የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ፲፬ኛው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ የቃለ ጉባኤ ማጠቃለያ እና የጋራ የውሳኔ ሐሳብ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ፲፬ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ግንቦት 30 እና ሰኔ 1/ 2017 ዓ/ም ከየአህጉረ ስብከቱ የተወከሉ የሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ አባላት፣ የዐዲስ አበባ ሀ/ስብከት አጥቢያ ሰ/ት/ቤቶች አባላት እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተካሔዷል። በመሆኑም በጉባኤው ከቀረቡ ዓመታዊ ሪፖርቶች፣ ተዘጋጅተው ከቀረቡ ጥናታዊ ሰነዶች፣ ከየአህጉረ ስብከት ከቀረቡ አስተያየቶች እና ከጉባኤው ተሳታፊዎች ከተነሡ የውይይት ሐሳቦች ግብዓት በመነሣት ባለ 12 ነጥብ የቃለ ጉባኤ ማጠቃለያ እና የጋራ የውሳኔ ሐሳብ በማውጣት ተጠናቋል፡፡
1.በጠቅላላ ጉባኤው የቀረበውን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነትና የአህጉረ ስብከት አንድነቶች የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትና የተሰጡ የሥራ አቅጣጫዎችን ጠቅላላ ጉባኤው ተቀብሎ ያጸደቀ ሲሆን የሰንበት ት/ቤቶች የ5 ዓመት መሪ ዕቅድ አፈጻጸም በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ጉባኤው ወስኗል።
2.በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀው መሪ ዕቅድን በተመለከተ በትኩረት የምንከታተለውና የብዙ ምሁራን ጊዜ፣ ዕውቀትና ጉልበት የፈሰሰበት ሥራ ወደ ተፈለገው ውጤት እንዳይመጣ የሚደረገው የማሰናከል ሥራ በእጅጉ ያሳዘነን ከመሆኑም ባሻገር እናት ቤተ ክርስቲያናችን ዘመኑን የዋጀ ስልታዊ አካሔድ እንዳትከተል አሉታዊ ተጽዕኖ እና ከፍተኛ ሥጋት አሳድሯል። የመሪ ዕቅድ ትግበራውን በተያዘበት አግባብ ማፋጠን፣ የሊቃውንቱ፣ የካህናት የምእመናን የሰ/ት/ቤት አባላትና ባለድርሻ አካላትን ሚና በሕግ ማውጣት ሥራ ላይ ከፍ እንዲል በአጽንዖት እንጠይቃለን።
3.በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በቃለ ዐዋዲ የተደነገገው የምእመናን፣ የካህናትና የሰንበት ት/ቤቶች ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ ሊኖራቸው የሚገባ የሰበካ ጉባኤ ሱታፌ በጽኑዕ እንዲተገበር እንዲሁም የሰ/ት/ቤት አባላት በጊዜ በጉልበትና በዕውቀት ከሚሰጡት የጎላ አስተዋጽዖ አንጻር ውክልናችን በቁጥር ከፍ እንዲል አበክረን እንጠይቃለን።
4.ልዩ ልዩ የአስተዳደርና የቀኖና ጥሰት እየተፈጸመ የቅድስት ቤተክርስቲያን አንድነቷ እንዲሸረሸር የሚደረጉ ድርጊቶችን በጽኑዕ እንቃወማለን። የቅዱስ ሲኖዶስ ልዕልና እንዲከበር፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲጸና፣ መለያየት እንዲወገድ ፣በዚህም የተፈጠሩ ልዩነቶች ተቀራርቦ በመነጋገርና የበደለ ክሶ፤ ያጠፋ በቀኖና ታርሞ እንዲስተካከሉ፣ በሀገር ሰላምና አንድነት ላይም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የቀደመ ሚናዋን እንድትወጣ እንጠይቃለን።
5.በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለው የሀብት ሥርጭት ፍትሐዊነት መጉደል ቤተ ክርስቲያን ከገጠር ወደ ከተማ እየተሰደደች መሆኗ በግልጽ የሚታይ በመሆኑ ለዚህ ችግር ትኩረት በመስጠት የአጥቢያ ዐቢይ ጉባኤን በማደራጀት ወደ ሥራ እንዲገባ እና በተደጋጋሚ እንደሚነሣው የፋይናንስ አስተዳደሩን የተማከለ የሚደረግበት ሥርዓት እንዲዘረጋ እንጠይቃለን።
6. አብዛኛው የቤተ ክርስቲያኗ ሀብት የሚመነጨው አጥቢያ ላይ በመሆኑ አስፈጻሚ አካላት ገንዘብ መልቀምና መጠበቅ ላይ በሀብት ምደባም ይሁን ለአስተዳደር ሥራ ብቻ ትኩረት በማድረጋቸው ሕፃናትን የማሠማራት፣ ወጣቶችንና ምእመናንን የመጠበቅ ሥራው በአብዛኛው ተዘንግቷል፣ ስለዚኽ ይኽ ጉዳይ በአስቸኳይ እንዲስተካከል እንጠይቃለን።
7.የሰንበት ትምህርት ቤቶች መዋቅር የበጀት ዕጥረት ከፍተኛ በመኾኑ፣ ሥርዓተ ትምህርቱን ማስፈጸም፣ የመጽሐፍ ስርጭቱንና ሌሎችንም ዘርፈ ብዙ የሰንበት ትምህርት ቤት ሥራዎች ከፍተኛ እንቅፋት በመፍጠሩ መፍትሔ እንዲሰጠው እንጠይቃለን።
8.ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት የጠነከረ የኢኮኖሚ አቅምና ማኅበራዊ መስተጋብር ፈጥረው ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጠብቁና ለሀገርም ረብ ያለው ነገር ማበርከት እንዲችሉ የማድረግ ሚናዋን ዘንግታለች፣ ስለዚህም ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በቂ ሀብት በመመደብና ተገቢ አመራር በመስጠት በአባላት ሁለንተናዊ ሕይወት ዙሪያ አስፈላጊ ለውጥ ማምጣት እንዲቻል ጥረት ይደረግ ዘንድ በአጽንዖት እንጠይቃለን።
9.የሰንበት ት/ቤቶችም ኾነ ሌሎች የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን የቅርብ ክትትል የሚፈልግ ኾኖ እያለ ሀገረ ስብከቶቻቸውን በዓመት ለውስን ጊዜያት አንዳንዴም አንዴ ብቻ በሚጎበኙ ሊቃነ ጳጳሳት የተነሣ አገልግሎቶች እየታወኩ ይገኛሉ፤ ስለዚህ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳቱ ሀገረ ስብከቶቻቸውን በተገቢው መልኩ እንዲከታተሉ የሚመለከተው አካል ተገቢ ቁጥጥር እንዲያደርግ በአጽንዖት እንጠይቃለን።
10.የሰንበት ት/ቤቶች ጠቅላላ ጉባኤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነቶች ተወካዮች ተሰባስበው የሚመክሩበት፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚወያዩበት ቀጣይ ሥራዎች የሚተልሙበት ጉባኤ ነው። ይኽ ጉባኤ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ከቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ከሌሎች የሥራ ሓላፊዎች ጋር የሚወያዩበትም ጭምር ነው። ይኹን እንጂ ይኽ ጉዳይ በትክክል ተፈጻሚ እየሆነ አይደለም። ስለዚኽ ይኽ ጉባኤ ከዚህ በኋላ የሚካሔዱ ጠቅላላ ጉባኤያት በቅዱስ ፓትርያርኩ ጸሎተ ቡራኬ ተከፍቶ፤ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቃለ ምዕዳን የሚዘጋ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ተገኝተው የሚመሯቸው እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች እና የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ተገኝተው የሰ/ት/ቤቶችን ጉዳይ በሓላፊነት የሚከታተሉባቸው እንዲኾኑ በአጽንዖት እንጠይቃለን።
11.. በዚኸ ጉባኤ ላይ በተለያዩ ምከንያቶች ያልተገኙ የአህጉረ ስብከት ተወካዮች እንዳሉ ቢታወቅም በተለይ ግን በትግራይ ከልል ከሚገኙ አህጉረ ስብከት ጋር በተፈጠረዉ እጅግ አሳዛኝ መለያየት የተነሣ የክልሉ አህጉረ ስብከት ተወካይ ወንድሞች እና እኅቶች ባለመገኘታቸዉ ጉባኤው ከፍተኛ ኀዘን ተሰምቶታል። ከዚህም በላይ ችግሩ ወደ ምእመናን እየሰፋ መሔዱ ጉባኤውን በእጅጉ አሳስቦታል፡፡ በ13ኛው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አበክረን፣ ከወንበራችን በመነሣት በልመናና በልጅነት መንፈስ መፍትሔ እንዲያገኝ ብንጠይቅም ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባለማየታችንና ይኸ መለያየት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ሔዶ በአንዲቷ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ አደጋና የማይጠገን ስብራት እያደረሰ በመሆኑ ልዩነቶችን አስወግዶ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አግባብ የክልል ትግራይ አህጉረ ስብከት ወደ መዋቅራቸው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ይመለሱ ዘንድ፤ በእኛ በኩል የተቻለንን ኹሉ እንደምናደርግ ቃል በመግባት አሁንም ችግሩን ለመፍታትና እርቀ ሰላሙን ለማምጣት ከፍተኛዉን ድርሻ ሊወጡ የሚችሉት ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን እንደኾኑ እናምናለን፡፡ ይኽንኑ ለመፈጸም ቅዱስነትዎ ቃል ይገቡልን ዘንድ የቤተ ክርስቲያን ልደት ተብሎ በሚታወቀው በዛሬው በዓለ ጰራቅሊጦስ ስም ልክ እንደ አምናው ኹሉ ከመቀመጫችን በመነሣት በታላቅ አከብሮት እና ትሕትና እንጠይቃለን።
12.እነዚህ የ14ኛው ሀገር ዐቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የጋራ የውሳኔ ሐሳብ በቀጣይ የሲኖዶስ ስብሰባ አጀንዳዎች እንዲሆኑ አበክረን እንጠይቃለን።
ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ/ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ