የነገረ ሰብእ ትምህርት ጉድለት የወለደው አገራዊ ቀውስ
በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ነገረ ሰብእ (አንትሮፖሎጂ) አንደኛው የጥናት ዘርፍ ነው። ይህ የጥናት ዘርፍ ስለ ሰው አፈጣጠርና ክብር የሚናገር ነው። ስለ ፍጥረት አመጣጥ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው መጽሐፍ ኦሪት ዘፍጥረት ሰው በእግዚአብሔር አርአያና ምሳሌ የተፈጠረ ክቡር ፍጡር መሆኑን ይነግረናል። ሊቀ ነቢያት ሙሴ ስለ አፈጣጠሩ ሲተርክልንም “እግዚአብሔርም አለ፤ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፣ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ፡ እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍ. ፩፡፳፮-፳፯) ይለናል። የሚወዱትን እንግዳ ሁሉን አዘጋጅቶ እንደሚጠሩት እግዚአብሔርም ለሰው የሚያስፈልገውን ሁሉ አስቀድሞ ካዘጋጀ በኋላ ሰውን የፍጥረት መደምደሚያና መካተቻ አድርጎ ፈጥሮታል። እግዚአብሔር ሌሎች ፍጥረታትን በኀልዮ (በማሰብ) እና በነቢብ (በመናገር) ሲፈጥራቸው ሰውን ግን በእጁ ሠርቶታል። “እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በፊቱም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ” (ዘፍ. ፪፡፯) የተባለው ለዚህ ነው። ስለሆነም ሰው ክብሩና ልእልናው ከፍ ያለ ነው።
ማኅበረሰብዊ፣ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ቀውሶች ሁሉ የሚመነጩት የሰውን ልጅ ክብር ካለመረዳትና ከመዘንጋት ነው። ሰው የተፈጠረው በዚህ ዓለም ኖሮ ለማለፍ ብቻ አይደለም። የፈጠረውን አምላክ ስሙን ለመቀደስ፣ ክብሩንም ለመውረስ ነው። ሰው የሚኖርበት ይህ ዓለም ጊዜያዊ መቆያው እንጂ መጨረሻ መዳረሻው አይደለም። በተለይም ከሞት በኋላ ከሚኖረው ዘለዓለማዊ ሕይወት አንጻር የዚህ ዓለም ቆይታው ምንም ነው ማለት ይቻላል። ፍጥረታትን በሙሉ ሰውን ጨምሮ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣው እግዚአብሔር ነው። ስለሆነም በፍጥረታት ላይ ፍጹም ሥልጣን ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። የፍጥረታት ገዢ ሆኖ የተሾመው ሰው ሌሎች ፍጥረታትን ሊጠቀምባቸው፣ ሊገዛቸውና ሊጠብቃቸው የውክልና ሥልጣን ተሰጥቶታል። ሥልጣኑ ግን ህልውናቸውን እስከ ማጥፋት የሚደርስ ፍጹም ሥልጣን አይደለም። “በምድር ላይ ያለው ሀብት ሁሉ የጋራችን ነው” የሚለው አባባልም መሠረቱ ፍጥረት የተፈጠረው ለሰው በመሆኑ ነው። ስለሆነም ሰው የሌሎች ፍጥረታት ገዢ እንጂ የራሱ የሰው ልጅ ገዢ እንዳልሆነ ሊያውቅ ይገባል።
ሰው በእግዚአብሔር አርአያ የተፈጠረ፣ የፍጥረታት ዘውድና ነፃነት ያለው ፍጡር ነው። እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው ከነፃ ፈቃድ ጋር ነው። ነፃ ፈቃዱን ተጠቅሞ እሳትን ወይም ውኃን፣ ሞትን ወይም ሕይወትን፣ ብርሃንን ወይም ጨለማን፣ እግዚአብሔርን ወይም ጣዖትን ሊመርጥ ይችላል። ሰው ነፃ ፈቃዱን ተጠቅሞ የሚያደርገውን እግዚአብሔር አይጋፋውም። ወደ መልካም እንዲሔድ በመጻሕፍትና በመምህራን ይመክረዋል፤ ወደ መልካም መንገድ ይመራዋል። ወደ ክፋት መንገድ ሲሔድ ይታገሠዋል፤ ይገሥጸዋል። ለባዊት፣ ነባቢትና ሕያዊት ነፍስ ሰጥቶታልና በነፃ ፈቃዱ የመረጠውን የምርጫውን ውጤት በጎም ሆነ ክፉ ይሰጠዋል፤ ማለትም እንደ ሥራው ይከፍለዋል። ሰው ግን የእግዚአብሔርን ፈቃድና የእግዚአብሔርን ትዕግሥት በመቀላቀል ወይም የእግዚአብሔርን ትዕግሥት ቸል በማለት ከሕይወት ይልቅ ሞትን ሲመርጥ ይታያል። ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ክብር ያቃልላል። አዳም በፍጥረታት ላይ ሁሉ ገዢ ሆኖ ሳለ የእባብን የአምላክ ትሆናለህ ምክር በመስማት አምላክ ለመሆን በመሻት ዕፀ በለስን በላ። በዚህም ምክንያት እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፣ ገነትን ያህል ቦታ አጥቶ ወደ ምድር ተጋዘ። አምላክነትን ሲመኝ ሰውነትን አጣ። የሰው ልጅ ዛሬም ድረስ ያለውን ክብር በማወቅ ከመጠበቅ ይልቅ ያልሆነውንና ሊሆን የማይችለውን በመመኘት ይኖራል። ይህን ምኞት መግታት የሚቻለው እግዚአብሔር ለሰው የሰጠውን ክብር በማስተማር ነው።
እግዚአብሔር ለሰው ያላደረገው ምንም ነገር የለም። እንደ ልቤ የተባለው ዳዊት “ምንት ውእቱ ሰብእ ከመ ትዝክሮ፣ ወምንት ውእቱ እጓለ እመሕያው ከመ ተሐውጾ – ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጎበኘውስ ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?” (መዝ. ፰፡፬) ብሎ ይጠይቅና ከመንፈስ ቅዱስ የተሰጠውን መልስ ሲናገር “አንሰ እቤ አማልክት አንትሙ፣ ወደቂቀ ልዑል ኵልክሙ – እኔ እላለሁ፤ አማልክት ናችሁ፤ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ” (መዝ. ፹፪፡፮) ይላል። ለሰው የተሰጠው ክብር አምላክ ተብሎ እስከ መጠራት ነው። ሙሴንም በፈርዖን ላይ አምላክ እንዳደረገው ነግሮታል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ “በጎውን ሁሉ ያልከለከለን እግዚአብሔር የሚጠቅመን ቢሆን ኖሮ ዕፀ በለስን አይከለክለንም ነበር” ይላል። እርሱ ሳንለምነው የሚሰጠን፣ የለመንነውን የማይነሣን፣ ከለመንነውም በላይ አብዝቶ የሚሰጠን ታማኝ አምላክ ነው። ሰው ደግሞ በተቃራኒው ከተደረገለትና ካለው ነገር ይልቅ አልተደረገልኝምና የለኝም የሚለው ይበዛል። ይህን ምኞቱን ለማሳካትም የሰውነት ክብሩን በመርሳት ወደ እንስሳነት ደረጃ ሲወርድ ይታያል። ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ እንዘ አልቦሙ ልብ፣ ወተመሰሎሙ – ሰውስ ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቀም፤ ልብ እንደሌላቸው እንስሳት ሆነ፣ መሰላቸውም” (መዝ. ፵፱፡፲፪) ይላል።
ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ ይህን የነቢዩን ቃል በተረጎመበት የቅዳሴው ክፍል ሰው ከእንስሳትም የሚከፋበት ሁኔታ እንዳለ ይነግረናል። ነቢዩ ዕዝራም እንስሳት ይበልጡናል ይላል። ይህ ሲባል ግን ሰው በግብሩ ከእንስሳት የሚያንስበት ጊዜ እንዳለ ለመግለጽ እንጂ ሰው እንስሳ ነው ለማለት አይደለም። ስለሆነም የሰውን ክብር ባለመረዳት “ማኅበራዊ እንስሳ ነው፤ ምክንያታዊ እንስሳ ነው፣ ወዘተ” የሚሉ አገላለጾች ፈጽሞ ትክክል አለመሆናቸውን ማሰብ ይገባል። ሰው ፍጡር ነው። ምክንያታዊ፣ የሚያስብ፣ የሚያሰላስል ፍጡር ተብሎ ቢገለጽ አይጸንም። ሰውን እንስሳ ብሎ መግለጽ ግን የሰውን ክብር ማሳነስ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪውንም መስደብ ነው። የእንስሳት ንጉሥ ደግሞ አንበሳ እንጂ ሰው አይደለም። ሰው የፍጥረት ንጉሥ እንደ መሆኑ መጠን እንስሳ ቢሆን ኖሮ የእንስሳትም ንጉሥ ይባል ነበር። ይህም ሰው ንጉሥነቱ ለፍጥረት ሁሉ እንጂ ለእንስሳት ብቻ እንዳልሆነ ቁጥሩም ከእንስሳት ወገን እንዳይደለ ማረጋገጫ ነው። ሰው ከእግዚአብሔር የተሰጠው ክብር ምን እንደሆነና ይህን ክብሩን ባለመረዳትና በማቃለል የደረሰበትን መከራና ጉስቍልና ቅዱስ አትናቴዎስ በቅዳሴው በሰፊው አብራርቶታል።
፩. ሰው ንጉሥ ነው፡- ሰው የምድር እንስሳትን፣ የባሕር ዓሦችን፣ የሰማይ አዕዋፍን እንዲገዛ የጸጋ አምላክነት የተሰጠውና በምድር ላይ ገዢ ሆኖ የተሾመ ፍጥረት ነው። ገነትን የመጠበቅና የማበጃጀት ኃላፊነትም ያለበት ነበር። ነገር ግን ይህን ክብሩን ትቶ በፈቃዱ ራሱን አዋረደ። “ወኮነ ገብረ፣ ወመለክዎ እለ ኢኮኑ አጋዕዝተ – ለአጋንንት ባርያ ሆነ፣ ጌቶቹ ያይደሉ፣ መናገር የማይችሉ ግዑዛንን አምላክ አድርጎ ያመልክ ያዘ”። አጋንንትም ልቡን ዙፋን፣ አንደበቱን ልሳን አድርገው የቆመ እያስቆረጡ፣ የወደቀ እያስፈለጡ ገዙት። አምላክ ነኝ ብሎ መናገር የማይችለውን እንጨት ጠርቦ፣ ድንጋይ አለዝቦ ያመልክ ጀመር። “መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፣ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል” ተብሎ የተነገረለትን አምላክ የሚሠራና የሚፈጠር በማድረግ “አሮን አሮን ግበር ለነ አማልክተ ዘየሐውሩ ቅድሜነ – አሮን አሮን በፊታችን የሚሔዱ አማልክትን ሥራልን” ብሎ እስከመናገር ደረሰ። ይህም ገዢነትን ባለመረዳት፣ የተሰጠውን ክብር ባለማወቅ አስቀድሞ ለሚገባው ባለመታዘዝ ራሱን አምላክ ለማድረግ፣ በኋላም ከእሱ በታች ያሉ ፍጥረታትን አምላክ በማድረግ ራሱን ተገዢ ማድረጉን የሚያሳይ ነው።
፪. ሰው ባለጸጋ ነው፡- እግዚአብሔር ለሰው ካለው ፍቅር የተነሣ ሁሉን በእጁ ጭብጥ፣ በእግሩ እርግጥ ብሎ እንዲገዛለት አድርጎ፣ የሚያስፈልገውን ሁሉ አዘጋጅቶ ፈጥሮታል። ግን ባለጸግነቱን ባለመረዳት በፈቃዱ ራሱን ደሀ አድርጎ ሆዱን ሲያስርብ ነፍሱን ሲያስጠማ ይኖራል። አትብላ የተባለውን ሕግ ተላልፎ ዕፀ በለስን ሰርቆ በላ። ፍጥረት የተፈጠረው ለሰው መጠቀሚያ ቢሆንም የገዢነትና የተገዢነት ምልክት የሆነውን አትብላ የሚለውን ሕግ በመሻር ከራሱ ንብረት ሰረቀ። ዛሬም በዚያው ልማድ ሰው የራሱን ንብረት ይሰርቃል። የወንድሙን ንብረት ይመኛል፤ ይቀማል። ምኞቱን ለማሳካትም ሕንፃ ሥላሴን እስከ ማፍረስ ይደርሳል። ባለጸግነቱን ቢረዳ ገድሎ ሳይሆን በእጁ ላብ ራሱን ያኖር ነበር። በተለይም የሚያጠፋውን ሰው ክብር ቢያውቅ ለመግደል ቀርቶ ለመስደብ ይሳቀቅ ነበር።
፫. የብርሃን ልብስ የለበሰ ነው፡- የብርሃን ልብስ የልጅነት፣ የአዋቂነት ምሳሌ ነው። ሰው ግን በፈቃዱ የጸጋ ልጅነቱን አጥቶ፣ ከዕውቀት ተራቁቶ በማይምነትና በድንቁርና መኖርን መርጦ ታይቷል። ከብርሃን ይልቅ ጨለማን፣ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን ይመርጣል። ነፃ ፈቃዱን ያለ አግባብ ሲጠቀም ዕውቀት የተሰጠው አይመስልም። ሰው ከሌሎች ፍጥረታት የሚለየው በእግዚአብሔር አርአያ የተፈጠረ መሆኑ ነው። የእግዚአብሔር አርአያ ያሰኘውም ነባቢት፣ ለባዊትና ሕያዊት ነፍስ ያለችው ፍጡር በመሆኑ ነው። ሰው በሕይወት ሲኖር ሥጋውን ለነፍሱ፣ ነፍሱን ለእግዚአብሔር በማስገዛት ብርሃን ለብሶ ብርሃን ተጎናጽፎ እንዲኖር እንጂ በጨለማ እንዲኖር አልተፈጠረም። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በመልእክቱ “ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ይኖራል” (፩ኛ ዮሐ. ፪፡፱-፲፩) እንዳለ ሰው ሰውን እየጠላ በብርሃን ሊመላለስ አይችልም።
፬. ሰው የፍጥረት ገዢ ነው፡- ሰው ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ገዢ ሆኖ የተሾመ ነው። ገዢነት መጋቢነትና ጠባቂነት ነው። ፍጥረትን በውክልና ይመግብና ይጠብቅ ዘንድ ተሹሟል። ሰው ግን ለራሱ ጠባቂ የሚያስፈልገው ሆነ። በለመለመ መስክ የሚያሰማራው እረኛ፣ የሚያስተምረው መምህር፣ የሚመራው መሪ አስፈለገው። ሰው ገዢ ሆኖ በራሱ የሚቆም ሳይሆን እንዲገዛቸው በተሰጡት ፍጥረታት ላይ የሚደገፍ ሆነ። በፍጥረት ላይ እንዲሠለጥን ተፈጥሮ ለገንዘብ ተገዢ ሆነ። በእግዚአብሔር ፍቅርና ጥበቃ ተከብቦ እየኖረ ለጥላቻ ተገዢ ሆነ። ስለ ሌሎች ነፍሱን አሳልፎ ከመስጠት የሚበልጥ ፍቅር የለም እያለ እየሰበከ ሰው የሚገድል ፍጡር ሆነ። አርአያ እግዚአብሔር ተሰጥቶት እግዚአብሔርን ወደ መምሰል እንዲያድግ የተፈጠረ ቢሆንም ከእንስሳት ግብር ባነሠ ሁናቴ በመኖር አምላኩን ያሳዘነ ፍጡር ሆነ። ስለ ሥላሴ አንድነትና ሦስትነት እየሰበከ፣ ሰው ከአራቱ መስተጻርራን እንደተፈጠር እያስተማረ፣ አንድ መሆን ያቃተው፣ እንደ እሱ ካለው ወንድሙ ጋር በሰላም መኖር የሚከብደው ፍጡር ሆነ።
የተፈጠሩበትን ዓለማ በመረዳት በቅድስና አጊጠው ያለፉ ቅዱሳን ሁሉ እንደ እኛው ሰዎች ናቸው። ኤልያስ እንደ እኛ ሰው ነው፤ ነገር ግን ሰማይ ዝናም እንዳይሰጥ ለሦስት ዓመታት ለጉሞታል። ኢያሱ እንደ እኛ ሰው ነው፤ ነገር ግን በገባዖን ሰማይ ፀሐይ እንዳትጠልቅ ማቆም ችሏል። በዙሪያችን እንደ ደመና የከበቡን ምስክሮች ሁሉ ደመና ጋርደው፣ መና አውርደው፣ ውኃ አፍልቀው፣ ባሕር ከፍለው፣ የአናብስትን አፍ ዘግተው፣ በእሳትና በስለት ተፈትነው ያለፉ ዋኖቻችን ናቸው። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ናቸው። እኛስ ግን በእርግጥ ሰዎች ነን? መሠረታዊው ጥያቄ ይህ ነው። ሰውነት ምንድን ነው? የሰውነት መለኪያው ምንድን ነው? ሰው የእግዚአብሔርን ክብር ለመውረስ የተለየ ፍጡር ነው። በፈቃዱም ሲጠፋ በደም ዋጋ ተፈልጎ የተገኘ ነው። “በዋጋ ተገዝታችኋልና የራሳችሁ አይደላችሁም” እንደተባለ ኃያል ወልድን የሰው ልጅ ፍቅር አገብሮት ወደዚህ ምድር መጥቶ የጠፋውን የሰው ልጅ በደሙ ዋጅቶታል፤ ተወዳጅቶታልም። እግዚአብሔር ሰውን ይወደዋል። ሰውም አምላኩን በፍጹም ልቡ፣ በፍጹም አሳቡ፣ በፍጹም ነፍሱ እንዲወድ ታዝዟል። በዚህ መጠን አምላኩን የሚወድ ሰው ወንድሙን ሊጠላ አይችልም። የሚያየውን ወንድሙን ሳይወድ አምላኩን እንደሚወድ የሚናገር ግን እርሱ ሐሰተኛ ነው። የሐሰት አባቷ ደግሞ ሰይጣን ነው። ሐሰተኛነት ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰይጣን ማድላት ነው። ስለሆነም ሰው የተሰጠውን ክብር፣ የተከፈለለትን ዋጋ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለውን መወደድ በመረዳት በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቢጽ ጸንቶ ሊኖር ይገባል። የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰው ልጅ አፈጣጠርና ክብር ያላትን አስተምህሮ በስፋትና በምልዐት በማስተማር ከሰውነት ክብር እንዳይወርድ፣ በጥፋት እንዳይኖር የማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል እንላለን።