ነፋስን ዘርተዋል፤ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ (ሆሴ. ፰፡፯)

ነፋስን ዘርተዋል፤ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ (ሆሴ. ፰፡፯)

ነፋስን ዘርተዋል፤ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ (ሆሴ. ፰፡፯)

ቸርነት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር “ብትወዱኝስ ትእዛዜን ጠብቁ” ብሏል። ትእዛዛቱን በመጠበቅ የሚገኘው ክብር ደግሞ የዘለዓለም ሕይወት መሆኑን ገልጾልናል። የምንጠብቃቸውን ትእዛዛት በተመለከተ ደግሞ አንድ ሕግ ዐዋቂ “ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ትልቅ ናት?” ብሎ በጠየቀው ጊዜ ጌታ የሰጠው መልስ “አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም አሳብህ ውደድ። ታላቂቱ እና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች። እርስዋም ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕግም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል” (ማቱ. ፳፪፡፴-፮፵) የሚል ነው። ከእነዚህ ከሁለቱ ትእዛዛት የሚወጣ ሕግ እና ትእዛዝ የለም። ሁሉም ሕግጋት ፍቅረ እግዚአብሔርን እና ፍቅረ ቢጽን መሠረት ያደረጉ ናቸው። እነዚህን ትእዛዛት ማክበር በምድር ላይ ሰላምን ይሰጣል፤ ዕድሜን ያረዝማል፤ በሰማይ የዘለዓለም ሕይወትን ያስገኛል።
የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ምድራዊ ጸጋ ሰማያዊ ዋጋ ያለው እንጂ እንዲሁ በከንቱ የሚደረግ አይደለም። በምድር ላይ ግን ለሕግ ካለመታዘዝ ጀምሮ ዐመጽ፣ ጠብ፣ ክርክር፣ አድማ፣ ሁከት እና ራስ ወዳድነት ተንሰራፍቶ ታያል። እንዲህ ያለው መጥፎ ጠባይ በማያምኑት መካከል ብቻ ሳይሆን እናምናለን በሚሉት እና የእግዚአብሔርን ቃል ዕለት በዕለት በሚሰብኩትም መካከል ያለ እንክርዳድ ነው። አልጫውን ዐለም ጨው ሆነው ያጣፈጡ የሐዋርያት ልጆች፣ ብርሃን ሆነው ያለማወቅን ጨለማ የገፈፉ የቅዱሳን ሊቃውንት ተከታዮች፣ ሁሉን ትተው አምላካቸውን የተከተሉ ቅዱሳን ጻድቃን ወዳጆች፣ ስለ ስሙ የተሰደዱና ስለ ስሙ የተገደሉ ቅዱሳን ሰማዕታት ልጆች ለዐለሙ የሚተርፍ ቀርቶ ለራሳቸው የሚሆን ሰላም ከሌላቸው ክርስትናን ከመግደል አይተናነስም።
ፍቅር ሒደት ሲሆን ውጤቱ ደስታና ሰላም ነው። ሰው እግዚአብሔርን እና ሰውን ከወደደ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት፣ በሰው ላይ ክፋት ስለማይሠራ ዐለም ሰላም፣ ሕይወትም በደስታ የተሞላች መሆኗ የታመነ ነው። ነገር ግን በዐለም ላይ በተለይም በአገራችን የምናየው ከዚህ በተቃራኒ ነው። የፍቅር መቀዛቀዝ፣ የመንፈስ ዝለት፣ አድመኝነት እና መለያየት ተንሰራፍቷል። የሰላም ዋጋ ቀንሷል። የእብድ ገላጋይ በዝቷል። በለው፣ ፍለጠው፣ ቁረጠው እንጂ ተዉ የሚል ጠፍቷል። አስታራቂ ሽማግሌ፣ ሰሚ ልጅም የለም። በዚህም ምክንያት ሰው ስለ ክፋት ሲያስብ፣ ሰውን ስለ ማጥቃት ሲያሰላስል ያድራል። ወንድም በወንድሙ ላይ፣ ወገን በወገኑ ላይ፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ ተነሥቷል። “ከባል የታመነ ከማን ጋር ይሔዷል?” እንዳልነበረ ተረቱ መንግሥትም የሕዝብን ሰላም መጠበቅ ኃላፊነቱ መሆኑን ዘንግቷል። በዚህም ምክንያት እንደ አገር አመጽ ነግሦ ሰዎች ያለመኖር ስጋት ውስጥ ይገኛሉ። ሌሎች ሊያጠቁኝ ነው ብሎ የሚያስብ አካል ደግሞ ራሱን ለመከላከል መነሣቱ ተፈጥሯዊ ነው። በዚህ ምክንያት ሽግግራችን ከጦርነት ወደ ጦርነት ሆኗል። የጦርነትን አስከፊነት የሚናገሩ አንደበቶች ብዙ ቢሆኑም በገቢር ጦርነትን ለማስቆምና ሰላምን ለማምጣት የሚሠሩ ግን ጥቂት ናቸው ወይም የሉም።
በአገራችን የሚከሠቱ አብዛኛዎቹ ችግሮች ቅንነት ማጣት የወለዳቸው ናቸው። ለሚጠየቁ ጥያቄዎች፣ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ ለሚደርሱ ጉዳቶች ተገቢውን መልስ ከመስጠት፣ ጥበቃ ከማድረግ እና ከመከላከል ይልቅ ቸል ማለት እና ኃላፊነትን መዘንጋት ብሎም ለአጥፊዎች ከለላ መስጠት ጎልቶ ይታያል። አገራዊ ዕሴቶችን ማቃለል፣ የሃይማኖት አባቶችን እና የአገር ሽማግሌዎችን ለተገቢው ሰላም ሳይሆን ለፖለቲካ ትርፍ ለመጠቀም ጥረት ይደረጋል። ይህ ዐይነቱ አካሔድ በጊዜው ካልታረመ አገርን ለከፋ ችግር በማጋለጥ ወደ መጥፎ አዘቅት ያወርዳል።
አገር የምትድነው በጥቂት ቅኖች ነው። በቅንነት አገር ለማቅናትና ሰላም ለማምጣት የሚተጉትን መግፋት ብሎም አገልግሎታቸውን ማጣጣል ጉዳቱ ለራሳቸው ለአጣጣዮቹ ነው። በጦርነት ላይ ያሉ ወገኖች ቆም ብለው ሊያጤኑት የሚገባው ጉዳይ አገርን በማስቀደም ሳይሆን በክፋት እና በተንኮል ጥቃት የሚፈጽሙ አወዳደቃቸው የከፋ መሆኑን ነው። ጠቢቡ ሰለሞን “የሰው አካሔድ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘው እንደ ሆነ በእርሱ እና በጠላቶቹ መካከል ስንኳ ሰላምን ያደርጋል” (ምሳ. ፲፮፡፯) ይላል። ስለሆነም ሁል ጊዜም ሰው የሚሔድበት የክፋት ወይም የቅንነት መንገድ መሆኑን ሊያስተውል ይገባል። በእልህ፣ በማን አለብኝነት እና በክፋት መንገድ ከመሔድ መቆጠብ ያስፈልጋል። ሰው የሌላውን መብትና ጥቅም በመጋፋት፣ ሌላውን ለመደበል በማሰብ የሚፈጽመው ተንኮል የሚጎዳው ራሱን ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ኀጢአተኞችን ክፋታቸው ይገድላቸዋል” እንዳለ በጠማማነት የሚጓዙ መጨረሻቸው ውድቀትና ሞት ነው። “በዋጋ ተገዝታችኋልና የሰዎች ባሪያዎች አትሁኑ” (፩ና ቆሮ. ፯፡፳፫) የተባሉትን ክርስቲያኖችን በኃይል ለመግዛት፣ በጉልበት ለማጥፋት በራሳቸው የሚመኩ ሁሉ ወደ ልቡናቸው ሊመለሱ ይገባል። ይህን ባያደርጉም እግዚአብሔር የምሕረት አምላክ ነውና የልጆቹን ነፍስ ይጠብቃል፤ ከጠላቶቻቸውም እጅ ያድናቸዋል። “የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ከሁሉ ያድናቸዋል፤ አጥንቶቻቸውንም ይጠብቃል፤ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም” (መዝ. ፴፫፡፲፱) የተባለው የሚገጥማቸው መከራ ብዙ ቢሆንም እግዚአብሔር ከመከራ ስለሚያድናቸው ነው።
በሰዎች ላይ ክፋትን የሚያደርጉ ግን በቆፈሩት ጉድጓድ ይገባሉ። “ጉድጓድ የሚምስ ይወድቅበታል፤ ቅጥርን የሚያፈርስ ጊንጥ ትነድፈዋለች። ድንጋይ የሚፈነቅልም ይታመምበታል፤ እንጨት የሚፈልጥ ይጎዳበታል” (መክ. ፲፡፲፰) ተብሎ ተጽፏል። “ጉድጓድ ስትቆፍር አርቀህ አትቆፍረው የሚገባበት አይታወቅምና” ተብሎ የተነገረው ያለ ምክንያት አይደለም። በተንኮል በመነሣሣት በሰዎች ላይ ክፉ ለማድረግ የሚፈልጉ ሁሉ ወደ ሰላም መንገድ ሊመጡ ይገባል። እንደ ልቤ የተባለ ዳዊት “አሕዛብ በሠሩት ጉድጓድ ወደቁ፤ በዚያች በሸሸጓት ወጥመድም ራሳቸው ተጠመዱባት” (መዝ. ፱፡፲፭) እንዳለ ክፋት የሚጎዳው ራስን ነው። የዚህን ሁሉ ማጠቃለያ ነቢዩ ሆሴዕ ገባርያነ እኪት ለክፋታቸው እጥፍ ሆኖ የክፋታቸው ዋጋ እንደሚከፈላቸው “ነፋስን ዘርተዋል፤ ዐውሎ ነፋስንም ያጭዳሉ” (ሆሴ. ፰፡፯) በማለት ገልጾልናል። ስለሆነም ከክፋታችን ልንመለስ፣ እግረ ልቡናችንን ወደ ሰላም ልናቀና እና የእግዚአብሔርን ፊት ልንፈልግ ይገባናል።
በዘመናችን የተከሠተው የሰላም መደፍረስ ሊስተካከል የሚችለው ወደ ራስ በመመለስ ስለሆነ ነፍጥ አንሥተው ሕይወት እያጠፉ ያሉ አካላት በሃይማኖት አባቶች፣ በሰብአዊ መብት ጥበቃ ተቋማት እና በሰብአዊ መብት ተሟጋች ሲቪክ ማኅበራት የሚቀርቡ የሰላም ጥሪዎችን ሰምተው ወደ ሰላም መንገድ ሊመጡ ይገባል። በተለይም መንግሥት በአገር ላይ ሰላምን የማስፈን፣ የዜጎችን ሰላም እና ደኅንት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት እንደ መሆኑ መጠን ከጦርነት በመለስ ያሉ መፍትሔዎችን ሁሉ አሟጦ መጠቀም ይጠበቅበታል። በንጹሐን ላይ ጥቃት እንዳይፈጸም የመጠበቅ፣ የማስከበር እና የመከላከል ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎችም በእውነት እና በቅንነት አገራዊ ሰላም እንዲመጣ ሊሠሩ ይገባል።

አሸናፊ በሌለበት የወንድማማቾች ጦርነት የዕርቅና የሰላም መፍትሔዎችን ማዘግየት ትርፉ የንጹሐንን እልቂት ማባባስ ብቻ ነው። ይህን ደግሞ በአገራችን ከሁለት እና ሦስት ጊዜ በላይ በተግባር ተገልጦ አይተነዋል። ስለሆነም የሰላም በሮች ይከፈቱ፤ የጦርነት ጉሰማዎች ይርገቡ፣ ከጦርነት ትርፍ ለማግኘት የሚሠሩ አካላት አደብ ይግዙ። መንግሥት በይቅርባይነትና በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት ፈቃድ ያሳይ፤ ለሚጠየቁ ጥያቄዎች አግባብነት ያለው ምላሽ ይስጥ። መሪዎች ይህን ቢያደርጉ የዜጎቻቸውን ጩኸት ሰምተዋልና መንግሥታቸውን ማጽናት ይችላሉ። ይህን ባያደርጉ እግዚአብሔር የግፉዐን አምላክ ነውና የጥቃቱ ተጋላጭ የሆኑ ምስኪኖችን ጩኸታቸውን ሰምቶ ሊፈርድላቸው የታመነ ነው። ምንዱባን ሲጠሯቸው ያልሰሙና ልባቸውን እልኸኛ ያደረጉ ግን እነርሱም የሚጣሩበትና የሚጮኹበት ጊዜ ሲመጣ ሰሚ አያገኙምና ቆም ብለው ቢያስቡ መልካም ነው።