ብሔር ተኮር ሃይማኖታዊ ስብከት

ብሔር ተኮር ሃይማኖታዊ ስብከት

ብሔር ተኮር ሃይማኖታዊ ስብከት

ቤተ ክህነቱ ታሟል

ጎሣን መሠረት ያደረገው የሀገራችን ፖለቲካ ኢትዮጵያዊነት ዕሴቶችን በማፈራረስ ሀገር የቆመበትን መሠረት ለመናድ መዶሻውን ካነሣ ምእተ ዓመት ሊያስቆጥር የመጨረሻው ሩብ ክፍለ ዘመን ብቻ ቀርቶታል፡፡ በሀገረ ምሥረታው ሒደት ምትክ የለሽ ሚና የተጫወተችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥፋቱ ሰለባ የሆነችው ገና ከጅምሩ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አሐቲነት አደጋ ላይ የወደቀበት እና በከፋ የፈተና ማዕበል እየተናጠች የምትገኝበት ዘመን ላይ መሆናችን ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡
በኦሮምያ ክልል የሚገኙ ጥቂት የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች ፖለቲካውን ተገን አድርገው አሐቲነቷን በሚፈታተን መንገድ ክልላዊ ቤተ ክህነት በማቋቋም ውስጣዊ አንድነቷን ለመስበር ፈታኝ ዘመቻ አደረጉ፡፡ እነርሱን አርአያ ያደረጉ በትግራይ የሚገኙ ጥቂት አገልጋዮችም በቤተ ክርስቲያን ላይ የቀደመውን ተጨማሪ ፈተና ለመሆን የምእመናንን አንድነት ለመክፈል በመሞከራቸው ቅዱስ ሲኖዶስ አውግዟቸዋል፡፡ መሠረቱን ዘውግ ያደረገው ፖለቲካ በትግራይ ክልል የሚገኙ አፈንጋጮችን አቅፎ ደግፎ ይዟል፡፡ ለገለልተኛ አካልን ጭምር በሚያሳዝን መልኩ መንግሥት መንግሥታዊ ሓላፊነቱን ቸል ብሎ በሕግ ዕውቅና ያላትን የሀገር አድባር፣ የነፃነት ፈር ቀዳጅ፣ የሥልጣኔ ማእከል የሆነችው ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ከባድ ችግር ላይ እንድትወድቅ አድርጓል፡፡ ሕግ የማስከበር ሓላፊነት ያለበት ማእከላዊ መንግሥት መንፈሳዊ አባትነታቸውን በፖለቲካዊ እሳቤ ገድበው ምድራዊ ዘውገኝነትን የመረጡ ውጉዝ ጳጳሳት ከፖለቲካ አመራሩ ጋር በቅንጅት የሚያደርጉትን ለሀገር የሚተርፍ አፍራሽ ተግባር ቤተ ክርስቲያን ብቻዋን እንድትጋፈጥ ትቷታል፡፡ ይህ አእምሮ ላለው ታሪክ ታዛቢ ሁሉ በሚያሳፍር እና የሚያሳዝን ተግባር ነው፡፡
ውስጣዊው የቤተ ክርስቲያን ፈተና ሁሌም የተዳከመች ቤተ ክርስቲያንን የማየት ዓላማ አንግበው ለሚንቀሳቀሱት የውጭ ጠላቶች ምቹ መደላድል ፈጥሮላቸው ውሻ በቀደደው ዘው ብለው ገብተዋል፡፡ የትግራይን ቤተ ክህነት ለማዋለድ፣ አዋልደው ለማሳደግ ጎምበስ ቀና የሚሉ መናፍቃን ከመጋረጃው ጀርባ በዝተው የታዩት በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ከመጀመሪያውም ፖለቲካውን እና ፖለቲከኞችን ተከልለው ይህን አጀንዳ በኦሮምያ ለሚገኘ ጥቂት አልጋዮች የሸጡት መናፍቃን ናቸው፡፡ እነዚህ ፀረ ቤተ ክርስቲያን ኃይሎች ጥቃታቸውን የከፈቱት በሰዓቱ መሥራት የሚገባንን እንዳንሠራ አሥሮ የያዘንን ቤተ ክህነታዊ ደዌ ተከልለው ነው፡፡ ይህም ቤተ ክህነቱ ለወንጌል አገልግሎት ድንዙዝ ለግለሰቦች ብልጽግና ደግሞ ንቁ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ለማስፈጸም ልፍስፍስ የግለሰቦችን ኪስ ለሚያደልብ ሥራ ፍጡን መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው፡፡ ለዚህ በሽታው በጊዜ መድኃኒት ካልተገኘለት ለወንጌል ሥምሪት እንዲያገለግል የተሠራው ቤተ ክህነታዊው መዋቅር ለወንጌል አገልግሎት መሰናክል ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ቤተ ክርስቲያንን ከግራ ቀኝ የሚያዋክባትን ውጫዊና ውስጣዊ ማዕበል አሸንፋ አራራትን ፍለጋ በምታደርገው አድካሚ ጉዞ የቤተ ክርስቲያን መሪ የሆኑት ጳጳሳት የመሪነት ሚና፣ የአመራር ክህሎት ወሳኝ ነው። እነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ከብዙ ምእተ ዓመታት በኋላ አሁንም የሚታወሱትና አብነት ተደርገው እንዲታወሱ ካደረጓቸው በርካታ ምክንያቶች አንዱ በመከራ ሰዓት ሕዝበ ክርስቲያኑን ለመታደግ በፈጸሙት አይረሴ መንፈሳዊ ተጋድሎ ነው። በዚህ ዘመን ግን መርከቧን በማዕበልና ወጀቡ መካከል አሳልፈው አራራት ላይ መልኅቋን እንድትጥል ለማድረግ ከልብ የሚተጉ አባቶች ቁጥር አንሶ ውጥንቅጡን አክፍቶታል፡፡ የምእምናንን አንድነት ለመጠበቅ መንፈሳዊ ሥልጣን የተሸከሙ ጥቂት የማይባሉ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የሚቀዝፉበት መቅዘፊያ በአድልዎና በወገተኝነት የተሠራ በመሆኑ መርከቧን ወደ ወደብ ሳይሆን ወደ ጥልቁ ለመውሰድ እየተፍጨረጨሩ ነው፡፡
ዛሬ ሁሉም በዘውግ መረብ ተጠልፎ ያለ አድልዎ ለመንጋው ሁሉ የሚራራ እረኛ ከንፍሮ ጥሬ ለማግኘት እንደ መድከም ተቆጥሯል፡፡ ቤተ ክህነቱ በዘውገኝነት በሽታ ከተጠቃ ቆየት ቢልም በዚህ ዘመን በሽታው የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በተለይ መንፈስ ቅዱስ ለመንጋው ሁሉ እንዲጠነቀቁ የሾማቸው ጳጳሳት በዚህ በሽታ መጠቃት አራራትን የማይደረስበት ተምኔታዊ ወደብ አድርጎታል፡፡ ይህን መሰል መታመም የምሥራቅ አውሮፓ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችም ታመውት ነበር፡፡
በኦቶማን ተጽዕኖ ሥር የነበሩ ከምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ወገን የሆኑት የባልካን ኦርቶዶክሳውያን ከቱርክ አገዛዝ ራሳቸውን ነጻ ለማውጣት ከፍ ያለ ብሔርተኝነት የተንፀባረቀበት ትግል አድርገው ነበር፡፡ እነዚህ ሕዝቦች በብሔር ተኮር ሃይማኖታዊ ስብከት ተፈትነው እንዳለፉ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ሀገራቱ ያለፉበትን ተመሳሳይ ችግር ደብተራ በአማን ነጸረ ተኀሥሦ በተሰኘ መጽሐፋቸው በጨረፍታ ዳስሰውታል፡፡ በዳሰሳቸው ቤተ ክርስቲያንን በየብሔሩ መሸንሸን ኩላዊነቷን የሚጋፋ፣ ቤተ ክርስቲያንን በየብሔሩ ልክ የሚሠፋና የሚያጠብ እንደሆነ በማሥረጃ ይሞግታሉ፡፡ እንዲሁም ወንጌልን ሳይሆን ብሔርን መነሻ ያደረገ ሃይማኖታዊ ማንነት የመገንባት እንቅስቅሴ ቤተ ክርስቲያንን ከመሠረታዊው ተልእኮዋ የሚያናጥባት አደገኛ ነገር መኾኑን በመረዳት የምሥራቅ አውሮፓ ኦርቶዶክሶች መንገዱን በጉባኤ አውግዘው አካሔዳቸውን ማረማቸውን ደብተራው በመጽሐፋቸው ያስረዳሉ፡፡
በጎሳ ላይ የተመሠረተው ፖለቲካ ከፍ ባለ ዲሞክራሲያዊ ባህል በሌለበት ሀገር ውስጥ ሊተገብሩት የሚያስቸግር ነጽሮት እንደሆነ በርካታ ዓለም አቀፍ ልኂቃን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ዘር ቀለም ሳያግዳት ለዓለም ሁሉ የሞተውን የክርስቶስ ኢየሱስን ወንጌል ለሁሉም የማድረስ ሐዋርያዊ ተልእኮ ከተሸከመችው፣ ድንበር ተሻጋሪ ቤተ ክርስቲያን ባሕርይ ጋር ፍጹም አይስማማም፡፡ እንኳን በአንድ ብሔረሰብ በአንድ ሀገር ጥላ ሥር መገደብ ከኩላዊነት ባሕርይዋ ጋር ይጣላል፤ በብሔር መከፋፈሉ ከአሐቲነቷ ጋር ይጋጫል፤ ከማይሻር ቅድስናዋ ጋር አይሔድም፡፡ ይህን እውነት መቀበል ያልፈለጉ፣ ከክርስትናቸው ይልቅ በብሔር ተኮር ሃይማኖታዊ ስብከት ይገኛል ብለው ያሰቡት ሹመት ወይም ሌላ ምድራዊ ጥቅም ያማለላቸው አገልጋዮቿ በሞከሩት ስዒረ-ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያን ታወከች፡፡ አፅራረ ቤተ ክርስቲያን አጋጣሚውን ተጠቅመው በልጆቿ መካከል የመለያየትን አጥር በእሾህ ለማጠር እየተረባረቡ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን አሁንም እንደ ክርስቶስ እንደራሴነታቸው ለሰው ልጅ ሁሉ ሊኖራቸው የሚገባውን ወገንተኛነት ቸል ብለው በዘውገኝነት በሽታ ጥላ ሥር የተሰባሰቡ ጳጳሳትን ጉዳይ ፈር ማስያዝ ካልቻለች የመጭው ጊዜ ፈተና ከባድ ይሆንባታል፡፡ ይህን የማድረግ ሓላፊነት ደግሞ የሲኖደሱ ብቻ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሁላችን ናትና የእያንዳንዱ ምእመን ሱታፌ ወሳኝ ነው፡፡ ከዛሬ ብንዘገይም ከነገ ለመቅደም እንዲቻል የምእመናን ሱታፌ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ወደ ነበረበት መንበር መመለስ አለበት፡፡ ምእመናንን በኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ እና በወሳኝ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ከነበራቸውን ሕጋዊ፣ ጥንታዊ እና ትውፊታዊ የውሳኔ ሰጭነት ሚና አራቁቶ ቤተ ክርስቲያንን በዘውገኝነት ለታመሙ ጳጳሳት አሳልፎ መስጠት በመጭው ዘመን ተልእኮዋ ላይ መሰናክል ማስቀመጥ ነው፡፡ ለዚህ ነው የለውጥ ጅማሬ መሆን የሚገባው ለምእመናን ሱታፌ ዕድል ፈንታ የሚነፍገውን በቅርቡ “የተሻሻለውን” ሕገ ቤተ ክርስቲያን በመከለስ ነው፡፡