ራስን በራስ መሾም በቤተ ክርስቲያን ላይ ያስከተለው መዘዝ
ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተማርነው አባቶቻችን “ኤጲስ ቆጶስ ሆናችሁ ሕዝበ ክርስቲያኑን ምሩ” ሲባሉ አደገኛ አውሬ እንዳየ የቤት እንስሳ ሸሽተው ይደበቁ ነበር። አባቶች ሢመቱን ይሸሹት የነበረው አንድም በትሕትና ሁለትም በራስ ኃጢአት ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጥፋት መጠየቅ ስላለበት ነው። በዘመናችን የኤጲስ ቆጶስነት ግብሩ የተለየ እስከሚመስል ድረስ ራስን በራስ እስከመሾም ተደርሷል። ከዚያ መንፈሳዊ ልዕልና ወርደን ለዚህ ውድቀት የተዳረግነው የኤጲስ ቆጶስነት ዓላማውና ግብሩ በመለወጡ ነው። ቤተ ክርስቲያ ለመከራ የተዳረገችውም ምእመናንን የሚጠብቁ ሳይሆኑ ምእመናንን ለኃላፊው ነገር መጠቀሚያ የሚያደርጉ ሰዎች አባት መሆን ሳይችሉ አባት ለመሆን መጣራቸው ነው። የኤጲስ ቆጶስ ተግባርና ኃላፊነት የሚያስገነዝበው “ኤጲስ ቆጶስ ማለት የምእመናን ላዕላዊ ጠባቂ ወይም አውራ ጠባቂ ማለት ነው፤ ይህም ማለት በተመደበበት ሀገረ ስብከት የመጨረሻው የምእመናን ጠባቂ እረኛ ማለት ነው ፤ ኤጲስ ቆጶስ በሚሊዮን በሚቈጠሩ ምእመናን ላይ በመንፈሳዊ የጥበቃ አገልግሎት የተሾመ ነው። ይህም በመሆኑ የሚሊዮኖች ዓይኖች እሱን ይመለከታሉ፤ ትምህርቱን፣ ንጽሕናውን፣ ቅድስናውን፣ ትጋቱን፣ ሃይማኖቱን፣ ጸሎቱን፣ ፍቅሩን፣ አመራሩን፤ አኗኗሩን፤ አነጋገሩን፣ በአጠቃላይ ሁለንተናዊ ሕይወቱ ለምእመናን ዓይንና አእምሮ የተጋለጠ ነው፡፡ ታዲያ ኤጲስ ቆጶሱ አኗኗሩ ሁሉ በእግዚአብሔር ቃል ብቻ የሚመራ ከሆነ ለብዙዎች መዳን መሪና ፊታውራሪ ነው” በማለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት በተሾሙበት ዕለት የተናገሩት ነው። ከቅዱስነታቸው ንግግር ብዙ ቁም ነገሮችን መረዳት ይቻላል። የመጀመሪያውና ዋናው ጉዳይ ኤጲስ ቆጶስ ለአገረ ስብከቱ ምእመናን ትጉህ ጠባቂ መሆኑ መነገሩ ነው። ትጉህ እረኛ ደግሞ በሁሉ ነገሩ አርአያ መሆን ይጠበቅበታል። አርአያ ሳይሆን መንፈሳዊነት ሳይኖረው አባት መሆን ያስከተለው መዘዝ ኤጲስ ቆጶስ መሆን እንዲህ የቅምጥል ኑሮ ከሆነ ሌላ እስከሚሾመኝ ለምን እጠብቃለሁ ራሴን በራሴ ለምን አልሾምም እስከማለት ያደርሳል። የኤጲስ ቆጶስ ዓላማና ግበሩ ሲቀየር የሚከተለውን ነገር ቅዱስነታቸው የገለጡት “ያ ካልሆነ ደግሞ ለብዙዎች መሰናክል ይሆናል” በማለት ነው። በእውነቱ አባት ተብሎ የአባትነት ተግባርን በሚገባ ካለመወጣት የከፋ ምን ውርደት አለ? ጥር ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በምዕራብ ሸዋ የተፈጸመው ሢመተ ኤጲስ ቆጶስ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ያፈነገጠ መሆኑ ሲገለጥ የከረመውም ምእመናንን አባት ሆኖ ሊጠብቅ የሚሰጠው ኃላፊነት አባቶቻችን ከሠሩልን ቀኖና ባፈነገጠ መንገድ መፈጸሙ ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የገጠማትን ችግር ለማስወገድ የሚቻለው ራስን በራስ በመሾም ሳይሆን መንፈሳዊነትን ገንዘብ አድርጎ በትሕትና በመቅረብ ነው።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፲፭ በተካሔደው የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ላይ “በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ባልተጠበቀና ባልተለመደ ሁኔታ ብቅ ብቅ ሲሉ የሚታዩት ራስን በራስ የመሾም አባዜ መገታት አለባቸው። ማንኛውም ችግር በውይይትና በምክክር የተበደለውንም በትክክል በመካስ መፈታት ይገባዋል። ከዚህ ውጭ በጥፋት ላይ ጥፋት እየተከሠተ የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚፈታተን ድርጊት ማቆም አለብን” በማለት የተናገሩት እየተፈጸመ ያለውን ጉዳይ በትክክል የገለጠ ነው። ቅዱስነታቸው እንደገለጡት ራስን በራስ የመሾም አባዜ የተጠናወታቸው አካላት ቢኖሩም እንዲህ ያለውን ድርጊት ከቤተ ክርስቲያን ቆርጦ የሚጥል አሠራር መከተል ይገባል። ዋናውና ቀዳሚው ተግባር ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን አክብሮ በመሥራት ራሳቸውን በራሳቸው ለመሾም እንቅልፍ የሚያጡትን ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማድረግ ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን መታረም የሚኖርበት ኤጲስ ቆጶስነትን የጊዜያዊ ጥቅም ማግኛ አድርገው የሚያስቡ ወገኖችን አስተሳሰብ ቀይሮ ኤጲስ ቆጶስ ማለት ኖላዊ፣ እረኛ፣ ትጉህ ጠባቂ መሆኑን የሚያስገነዝብ በተግባር የተፈተነ ሥራ መሥራት ነው።
እግዚአብሔርን ብቻ ያስቀደመ ለማንም የማያደላ አሠራር ተግባራዊ ከተደረገ የኤጲስ ቆጶሳትን ኃላፊነት የተረዱትን ብቻ መሾም ይቻላል። እስከ አሁን ስንሠራበት ኖረናል በማለት ቤተ ክርስቲያን ልትወጣው ከማትችለው መከራ ውስጥ የሚጥል ተግባር መፈጸም ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። በዚህ መንገድ ወደ ኤጲስ ቆጶስነት የሚመጡ ግለሰቦችን አባቶቻችን ብሎ በሙሉ ልብ የሚቀበላቸው ወጣት አያገኙም። በዚህ ተግባር የተባበሩትንም መከራ ቢገጥማቸው እንደገባችሁ ተወጡት ይላል እንጂ አብሯቸው እንደማይቆም መረዳት ያስፈልጋል። ቅዱስነታቸው በማስከተል “ሊቃነ ጳጳሳት የምንናገረውንና የምናስተምረውን፣ የምንመራውንም ሕዝብ በውል አውቀን ትክክል መምራትና ማገልገል ይገባናል፡፡ ችግሩ እየመጣ ያለው ከውጭ ሳይሆን ከእኛው ከራሳችን ነው፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ከሁለተኛ ፓትርያርክ አንሥቶ እስካሁን የመጣንበት ጉዞ ሲገመገም አመርቂ አይደለም፡፡ አካሔዳችን ሁሉ ለፈተና የሚዳርግ ነበረ። አሁን ወደ ልባችን እንመለስና ቤተ ክርስቲያንንና ቤተ ክርስቲያንን ብቻ ማእከል አድርገን መሥራት አለብን፡፡ ኤጲስ ቆጶሳትን መሾም የጐደለውን ለመሙላት እንጂ የጐደላቸውን ለመሙላት አለመሆኑ ሊሠመርበት ይገባል” በማለት የተናገሩት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተበላሸውን ለማስተካከል፣ የጠመመውን ለማቅናት፣ የጎደለውን ለመሙላት፣ የተዛለፈውን ለመመለስ ከእስከ አሁኑ በበለጠ ብዙ መሥራት ብቻ ሳይሆን የአስተዳደር ለውጥ ማድረግ እንዳለባት የሚያስገነዝብ ነው። እንዲህ ያለውን እውነት ከመናገር ባለፈ ወደ ተግባር መቀየር ቤተ ክርስቲያንን ከጥፋት ይታደጋል። በልጆቿ ላይ የተፈጠረውን ብዥታም ያጠራል ብለን እናምናለን። ቅዱስነታቸው “ከሁለተኛ ፓትርያርክ አንሥቶ እስካሁን የመጣንበት ጉዞ ሲገመገም አመርቂ አይደለም። አካሄዳችን ሁሉ ለፈተና የሚዳርግ ነበረ” በማለት የተናገሩት ኃይለ ቃል ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ኀምሳ ዓመታት ያሳለፈችውን መከራ በግልጥ የሚያሳይ ነው። የሚገርመው ደግሞ የፈተናው ምንጭ ከውጭ ልቅ ከውስት በተለይም ከጳጳሳት መሆኑ መገለጡ ነው። መታወቅ ያለበት ቅዱስነታቸው ቢገልጡትም ምእመናን የማያውቁት አለመሆኑ ነው። ቤተ ክርስቲያን ለኀምሳ ዓመታት የተጓዘችበት መንገድ ውጤታማ ካልሆነ የአሠራር ብልሃትን፣ የአመራር ዘይቤን መቀየር ይገባል። ችግሩን የሚፈጥሩት ጳጳሳት መሆናቸው ከታመነበትም በሃይማኖትም፣ በምግባርም የተመሰከረላቸውን አባቶች መርጦ መሾም ቀዳሚው ተግባር ሲሆን ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን የሚዳፈሩትንም ሥርዓት ማስያዝ፣ አልታረም ብለው በጥፋታቸው ሲገፉበትም አውግዞ መለየት ይገባል።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ማካሔድ አንዱ ተግባሩ ከዘመናት አስቀድሞ በአባቶች የተሠሩ ቀኖናዎችን የዘመኑን ችግር ለመፍታት በሚያስችል መልኩ መተርጎም መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። አጠያያቂ የሚሆነው ካለሥርዓት መጓዝ ነው። ከቀኖናዎች አንዱ በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ የምእመናን ተሳትፎ ነው። ከዚሁ ጋር የሚሔደው ለኤጲስ ቆጶስነት የሚመጥኑ አባቶችን አፈላልጎ እንዲያቀርብ ኃላፊነት የተሰጠው ኮሚቴ የምርጫ መስፈርቱን ግልጽ አድርጎ በዚያ መመራት የሚገባው መሆኑ ነው። ይህን የምናነሣው ያለፈው ነገር እንዳይረሳ ሳይሆን ጥፋቱ እንዳይደገም ነው። ቅዱስነታቸው የመሰከሩለትን አባት ተገኝቶ ለኤጲስ ቆጶስነት የሚመረጠው የማንም ጣልቃ ገብነት ሳይኖር በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ሲፈጸም እንጂ በወገንተኝነት ሲከናወን አይደለም። በያዝነው ዓመት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያሳለፈችውን ፈተና እንኳን በውስጧ የምንገኘው ክርስቲያኖች ዓለም ሁሉ የተረዳው እውነታ ነው። ዘመኑን መዋጀት ማለትም ችግሩን እየተናገሩ ከችግሩ ጋር መኖር ሳይሆን ችግሩን ከቤተ ክርስቲያን ነቅሎ የሚጥል ተግባር መፈጸም ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የገባችበትን አጥብቂኝ ሐምሌ ፱ ቀን በተፈጸመው ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት አባቶቻችን ተናግረውታል። እኛም እናውቀዋለን። እንዲህ ያለውን ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት እንድታካሔድ ያስገደዳትም ይህ ነው። ፈተና ከቤተ ክርስቲያን ተለይቶ ስለማያውቅ ወደ ፊት ከዚህም የከፋ ችግር ሊከሠት ስለሚችል መንግሥትንም ሆነ ሌሎች አኩራፊ አካላትን ለማስደሰት በማሰብ የሚፈጸም ሢመትም ይሁን ሌላ ነገር በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ለይቶ አባቶቻችንን ከምእመናን እንዳያቆራርጣቸው ለወደፊቱ ከወገንተኝነት የጸዳ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ ነው። የተፈጸመውን ድርጊት ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ ነው በማለት ብዙዎች ቢተቹትም የተጋረጠውን መከራ ለመሻገር የተፈጸመ መሆኑን የሚጠቁም መልእክትም ሲተላለፍ ሰምተናል። ያለፈውን መመለስ ስለማይቻል የሚገባው ለወደፊቱ ትምህርት ወስዶ እግዚአብሔርን ብቻ የሚያስደስት ተግባር ለመፈጸም ወስኖ በሥራ ላይ ማዋል ነው። ለኤጲስ ቆጶስነት የሚመጥን አባት አፈላላጊ ኮሚቴው የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት በሚገባ መወጣት አለመወጣቱን መገምገም የሚቻለው በግንቦቱ ርክበ ካህናት የተሰጠውን ተግባር ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ኮሚቴው የፈጸመው ተግባር ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ችግር ለመፍታት እገዛ የማያደርግ መሆኑን ብዙዎች ቢስማሙበትም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አጣብቂኝ ውስጥ በመግባቷና አማራጭ በማጣቷ የተወሰነውን የማኅበረሰብ ክፍል ለመታደግ የተገበረችው መሆኑን ገልጣለች። እንዲህ ያለው አሠራር መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ ሌላ ችግር እየያዘ አባቶችንም ከትክክለኛው አሠራር እያወጣቸው፣ ከእግዚአብሔርም ከሰውም እየለያቸው ስለሚሔድ ለወደፊቱ መጠንቀቅ ብልህነት ነው። በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ራስን በራስ መሾም ባይለመድም፤ እንዲመረጡ ልዩ ልዩ ምድራዊ ድርጊቶችን ፈጽመው መሾማቸው ራስን በራስ እንደመሾም ይቈጠራል።
በዘመናችን ትኩረት ሊሰጠውና ቤተ ክርስቲያንም አባቶችን ከማመንኮሷና አባት ከማለቷ አስቀድሞ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጥንቅቅ አድርገው እንዲረዱ ማስተማር ይገባታል። “በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ባልተጠበቀና ባልተለመደ ሁኔታ ብቅ ብቅ ሲሉ የሚታዩት ራስን በራስ የመሾም አባዜ መገታት አለባቸው:: ማንኛውም ችግር በውይይትና በምክክር የተበደለውንም በትክክል በመካስ መፈታት ይገባዋል። ከዚህ ውጭ በጥፋት ላይ ጥፋት እየተከሠተ የቤተ ክርስቲያንን ህልውና የሚፈታተን ድርጊት ማቆም አለብን” በማለት ቅዱስነታቸው የተናገሩትን ችግር ማስወገድ የሚቻለው እንዲህ ያሉ ግለሰቦች ወደ ሢመት እንዳይመጡ የሚከለክል ሥርዓት ተግባራዊ ሲሆን ነው። ሥርዓት ይበጅ የምንለው የተሠራው ቀኖና በቂ አይደለም ብለን ሳይሆን አባቶቻችን የሠሩት ያለማንም ጣልቃ ገብነት በተግባር ይገለጥ ለማለት ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫን በተመለከተ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሁለንተናዊ አገልግሎቷን ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ ሁለት ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅባታል ብለን እናምናለን። የመጀመሪያው ለዘመናት ስትሠራበት የኖረችውን የአብነት ትምህርት አጠናክሮ በመቀጠል ሃይማኖት ከምግባር የሠመረላቸው አባቶችን ማግኘት ነው። ሁለተኛውና ከዚሁ ጋር የሚዛመደው ወደ አብነት ትምህርት ቤት የሚገቡ ሕፃናትን ከሁሉ አስቀድሞ የሰውን ልጅ ክብር በሚገባ ማስተማር ነው። ሃይማኖተኛ ሰው የቋንቋ፣ የጎሳ፣ የአካባቢና የሌላም ተጽዕኖ የማያሸንፈው፣ የሰው ልጅ ሁሉ አባት እናቱ፣ እኅት ወንድሙ መሆኑን እንዲያምን ከሕፃንነት ጀምሮ አእምሮውን መገንባት ያስፈልጋል። እግዚአብሔርን የሚያከብሩ በአደራነት የተሰጧቸውን ምእመናን ለድኅነት የሚያበቁ አባቶችን ማግኘት የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው። በዚህ መንገድ ቤተ ክርስቲያን ጠንክራ ከሠራች ራሳቸውን በራሳቸው የሚሾሙ አባቶች ኤጲስ ቆጶሳት ሆነው ለመቅረብ የሚጓዙበት መንገድ ይዘጋል። ቅዱስነታቸው እንደገለጡት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለኀማሳ ዓመታት የተጓዘችበት መንገድ ራሳቸውን በራሳቸው የሚሾሙ ግለሰቦች ወደ ኤጲስ ቆጶስነት እንዲመጡ ምክንያት ከሆኑ የሚያስፈልገው ማርሽ ቀያሪ የሆነ ተግባር መፈጸም ነው ብለን እናምናለን