ባይተዋርነት እስከ መቼ?
መስከረም ፲፭ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም. በአርሲ ሀገረ ስብከት በሆንቆሎ ዋቤ ወረዳ ቤተ ክህነት ኦርቶዶክሳውያን ተገደሉ (ሰባት ኦርቶዶክሳውያን)፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ጨቅላ ሕፃናትን ጨምሮ የካህናት ቤተሰብ በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ተደብድበው ተገደሉ፡፡ በርካቶች ቆሰሉ፡፡
ካህናት እና ቤተሰቦቻቸው ከቤተ ክርስቲያን እስከ ቤታቸው ታድነው ይገደላሉ፡፡
መስከረም ፳፫ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም.) በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በአዳማ ዙሪያ ወረዳ ቤተ ክህነት በአርቱ መካነ ቅዱሳን ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የሆኑት አባ ተክለ አብ እና ቀሲስ መሠረት ተገደሉ፡፡ በደራ፣ በወለጋ፣ በቤንሻንጉል ወዘተ
አሮጌው ዓመት(፳፻፲፭ ዓ.ም.) በስልጤ ዞን የተለመደውን የኦርቶዶክሳውያን ደም በማፍሰስ፣ ሀብት ንብረታቸውን በማቃጠል እና በማሳደድ ነው የተሰናበተን፡፡ አዲሱ ዓመት ደግሞ የአሮጌውን ዓመት የደም ግብር መገበርን አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡
ካህኑ በዐውደ ምሕረት በአገልግሎት ላይ እያሉ በጥይት የተመቱት ጠረፍ አካባቢ በምትገኘው አጥቢያ አይደለም፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡
እጅግ ጥቂቱን ያውም ከቅርቦቹ ለማሳያ ያህል አነሣን እንጂ ሞትና ስደት የኦርቶክሳውያን የሰርክ ሕይወት ነው፡፡ የዓመቱ ዕለታት ሁሉ ለኢትዮጵያ ክርስቲያኖች የቀን ጨለማ ሳይሆኑ እንዳያልፉ ከተወሰነ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ እውነተኛውን ክርስትና፣ ኦርቶዶክሳዊ ወንጌልን በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ይዞ መገኘት ወንጀል ተደርጎ ከተቆጠረ ዘመናት ሔደዋል ዘመናት መጥተዋል፡፡ ምላጩን በኦርቶዶክሳውያን እና በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ላይ ለመሳብ የማያወላውለውና የብሔርተኝነት ሒጃብ የተከናነበው አክራሪው የውሃቢያ ኃይል በቻለው መጠን የክርስትናን ዘር ለማጥፋት ያለ ከልካይ ይደራጃል፣ ጥላቻንና ጦር መሣሪያን በታጠቀ ኃይሉ የተደራጀ ጥቃት ሲሻው በገጀራ ሲፈልግ በጥይት ይፈጽማል፡፡ ኢትዮጵያችን ለኦርቶዶክሳውያን የሕግ ጥበቃ ለማድረግ ፍላጎት ያላት አትመስልም፡፡
በሕዝቡ ልብ የሀገር ፍቅርን ጽፋ፣ በልጆቿ ልብ ለሀገር ነጻነትና አንድነት የመሞትን ክብር ቀርፃ እና የአልሸነፍ ባይነትን ወኔ አስታጥቃ ኢትዮጵያን የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ቀንዲል ማድረግ የቻለች ቤተ ክርስቲያን ልጆች ዛሬ በሀገራቸው ተሳዳጆች ሆነዋል፡፡ ይህች የሀገር ትእምርት የሆነች ቤተ ክርስቲያን በፖለቲከኛው ፕሮፖጋንዳ ወደ ጠርዝ የተገፋች፣ የፕሮፖጋንዳው ሰለባዎች በጥላቻ ተሞልተው የሆነ ልጆቿን ለእሳት ለስለት የሚዳርጉባት ተሳዳጅ ሆናለች፡፡
ኢትዮጵያን የነጻነት ትእምርት በማድረግ የአንበሳውን ሚና የተጫዎተች ቤተ ክርስቲያን ልጆች በሀገራቸው ነጻነት አጥተው ለሞት እና ለስደት ተላልፈው ተሰጥተዋል፡፡ የሀገሪቱ ከግማሽ በላይ የሆኑት ዜጎች የሚከተሏት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥርስ የገባች ሃይማኖት ሆናለች፡፡ በተለይ የፖለቲካው መድረክ ‹‹ለውጥ›› ብሎ የጠራው ሒደት ከተጀመረ ጀምሮ ደግሞ ከመንግሥት ባለሥልጣንና የፀጥታ ኃይል ጀምሮ ራሱን ከዐማፅያን ወገን ያደረገው ሁሉ ያለ ከልካይ ዝናሩን የሚያራግፈው ቤተ ክርስቲያን ላይ ሆኗል፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ይገደላሉ፤ ይሳደዳሉ፤ ቤተ ክርስቲያናቸውና ሀብት ንብረታቸው ይቃጠልባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን የመከራ ቋት ውስጥ ገብታለች፡፡ አቤቱታችን በምድር ገዥዎች ፊት ሰሚ አጥቷል፡፡ ባልተጻፈ ሕጋቸው ኦርቶዶክሳዊነትን ወንጀል ያደረጉ ባለሥልጣናት በዝተዋልና፡፡
ይህን ሁሉ ግፍ ማስቆም ካልተቻለ መጭው ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ኦርቶዶክሳውያን በአናሳነት የምንመዘገብበት ጊዜ ላለመሆኑ ዋስትና የለንም፡፡ አልያም የመከራውን ቀንበር የሚሰብር ኦርቶዶክሳዊ ኃይል ግፉን በመጣበት መንገድ ለማስቆም ይነሣል፡፡ የከፋው ሳይመጣ የተሻለውን ለማድረግ ለሚሻ የመንግሥት አካል ጊዜው አሁን መሆኑን ዛሬ መንገር የተገባ ነው፡፡ ኦርቶዶክሳውያንም የመጣብንን የመከራ ዶፍ በተናጠል ሐዘንም ሆነ በተደራጀ ለቅሶ አልያም ከንፈር በመምጠጥም ሆነ ግብረ መልስ በሌለው ቁጭት ብቻ ልናኮላሸው እንደማንችል መረዳት ይኖርብናል፡፡
ለምን ይህ ሁሉ በእኛ ላይ?
ይህን ጥያቄ ሁሉም ክርስቲያን ቤተሰብ ራሱን መጠየቅ አለበት፡፡ ለምን ለሚለው ጥያቄ ከእኛ ምልከታ አንፃር ምጥን መልስ ለመስጠት እንሞክራለን፡፡
እውነትን የያዙ ይሰደዳሉ፡፡ እውነት እና ሕይወት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው (ዮሐ. ፲፬፥፮)፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረቷ እና ጉልላቷ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ጌታም ‹‹በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ ይገድሏችኹማል፤ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ›› (ማቴ. ፳፬፥፱) ብሏል፡፡ እንግዲህ የመከራ ተቀላቢዎች የሆንበት ቀዳሚው ምክንያት ተዋሕዶ ሃይማኖት የሰማያዊው ርስት ተስፈኞች ፍኖት መሆኗ ነው፡፡ በጽድቅ መንገድ ላይ የሚጓዙ ክርስቲያኖችን የሐሰት አባት ከእውነት ጎዳና እንዲወጡ ያለማቋረጥ ይዋጋቸዋል፡፡ በጽድቅ ጎዳና ላይ የጽድቅ ጠላት መሰናክሉን ያስቀምጣል፡፡ በእርግጥ መከራ መስቀሉን መሸከም ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ያለፈችበት ፍኖት ነው፡፡ ከዚያ ዘመን የሚለየው ክርስቲያኖች ለመከራው በምንሰጠው ግብረ መልስ ነው፡፡ እነርሱ መከራውን የክብር በር መክፈቻ ቁልፍ አድርገው ይመለከቱታል እኛ ደግሞ መከራው ያስበረግገናል፤ ወይም ‹‹ልሔድ ከክርስቶስ ጋር ልኖር እናፍቃለሁ›› የሚያስብል ክርስቲያናዊ ሕይወት የለንም፡፡
ክርስቲያን በመሆናችን ምክንያት በተናጥል የሚያጋጥመንን መከራ የክብር በር አድርገን መቀበል ያቃተን ብዙዎች ነን፡፡ የክርስትናን ዘር ለማጥፋት ታልሞ በቤተ ክርስቲያን ላይ እንደ ተቋም የሚሰነዘረውን ጥቃት ግን እንዴት በአኮቴት መቀበል እንዳለብን መካሪዎች ሆነን የምንገኘውም እኛው ነን፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ሁለት ሺሕ ዘመናትን ተሻግራ እዚህ ዘመን ላይ የደረሰችው በመከራ ሸለቆ እያለፈችም ቢሆን የእውነት ቃል የሆነውን ወንጌልን ለአዲሱ ትውልድ ማድረስ በመቻሏ ነው፡፡ የክርስቲያኖች ሰማዕትነት ትርጉም የሚኖረው ብቸኛው የመዳን መንገድ የሆነውን ክርስቶሳዊውን መንገድ ያወቀ እና የተረዳ በእርሱም የሚጓዝ ትውልድ እስከኖረ ድረስ ነው፡፡ አሁን አፅራረ ቤተ ክርስቲያን በኦርቶዶክሳውያን ላይ የከፈቱት የተቀናጀ ጥቃት ግን የክርስትናን ህልውና የሚፈታተን አደገኛ ጥቃት ነው፡፡
ሌላው ይህ ሁሉ መከራ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን ላይ የሚደርስበት ምክንያት የጥቃቱን ክብደት በትክክል ካለመረዳት ሥር የሰደደ ችግር ይመነጫል፡፡ ኦርቶዶክሳውያንን መግደሉ፣ ማሳደዱ እና ሀብት ንብረታቸውን አቃጥሎ ምንዱባን የማድረጉ ዘመቻ በተጋድሎ ላይ ላለችው ቤተ ክርስቲያን (The Church Militant) ቀጥተኛ የህልውና ሥጋት የፈጠረ መሆኑን በተገቢው መጠን መረዳት አለመቻላችን ግልጽ ሆኖ ታይቷል፡፡ ይህ ያለመረዳት ችግር ሕዝበ ክርስቲያኑ ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊ እና ሕጋዊ መብቱን እንዳይጠቀም አዘናግቶታል፡፡
ሦስተኛው ምክንያት ጠንካራ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት መፍጠር አለመቻል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ወደ ውስጣችን በማየት ከውስጥ በቤተ ክርስቲያኗ ልጆች መካከል አንዱ ለሌላው ከለላ መስጠት በሚችል ደረጃ የትብብር መረብ መዘርጋት አለመቻሉ ነው፡፡ ወደ ውጭ በማየትም ዓለም አቀፋዊ እና አካባቢያዊ ለውጦችን በአግባቡ ማንበብ፣ መገምገም እና የገፈቱ ተካፋይ ከሆኑ ኦርቶዶክሳውያን ሀገራት ጋር ክርስቲያናዊ ትብበር (Orthodox Solidarity) መፍጠር አለመቻላችን ለበለጠ ተጋላጭነት አሳልፎ ሰጥቶናል፡፡
ማርቲን ኒይሞለር (1892-1984) የተባለ ጀርመናዊ የፀረ ጦርነት አንቂ (Pacifist and anti-war activist) እና ፓስተር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የጀርመን ናዚዎች ያን ኢሰብአዊነት የተሞላ አሰቃቂ ጥፋት ያደረሱት በእነርሱ ጥንካሬ ብቻ እንዳይደለ በፀፀት ስሜት ሆኖ ደጋግሞ ተናግሯል፡፡ የማርቲን ልምድ እዚህ ላይ መነሣቱ ከታሪክ ለመማር ይረዳን ይሆናል ከሚል ዕሳቤ ነው፡፡ የጀርመን ናዚዎችን የዘር ፍጅት ዕቅድ እንዲያስፈጽም በናዚ የዘር ፍጅት መሐንዲሶች የተቋቋመው ጀስታፓ የተባለው ወታደራዊ ክንፍ ያን ያህል ጥፋት ያደረሰበትን ምክንያት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፤
‹‹ናዚዎቹ ኮሚኒስቶችን ሊወስዱ ሲመጡ እኔ ዝም አልኩ፤ ምክንያቱም ኮሚስት አይደለሁምና፡፡ በካቶሊኮች ላይ ሲነሡ አንዳች ነገር አልተናገርኩም፤ እኔ ፕሮቴስታንት ነኝና፡፡ ሶሻል ዲሞክራቶችን ሊወስዱ ሲመጡ መልሴ ዝምታ ነበር፤ የእነርሱ አባል አይደለሁምና፡፡ አይሁዳውያንን ሊወስዱ ሲመጡም ድምፄን አላሰማሁም፤ አይሁድ ስላልሆንኩ፡፡ መጨረሻ ወደ እኔ መጡ፤ ለእኔ ድምፅ ሊሆነኝ የሚችል አንድስ እንኳ አልነበረም፡፡››
አሁንም በኢትዮጵያውያን የተዋሕዶ ልጆች መካከል ያለው መንፈሳዊ፣ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መደጋገፍ እጅግ የሳሳ ነው፡፡ እርስ በእርሳችን በክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ስንደጋፍ አንታይም፡፡ የዳር ሀገሩ ግፍ የዳር ሀገር ኦርቶዶክሳውያንን ብቻ በልቶ የሚቆም አድርገን ቆጥረነዋል፡፡ ዳሩ ከፈረሰ መሐሉ ዳር መሆኑ ተፈጥሯዊ ሐቅ ነውና ግድያውና ማፈናቀሉ እየዳኸ ወደ መሐል መጥቷል፡፡ አለፍ ብሎም “የአንድ ሰው ሞት አሳዛኝ ነው፡፡ የብዙዎች ሞት ግን የስታትስቲክስ ጉዳይ ነው፤” እንደተባለው ለኦርቶዶክሳውያን ሞት ትኩረት ያለመስጠት የከፋ ቸልተኝነት ይንፀባረቃል፡፡ በሀገራችን እንዲህ ባይተዋር ላደረገን ጉዳይ ጀርባችን ሰጥተን በቸልተኝነት ፍራሽ እስከ መቼ ይሆን የምንተኛው? “አንተ ታካች እስከ መቼ ትተኛለህ; ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሣለህ?” (ምሳ. ፮፥፱)።
ምን እናድርግ የሚለውን ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በቀጣይ ይዘን እንቀርባለን፡፡