የትግራይ ቤተ ክህነት እንቅስቃሴ ለተሐድሶ መናፍቃን ሰርግና ምላሽ

የትግራይ ቤተ ክህነት እንቅስቃሴ ለተሐድሶ መናፍቃን ሰርግና ምላሽ

የትግራይ ቤተ ክህነት እንቅስቃሴ ለተሐድሶ መናፍቃን ሰርግና ምላሽ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ካበረክተችው አስተዋጽኦ አንዱ የሀገር አንድነት ምክንያት ሆና መኖሯ ነው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያን ማዳከም የሚፈልጉ ኃይሎች ሁሉ መጀመሪያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ማዳከምን ዋና አጀንዳቸው የሚያደርጉት። በተለይም ከ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ሚስዮናውያን ቤተ ክርስቲያንን በማጥፋት ኢትዮጵያን መረከብ አጀንዳቸው ካደረጉ ከአራት መቶ በላይ ዘመናትን አስቈጥረዋል። በዘህ ጊዜ ውስጥ ራሳቸውን ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት የሚመኙትን ያህል ምናልባትም ከዚያ በላይ ቤተ ክርስቲያንን የሚጠሉ “ኢትዮጵያውያን ፈረንጆችን” ማፍራት ችለዋል። እነዚህ ከውጪ የሚላክላቸውን አጀንዳና ፍርፋሪ ተቀብለው በውስጥ ሆነው ቤተ ክርስቲያንን ያጠቃሉ።

የምዕራባውያን አንዱ ተንኮል ኢትዮጵያን ለመበታተን ይጠቅመናል ያሉትን አጀንዳ አቀብለው ዕቅዳቸው መሥራት ከጀመረ ወዲህ ቤተ ክርስቲያንንም ሀገሪቱ በቆመችበት የርእዮተ ዓለም ትርክት (የጎሣ ፌደራሊዝም) ለመከፋፈል ቀጣይ ዓላማቸውን ማምጣታቸው ነው። እንዲህ ዐይነት ተግባር ዛሬ በራሳችን ወንድሞችና እኅቶች የሚከወን ሆኗል። በክልል ደረጃ ቤተ ክህነት የማቋቋም (የፌደራልና የክልል ቤተ ክህነት ለመፍጠር) እንቅስቃሴም የዚህ ክፍፍል ዋና መሣሪያ እንደሚሆን ታምኖበት የመጣ አጀንዳ ነው። ይህን ዓላማ የሚደግፉ ብቻ ሳይሆን የርእዮተ ዓለማቸው አካል ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸውን ስንመለከት ደግም ጉዳዩ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደ ሆነ እንረዳዋለን።

የትግራይ ቤተ ክህነት መነሻ

የትግራይ ቤተ ክህነት እንቅስቃሴ አጀማመሩ ከጎሣ ፖለቲካ ንቅናቄ ጋር የተያያዘ ነው። በትግራይ ክልል ያሉ አብያተ ክርስቲያንን ከሌላው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ገንጥሎ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ የማድረጉ ፍላጎት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመን ብዙ ጊዜ ተነሥቶ እሳቸውን ጨምሮ በቤተ ክህነቱ መዋቅር ውስጥ ያሉ አባቶች በመቃወማቸው ሳይፈጸም እንደቆየ ይነገራል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ውስጥ ውስጡን ሥራዎች መሠራታቸው ግን አልቀረም። አሁን ጉዳዩ ጎላ ብሎ መሰማት የጀመረው የኦሮምያ ቤተ ክህነት የሚባለው አጀንዳ በስፋት መነሣት ከጀመረ ወዲህ ነው። ከሰሜኑ የሀገራችን ጦርነት በፊት የሚመራው ፖለቲካውን በሚዘውሩ አክቲቪዝቶችና ቤተ ክህነት ውስጥ ባሉ አንዳንድ ግለሰቦች ነበር። እንቅስቃሴው የክልሉን መገንጠል በሚደግፉ ፖለቲከኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎች እንዲሁም በቤተ ክህነቱ ውስጥ ልንባረርና ቦታ ልናጣ እንችላለን በሚሉ ሰዎች ይደገፋል። ከዚህ እንቅስቃሴ ጋር ስማቸው ተደጋግሞ የሚነሡት ግለሰቦች፡- መሐሪ ዮሐንስ፣ አሉላ ሰሎሞን፣ ገብረ ኪዳን ደስታ፣ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል፣ “አባ” ሳሙኤል ወልደ ሰላማና አባ ገብረ መድኅን ገብረ ጊዮርጊስ ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የሌላቸውና ከቤተ ክህነት ጋር ምንም ዐይነት ግንኙነት የሌላቸው ግለሰቦች ናቸው።

መሐሪ ዮሐንስ “የትግራይ ሐርነት ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ” የተባለ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁሟል። የፓርቲው ርእዮተ ዓለም ትግራይን ሀገር ማድረግ የሚል ነበር። ይህን እንቅስቃሴ የሚያግዝ ማንኛውንም ሐሳብ ይደግፋል። ትግራይን ለመገንጠል ራሱን የቻለ የክልል ቤተ ክህነት ዕውን ማድረግ ለፓርቲው ርእዮት አጋዥ ይሆናል የሚል ዓላማ አንግቦ የሚሠራ ነው። ገብረ ኪዳን ደስታ ደግሞ በተሐድሶ መናፍቃን በተደጋጋሚ የተሐድሶ ቀንዲል ተደርጎ እየተጠቀሰ ያለውን የደቂቀ እስጢፋኖስ እንቅስቃሴ በማቀጣጠል ራሱን የቻለ ማኅበር እንዲኖር ይሠራል። የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት “የእነ ቄስ በላይን ውሳኔ መቶ ፐርሰንት እደግፈዋለሁ፤ ትግራይም የራሷ ሲኖዶስ ሊኖራት ይገባል” በማለት ተደጋጋሚ ማብራሪያዎችን ይሰጥ ነበር። ከሕወሓት ምሥረታ ጀምሮ ቤተ ክህነቱን ፖለቲካ በማስታጠቅና በማሠልጠን የትግራይ ቤተ ክህነትን በማዋለድ ትልቅ አስተዋጽዖ የነበረው ሰው ሲሆን ከቅርብ ጊዜያት በፊት አርፏል።

ከጦርነቱ በፊት በእንቅስቃሴው ደጋፊዎች ተዘጋጅቶ የነበረው ሎጎ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የትግራይ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት” የሚል የነበረ ሲሆን በወቅቱ የክልሉ መንግሥት እንቅስቃሴውን በመደገፍ ረገድ ያሳየው ነገር አልነበረም። መዋቅራዊ ድጋፉንም በተመለከተ የትግራይ ቤተ ክህነት መመሥረት የሚለው አጀንዳ ከላይ ከተጠቀሱት ግለሰቦችና እነርሱ ካደራጇቸው ቡድኖች ውጪ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የሚደገፍ አልነበረም። ነገር ግን በወቅቱም ቢሆን በትግራይ ክልል የነበሩ ሊቃነ ጳጳሳትና የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ለጉዳዩ ስስ ልብ እንደ ነበራቸው ከአሁኑ እንቅስቃሴያቸው መረዳት ይቻላል። ከጦርነቱ በኋላ ጉዳዩን በበላይነት የመሩት ጳጳሳቱ ራሳቸው ሆኑ። ጉዳዩንም ቤተ ክርስቲያን ጦርነቱን ባለማውገዟ ምክንያት የመጣ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ ክሥተት አድርገው ማቅረብ ተያያዙት። ጉዳዩ ከዚህ ጊዜ በፊት ተነሥቶ የማያውቅና ያልታሰበበት በማስመሰል ያቀርቡት ጀመር። በዚህ ቅስቀሳም የሕግና የሥርዓት ምንጭ በነበረችው አክሱም ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እስከ መፈጸም ድረስ ድጋፍ አሰባስበውበታል።

ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሢመቱም ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ እስከሚመቻች ድረስ ሲጠበቅ የቆየ እንጂ ዐዲስ ውሳኔም፣ ዐዲስ ክስተትም አይደለም። በ፳፻፲፪ ዓ.ም ፲፰ አባላት ያሉት የትግራይ ቤተ ክህነት እንቅስቃሴን የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲሠራ ነበር። የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም ከቤተ ክህነትና ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ሰዎችን ቃሌ ላይ ሰብስበው ነበር። በቤተ ክህነቱ በኩል ባሉት ሰዎች ከቅዳሴ ውጪ ያሉት ምስክር ቤቶች ከክልሉ ውጪ ስለሆኑ የምስክር ጉባኤ ቤቶች በክልሉ መከፈት አለባቸው የሚል አጀንዳ ተነሥቶ ሊሠራበት እንደሚገባ ተወስኗል። ሌላኛው የተነሣው አሳብ አሁን ባለው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የምንፈልገውን አጀንዳ ማስወሰን አንችልም። ምክንያቱም ከውጪ ያሉት አባቶች ከውስጡ ካሉት ጋር ሲዋሐዱ በቁጥር ከእኛ ክልል ጳጳሳት ስለሚበልጡ በድምፅ ብልጫ ይበልጡናል። ስለሆነም አንድ ጊዜ የራሳችን ቤተ ክህነት አቋቁመን አዳዲስ ጳጳሳትን መሾም አለብን። ከዚያ በኋላ ተገንጥለን ብንቀርም እንቀጥላለን፤ ተመልሰን ብንዋሐድም የምንፈልገውን ቁጥራችን ብዙ ስለሚሆን የምንፈልገውን አጀንዳ ለማስወሰን አንቸገርም የሚል አሳብ ተነሥቶ በተሰብሳቢዎች ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት የጸደቀውና ሲሠራበት የነበረው ከሦስት ዓመታት በፊት መሆኑን የሚያስረዳ ነው።

በወቅቱም የዚህ እንቅስቃሴ አስኳል አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤልና የአሲራ መቲራ ገዳም አስተዳዳሪ አባ ገብረ መድኅን ገብረ ጊዮርጊስ ነበሩ። ሁሉም አካላት በእነርሱ መሪነትና አቅጣጫ ሰጪነት ነበር የሚንቀሳቀሱት። አባ ሠረቀ አክሱም አካባቢ ለዚሁ እንቅስቃሴ ያደራጇቸው ሰዎች ነበሯቸው። አዲስ አበባም በተለያዩ ምክንያቶች ልንባረር እንችላለን ብለው የሚፈሩና የክልል ቤተ ክህነት ቢቋቋም ቦታ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ በአባ ሠረቀ አስተባባሪነት የእንቅስቃሴው ደጋፊ የሆኑ ካህናት ነበሩ። ከዚህም በተጨማሪ አባ ሠረቀ ሲያትል የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆችን ተገፍተናል አግዙን በሚል በተደጋጋሚ በስካይፒ ይሰበስቡ ነበር። በአጠቃላይ ሲታይ ይህን እንቅስቃሴ ከጀርባ ሆነው የሚዘውሩት አካላት የተሐድሶ መናፍቃን ድርጅቶችና በቅዱስ ሲኖዶስ ውግዘት ከቤተ ክርስቲያን የተለዩ አካላት ጭምር ነበሩ።

፩. ማኅበረ ሰላማ

በቀድሞው ወልደ ሥላሴ አስገዶም የሚመራ የተሐድሶ ማኅበር ነው። ማኅበሩ በ፳፻፬ ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከተወገዙት ማኅበራት ውስጥ አንዱ ሲሆን ወልደ ሥላሴ አስገዶምም በዚያኑ ጊዜ ከተወገዙት ፲፮ ግለሰቦች አንዱ ነው። ወልደ ሥላሴ አስገዶም ኤርትራ ሐጎስ አስገዶም በመባል የሚጠራ ሲሆን የሚታወቀውም በጠንቋይነቱ ነው። በ፳፻፬ ዓ.ም ከተወገዘ በኋላ ወደ እስራኤል አገር ሔዶ ጥቂት ጊዜ የተደበቀ ሲሆን ስሙን አባ ሳሙኤል ወልደ ሰላማ ብሎ በመቀየር ምንኵስና ተቀብሏል። በ፳፻፲፪ ዓ.ም ደግሞ አባ ጴጥሮስ ብሎ ስሙን በመቀየር መቀሌ ገብቶ በማኅበረ ሰላማ ስም የሕፃናት መርጃ ማእከል አቋቁሞ ሲሠራ ቆይቷል። መርጃ ማእከሉ በመንግሥት ተቀባይነት አግኝቷል። በመርጃ ማእከሉ ውስጥ ያሉት ብዙዎቹ የእንቅስቃሴው ደጋፊዎች እንደሆኑ ይታያል። ነገር ግን ማኅበረ ሰላማ እንደ ማኅበር የተወገዘ እና በሕዝብ ክርስቲያኑ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ እንቅስቃሴውን ከጀርባ ሆኖ እንጂ ፊት ለፊት ለመምራት አይችልም። እንቅስቃሴው ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የማኅበሩ ሚና ቀላል አይደለም።

፪. ማኅበረ ደቂቀ እስጢፋኖስ

የዚህ ቡድን አንቀሳቃሽ ገብረ ኪዳን ደስታ ነበር። የአሲራ መቲራ ገዳም አስተዳዳሪ አባ ገብረ መድኅንም የዚህ እንቅስቃሴ አካል ናቸው። የትግራይ ቤተ ክህነት የሚባለው እንቅስቃሴ ዋነኛ መሪ ይህ ቡድን ነው። ማኅበሩ ከተሐድሶ እንቅስቃሴ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ማኅበር ነው። ገብረ ኪዳን ደስታ ደግሞ የኦሮሚያ ቤተ ክህነትን እንቅስቃሴ እንደሚደግፍና ትግራይም የራሷ ቤተ ክህነት እንደሚኖራት በሚዲያ ሲናገር የነበረ ሰው ነው። ስለዚህ ከዚህ ማኅበር ዓላማዎች አንዱ የትግራይ ቤተ ክህነት እንቅስቃሴን መደገፍ ነው። በእርግጥ ማኅበሩ በገብረ ኪዳን ደስታ የተቋቋመ ነው ቢባልም ከቤተ ክህነት ሰዎችም እንዳሉበት የእነ አባ ገብረ መድኅን መኖር ሁነኛ ማሳያ ነው። ደቂቀ እስጢፋኖስ በብዙ የተሐድሶ ቡድኖች የእንቅስቃሴያቸው መነሻና አስኳል ተደርገው መጠቀስ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። በተለይም የጌታቸው ኃይሌ ደቂቀ እስጢፋኖስ ከታተመ በኋላ ብዙ ተሐድሶ መናፍቃን ደቂቀ እስጢፋኖስን በኢትዮጵያ የተሐድሶ እንቅስቃሴ መሥራች አድርገው ሲናገሩ ይሰማል። ተሐድሶ መናፍቃን ደግሞ ባልበላው ጭሬ አፈሰዋለሁ በሚል ፈሊጥ እንቅስቃሴውን ይደግፉታል።

፫. ያሬዳዊት ቤተ ክርስቲያን ጽዋ ማኅበር/ የቅዱስ ያሬድ የጽዋ ማኅበር

ማኅበሩ ሲመሠረት በቀና መንፈስ በተነሣሡ ኦርቶዶክሳውያን የተቋቋመ ነበር። አብዛኛዎቹ አባላቱ በትግርኛ የተተረጎመው መጽሐፍ ቅዱስ እንዳይሠራጭ ሲታገሉ የነበሩ ናቸው። አሁን ግን የትግራይ ቤተ ክህነት ለማቋቋም ለሚሠሩት አካላት ቀኝ እጅ ሆነው የሚያገለግሉ ግለሰቦችም ገብተውበታል። የትግራይን መገንጠል የሚያራምዱት ፖለቲከኞች ደግሞ ይህን መሰል እንቅስቃሴ ስለሚፈልጉት ይደግፏቸዋል። ስለሆነም ፖለቲከኞችና የትግራይ ቤተ ክህነት ለማቋቋም የሚሹ አካላት ይኸኛውን ማኅበር ተጠቅመው ወደ ሕዝብ ለመድረስ እየሠሩ ነው። እንቅስቃሴው በተቻለ መጠን በኅቡዕ እየተካሔደ ቆይቶ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረውን ጦርነት መነሻ በማድረግ የቀደመ ተምኔታቸውን በተገፍተናል ስሜት ለመፈጸም በቅተዋል። ከሦስት ዓመታት በፊት ይህን እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያንን የሚከፍል አደገኛ ሴራ ስለሆነ በጥንቃቄ እንዲታይ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ሲሰጥ የነበረው ሐሳብ ሰሚ አላገኘም። በዚህም ምክንያት እነዚህ አካላት የነበረና የቆየ ፍላጎታቸውን ዐዲስ ወቅታዊ ምክንያት በመጥቀስ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ በጵጵስና ደረጃ ባሉ አባቶችን ሳይቀር የእንቅስቃሴያቸው አካል ማድረግና ቤተ ክርስቲያንን የማዳከም ተልእኳቸውን ማሳካት ችለዋል።

በቤተ ክህነቱ በኩል እንቅስቃሴው ዝም ተብሎ በመታየቱ፡-

  • የቤተ ክርስቲያንን አስተዳዳራዊ መዋቅር ወደ መክፈልና ምእመናንን ወደ መበተን ደረጃ ደርሷል።
  • በአባቶች መካከል ከፍተኛ የሆነ መከፋፈልን በመፍጠር የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚፈታተን ሆኗል።
  • በክልሉ የሚገኙ የእንቅስቃሴው ደጋፊ ያልሆኑ አብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት ከፍተኛ የሆነ ስጋት ላይ ወድቀዋል።
  • የእንቅስቃሴው ደጋፊ አይደላችሁም ተብለው የሚታሰቡ አካባቢዎች የሚገኙ አብያተ ክርስቲያን የመዘጋት ዕዳ ሊያጋጥማቸው ይችላል።
  • በክልሉ ሕዝብ መካከል ከፍተኛ የእርስ በእርስ ግጭት ሊያስነሣ ይችላል።
  • ከሌሎች ክልሎች ጋር የሚያጋጩ እንቅስቃሴዎች በሚያደርጉ የሴራ ፖለቲከኞች ምክንያት የክልሉ ሕዝብ ከሌሎች ክልሎች ሕዝቦች ጋር ቂምና በቀል ውስጥ ይገኛል።
  • ምናልባትም ከፍተኛ የሆነ ሀገራዊ ቀውስም ሊያስከትል ይችላል።

ስለሆነም፡-

  • ጉዳዩን ከውግዘት ባለፈ በሰከነ መንገድ መያዝና መከታተል ይፈልጋል።
  • የተሐድሶ መናፍቃን እና የፖለቲከኞች እጅ ከዚህ እንቅስቃሴ የሚወጣበት አግባብ ላይ ተግቶ መሥራት
  • በወቅታዊ ኩርፊያ፣ በብዙኀን ግፊት በየዋህነት እንቅስቃሴውን የሚደግፉ አካላትን ማስረዳት የሚቻልበትን ስልት ነድፎ መሥራት
  • በመዋቅርም ይሁን መደበኛ ባልሆነ መልኩ የእንቅስቃሴውን አደገኛነት እና ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያመጣውን አደጋ በሚገባ ማሳወቅ
  • ቅዱስ ሲኖዶስ ከውግዘት ባሻገር አስፈላጊ ሆኑ ሌሎች ሥራዎችን በጥናት ላይ በመመሥረት ከዘላቂ ክፍፍል ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ
  • የክልሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ከመግባት በመቆጠብም ሆነ ለውይይት ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ መጠየቅ ይገባል እንላለን።