ብፁዕ አቡነ አብርሃም ከትግራይ ክልል ጋር ተያይዞ ባለው ወቅታዊ ጉዳይ የሰላምና የአንድነት መልዕክት አቀረቡ

 

ብፁዕ አቡነ አብርሃም ከትግራይ ክልል ጋር ተያይዞ ባለው ወቅታዊ ጉዳይ የሰላምና የአንድነት መልዕክት አቀረቡ

ብፁዕ አቡነ አብርሃም ከትግራይ ክልል ጋር ተያይዞ ባለው ወቅታዊ ጉዳይ የሰላምና የአንድነት መልዕክት አቀረቡ

አርብ ሐምሌ 14 ቀን 2015፤ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች በተለይም በትግራይ ክልል ባሉ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን እና ከሕግ ውጭ በሆነ መልኩ ” ኤጲስ ቆጶሳትን ” እንሾማለን በማለት  እየተደረገ ያለው ዝግጅት አስመልክቶ እንዲቆምና  የውይይት መድረኮች ተመቻችተው  ችግሮችን በሰላማዊና የቤተ ክርስቲያንን አንድነት  በጠበቀ መልኩ ለመፍታት በቦታው ካሉ ሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ ለሊቃውንት ኦቶዶክሳውያንና ለሌሎች እምነት ተከታዮች እንዲሁም ለፌደራልና ለክልሉ መንግሥት የሰላምና የአንድነት ጥሪ ሐሙስ ሐምሌ 13 ቀን 2015 በሰጡት መግለጫ አቅርበዋል።

ብፁዕ አቡነ አብርሃም  በመገለጫቸው ጉዳዮቹን ለማጥራትና  ሁሉም አካል ወደልቡ እንዲመለስ ያለመ መሆኑን በመግለጽ  መልእክታቸውን ማስተላለፍ የቀጠሉ ሲሆን በሰሜኑ ኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በሞቱ  የተጎዱና ከቀያቸው በተፈናቀሉ በአጠቃላይ በደረሰው መከራና ሞት እጅግ ማዘናቸው ገልጸዋል።  ይሁን እንጂ  ጉዳዮች እዚህ ከመድረሳቸው  በፊት በሰዓቱ  አባቶች ከግል ጀምሮ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ድረስ  የተደረጉ ሰላማዊ  ተግባራት እንደነበሩ አብራርተዋል።

ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩን በትኩረት ከማየቷ በተጨማሪ “በችግሩ ወቅት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጊዜ  የሀገር ሰላምን በተመለከተ በያዘው አጀንዳ በተወያያበት ሰዓት  ከብፁዓን አባቶች የተወጣጣ የሰላም ኮሚቴ ተዋቅሮ ችግሩ  እንዲፈታ የሰላም አየር እንዲነፍስ በሚባልበት ወቅትም በአሁኑ ሰዓት በትግራይ ክልል አህጉረ ስብከት ከሚገኙት ሊቃነ ጳጳሳት መካከል “እኛ ጋር ሰላም ነው ችግር ወዳለበት አካባቢ ሂዱ” የሚል ምላሽ እንደሰጡ ኦርቶዶክሳውያን ሊያውቁ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ ይልቅ ችግር በችግር አይወገድምና እንደጥፋትም ከሆነ የጋራ እንጂ  ራስን ንጹሕ አድርጎ ሌላውን እንደበደለኛ መቁጠር ተገቢነት እንደሌለው ገልጸዋል።

አያይዘው ብፁዕነታቸው ‘ሊቃውንት በጎጥ በጎሳ በቋንቋና በብሔር በሌላ ምድራዊ ሐሳብ ሳትከፋፈሉ ለሰማያዊ መንግሥት ዓላማ ያለውን  መልካም ተግባር  በማድረግ አደራችሁን  እንድትወጡ” በማለት አሳስበዋል።

ቀጥለው ለኦርቶዶክሳውያን  በሙሉ ባስተላላፉት መልእክት ትናንት እናት ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ከፍተኛ ችግር በእስከ መሥዋዕትነት በደረሰ ሁለንተናዊ ራስን መስጠት የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንደተወጣችሁ ሁሉ ዛሬም ቤተ ክርስቲያን አንድነቷን ጠብቃ ለመሄድ በምታደርገው የእውነት መንገድ  ከምንም በላይ ክርስቶስ በገዛ ደሙ ፈሳሽነት ለመሠረታት ሐዋርያዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክብር በመሸነፍ  ለአንድነቷና ለሰላሟ በጸሎት በሐሳብና በተግባር በተገለጠ ሕይወት እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።

አያይዘውም በልዩ ልዩ ሃይማኖት ላሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ መልዕክታቸውን የቀጠሉት ብፁዕነታቸው  የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንድትጠበቅ ከዚህ በፊት ያደረጋችሁትን  መልካም አስተዋጽኦ ዛሬም  ጥንታዊት  እና ባለውለታ ቤተ ክርስቲያን አንድነቷና ሰላሟ ተጠብቆ እንዲቀጥል የበኩላችሁን አስተዋጽኦ  እንድትወጡ እንጠይቃለን በማለት መልእከታቸውን አድርሰዋል።

የኢፌዴሪ መንግሥት  ትናንት ተፈጥሮ በነበረው የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት ችግር  በውይይትና በምክክር  በከፍተኛ ኃላፊነት እንዲፈታ ማድረጉን ያስታወሱት ብፁዕነታቸው  አሁንም በትግራይ  ክልል ባሉ የአህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንት እየተከተሉት ያለውን መፍትሔ የማይሆነውን ችግር  በማስቆምና ሰላማዊ የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ እምነታችን ነው ብለዋል።

ይህ ካልሆነ ግን ይላሉ ብፁዕነታቸው “በታሪክ የቤተ ክርስቲያንን አንድነትን ማን ከፋፈለ ሲባል የፌደራልና የክልሉ መንግሥት” የሚል  የታሪክ ተወቃሽ ሆኖ በታሪክ የሚመዘገብ ይሆናል። ስለሆነም   ይህን በትግራይ ክልል ይፈጸማል የሚለውን ከቀኖና ቤተ ክርስቲያንና ሕገወጥ የሆነ ሹመት እንዲቆም ብሎም  ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ  በማመቻቸት ታሪካዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ቤተ ክርስቲያን ታሳስባለች ብለዋል።

ቅዱስ ሲኖዶስ ለትልቁ ጉልበትና ቅዱስ ትዕዛዝ “ለይቅርታ” ራሱን በማስገዛት መንጋው እንዳይበተን ይፋዊ ይቅርታ ከመጠየቅ አልፎ  የቤተ ክርስቲያናችን  ቅዱስ ሲኖዶስ ርዕሰ መንበር  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእስ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በመሩት የሰላም ልዑክ  ወደ መቐለ አቅንቶ ችግርን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ተወቃቅሶ ለመፍታት ቢሞከርም አለመሳካቱ  አስታውሰው ጉዳዩ እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

 

በመጨረሻም የባለውለታዋ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚያሳስበው ሰላሟ የሚናፍቀው  ሁሉም አካል ከትልቁ ጉልበት ጸሎት ጀምሮ  የሚቻለውን  አበርክቶት እንዲወጣ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ አብርሃም አሳስበዋል። [ኢኦተቤ መገናኛ ብዙኅን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/EOTC]