሀገረስብከት ሊቀጳጳስና የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ የሰሜን አሜሪካ የኒውዮርክ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ቀለሜንጦስ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃነ ጳጳሳት የጠቅላይ ቤተክህነት መምሪያ ኃላፊዎች የጠቅላይ ቤተክህነት የየመሪያው ኃላፊዎች ፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እና የክፍለ ከተማ ቤተክህነት የየክፍሉ ኃላፊዎች የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አመራሮች ተመራቂ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ውሏል።

የምርቃት መርሐ ግብሩ ልጅህን በሚሄድበት መንገድ ምራው በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም በሚል መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን በመጀመሪያ በብጹዕ አቡነ ቀለሜንጦስ መሪነት በጸሎተ ወንጌል ተከፍቷል። በመቀጠልም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ሰብሳቢ ላዕከ ኄራን መንክር ግርማ የመግቢያ ንግግር የተደረገ ሲሆን በንግግራቸውም በአዲስ አበባ ከሚገኙ 250 አድባራት 157 የሚሆኑት በ2015 ዓ.ም ሥርዓተ ትምህርቱን መተግበራቸውንና በዛሬው ዕለት ግን 77 የሚሆኑ አድባራት በአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ እርከኖች ተማሪዎቻቸውን ማስመዘናቸውን ገልጸዋል። በዚህም ከተፈተኑት 4500 ተማሪዎች ውስጥ 4030 የሚሆኑት ወደ ቀጣይ ክፍል መዘዋወራቸውን አብስረዋል። በ2016 ዓ.ም በ205 ደብራት 72,000 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት እንዲማሩ እንደ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የዕለቱን ወንጌል የሰንበት ትምህርት ቤት ፍሬ የሆኑት ዲያቆን ህሊና በለጠ “እኔ የሳሮን ጽጌሬዳ የቆላም አበባ ነኝ” መኃ 2:1 በሚል ቃል መነሻነት ቃለ እግዚአብሔር አስተላልፈዋል። በመቀጠልም ብጹዕ አቡነ አብርሃም ለተመራቂ ተማሪዎችና ለወላጆች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም “የሳንቲም ውርስ ልጆችን ያጋጫል የሃይማኖት የእውቀት የምግባር ውርስ ግን እስከ መጨረሻው ለወላጆች የሚጠቅሙ ሀገርን ሀገር የሚያሰኙ የነገዋን ቤተክርስቲያንን የሚገነቡ ተስፋዎች ያደርጋችዋል። ስለዚህም ቤተክርስቲያንን እንጠብቃት እንታዘዛት አገልግሎታችሁ ከጥቅማ ጥቅም የተነሳ ሳይሆን በነጻ የምታገለግሉበት ነውና ብዙ ጸጋና ሀብትን ይሰጣችኋል በዚህም ቤተክርስቲያናችሁ እጅግ ትደሰታለች።” ሲሉ አባታዊ ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል።

በመጨረሻም የሽልማትና የምስጋና መርሐግብር የተካሄደ ሲሆን ከ77 አድባራት በብዙ የተማሪዎች ቁጥር ያስፈተኑንና ከተፈተኑት ውስጥ የደረጃ ተማሪዎች የነበሩትን ከብጹአን ሊቃነ ጳጳሳት እጅ የማበረታቻ ሽልማት ተሰቷቸዋል። በብጹዕ አቡነ ቀለሜንጦስ የመጨረሻ አባታዊ ቡራኬ እና መልእክት የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።

(የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት)

✍️YouTube 👇
https://www.youtube.com/@eotc-gssu
✍️ FaceBook 👇
https://www.facebook.com/EOTC.GSSU
✍️Telegram 👇
https://t.me/EOTCNSSU
✍️Website👇

✍️Tiktok👇

@sundayschoolunion