፵፫ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጀመረ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የሚደረገው የመንበረ ፖትርያርክ የጠቅላይ ቤተክህነት ፵፫ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤበዛሬው ዕለት ተጀመረ። በመክፈቻው ጉባኤ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያት ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት “እንደ ዐስራ ኹለቱ ሐዋርያት መንጋውን ትጠብቁት ዘንድ መንገዱን አሳምሩ” በሚለው በቅዱስ ያሬድ ቃል ተነስተው በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መልዕክትን አስተላልፈዋል።

የመጀመርያው መልዕክታቸው አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን “በዚህ ዘመን በሐዋርያት መንበር ላይ ለመንጋውና ለመንግሥተ እግዚአብሔር የተሾምን እንደመሆናችን በመልካም አስተዳደርና በቀና እምነት ልናስተዳድር ይገባል። በአሁን ሰዓት የቤተክርስቲያን አስተዳደር ችግር በብዛት የሚስተዋልበት እንደመሆኑ ይህን ችግር ለመቅረፍ በጥናት ላይ በመመስረት በፍጥነት መስራት ይጠበቅብናል” ብለዋል።

ኹለተኛው መልዕክታቸውም የምዕመናንና የአገልጋዮች ሰቆቃና ሞት ላይ ያተኮረ ነው። በምዕመናንና በአገልጋዮች ላይ እስከ አሁኗ ሰዓት እያጋጠመ ያለውና ያልተቋረጠው እንግልትና ሞት እንደ ምሳሌ በምስራቅ ሸዋ ከነቤተሰቦቻቸው የተገደሉትን አባት በማንሳት እንዲህ አይነቱ ተግባር ሊቆም እንዲገባ መልዕክትን በማስተላለፍ ስብሰባው በይፋ መጀመሩን አብስረዋል።

በመቀጠል ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕርዳርና ምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የሰበካ ጉባኤን ጅማሮና አሁን እስካለበት ድረስ ያለውን ታሪክ በማንሳት ይህን ሥርዓት ላበጁ አባቶች ክብርና ለዚህ ያደረሰንን አምላክ ልናመሰግን ይገባል ብለዋል። በመቀጠልም የመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችን ሪፖርት አቅርበዋል።

ጉባኤውም እስከ ጥቅምት 10 የሚቀጥል ሲሆን የየሀገረ ስብከቶችን የሥራ ሪፖርትና በተለያዩ ጉዳዮች ውሳኔ ይተላለፍበታል ተብሎ ይጠበቃል።