ክርስትና ከዘውግ ባሻገር የሆነ ማንነት

ክርስትና ከዘውግ ባሻገር የሆነ ማንነት

ክርስትና ከዘውግ ባሻገር የሆነ ማንነት

የሰው ልጅ ሁሉ ከአዳም የተገኘ የእግዚአብሔር አምላክ የእጅ ሥራ ነውና ከላይ በቀለም በቅርፅ ወዘተ ልዩነት ቢኖረው እንኳ የሚመሳሰልበት ከውስጥ የሆነ ሥነ-ሕይወታዊ አንድነት አለው፡፡ ይህም ተመሳሳይ ተፈጥሮአዊ እና ሥነ ልቡናዊ (Bio-Psychic Union) ውቁር እንዲኖረው አድርጓል፡፡ በማኅበራዊ ፍጡርነቱ በፈጠረው በማኅበራዊ መስተጋብሩ ምክንያት ደግሞ በሒደት ራሱን ካንድ የባህል መሠረት ካለው ማንነት ጋር ያዛምዳል፡፡ ይህ ልዩነት ደግሞ የተለያየ አስተሳሰብ/ እና የአረዳድ አድማስ እንዲኖረው ያደርገዋል፡፡ ክርስትና ለነፍሳችን መድኅን የሆነው የእውነትና የሕይወት መንገድ ጌታችን መድኃኒታችን ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ መሆኑን ያስተምራል፡፡ ክርስቲያንም ይህን እውነት ብቻ ይከተላል፡፡ ከአምልኮ መልስ ባለው ማኅበራዊ መስተጋብር ግን ብዝኃነትን ያከብራል፡፡
ክርስትና የባህል ማንነትን ሳይጨፈልቅና ባህል የፈጠረውን የቋንቋ እና የአኗኗር ዘይቤ ህላዌነት ካላጠፋሁ ሳይል ህያዊት ለሆነች የሰው ልጆች ነፍስ ዘላለማዊ ዕረፍት ለመስጠት ከእውነተኛው አምላክ በእግዚአብሔር የተበረከተ መለኮታዊ መገለጥ ነው፡፡ የሰው ልጆች ሁሉ የመጡበት የተለያየ ማኅበራዊ ዳራ ዓለምን ለማዳን ከድንግል ማርያም ሰው በሆነው በእግዚአብሔር ልጅ ከማመን እስካልከለከላቸው ድረስ ሰማያዊ ዜግነት ከሚያስገኘው ክርስትና የሚለያቸው አንዳች ነገር አይኖርም፡፡ ክርስቲያን ሆነው ከምእመናን ኅብረት ለመደመር የፈጠራቸውን ኋላም ሰው ሆኖ በደሙ ያዳናቸውን አምላክ ማመንና ለእርሱ መስከር እንጂ የባህል ማንነታቸውን መወርወር አያስፈልጋቸውም፡፡
በ፶፩ ዓ.ም. በቅዱስ ያዕቆብ ሊቀ መንበርነት በኢየሩሳሌም የጉባኤዎች ሁሉ መሠረት ተደርጎ በሚቆጠረው የመጀመሪያው የሐዋርያት ጉባኤ የተወሰነውም ይኸው እውነት ነው፡፡ ክርስትና አንዱ ብቻውን በባለቤትነት ሊይዘው የማይችል፣ የዘርና የባህል ማንነትን የተሻገረ፣ ሁሉም የእኔ የሚለው፣ ለሁሉም ሕይወትን የሚሰጥ መንገድ መሆኑን የተረጋገጠበት ታላቅ ጉባኤ ነበር፡፡ በኢየሩሳሌም ሳሉ ክርስትናን መርጠው አይሁድነትን ተሰናብተው የመጡት እና አሕዛብነት ንቀው ወደ ዕረፍት ውኃ የገቡት የትመጣቸው ወይም የኖሩበት የባህል ዳራ ወደ ፉክክርና ንትርክ ገፍቷቸው ነበር፡፡ ሕዝብን ከአሕዛብ አንድ ባረገው ጌታ እያመኑ የቀደመ ልዩነታቸውን ተከትለው ድንበር ሊያሠምሩ ፈለጉ፡፡ ጉባኤተኞቹ ግን የሰውን ሳይሆን የእግዚአብሔር ወልድን አሰረ ፍኖት የተከተሉት፣ ጌታ ነፍስን ከሥጋ፣ ሕዝብን ከአሕዛብ፣ ሰማይን ከምድር እንዳስታረቀ ምስክር የሆኑት ሐዋርያት ነበሩ፡፡ እናም አይሁዳዊውን እሳቤ ገሥጸው አሕዛባዊውን ልማድ ከርክመው ለቅዱሳን አንድ ጊዜ በተሰጠች በአንዲት ሃይማኖት ጥላ ሥር ተሰባስበው የሚኖሩበትን ሥርዓት ሠሩላቸው፡፡ ይህም በክርስትና ልጅና ባርያ እንደሌለ ሁሉም እኩል በልጅነት ጸጋ እንደከበረ እንዲታወቅና ነገድ ተኮር ዘውገኝነት እና ስብከት በክርስትና ቦታ እንዳይኖረው አድርጓል፡፡
ለሰማያዊ ዜግነት የሚሮጥ መንፈሳዊ ሯጭ ደመናን የማይሻገረው ምድራዊ ማንነት አይበልጥበትም፡፡ ቀራኒዮ ላይ የተከፈለው ዋጋ አይሁድ ከግሪክ ሳይለይ፣ ያለ አድልኦ ለሕዝብና ለአሕዛብ የተከፈለ
ከጉባኤው በኋላም ከአይሁድነት አዳኙን መሲሕ ወደ ማመን የመጡት ወገኖች አይሁዳዊነታቸው ሙሉ ለሙሉ ተገፍፎ አልወደቀም፡፡ ለግዝረትና ለሌሎች የኦሪት ሕጎች ያላቸው መቆርቆር በተወሰነ መጠን አብሯቸው ነበረ፡፡ ነገር ግን ለክርስትና ያላቸው ከፍተኛ ቀናዒነት ለምሥራቃዊዋ ኮከብ አንጾኪያ ነዋሪዎች ጎልቶ የታየ እውነት ነበረ፡፡ የመጀመሪያውን የሲኖዶስ ጉባኤ ውሳኔ ለመተግባር ያሳዩት መትጋት ከኦሪት ይልቅ ለሐዲስ ኪዳን ያላቸውን መንበርከክ ያመላክታል፡፡ ከአሕዛብ ወገን ወደ ክርስትና የገቡትንም ኅሩያን መሆናቸው፣ የመንገዱ ተከታይነታቸው ሕይወታቸውን በበጎ ለውጦታል፡፡
በኢየሩሳሌም አይሁድ በክርስቲያኖች ላይ በክፉ ተነሡባቸው፡፡ ክፋታቸው ከብዶ ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ የነበረውን ትጉሑን አገልጋይ እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግረው ገደሉ፡፡ በምድር በክርስትና ሰማዕታት ታሪክ ቀዳሚ ገጽ ላይ (ገጽ አንድ ላይ) የቀዳሚው ሰማዕተ ጽድቅ ታሪክ ተከተበ፡፡ በአርያም በሰማያዊ መዝገብ ላይ ስሙ በማይጠፋ ቀለም ተጻፈ፡፡ የአይሁድ ጭከና ክርስቲያኖችን አስደንግጦ የመጀመሪያውን ስደት ወለደ፡፡ ወደ አንጾኪያ ተሰደዱ፡፡ ሲሰደዱ ሐዋርያት በጉባኤው የሠሩላቸውን ሥርዐት ይዘው ነው የተሰደዱት፡፡
በአይሁድ አኗኗር ውስጥ ጎልቶ ይታይ የነበረው የአሕዛብን ልምድ የመጸየፍ ትምክህት ሰው ሁሉ በአርአያ ሥላሴ የተፈጠረ ነው በሚለው ክርስቲያናዊ የሥነ ሰብ አስተምህሮ ረግቧል፡፡ የሰውን ልጅ ሁሉ በእኩል ዐይን ልጄ ወዳጄ በሚለው በክርስቶስ ፍቅር ተሸንፏል፡፡ በአሕዛብ ዘንድ የነበረው አይሁድን የመናቅና የመጠራጠር አባዜም እርስ በእርሳችሁ ተዋደዱ በሚለው ክርስቶሳዊ ትምህርት ተገርቷል፡፡ ይህን ያስተዋሉ አንጾኪያውያን ደቀ መዛሙርቱን አይሁድና ግሪካዊ ማለት ትተው የክርስቶስ ወገን ናቸው ሲሉ ክርስቲያኖች በማለት ሰየሟቸው፡፡ ተግባራቸው ወገናቸውን ተናገረ፡፡ አዲሱ ዘውግ ያመነ የተጠመቀን ሁሉ የሚቀበል የቋንቋና ባህል፣ የድንበርና ዘር አጥር ያልከለለው የቀራንዮን ማኅተም የያዘ ሁሉ ውግንና የሚያገኝበት ኅብረት ነው፡፡ የክርስቶስ በሆነው መጠራት ታላቅ ጌጥ እንደ ሆነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ተናግሯል፡፡
የጌታ ደቀ መዛሙርት ክርስቶሳዊነታቸውን ብርቱ በሆነ ልሳን ዘወትር የሚመሰክረውን ክርስቲያን የተሰኘውን የወል ስያሜ መጀመሪያ ያገኙት የመጡበትን ማኅበረሰባዊ ማንነት አሽቀንጥሮ መጣል ሳያስፈልጋቸው ነገር ግን በጋራ ወይም የሁሉ ከሆነው ሕዝብን ከአሕዛብ፣ አይሁዳዊውን ከግሪካዊው ካስተሣሠረው ክርስቲያናዊ ማንነት በታች ማድረጋቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው፡፡ ደቀ መዛሙርት መጀመሪያ ክርስቲያኖች (የክርስቶስ ወገን) የተባሉት በአንጾኪያ ነው ብለናል፡፡ በኖሩበት፣ ከጌታ አንደበት በተማሩበት በኢየሩሳሌም ሳይሆን የተማሩትን በተግባር በኖሩበት አንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ፡፡ ይህ ልብ ላለው ኦርቶዶክሳዊ ሁሉ ክርስቲያን ተብሎ የክርስቶስ በሆነው ለመጠራት ክርስትናውን ዋነኛ መገለጫው አድርጎ መቀበል እና በዚያ መኖር እንዳለበት ይገነዘባል፡፡

እነኛ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አሕዛብን ወደ ክርስትና የሳቡት በቃልና በሕይወት በማስተማር ነው፡፡ ስለ ፍቅር ይናገራሉ ሰውን ሁሉ ያለ ልዩነት የወደደውን አምላክ አርአያ ተከትለው ፍቅራቸውን ለሁሉ ይገልጻሉ፡፡ ከዝሙት፣ ከአምላኮ ጣዖት፣ የሰውን ክብር ከሚያዋርዱ ተግባራት፣ በዘመኑ በሮማ ግዛት ገንኖ ከነበረውና ክቡሩን ሰው በኮሎዚየም አደባባይ ውስጥ ከሚያጨፋጭፈው እንስሳዊ ተግባር ሁሉ እጅግ የሚገርም ተዐቅቦ ነበራቸው፡፡ ይህ አኗኗራቸው ደመ ነፍሳዊነት በተንሰራፋበት አሕዛባዊው የማኅበረሰብ መስተጋብር ውስጥ እንደ ዕንቁ ተለይተው እንዲያበሩ አድርጓቸዋል፡፡ እንስሳዊነት የተጣባው ትርጉም የለሽ አኗኗር የሰለቻቸውና እንደ ሰው የክብር ሕይወት ኖረው መሞት የሚፈልጉ አሕዛብ ሁሉ ነገረ-ክርስትናን እና የክርስቲያኖችን አኗኗር በቅርብ መከታተል ቀጠሉ፡፡ ክርስትና ሰዎች ትርጉም ላለው እና ከፍ ላለ ግብ ሰብአዊነትን ተላብሰው፣ ትርጉም ያለው አኗኗር የሚኖሩበት ሕይወት መሆኑን ከቃላቸውና ከተግባራቸው ሲረዱ ወደ ክርስትና በብዛት መግባት ጀመሩ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ብዙ አሕዛብ ስመ ውልድና ያገኙትም በአንጾኪያ ነበር፡፡
በአንጾኪያ ያሉ አሕዛብ የጌታን ተከታዮችን ውሎ አዳር ዐዩ፤ በእርስ በእርስ መስተጋብራቸው ያለውን መዋደድ አስተዋሉ፡፡ በመካከላቸው ያለው ባህላዊ ልዩነት ሳያግዳቸው እንደ ወንድምና እኅት ሲተሳሰቡ ተመለከቱ፡፡ እናም ከነባር ነገዳዊ ማንነታቸው በላይ አዲስ ፍጥረት ላደረጋቸው ክርስትና የነበራቸው ልባዊ አቀባበል ክርስቲያን አስባላቸው፡፡ ለዚህ ነው ዘውግ ተኮር ሃይማኖታዊ ስብከት ፈጽሞ ክርስቲያናዊ መሆን የማይችለው፡፡ አንድ ክርስቲያን በክርስትናው ያገኘው መንፈሳዊ ኅብረት ሰው ሠራሽ ከሆነው ባህልና ቋንቋ ያገኘው ማንነት ከበለጠበት ከክርስትና ጎዳና ውጭ ሆኗል፡፡ በክርስትና ጀልባ ተሳፍረን የተሻገረርነውን ንዑስ ማንነታችንን ከፍ ያለ ጸጋ ከሚያሰጠው ክርስቲያናዊ ማንነታች ካስበለጥነው ክርስትናችን ከወዴት አለ?
ክርስቲያን የሚለው ስም ከአንድ የባህል ማንነት ለተቀዳ ወገን ብቻ የተሰጠ መጠሪያ አይደለም፤ ሆኖም ዐያውቅም፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ ለአመኑ፣ በስመ ሥላሴ ተጠምቀው አዲሱን ተፈጥሮ ገንዘብ ያደረጉ የሰው ልጆች ሁሉ የተጎናጸፉት ሰማያዊ እና ዘላለማዊ ጸጋ ነው፡፡ ይህ ከውኃና ከመንፈስ ዳግም በመወለድ የተገኘ ማንነት ሰዎች ቀድሞ ከነበራቸው ከየትኛውም ሰዋዊ ማንነት በላይ የከበረና ከሰማይ በታች የማይቀር ስምና ማንነት ነው፡፡
ከድሮም የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ክርስቲያን የሚለውን መጠሪያ ያገኙት ተናጠላዊው የባህል ወይም የነገድ ማንነታቸው የጋራ ለሆነው ክርስቲያናዊ ማንነታቸው ተሸንፎ እጅ ከሰጠ በኋላ ነው፡፡ ይህ ግሩም የሆነ በስሙ የመጠራት ጸጋ ዓለምን ሁሉ ያለ አድልኦ እንዲሁ በመውደድና ለሰው ዘር ሁሉ ሕይወቱን በመስጠት የተቤዠን ጌታ በተጓዘበት ፍኖት በመጓዝ የተገኘ ጸጋ ነው፡፡ ይህ ከነገድ ሳይሆን የነገድ ፈጣሪውን ሰውን በፈጠረ አምላክ ስም የመጠራት ክብር የጌታን መርሕ ለተከተሉ ደቀ መዛሙርት በአንጾኪያ ተሰጠ፡፡ እኛም በዚሁ በክርስቶስ ሥጋ እና ደም ያገኘነው ፍጹም አንድነት ከጎሳም ሆነ ከባህል ማንነታችን በላይ አድርገን አክብረን እንይዘው ዘንድ ክርስቲያኖች ተብለን በስሙ ተጠራን፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ክርስቲያንነት የማንነቶቻችን ሁሉ አክሊል መሆኑን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፤ ‹‹ሰው ማንነቱን ሲጠይቁት ‹እኔ ክርስቲያን ነኝ!› ብሎ ከመለሰ ሁሉን በአንድ ላይ ዐውጇል፡፡ ሀገሩን፣ ሙያውን፣ ቤተሰቡን፡፡…››