የአምቡላንሱ ችግር የሰርክ ችግር እንዳይሆን

የአምቡላንሱ ችግር የሰርክ ችግር እንዳይሆን

የአምቡላንሱ ችግር የሰርክ ችግር እንዳይሆን

ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. የተፈጸመው ሕገ ወጥ ሢመተ ጳጳሳት በነገ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እና በዛሬው አገልግሎቷ ጥቁር አሻራ የተወ ክሥተት ሆኖ እየታወሰ ይኖራል፡፡ ሕገ ወጥ ሹመቱ የፈጠረውን ችግር ለማረም ቅዱስ ሲኖዶስ የሔደበትን መንገድ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን እና በሕገ ቤተ ክርስቲያን ሚዛን መዝነው የሚተቹ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን ልጆች በርካታ ናቸው፡፡ የሲኖዶስ አባላት የሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት ደግሞ የችግሩን ምንጭ ያደርቃል ብለው ያሰቡትን ወስነዋል፡፡ በውጤቱም የተከሠተውን ችግር ለመፍታት በዋናነት ኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ ሀገረ ስብከቶች በአፋን ኦሮሞ ማስተማር የሚችሉ ኤጲስ ቆጶሳትን መርጠው ሾመዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰደውን የመፍትሔ አቅጣጫ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ለማስረዳት ብፁዐን አበው በቤተ ክርስቲያኗ መገናኛ ብዙኃን ቀርበው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫው ላይ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ሲኖዶሱ የቆየበትን ፈታኝ ቅርቃር እንደሚከተለው በፈሊጥ ነበር የገለጹት፡፡

ይህ በአምቡላንስ የመጣ ችግር ነው፤ በአምቡላንስ ለመጣ ታካሚ ደግሞ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል›› ነበር ያሉት፡፡ እርግጥ ነው የኦሮሚያ ቤተ ክህነት በማቋቋም በቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ላይ ኩፋሌ ለማምጣት ሙከራ መደረግ ከጀመረ ጥቂት ዓመትታ ተቆጥረዋል፡፡ ጥር ፲፬ ቀን በወሊሶ የተደረገው ሕገ ወጥ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ግን ለአእላፍ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ላይ የወረደ የበጋ መብረቅ እንደ ሆነባቸው የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ጥያቄው ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በጣሰ ሁኔታ በዘመነኛው ፖለቲካ ታዛ ተጠልሎ ነው የቀረበው፡፡ ከጥንትም ቤተ ክርስቲያን ለሐዋርያዊ አገልግሎቷ ስኬት እንደ በረከት የምትመለከተውን እና የምትጠቀምበትን በሕዝቡ ቋንቋ መስበክን የማታምንበት የሚያስመስል የስም ማጥፋት ዘመቻን አስቀድሞ ነው የተንፀባረቀው፡፡ ለዚህ ድንገተኛ ችግር የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማስጠበቅ የሚያስችል አስቸኳይ ግብረ መልስ ያስፈልገው ነበርና ችግሩን በአምቡላንስ የመጣ ችግር ነው መባሉ ያስሔዳል፡፡

የችግሩን ፈጣሪዎች ወደዚህ ኢቀኖናዊ ድርጊት ለመግባት የገፋፏቸው ምክንያቶች ብዙ እንደ ሆኑ ይገመታል፡፡ ጥቂቶቹም ግለሰባዊ፣ ፖለቲካዊ እና ‹‹መንፈሳዊ›› ምክንያቶች(ጉድለቶች) የመሆናቸው ነገር የተሠወረ አይደለም፡፡ በዚሁ ፳፻፲፭ ዓ.ም. ቅዱስ ሲኖዶስ በርክበ ካህናት ባካሔደው መደበኛ ጉባኤው ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ዘጠኝ ጳጳሳት እንዲሾሙ ወስኗል፡፡ በውሳኔው መሠረትም ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም. ለዘጠኝ መነኮሳት ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ተከናውኗል፡፡ ይህ ለአምቡላንስ ለመጣ ችግር መፍትሔ ለመስጠት የተወሰደ ውሳኔ ቅዱስ ሲኖዶሱን ወደዚህ ሢመት በጥድፊያ እንዲገባ ካደረጉት ገፊ ምክንያቶች ለምን ያህሎቹ መልስ ሰጥቷል? የሚለው ግን መልስ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡

 

ጥያቄው ለበሽታው ትክክለኛ መድኃኒት መታዘዙን ለማረጋገጥ ይረዳን ይሆናል፡፡ ይህን በትክክል ተንትኖ መፍትሔ መስጠት ካልተቻለ ግን ለመደበኛ ሕክምና የሚመጣው የታካሚ ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ሁሉም የነፍስ ሕክምና ማዕከል ወደ ሆነች ቤተ ክርስቲያን ሥጋዊ ጥያቄውን ይዞ በአምቡላንስ መምጣት አዋጭ መንገድ እንደ ሆነ እንዲያስብ ያደርጋል፡፡ በአምቡላንስ ለመጣ ታማሚ የሚሰጠውን መስተንግዶ ለማግኘት በሥጋዊ ጥበብ አስልቶ ላለመንቀሳቀሱም ዋስትና የለም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም መደበኛ የወንጌል አገልግሎቷን ገትታ ዘወትር እሳት የማጥፋት ሥራ ላይ ጊዜዋንና ሀብቷን እንድታጠፋ፣ በየጊዜው በሚነሡ ሁከቶች ሰማያዊ ተልእኮዋ እንዲታወክ ያደርጋል፡፡

 

ከላይ ከሢመቱ መግፍኤዎች መካከል የተወሰኑት ፖለቲካዊ፣ ግለሰባዊ እና ‹‹መንፈሳዊ›› ምክንያቶች እንደ ሆኑ አንሥተናል፡፡ በእርግጥ በግልጽ የተነገረውና በፊት መሥመር ላይ የሚገኘው መግፍኤ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ለማከናወን ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ ጳጳሳትን መሾም የሚል ነው፡፡ በተሰጠው ሹመት ከእነዚህ ገፊ ምክንያቶች ስንቱ ተመልሰው ይሆን?

  1. ፖለቲካዊ መግፍኤ፤ ላለፉት ሦስት ዐሥርት ዓመታት ያህል ሀገራችን በዘውግ ምሕዋር ላይ በሚሽከረከር ፖለቲካ ነው እየተመራች ያለችው፡፡ ገዥውን ድርጅት ጨምሮ አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች በዚህ ምሕዋር ዙሪያ ይዞራሉ፡፡ በዋናነት ቋንቋን ማዕከል አድርጎ የተዋቀረው ያልተማከለ (ፌደራላዊ) አስተዳደርን ያነበሩ የፖለቲካ ልኂቃን ቤተ ክርስቲያንን ቢችሉ ለማጥፋት ብዙ ሠርተዋል፡፡ ያ አልሆን ሲላቸው መንግሥታዊ መዋቅሩ የቆመበትን የዘውግ ፖለቲካቸውን በሚያጠናክር አወቃቀር ተደራጅታ ማየት እንደሚሹ በቂ አመላካች ነገሮች አሉ፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በባሕርይዋ እንኳን በነገዳዊው ማንነት በብሔራዊው ድንበርም አትወሰንም፡፡ ዓለም ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሞት ያገኘውን ዘላለማዊ ሕይወት ዐውቆ የትንሣኤው ተካፋይ እንዲሆን የምትሰብከው ኩላዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘውጋዊው የአስተሳሰብ ውቁር ተግዳሮት ተደርጋ ተሥላለች፡፡ የቋንቋና የባህል ብዝኃነትን አክብራና ልዩ ልዩ ሰውኛ ማንነቶችን አስተሣሥራ የያዘችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረቱን ግንጥል ማንነት ላይ ባቆመው ፖለቲካ ዐይን ተፈላጊ አለመሆኗ የሚያስገርም አይሆንም፡፡ክልላዊ ቤተ ክህነትን ማዋቀር የሚሻው በዚህ የጥላቻ አስተሳሰብ መሠረት ላይ የቆመው የፖለቲካ ልኂቅ ነው፡፡ ለፍላጎቱ እውን መሆንም ከመንፈሳዊነት ፈቀቅ ብለው የዘውጋዊ መርሑ ተገዥ የሆኑ የቤተ ክርስቲያኗን አገልጋዮች መልምሎ ከጎኑ አሰልፏል፡፡ በዚህ ፖለቲካዊ ፍላጎት ጥላ ሥር የወደቀው ቡድን ደግሞ የእኔ ከሚለው ዘውግ ጳጳሳት ስለተሾሙለት ብቻ ረክቶ ቤተ ክርስቲያን ትኩረቷን ወደ ሰማያዊ ተልእኮዋ እንድትመልስ ዕድል ፈንታ መስጠት አይፈልግም፡፡

 

ከፀሐይ በታች ባለ ማንኛውንም ዕድል በመጠቀም ቤተ ክርስቲያንን ከሐዋርያዊ ተልእኮዋ የማናጠብ ዓላማ ያነገቡ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጠሩ ሁከቶችን ተጠቅመው ምእመናንን ከቤተ ክርስቲያን ዕቅፍ ማስደንበርና በተመረዘ መረባቸው ማጥመድን ግባቸው አድርገዋል፡፡ እነዚህ በቅሰጣ መንገድ መሻታቸው ያልተሳካላቸው አካላት በዘውግ ፖለቲካ ተጠልለው ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም እየጣሩ እንደሆነ የትየሌሌ ማሳያዎች አሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ለታየው አፈንጋጭነት መንግሥታዊ ድጋፍ ሲሰጡ የሚታዩት አብዛኞቹ ባለ ሥልጣናት ፖለቲካዊ ግብ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ተልእኮ የተሸከሙ ናቸው፡፡ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው በቤተ ክርስቲያን ሁከት እንዲፈጠር በማድረግ እና የተፈጠሩ ክፍተቶችን በማራገብ በአዳራሽ የተቀበሉትን አደራ ለመወጣት ታጥቀው ተነሥተዋል፡፡

 

በአጭሩ በዘውግ ምሕዋር ላይ ለተመሠረተው ፖለቲካ የተለያዩ ምድራዊ ማንነቶች ያሏቸውን ምእመናን አዋሕዳ የያዘች ቤተ ክርስቲያንን ዕንቅፋት አድርጎ የሚቆጥር ቡድን አለ፡፡ በአናቱም በፖለቲከኛነት ካባ ሥር ሃይማኖታዊ ፍላጎቱን ለማሳካት ታጥቆ የተነሣ ቡድን አለ፡፡ የእነዚህ ሁለትም አንድም የሆኑ አካላት ፍላጎት በዘንድሮው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ረክቶ ሥራዋን ትሠራ ዘንድ ቤተ ክርስቲያንን አይተዋትም፡፡ ስለዚህ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳቱ በፖለቲከኞች ዐይን ሲመዘን ከሌላ ዙር ሥጋት እፎይታ ሊሰጣት አይችልም፡፡ ለዚህ ነው የአምቡላንሱ ችግር የተያዘበት መንገድ የሰርክ ችግር ጥሎብን አልፎ እንዳይሆን ለማስተዋል የምንገደደው፡፡

  1. ግለሰባዊ መግፍኤ፤ ሌላው በአምቡላንስ ለመጣው ድንገቴ ደራሽ ችግር አጋልጦ የሰጠን የመነኮሳቱ የገነነ ፍቅረ ሢመት እና ፍቅረ ነዋይ ነው፡፡ የግለሰቦቹ ጣራ የነካ የሥልጣንና የጥቅም ፍላጎት ብዙኃኑን ሕዝበ ክርስቲያን ለማሳሳት ጉልበት ያገኘው ቋንቋን ከለላ አድርጎ በመምጣቱ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል፤›› ብሏል፡፡ ለዚህ አገልግሎት ራሱን ያጨ አባት እጅግ ብዙ ተጋድሎ ለመጋደል የተዘጋጀ መሆን ይገባዋል፡፡ እንጦሳዊው ምንኩስና የቆመባቸውን መሠረቶች፣ ራስን መካድ፣ ፍቅረ ነዋይን መግደል፣ ብርቱ ጸሎተኛነትን፣ ትሕትና፣ ወንድማዊ ፍቅር ወዘተ ገንዘብ ማድረግ ይገባዋል። በዚህ ዘመን ኤጲስ ቆጶስነትን የሚያሳድዷት መነኮሳት ደግሞ ከእነዚህ መንፈሳዊ ሀብቶች የተራቆቱ ናቸው፡፡ ነገር ግን በሁለት ምክንያቶች ማዕረገ ጵጵስናውን ይፈልጉታል፤ የተሻለ ምድራዊ ሕይወት ፍለጋ እና የሥልጣን ፍላጎታቸው ማርኪያ አድርገው ስለቆጠሩት፡፡ በዚህ ረገድ የዘንድሮው የሐምሌ ወር ሢመተ ጵጵስና እጅግ ጥቂት የሚባሉትን መነኮሳት ፍላጎት ነው ያሟላው፡፡ ይህ ሹመት ለጥያቄያቸው ፖለቲካዊ ዳራ ሰጥተው በውጤቱ የሥልጣን እና የጥቅም ጥማታቸውን ለማርካት ሲሯሯጡ የነበሩትን በፍትወተ ሢመት የወደቁ ጥቂት መነኮሳትን ከማባበል የሚያልፍ ውሳኔ እንዳልሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

ስለዚህ የመነኮሳቱ መቋጫ የሌለው ፍቅረ ሢመት እና ጵጵስናን የሀብት ጎተራ አድርጎ የመቁጠር አተያይ አሁንም ቤተ ክርስቲያንን ወደ ሌላ ዙር ፈተና ማስገባቱ፡፡ ይህም በአምቡላንሱ ለመጣው ችግር የተሰጠው ግብረ መልስ የአምቡላንሱን ችግር የቤተ ክርስቲያን የሰርክ ችግር ወደ መሆን ያሳድገዋል፡፡

  1. መንፈሳዊ ግፊት፤ ቤተ ክርስቲያናችን በኦሮምኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ በርካታ መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል አሏት፡፡ ይህ ግን በኦሮምያ ክልል ያለውን የቤተ ክርስቲያንዋን የወንጌል ተልእኮ ለመፈጸም በቂ አይደለም፡፡ በእርግጥም ሕዝቡን በአፍ መፍቻው ቋንቋ በማስተማር በኦርቶዶክሳዊ እምነቱ ማጽናት በቤተ ክርስቲያን አባቶች ትከሻ ላይ የወደቀ ሓላፊነት ነው፡፡ በቋንቋው የሚሰብክ የሚያስተምር በማጣት ከሰማያዊ ጸጋ የምትለይ አንድስ እንኳ ነፍስ ብትኖር በእግዚአብሔር ፊት ያስጠይቃል፡፡ ይህ ተግዳሮት መንፈሳዊ መፍትሔ እንደሚሻ በአግባቡ በመረዳት ለአገልግሎቱ ሥምረት ኦሮምኛ የሚናገሩና የሕዝቡን ሥነ ልቡና የተረዱ ኤጲስ ቆጶሳትን መሾም እንደ አንድ መፍትሔ ሆኖ ቀርቧል፡፡

በአምቡላንስ ለመጣው ችግር የተሰጠው ኤጲስ ቆጶሳትን የመሾም መፍትሔ በተሻለ ደረጃ ያሳካው ነገር ቢኖር ለዚሁ መንፈሳዊ ግፊት መልስ መስጠት መቻሉ ነው፡፡ እርግጥ ነው መንፈሳዊ መፍትሔ ለመስጠት የተሔደበት መንገድ፣ የአስመራጭ ኮሚቴውን ከማቋቋም ጀምሮ፣ የጥቆማ ሒደቱ እና የተሹዋሚዎቹ አመራረጥ ክፍተት አግባብነት አጠያይቋል፡፡ ምክንያቱም ለዕጣ ዕድል ባለመስጠት የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ እንዲገለጽ አልተደረገም፤ ይህም ከሐዋርያት ፍኖት መውጣት ነው፡፡ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን እረኛቸውን በመምረጥ ረገድ የካህናት እና የምእመናን ሡታፉ እጅግ ዋጋ ያለው ትውፊታዊና ቀኖናዊ አሠራር ነበር፤ በዚህ የምርጫ ሥርዐት ግን ምእመናን የሚሾምላቸውን የመምረጥ ዕድል ስላላገኙ የተሾመባቸውን ለመቀበል ተገድደዋል፡፡ እነዚህና መሰል ጥሰቶች ምርጫው በአምቡላንስ የመጣን ችግር ከማስተናገድ አንፃር የተከናወነ ቢሆንም እንኳ በአመራረጥ ሒደቱ መጣስ ያልነበረባቸው ቀኖናዎች መጣሳቸውን ያመላክታሉ፡፡ ይህም በአምቡላንስ የመጣው ችግር የተስተናገደበት መንገድ ሌላ መሰል ችግርን እንዳይፈጠር በሚያስቀር ደረጃ አለመሆኑን ያመላክታል፡፡

የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል ያሉ አራት ጳጳሳት ተመሳሳይ አፈንጋጭነት አሳይተዋል፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ በሕገ ወጥ መንገድም ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾም ዋዜማ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያናችን ወደ ፊትም ቢሆን ችግር በአምቡላንስ የመምጣቱ ነገር የማይቀር ጽዋ እንደሆነባት ተጨባጭ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ አካሔድ የአምቡላንስ ችግር በሚል ተቀብለን የገባንበት እሳት የማጥፋት ዘመቻ የሰርክ ፈተና ሆኖ እንዳይቀጠል መፍትሔ መስጠት ይኖርብናል፡፡ የሚከተሉት ችግሩን ለመቅረፍ ሊረዱን የሚችሉ የመፍትሔ ሐሳቦች ናቸው፡፡

  • በኤጲስ ቆጶሳት አካባቢ በተለያየ መንገድ የሚታየው የመንፈሳዊነት ጉድለት የዚህ ሁሉ ቀውስ መነሻ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን መረዳትና ጉድለቱን ለማከም የሚረዱ ተግባራትን በፍጥነትና ከልብ በሆነ ቁርጠኝነት መፈጸም፡፡
  • የቤተ ክህነትን መዋቅር ለወንጌል አገልግሎት መዋጀት፡፡ የቤተ ክርስቲያን መዋቅር የተዘረጋው የቤተ ክርስቲያኗ ዋነኛ ተልእኮ የሆነውን ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማሳለጥ ነው፡፡ ነገር ግን ጥቂት በማይባሉአህጉረ ስብከትየእግዚአብሔርን መንግሥት ለሁሉ የማዳረስ ጉዳይ ቤተ ክህነቱን ተጠግተው የሚኖሩ ምንደኞችን የግል ጉዳይ ከማስተናገድ በኋላ የሚታይ ትኩረት የተነፈገው ጉዳይ ሆኗል፡፡ ይህን አሠራር አስወግዶ የቤተ ክህነትን መዋቅር ለወንጌል አገልግሎት መዋጀት ግድ ይላል፡፡
  • በቤተ ክህነት ውስጥ የተንሰራፋው በዘውግ፣ በዘመድ አዝማድ፣ በግቦ ሥራ የሚያዝበትና ሓላፊነት የሚሰጥበትን አካሔድ ነቅሎ የሚጥል አስተዳደራዊ ለውጥ ማስፈን፡፡
  • ብዙ መነኮሳት ኤጲስ ቆጶስነትን በፍቅር የሚያገለግሉበት ማዕረግ ሳይሆን የፈለጉትን አዝዘው ናዝዘው፣ ሹመው ሽረው የሚኖሩበት በትረ ሥልጣን አድርገው እንዲያዩትና ለጵጵስና የሚያበቃ ትምህርት እና ሕይወት ሳይኖራቸው አጥብቀው እንዲፈልጉት ያደረጋቸውን ልማዳዊ አሠራር ማረም፡፡
  • የጳጳሳትን የተቀማጠለ አኗኗር በማስቀረት በጥንቱ ትውፊት መሠረት ጳጳሳት አልቦ ጥሪት ሆነው፣ የሚያስፈልጋቸው የዕለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስ፣ ለአገልግሎት የሚሆን መጓጓዣ ተሟልቶላቸው በሰማይ ለሚገኝ ክብር ብቻ ብለው የሚያገለግሉበትን መንገድ ማመቻቸት፡፡
  • በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የምእመናን ሡታፌ ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ታሪክ ጋር በሚሔድ መልኩ ዳግም መቃኘት ያስፈልገዋል፡፡ ምክንያቱም ጳጳሳት ይሾማሉ፣ በሚሾሙባቸው አህጉረ ስብከት ያሉ ምእመናን ግን አንዳች ሚና የላቸውም፡፡ ይህም ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር ከሚከብርበት፣ ከሐዋርያዊ ትውፊቷ እና ከጥንታዊ መገለጫዋ ማለያየት ነው፡፡ ምእመናንን ከዚህ ትውፊታዊ እና ቀኖናዊ መብት መነጠል ያላቸውን መንፈሳዊና ሥነ ልቦናዊ ትሥሥር እንደ መቁረጥ ነው፡፡ ከፍ ሲልም ምእመናን የሚፈለጉት የጳጳሳትን ጥቅም የሚጋፋ ነገር ሲመጣ ሰማዕት እንዲሆኑ፣ የዘንዶን ጉድጓድ ሊለካባቸው፣ የቤተ ክርስቲያንን ሳይሆን የጥቂት ጳጳሳትን ጩኸት እንዲጮኹ፣ በሰላም ጊዜ የተዘቀዘቀውን ጃን ጥላ በድካማቸው ፍሬ እንዲሞሉ ብቻ ይመስላል፡፡

 

በወፍ በረር መረዳት እነዚህን የመፍትሔ ሐሳቦች አቀረብን እንጂ በብዙ ኦርቶዶክሳውያን አእምሮ እጅግ በርካታ የመፍትሔ ሐሳቦች እንደሚዘዋወሩ ይሰማናል፡፡ ሁሉም የሚያገኘውን ዕድል ሁሉ በመጠቀም ቤተ ክርስቲያን ካለችበት ፈተና በዘላቂነት መውጣት የምትችልበትን ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ የሚቀርቡ ሐሳቦች በውይይት ዳብረው ቤተ ክርስቲያንን የአምቡላንስ ችግር ፈጣሪዎች ፈቃድ ፈጻሚ ከመሆን ልንታደጋት ይገባል፡፡