በላዔ ሰብ እና እሥራኤል ዘሥጋ

በታሪክ እንደሚታወቀው እሥራኤል ዘሥጋ በግብጽ ባርነት ለ430 ዓመት ተገዝተው ነበር፡፡ እግዚአብሔርም የሲዖል ምሳሌ ከምትሆን ግብጽ በዘጠኝ ታላላቅ ተዓምራት በአሥረኛ ሞተ በኵር በአሥራ አንደኛ ስጥመተ ባሕር ግብጽን በመቅሰፍ ነጻ አውጥቷቸዋል፡፡

እስራኤል ዘሥጋ ግን ይህንን ታላቅ ውለታ በማሰብ ፈንታ አምላካቸው እግዚብሔርን አሳዘኑ ቀልጦ ለተሠራ ጣዖት ሰገዱ ሰዉለትም፡፡ ‹‹እስራኤል ሆይ ስማ እነዚህ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አሉ፡፡›› ዘጸ 32፡1-14 መዝ 105፡23 የእግዚአብሔርም ቁጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ፡፡ ያጠፋቸውም ዘንድ ከተመረጠው መስፍን ከሊቀ ነቢያት ሙሴ ጋር መከረ፡፡ ‹‹ይህንን ህዝብ አየሁት እነሆ አንገተ ደንዳና ነው፡፡ አሁንም ቁጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ፡፡ አንተ ግን ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለው፡፡›› አለው፡፡ ዘጸ 32፡9-10

ሙሴም ሕዝቡን እንዳያጠፋቸውና ከቁጣው ይመለስ ዘንድ ስለ ሕዝቡ ያማልድ ጀመር፡፡ በተለይም እግዚአብሔር ከቅዱሳኑ ከአብርሃም ከይስሐቅ እና ከያዕቆብ ጋር የገባውን ቃልኪዳን ያስብ ዘንድ ለመነ፡፡ ‹‹ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ምድር አሸዋ አበዛዋለው፡፡ ይህችንም የተናገርኳትን ምድር ለዘራችሁ ሁሉ እሰጣለው፡፡ ለዘላለምም ይወርሷታል ብለህ በራስህ የማልክላቸውን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ፡፡›› አለው፡፡ ዘጸ 32፡13

እግዚአብሔርም የቅዱሳኑ ስም ተጠርቶ ሲሰማ የገባላቸውን ቃል ኪዳን አሰበ፡፡ በሕዝቡ ላይ ሊያደርገው ስለነበረው መቅሰፍት ፈጽሞ ራራላቸው፡፡ ይቅርም አላቸው፡፡ ‹‹ከመረጥኳቸው ጋር ቃልኪዳኔን አደረግሁ፡፡›› ያለ አምላክ ከተመረጡት ቅዱሳን ከአብርሃም ከይስሐቅ ከያዕቆብና ከሌሎችም ቅዱሳን ጋር ቃልኪዳኑን እንዳደረገ እንዲሁ ከተመረጡ የተመረጠች ከተለዩ የተለየች ከእናታችን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያምም ጋር እንዲሁ ቃልኪዳኑን በዛሬው ዕለት የካቲት 16 ቀን አድርጓል፡፡ እመቤታችንም ‹‹መታሰቢያዬን የሚያደርገውን፣ በስሜ ቤተ ክርስቲያን የሚያንጸውን ፣ የተራቆተ የሚያለብሰውን፣ በሽተኛ የሚጎበኘውን፣ የተራበ የሚያበላውን፣ የተጠማ የሚያጠጣውን፣ ያዘነን የሚያረጋጋውን የተበሳጨ የሚያስደስተውን፣ መመስገኛየን የጻፈና ያጻፈ ፣ ወንድ ወይም ሴት ልጁን በስሜ የሰየመውን፣ በምመሰገንበት ቀን ዝማሬ ያቀረበውን ዓይን ያላየውን ጆሮ ያልሰማውን የሰው ኅሊና ተመራምሮ ያልደረሰበትን መልካም ዋጋ ትሰጥልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ፡፡›› ብትለው፡ ጌታም ‹‹መሃልኩ ለኪ በርዕስየ በከመ ኢይሔሱ ኪዳንየ›› ያልሽውን ሁሉ ላደርግልሽ ቃል ኪዳኔንም ልጠብቅልሽ በራሴ ማልሁልሽ በማለት የምህረት ቃል ኪዳን ገብቶላታል፡፡

የአብርሃም የይስሐቅ እና የያዕቆብ ቃልኪዳን የእግዚአብሔርን ሕልውና ለካዱ ቀልጦ ለተሠራ ጣዖት ለሠገዱ ለእስራኤል ዘሥጋ መትረፉን መጽሐፍ ቅዱስ ከነገረን በተዓምረ ማርያም ላይ ደግሞ ስምዖን በግብር ስሙ በላዔ ሰብ 70 ሰዎችን በልቶ በቃል ኪዳኗ ተጠቅሞ መዳኑን ይነግረናል፡፡ እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ቃልኪዳን የማይሆነውን እንዲሆን የሚሆነን ደግሞ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡ ያጠረውን ያስረዝማል፡፡ የረዘመውን ያሳጥራል፡፡ ኃጥኡን ያጸድቃል፡፡

ዛሬም እስራኤል ዘነፍስ የምንሆን እኛ ክርስቲያኖች በእመቤታችን ቃልኪዳን በመታመን ሀገራችን ላይ እና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የተቃጣውንና እየደረሰ ያለውን መከራ እርሱ በቸርነቱ ያርቅልን ዘንድ ስለ እናትህ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብለህ ማረን ይቅር በለን እያልን ተግተን ልንለምነው ይገባል፡፡
የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ ስም ሲነሳ በእስራኤል ዘሥጋ ላይ ያልጨከነ ለድካማቸውም የራራ አምላካችን የእናቱን ስም ጠርተን በቃልኪዳኗ ብናምለው እንደምን አይራራልንም?