የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ሂደት ላይ ያለውን ጥያቄ በደብዳቤ አሳወቀ

ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ

ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ

የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ሂደት ላይ ያለውን ጥያቄ ለአስመራጭ ኮሚቴው በደብዳቤ አሳውቋል። የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት፤ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን አግባብ የኢጲስ ቆጶሳት ምልመላ፣ መስፈርት እና ሂደት ለሕዝብ ይፋ ሆኖ በግልፅ መከናወን እንደሚኖርበት በደብዳቤው አጽእኖት ሰጥቷል። በተጨማሪም፤ እስካሁን በተኼደበት መንገድ ከተቀጠለ፤ የሕግና የቀኖና ጥሰት፣ እንዲሁም ይሁንታ የማጣት ጉዳይ ሊከሰት እንደሚችል አሳስቧል። ደብዳቤውን የተረከቡት የአስመራጭ ኮሚቴው ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ፣ ደብዳቤውን ለኮሚቴው አቅርበው እንደሚመክሩበት አሳውቀዋል።
በሌላ በኩል፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በግቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የወሰነውን የአዳዲስ ኢጲስ ቆጶሳት ሢመት በተመለከተ በምልዓተ ጉባኤው የተሰየሙት የአስመራጭ ኮሜቴ አባላት ሥራቸውን ያጠናቀቁ መሆኑን በመግለጽ ኮሚቴው አዘጋጅቶ በሚያቀረበው እጩ ኢጲስ ቆጶሳት ምርጫ ዙርያ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ ይቻል ዘንድ በሚል ለሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ምልዓተ ጉባኤ ጠርቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ፤ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ለአስመራጭ ኮሚቴው በደብዳቤ ያሳወቃቸው ጥያቄዎች ከተጠራው ምልዓተ ጉባኤ መስየም እና የመጨረሻ ውሳኔ በፊት ታይተው የተዛቡ አካሄዶች ይስተካከላሉ የሚል እምነት አሳድሯል።