በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ አባቶች
የመንፈስ ቅዱስ መሰንቆ የቃኛቸው አባቶች በመንፈሳዊ ሥልጣን ላይ ሲቀመጡ ራሳቸውንም ሌሎችንም ይጠቅማሉ። በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ አባቶች በፈቃደ እግዚአብሔር ስለሚመሩ ክርስቲያኖች ሁሉ እግዚአብሔር በሚፈቅደው መንገድ እንዲጓዙ ያደርጋሉ። እንዲህ ማድረጋቸው ሃይማኖት እንዲጸና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዲጠበቅ ሳይታክቱ ይሠራሉ። መሥራት ብቻ ሳይሆን ራሳቸው አርአያ ሆነው ፈጽመው ያሳያሉ።
ለዚህ አብነት የሚሆኑ ብዙ ቅዱሳን አባቶችን መጥቀስ ይቻላል። መፍቀሪተ ንዋይ ገፋዒተ ነዋይ የነበረችው የአርቃዴዎስ ሚስት ንግሥቲቱ አውዶክስያ የአንዲትን ደሀ መበለት መሬት በነጠቀቻት ጊዜ የተገፋ ለንጉሥ አቤት ማለት ትውፊት ቢሆንም የገፋት ቤተ መንግሥቱ ስለነበር አቤቱታዋን ያሰማችው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነበረ። በዘመኑ የቍስጥንጥንያ ፓትርያርት የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በደሏን ሰምቶ፣ መገፋቷን ዐይቶ መሬቷን እንድትመልስላት፣ የደሀዋ ጠበቃ መሆን ሲገባት ምንም የሌላትን ደሀ ማሠቃየትን ሙያዋ በማድረጓ ከድርጊቷ እንድትቆጠብ የሚያሳስብ መልእክት ለንግሥቲቷ ላከባት።
ንግሥቲቱም ‘በብላሽ አልወሰድኩባትም፤ መሬት ከፈለገች መሬት፣ ገንዘብ ከፈለገች ወርቅ ልስጥሽ ብያት ነበር’ በማለት መለሰችለት። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም ንግሥቲቱ እንዲህ ብላለች በማለት ለደሀይቱ ነገራት። ደሀዋም መሬቴ ከቤተ ክርስቲያን አጠገብ ናት። በዓመት ሦስት ጊዜ ዘርቼ የማመርትባት ናት። በዚህም ላይ ርስት የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ በመሆኑ ርስቴን አልሰጣትም። ልጆቼንም ከርስት መንቀል አልፈልግም አለችው፡፡ የደሀዋን ቃል ሰምቶ ለንግሥቲቱ ርስቷን መልሽላት ብሎ ቢልክባትም ስላልሰማችው ከምእመናን እንዳትገናኝ፣ ከቤተ ክርስቲያን እንዳትገባ፣ ሥጋ ወደሙም እንዳትቀበል አውግዞ ለያት፡፡
እርሷም በሥልጣኗ የምትመካ ከንቱ ሴት ስለነበረች እንዴት ተደፈርኩ በማለት ቅዱሱን አባት ከመንበሩ ለማሳደድ አሳብ እንዲሰጧት ያማከረቻቸው በኑፋቄያቸውና በመጥፎ ምግባራቸው አውግዞ ከቤተ ክርስቲያን የለያቸውን ግለሰቦች ነበር። እነርሱም ቤተ መንግሥቱን መበቀያ አድርገው ቅዱሱን አባት እንድታሳድደው መከሯት። ንግሥቲቱም ጳጳሳትን ከየአገረ ስብከታቸው አስመጥታ ቅዱስ ዮሐንስ ከግዝቱ ካልፈታኝ ‘አብያተ ክርስቲያንን ዘግቼ፣ አብያተ ጣዖታትን እከፍታለሁ’ በማለት ዛተች፡፡ ጳጳሳቱም ከቅዱሱ አባት ጋር እንዲማከር ቅዱስ ኤጲፋንዮስን ወደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ላኩት። ቅዱስ ኤጲፋንዮስም ሔዶ ‘የምግባር እንጂ የሃይማኖት ሕጸጽ ሳይኖርብኝ አወገዘኝ’ ብላለች እና ከግዝቱ ፍታት በማለት ለመነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም ይህም እንጂ የሃይማኖት ጉዳይ ነው፤ ለንግሥቲቱ ስናደላ ደሀይቱስ ርስቷን ስለቀማቻት ታዝን የለምን? ለደሀይቱ ቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ካልሆነቻት ሃይማኖቷን ትክድ የለምን? በማለት መለሰለት፡፡ ንግሥቲቱ በዚህ አልሆን ሲላት ከኢጲፋንዮስ ጋር ልታጣላው ብትሞክርም አልተሳካላትም፡፡ ቁጣዋ ከልክ በማለፉ በሌሊት ከመንበሩ አስወጥታ አክራጥያ ወደ ሚባል ደሴት አጋዘችው። የሮሙ ንጉሥ አኖሬዎስ እና ሊቀ ጳጳሳቱ ዮናክኒዶስ ንግሥቲቱ የፈጸመችውን ግፍ ሲሰሙ ወደ መንበሩ እንዲመልሰው ለንጉሡ ለአርቃዴዎስ ደብዳቤ ላኩበት፡፡ የእነርሱን ቃል ሰምቶ፣ የንግሥቲቱን ቁጣ ችላ ብሎ ቅዱስ ዮሐንስን አስፈታና ወደ መንበሩ መለሰው፡፡ ንግሥቲቱም ጥቂት ቆይታ፣ ምክንያት ፈጥራ መልሳ አጋዘችው። ቅዱሱ አባት በግዞት ላይ እያለ በደሴተ አጥራጥያ ዐረፈ፡፡ ድርጊቱን የሰማው የሮሙ ሊቀ ጳጳሳት ዮናክኒዶስ ከምእመናን እንዳትገናኝ፣ ቤተ ክርስቲያንን እንዳትሳለም፣ ሥጋ ወደሙንም እንዳትቀበል አወገዛት፡፡ ወዲያውም ጽኑ ደዌ ስላደረባት ትሰቃይ ጀመር፡፡
ንግሥቲቱ ገንዘቧን ሁሉ ለባለመድኃኒት ሰጥታ ብትጨርስም ከደዌዋ አልዳነችም። ለክፉ አድራጊ በጎ አስታራቂ አይጠፋምና ከሊቀ ጳጳሳቱ አስታርቋት፣ ከግዝቱ ቢፈታትና ሥጋ ወደሙ ብትቀበልም ደዌው አልለቀቃትም፡፡ ዳግመኛም በጎ መካሪ ሰዎች ሔደው እንዲህ ያለው ደዌ የደረሰብሽ በደጉ አባት በቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ላይ ግፍ ስለሠራሽበት ነው። አሁንም ከመቃብሩ ሔደሽ ተማጸኝው ብለው መከሯት። ንግሥቲቱም ከቅዱሱ መቃብር ሔዳ እባክህ ማረኝ በማለት ተማጸነችው። ቅዱሱ አባትም ይቅር ባይ ነውና ይቅር ብሏት ከደዌዋ ተፈወሰች”፡፡
በመንፈስ ቅዱስ የተቃኙ አባቶች እንዲህ ያለ የደሀ ጠበቃነታቸውን ሲፈጽሙ በአባትነት ካባ የተሸፈኑ የዘመናችን አንዳንድ ግለሰቦች ኃላፊነታቸውን ተረድተው እንኳን ደሀ ሲበደል፣ ፍርድ ሲጓደል ሊጮሁ ለቤተ ክርስቲያን ተጨማሪ ፈተና ሆነው በማስጨነቅ ላይ ናቸው። በዚህ ዘመን ምእመናን የሚሹት ግን እንደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ያለ አባት ነበር። እንደ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ያለ አባት ምድራዊውን ከሰማያዊው፣ የእግዚአብሔርን ከቄሣር አይቀላቅልም። ምእመናንን የሚፈልጋቸው ገንዘብ ለማግኘት ሳይሆን እነርሱን መርቶ ለመንግሥተ ሰማይ ለማብቃት ነው።
በዚህ ዘመን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሾም የሚገባት እንደነዚህ ያሉ አባቶችን ነው። አሁን በየሀገረ ስብከቱ የተመደቡ አባቶች እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ያለ ጥብዓት ባይኖራቸው እንኳ ለቤተ ክርስቲያን ውለታ የሚውሉላት ከእነርሱ የተሻሉ አባቶች በተጓደሉ መናብርት ላይ እንዲቀመጡ በማድረግ ነው ብለን እናምናለን።