ጦርነቱን ወደ ሰላም በማሸጋገር ምድሪቱንም፣ ትውልዱንም ማሳረፍ ከሁሉም ወገን ይጠበቃል
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ተግባር ሐዋርያዊ አገልግሎትን ማከናወን ቢሆንም የአገር ሰላም እንዲሰፍን የመሪነት ሚናስትጫወት ኖራለች። የምንገኝበት ዘመንም ከእስከ አሁኑ የበለጠ የሰላም ሐዋርያ መሆንን የሚጠይቅ ነው። እንኳን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል አካል ሁሉ ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ መፈለግ ከሚያስፈልግበት ደረጃ ላይ እንገኛለን። የቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰላም አምባሳደርነት ለአንድ ወገን ያደላ ሳይሆን የሁሉም እናትነት መሆኗን በተግባር መግለጥ ይገባዋል።
የአገር ሰላም ካልተጠበቀ ወጥቶ መግባት፣ ተኝቶ መነሣት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል። ነገር ግን ካለፉት ኀምሳ ዓመታት ወዲህ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ድምፅ የሚሰማ ትውልድ ማግኘት እንደ ሰማይ እየራቀ ነው። ትውልዱ የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ የማይሰማ መሆኑ ቢታወቅም እርሷ ግን በአገር ላይ ጦርነት ሲነሣ የሰላም ጥሪ ማስተላለፏን አጠናክራ መቀጠል ይገባታል። እንዲህ ማድረጓም ጥሪዋ አንድ ቀንሰሚ ያስገኝ ይሆናል።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰውን ልጅ በትክክል መርታ ለመንግሥተ ሰማያት ማግባት ዋና ተልእኮዋ ቢሆንም ሰው በዚህ ምድር ሲኖር ሰላማዊ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ማግኘት የሚገባው ሰላም እንዳይደፈርስበትከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስታበረክተው የነበረው ሚና ውስን ስለነበር የአንድ ወገን ደጋፊ ሲያስመስላት ቆይቷል። በትግራይ አህጉረ ስብከት የሚገኙ አባቶች በራሳቸው ተነሣሽነት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ ኤጲስ ቆጶሳትን ለመሾምካደረጋቸው ምክንያት አንዱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጦርነቱን አላወገዘችም የሚል መሆኑ የሚታወቅ ነው። የቀረበው ምክንያት ትክክል ሆነም አልሆነም የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል “ውረድ እንውረድ”ዓይነት ፉከራ ሲከሠት ቤተ ክርስቲያን የሰላም ጥሪዋን ማሰማቷ ተገቢ ነው። የክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆች ሁሉ ደም በከንቱ እንዳይፈስ የአስታራቂነት ሚናዋን አጠናክራ መቀጠልም ይገባታል።
ንጉሠ ነገሥቱ ዐፄ ዮሐንስና የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ለጦርነት በተሰላለፉ ጊዜ በትግራይ የሚገኘው የአጽቤ ገዳም መነኰሳትና የአንኮበር ሊቃውንት የተጫወቱት ሚና ቀላል እንዳልነበረ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ ወልደ አረጋይና የታሪክ ምሁሩ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ በየመጽሐፎቻቸው ያስነብቡናል። ለጦርነት ተሰላልፈው የነበሩት ሁለቱም ወገኖች የአባቶችን ምክር የሚሰሙ ስለነበሩ ፉከራው ወደ ሰላም፣ ጦር መማዘዙ ወደ መተቃቀፍ ተቀየረ።
ሁለቱ ወገኖች ለደረሱበት ስምምነት በአንኮበር ሚካኤል ወንበር ዘርግተው አራቱን ጉባኤያት ያስተምሩ የነበሩትፈሊጠኛው አለቃ ምላት የተጫወቱት ሚና በታሪክ ሲዘከር የሚኖር ነው። ሁለቱ ወገኖች በ፲፰፻፸ ዓ.ም. ለጦርነት ተሰላልፈው በነበረ ጊዜ ዐፄ ዮሐንስን እና ንጉሥ ምኒልክን ያስታረቋቸው አለቃ ምላት ነበሩ። ዐፄ ዮሐንስ የካቲት ፭ ቀን በ፲፰፻፸ ዓ.ም. በመንዝ በኩል አልፈው በይጣ ቅዱስ ሚካኤል ከተባለው ቤተ ክርስቲያን አጠገብ መስፈራቸው ይሰማል። በዚህ ጊዜ አለቃ ምላት የአንኮበር ሚካኤልን፣ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስ የአንኮበር መድኃኔ ዓለምን፣ አለቃ እሸቱ የአንኮበር ማርያምን፣ አለቃ ኪዳነ ማርያም የአንኮበር ጊዮርጊስን ታቦታት አስይዘው ሥዕል እና መስቀል አስቀድመው ወደ ዐፄ ዮሐንስ ሔደው ወደራ ከሚባል ቦታ ላይ አገኟቸው። ዐፄ ዮሐንስ አለቃ ምላትን በሩቁ ሲያዩዋቸው ከበቅሏቸው ወረዱ። ንጉሡ እስከ ነበሩበት ቦታ እንዲሔዱም አጋፋሪያቸውን ወደ አለቃ ምላት ላኩባቸው። በእንደዚህ ዓይነት ሥርዓት አለቃ ምላት ከዐፄ ዮሐንስ ተገናኙ።
ፈሊጥ ዐዋቂው አለቃ ምላት ንጉሠ ነገሥቱን “ጌታዬ ከሁሉ አስቀድሞ አንድ ነገር አስቸግሮኛል፤ አንተ እንዳልል እግዚአብሔር ቀብቶ ያነገሠህ ነህ፤ እርስዎ እንዳልል ገና ልጅ ነህ” አሏቸው። በዚህ ጊዜ ንጉሠ ነገሥቱ ዐፄ ዮሐንስ “አባቴ ፈቅጀልዎታለሁ አንተ ይበሉኝ” በማለት ተናገሩ። አለቃ ምላትም “ለእኔም ይስማማኛል” ብለው በመቀጠል “ጌታዬ ምኒልክን ታረቀው፤ አንተ የታዘዝከው ሃይማኖት እንድታጸና፣ ቤተ ክርስቲያንን እንድታቀና ነው” ብለው የብቃት አነጋገር ጨምረው ስለነገሯቸው ንጉሡ አሳባቸውን ተቀበሉ።
ከቤተ ክርስቲያን የሚጠበቀውም እንዲህ ያለው የአርአያነትተግባር ነው። በዘመናችን የሚታየው ግን በተፈጠረ ክፍተት የራስን ጥቅም ማሳደድ ነው። በተግባር የምናየው በአባትነት መዓርግ የሚጠሩት ሳይቀሩ ቤተ ክርስቲያንን ለመክፈል እንቅልፍ ሲያጡ ነው። በአንጻሩ ደግሞ የጥንቶቹ አባቶች ጭንቀት የሰው ልጅ እንዳይጎዳ ስለነበር ንጉሠ ነገሥቱን አለዝበው፣ ንጉሡንም ተቆጥተው ሰላም አስፍነዋል። መቀጠል የሚገባው እንዲህ ያለው ተግባር ነው። የዛሬው ዘመን ሽምግልናና የሰላም ዘብነት ስሙ እንጂ ግብሩ እንዳይገለጥ ያደረገው ተልእኮው ወደ አንድ ወገን ያደላ በመሆኑ ነው። መሆን የሚገባው ግን አጥፊውን ገሥጾ፣ ጦር የሰበቀውንም አለዝቦ ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ የመሪነት ሚናን መጫወት ነው።
ሰሞኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አማካኝነት ለጦርነት የተሰላለፉ ወገኖች ወደ ሰላም እንዲመጡ ያደረገችው ጥሪ የቤተ ክርስቲያንን የሰላም መልእክተኛ መሆን በተግባር የሚገልጥ ነው። ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚጠበቀውም እንዲህ ያለው ተግባር ነው። የሰላም ጥሪ የተደረገላቸው ወገኖችም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ሰምተው፣ ጦራቸውን በማውረድ መወያየት ቢችሉ በአገራችን ሰላም መስፈን የበኩላቸውንና የሚጠበቅባቸውን ተወጡ ማለት ነው።
በዘመናችን እያታየ ያለው የተፈጠረውን ልዩነት በሽምግልና እንጨርሰው ተብሎ ከተጀመረ በኋላ የሽምግልናን ዋጋ የሚያቃልል ተግባር ሲፈጸም መታየቱ መታረም ይገባዋል። የተመቸ በመሰለን ጊዜ ያቃለልነው ሽምግልና ችግር በተፈጠረ ጊዜ በመብራት ብንፈልገው የማናገኘው መሆኑንም መረዳት ይገባል። ሰላማዊው መንገድ በሩን እየተዘጋ ሲመስል ብቸኛው አማራጭ ጦር ሰብቆ መነሣት ስለሚሆን መገነዛዘብ ያስፈልጋል። የይዋጣልን ተግባር ሰውን ያለ ንብረት ብቻ ሳይሆን ሀገርን ያለ ትውልድየሚያስቀር በመሆኑ ሁሉም ወገኖች ልብ ሊሉት ይገባል። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጦርነት ይቆም የምትለው ከጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ ስለማይገኝ ነው። በሁለቱም ወገን የተሰላለፉ ወገኖች እልሁ ሲበርድላቸው፣ ያላቸውን የጦር መሣሪያና ያሠለጠኑትን ኃይል ሲጨርሱ ወደ ሰላም መምጣታቸው ካልቀረ አስቀድመው ወደ ሰላም መጥተው በከንቱ የሚያወድሙትን ትውልድ፣ እንዲሁም ሀብትና ንብረት ለሌላ ተግባር ቢያውሉት ሀገር ትጠቀማለች።
ቅዱስ ፓትርያርኩ “በዘመናችን የሰላምን እና የነፃነትን ጥልቅ ትርጕም ባለመረዳት ለውጦች በነውጥ ተተክተው ከእኛ የሚጠበቀውን ሳንተገብር በምኞት ከመዛል በቀር የሚጨበጥ ነገር እየራቀን አገራችን ኢትዮጵያ ቋሚ ነገርን እያጣች ሕዝቦቿም በሰላም መኖር ሲችሉ አንዳቸው ለአንዳቸው ወጥመድ የሚያስቀምጡ ጠላት ሲያረፍድ እርስ በርስ የሚተላለቁ ሆነዋል። በዚህ ምክንያት ቀደም ሲል በትግራይ ክልል ዓመታት ያስቈጠረውን አስከፊ ጦርነት ለመቋጨት በተበሰረው የሰላም ስምምነት የታየውን የተስፋ ጭላንጭል ሕዝቡ በሚገባ ሳያጣጥመው በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል እያገረሸ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት አስደንጋጭና አሳዛኝ ክስተት ሆኖ ተመልክተነዋል” በማለት የገለጡት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው።
ከቅዱስነታቸው መልእክት መረዳት የሚቻለው ቀዳሚው መልእክት ሰዎች የነፃነትን ትርጕም ባለመረዳታቸው ለውጥ ቢካሄድም ለውጡ በነውጥ መተካቱን የሚያስገነዝብ ነው። በመሠረቱ ለውጥ የሚደረገው ለመሻሻል ቢሆንም የአገራችን ጉዳይ ግን እየባሰበት እንጂ እየተሻሻለ አልሄደም። ኢትዮጵያዊው በሀገሩ ወጥቶ መግባት ብርቅ ሆኖበታል። ለውጥ ያስፈልግ የነበረው የተበላሸውን ለማስተካከል፣ የጠመመውን ለማቅናት፣ የተሰበረውን ለመጠገን ቢሆንም በአገራችን ግን በተለይ ክርስቲያኖችን በማሳደድ፣ ለዘመናት ለፍተው ያፈሩትን ንብረት ዘርፈው የተረፋቸውን አውድመው ባዶ እጃቸውን በማስቀረት፣ ይህ የእናንተ አካካቢ አይደለም ውጡ ብሎ በማፈናቀል፣ ለዘመናት ሲጠቀሙባቸው የኖሩትን ይዞታቸውንና የአምልኮ ቦታቸውን በልማት ስም ነጥቆ ለሌላ ዓላማ በማዋል ተተክቷል። እንዲህ ያለው ከአራዊት የከፋ ድርጊት ከቀን ወደ ቀን ይሻሻላል ቢባልም እየባሰበት ሔዶ በዚህ ወቅት እንኳን በእግር በመኪናም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ከማንችልበት ደረጃ ደርሰናል። ከዚህ አስከፊ ሁኔታ ላይ የደረስነው የነፃትን ትርጕም ባለመረዳት ሌሎችን ማስጨነቅን እንደ ነፃነትና መብት መታየት በመለመዱ ነው። እንዲህ ያለው የተዛባ አመለካከት በአግባቡ ካልተያዘና ወደ ሰላም ካልተሸጋገረ ነገ የሚሆነውን ለመተንበይ ነቢይ መሆንን አይጠይቅም።
ሌላው ከቅዱስነታቸው መግለጫ የምንረዳው ጠቃሚ ነገር ጦርነት ቋሚ ነገር እንዳይኖረን እያደረገን መሆኑን ነው። የዚህ ምክንያቱ አንዱ ለሌላው ጌጥ መሆን ሲገባው የማጥመጃ ወጥመድ ማስቀመጥን እንደ መብት ስለቈጠረው ነው። መስተካከል የሚኖርበትም እንዲህ ያለው እኩይ ድርጊት ነው። ወገን በወገኑ ላይ እምነት እንዲያሳድር የሚያደርግ በጎ ተግባር መፈጸም እንጂ በመጠባበቅ እንዲኖር የሚያቃቅር እኩይ ድርጊት መፈጸም የሚጎዳው የሚፈጽሙትን ጭምር ነው። እንዲህ ያለው እኩይ ድርጊት ከምን እንዳደረሰን ስለታየ የሚበጀው አካሔድን ማስተካከል ነው።
በዚህ ዘመን ነፍጥ አንሥተው የሚዋጉ ወገኖች ለሀገራቸው የሚያስቡ ከሆነ ጦርነቱን አቁመው ወደ ሰላም በመምጣት ምድሪቱንም፣ ትውልዱንም ማሳረፍ እንደሚኖርባቸው መረዳት ይገባቸዋል።ቅዱስ ፓትርያርኩ “ከአካላዊ ጦርነት እስከ ቃላት ውርወራ ብዙ ጥላሸት የመቀባባት ሰለባ ሆነው የወደቁት በሚሊዮን የሚቈጠሩት ልጆቻችን ትምህርት ሆነውን ልባችን ዘንበል ባለማለቱ ለወደፊት ሊመጣ የሚችለው ሲታሰብ እጅግ ያስፈራልና በአራቱም ማዕዘን ነፍጥ አንሥታችሁ ያላችሁ በሙሉ ያነገባችሁትን ገዳይ መሣሪያ አውርዳችሁ ለሰላምና ለዕርቅ ቅድሚያ በመስጠት ለአንዲት አገራችሁ ህልውና ተገዥዎች እንድትሆኑ፣ መንግሥትም ሆደ ሰፊ ሆኖ ሁሉንም ለውይይት እንዲሰበስብ በጽኑ እንለምናለን” በማለት ያቀረቡትን ተማጽኖበተግባር ላይ ማዋል ሁሉንም ወገኖች አሸናፊ ያደርጋል፣ አገርንም ከመፍረስ ይታደጋልና የአባቶችን ድምፅ መስማት ማንንም አይጎዳም ብለን እናምናለን።