ወቅታዊ መልእክት
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ (ሀገር አቀፍ) የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከውጪና ከውስጥ የሚቃጡባትን ፈተናዎች በመቋቋም ከውጭ የሚቃጡባትን ፈተናዎች ሰማዕትነትን በሚቀበሉ ልጆቿ ምስክርነት፣ ምንፍቅናን በቃል የመጣውን በቃል በመጻሕፍት የመጣውን በመጻሕፍት በመመከት ሐዋርያዊ ቅብሎሿን ጠብቃ መሠረተ እምነቷን፣ ዶግማና ቀኖናዋን ቅዱስ ትውፊቷን ለትውልዱ እያስተማረች ጸንታ ቆይታለች፤ ወደ ፊትም ትኖራለች፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ በልዩ ልዩ ውጫዊ ፈተናዎች ዋጋ እየከፈለች ያለች ቢሆንም ከሁሉ የከፋው ግን ከክብር በላይ የላቀ ክብር ባጎናጸፈቻቸውና እረኛና ጠባቂ እንዲሆኑ ባሰማራቻቸው ልጆቿ በተደጋጋሚ እየገጠማት ያለው የቀኖና ጥሰት ነው። የጥር ፲፬ ጳጳሳት ሹመት፣ የትግራይ ሲኖዶስ፣ የቅባት ጳጳሳት ሹመት ፤ ፖለቲካን ተጠግቶ ቤተክርስቲያንን የማጥቃት ክፉ ግብር ሳያንሳት ፤በተገኘው አጋጣሚ ኹሉ የምንፍቅና ትምህርቶች የሚያስተላፉትን በዝምታ መመልከት እየበዛና በዚህም በጎቿን ከበረቷ ለማስነጠቅ ለሚሠሩ ሁሉ ተባባሪ በመሆን የሚኬድበት ርቀት ቤተክርስቲያኒቱን ዋጋ እያስከፈለ በመሆኑ በቃ ሊባል ይገባዋል፡፡ ለማሳያ ይሆን ዘንድ በአቡነ በርናባስ መባልእትንና ነገረ ክርስቶስን አስመልክቶ፤ በአቡነ ፊልጶስ እመቤታችንና ሥላሴን አስመልክቶ የተናገሩትን የስሕተት ትምህርቶች ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ የሊቃውንት ጉባኤ በወቅቱ ማስጠንቀቂያም ሆነ የእርምት እርምጃ ባለመውሰዳቸው ዛሬ በአቡነ ገብርኤል እመቤታችንንና ነገረ ክርስቶስን አስመልክቶ ያውም በዐውደ ምሕረት፣ እንዲሁም በዕለተ ስቅለት በተደረገ የአዳራሽ ጉባኤ ለተናገሩት የኑፋቄ ትምህርት አድርሶናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን ገፊ እንደሆነች እና ስለክርስቶስ የሚዘምሩትን እንደምታባርር እርሷም ስለ ክርስቶስ እንደማትዘምር በአደባባይ በጉባኤ ያለምንም ፍርሀት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የማኅበራት ምዝገባ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያን ጨምሮ የተለያዩ ሊቃነ ጳጳሳት በኑፋቄ ትምህርት ማስፋፋት ላይ የተሰማራውን “ፍኖተ ጽድቅ” ማኅበርን በገንዘቡ በሚሠራቸው የስቱዲዮ ግንባታ፣ የመጽሐፍ ኅትመት እና የመሳሰሉት ተግባራት በመማረክ የቤተክርስቲያንን ክብር አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ሂደት ላይ አንዳንድ መምህራን እና ማኅበራትም ተሳታፊ መሆናቸው በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡
ይህ እንዲሆን ምክንያት ከሆኑ ነገሮች መካከል የሚከተሉት በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው።
1. የአስተዳደር ብልሹነት የወለደው ዘርፈ ብዙ ችግር
በእኛ መረዳት አሁናዊው ፈተና እና ችግር ከውጪያዊው የዝግጅት ጥቃትና ፈተናም በላይ የበረታው የውስጥ ችግር ነው። ለዚህም ዋናውና አንደኛው የሁለንተናዊ ድካማችን ምክንያት የቤተ ክህነቱ ብልሹ አስተዳደር ነው።
አሁን ላይ ያለው የቤተ ክህነት አስተዳደር ዘመኑን በመዋጀት የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ተልዕኮ በማስፈፀም ነፍሳትን ለመንግሥተ እግዚአብሔር ለማብቃት የሚያስችል ቁመና እና ብቃት ላይ አይገኝም ። ሕግ አውጪ፣ ሕግ ፈፃሚ እና ሕግ ተርጓሚ አንድ አካል በመሆን፣ ተጠቅልሎ በተያዘ ሥልጣን ቤተ ክርስቲያኒቱ እጅ ተወርች ተቀፍድዳ ወደ ትውልዱ እንዳትደርስ እየተሠራ ይመስላል።
ቤተ ክርስቲያን በማይመጥናት ደካማ አስተዳደር ምክንያት ከተመሠረተችበት ነፍስ የማዳን መንፈሳዊ ተግባር ተናጥባለች። አስተዳደሩ ምእመናንን ለመንፈሳዊ ፍሬ ከማብቃት ይልቅ ለውድቀታቸው ምክንያት ሆኗል። በተለያዩ ጊዜያት ተጠንተው የቀረቡ ልዩ ልዩ የአስተዳደር ማሻሻያዎች እየተኮላሹ ጉዞው ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል:: በ ፳፻ወ፬ ዓ.ም ለሲኖዶስ የቀረበው የመሪ ዕቅድ ትግበራ ጥያቄ ፲፫ ዓመታት ሲገፋ ቆይቶ አሁንም ቦታ ተነፍጐታል። አስተዳደራዊ ለውጥ ጠልነቱ ተባብሶ ቀጥሏል። እኔ ብቻ በሚሉ ፣ ቤተ ክርስቲያን እንደ ግል ተቋማቸው በሚያዩ አካላት ተወራለች:: በሃይማኖት ችግር ፣ በቀኖና ጥሰት እና በሙስና ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው አካላት የተሻለ ሹመትና ሽልማት ይሰጣቸዋል፡፡
2. ለሊቃውንት ጉባኤ ትኩረት መነፈጉ
የሊቃውንት ጉባኤ ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው በመቅረቱ ፣ እንዲሁም ሊቃውንት ክብራቸው ባለመጠበቁ እና ከውሳኔ ሰጪነት ድርሻ በመገለላቸው ፤ ለስሑት ትምህርት በሚገባው መልኩ ምላሽ መስጠት የማይችል ሆኗል:: እንዲሁም በቤተክርስቲያኒቱ ስም ለሚታተሙና ለሚሰራጩ መጻሕፍትና ልዩ ልዩ የምስልና የድምፅ እንዲሁም የኅትመት ውጤቶች የመገምገምና ዕውቅና የመስጠት ሥልጣኑ ተነጥቋል። የአደረጃጀትና የመከላከል አቅሙ በመዳከሙ፤ በመዋቅሩ ውስጥ የተሰገሰጉ ሐሰተኛ መምህራን በአፍም በመጽሐፍም ስሁት ትምህርታቸውን በቤተ ክርስቲያኒቱ ዐውደ ምሕረት እያሰራጩ ይገኛሉ።
ትናንት አባቶች ያቆዩትን ሀብት መንዝሮ መጠቀም እንጂ የራሳቸውን አሻራ የማያኖሩ፣ ሀብት ንብረቷን ጠብቀው ከማቆየት ይልቅ ለግል መዝብረው ቀሪውን ለዘራፊ አሳልፈው የሰጡ ከመንፈሳዊ ክብር በጐደሉ፣ በሥጋ ሐሳብ ጨርሶውኑ በተወሰዱ፣ ምግባር በጎደላቸው ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ሊቃነ ጳጳሳት ድረስ ባሉ አገልጋዮች እየተፈተነች ትገኛለች።
ያለ ዋጋ ከሚሰጠው መንፈሳዊ ሹመት ጀምሮ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚጎዳ እኩይ ተግባር በእጅ መንሻ የሚፈጽሙ አካላት በሁሉም መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችበትን ዓላማ እንዳታሳካ ሳንካ ሆነውባታል።
ስንዱዋ እመቤት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሕግ እና በሥርዓት ዝግጅቷ እንከን አይወጣላትም። ነገር ግን ከሕግና ከሥርዓት ባፈነገጡ፣ ሐሰተኛ ትምህርት በሚያሰራጩ እና ኢ-ክርስቲያናዊ በሆነ ሕይወት ወስጥ በሚመላለሱ በተለይ በሁሉም መዋቅር ወስጥ በሚገኙ አገልጋይ ሠራተኞች ላይ ተግባራዊ ርምጃ አለመወሰዱ ለምእመናን ተስፋ መቁረጥ እና ፍልሰት ምክንያት ሆኗል።
3. በሕግ ከተሰጣቸው መብት ውጪ በማስተማር የሚሰማሩ ማኅበራትን በሕግ አግባብ ወደ መስመር አለማስገባት
የሰሞኑ ስሁት ትምህርት በሕጋዊ ዕውቅና ስም የሚንቀሳቀሱ ማኅበራት እኩይ ተግባር ከትናንት የቀጠለ የብልሹ አስተዳደር መገለጫ ነው። የማኅበራት አስተዳደር ደንብ ፀድቆ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ደንቡ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስረጃ በማስደገፍ የማሻሻያ ሐሳብ ብናቀርብም ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። በመሆኑም የፈራነው ደርሶ ፤ ደንቡን ለማስፈፀም የተቀመጠው የማኅበራት ምዝገባ ክትትል እና ቁጥጥር መምሪያ፤ በማኅበራት አስተዳደር ደንብ አንቀጽ ፲ ላይ የማኅበራት ዓለማ “ለትምህርት ተጠሪ ተቋማት ድጋፍ መስጠት ነው” በሚል የተደነገገ ቢሆንም እንደ ‹‹ፍኖተ ጽድቅ›› ያለ ማኅበር ድጋፍ ሰጪ ሳይሆን ፈፃሚ ሆኖ፣ ማኅበሩ ከተመሠረተበት ዓላማ ውጭ ትምህርተ ወንጌልን በአዳራሽ ውስጥ ሲሰጥ፤ በሚዲያ ትምህርት ሲያስተላልፍ አልፎ ተርፎ የቤተ ክርስቲያን መዝሙሮቿን ከሥርዓቷና ከቀኖናዋ ውጪ በሆነ ሁኔታ በሚዲያ እያቀናበረ ሲያስተላልፍ ተገቢው አስተዳደራዊም ሆነ ቀኖናዊ እርምጃ እንዲወሰድ ከማድረግ ይልቅ በማኅበርነት በመመዝገብ እንዲሁም በደንቡ የተሰጠውን የመቆጣጠር ሓላፊነት የማኅበራት ማደራጃ ምዝገባ ክትትል እና ቁጥጥር መምሪያ ባለመወጣቱ ዛሬ ለደረሰው ስሑት ትምህርት ዝግጅትና ስርጭት አብቅቶናል፡፡
ይኽ ማኅበር ከኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተህምሮ ውጪ ስሑት ትምህርት የሚሰጥበት ተቋም እንደሆነ በተጨባጭ እየታወቀ እና በአካል ቀርበው አረጋግጠው እንኳን ቅዱስ ፓትርያርኩን በዚያ ሥፍራ እንዲገኙ በማድረግ ቤተ ክርስቲያንን አሳልፈው የሰጡ የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች መኖራቸው የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡
በመሆኑም ከዚህ በታች የዘረዘርናቸው ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ተገቢው ትኩረት እንደሚሰጣቸው እና የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው እናምናለን።
1. የሊቀ ጳጳሱ ኢ-ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ቀኖናዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት ብናምንም በሚገባ እና በትኩረት ጉዳዩ እንዲታይና መፍትሔ እንዲሰጠው፡፡ እንዲሁም በተመሳሳይም ስሑት ትምህርቶችን የሚያስተምሩ እና ያስተማሩ ሌሎች ጳጳሳት እና መምህራን ጉዳይም አብሮ እንዲታይ፣ ይኽን አጋጣሚ ተጠቅሞ የሊቃውንት ጉባኤም በስሑት አስተምህሮዎች ላይ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ቢደረግ፡፡
2. ሓላፊነቱን በአግባቡ ያልተወጣው የማኅበራት ምዝገባና ክትትል እና ቁጥጥር መምሪያ ከሊቀ ጳጳሱ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ሓላፊዎች እንዲጠየቁ፡፡
3. የማኅበራት ምዝገባ ክትትልና ቁጥጥር መምሪያ የዕውቅና ሰርተፊኬት ከመቸርቸር ወጥቶ፣ ደንቡና አሠራሩን ዳግመኛ በመፈተሽ፣ የዕውቅና አመዘጋገብ፣ ክትትልና ቁጥጥር ሒደቱም ንጥር ያለ እና መስፈርቶች የወጡለት እንዲሆን፡፡
4. ቅዱስ ፓትርያርኩን በማሳሳት ” ፍኖተ ጽድቅ ” በተባለው ማኅበር ዝግጅት ላይ እንዲገኙ ያደረጉ የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ሓላፊና የፖትርያርኩ የፕሮቶኰል ሹም እንዲጠየቁ፡፡
5. ‹‹ፍኖተ ጽድቅ›› የተሰኘው ማኅበር በቤተክርስቲያን ላይ እያደረሰ ያለውን የተሐድሶ ኑፋቄ ትምህርት ባለማረሙ ምክንያት ማኅበሩ የምዝገባ ፈቃዱ ተሰርዞ ባስተላለፈው ትምህርቶች በቀኖና እንዲጠየቅ እና በዚሁ አጋጣሚ ከመምህራን እስከ ሊቃነ ጳጳሳት “ፍኖተ ጽድቅ” ከተባለ ማኅበር ጋር የጀመሩት በነዋይ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት በአስቸኳይ እንዲቆም እንዲደረግ። እንዲሁም በቤተ ክህነቱ የበላይ ሓላፊዎች በኩል እናት ቤተ ክርስቲያናችን አንዳች ሳይጎድልባት ባልተገባ መሻት ከባለ ጸጋ እጅ ለማኝ በማድረግ ቅድስት ቤተክርስቲያንን የማዋረድ እና አሳልፎ የመስጠት እኩይ ተግባር እንዲቆም።
6. የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎቷን እንዳታሰፋ እጅ ተወርች ቀፍድዶ የያዛት ደካማ፣ ብልሹ አስተዳደር እንዲስተካከል በልጅነት መንፈስ በተደጋጋሚ የችግሮቹን ማሳያና መፍትሔዎቹን፣ ሥርዓተ መዋቅርን በመጠበቅ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ድረስ ቢያቀርብም ተጨበጭ ምላሽ አልተሰጠውም ። ይህም ጉዳይ ከግንዛቤ ገብቶ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል።
ነገር ግን አሁንም እንደ ቀድሞው ተሸፋፍኖ የሚታለፍ እና መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ታላቋን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስትያን የማይመጥነው ብልሹ አስተዳደር የሚቀጥል ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ሊቃውንት፣ ምእመናን፣ እና የሰንበት ት/ቤት አባላት ጋር በመሆን የምንረከባትን እና ለትውልድ የምናሰረክባትን እናት ቤተ ክርስቲያን የምንታደግበትን መንገድ የምንከተል መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለፅ እንወዳለን።
የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት
ሚያዚያ ፳፩ቀን ፳፻፲ወ፯ ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
የሰ/ት/ቤቶች አንድነት የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን ቤተሰብ ይሁኑ!
(የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት)
Youtube
https://www.youtube.com/@eotc-gssu
https://www.facebook.com/gssu.eotc
Telegram
https://t.me/eotcgssu21
Tiktok
@eotc_gssu