“ልባችሁ በጸጋ ቢጸና መልካም ነው እንጂ በመብል አይደለም” ዕብ. ፲፫፡፱
በቅርቡ የመስኖ ፕሮጀክት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌለውን ጥናት በመጥቀስ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው የሚከተለውን ጽሑፍ አጋርተዋል።
በግርድፉ ወደ አማርኛ ሲመለስ “ጤናማ አመጋገብ፣ የምግብ ብዝኀነት እና የምግብ ዋስትና ማኅበራዊ ጤናን፣ የሥራ ምርታማነትን፣ ጤናማ ሰብአዊ ግንኙነትን፣ ሰላምና የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማምጣት ቁልፍ ሒደቶች ናቸው። የኢትዮጵያ አመጋገብ ባህል (በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያ) በሃይማኖት ተጽፅኖ ሥር የወደቀ ስለሆነ ጤናማ ላልሆነ አመጋገብ አጋላጭ ነው። እነዚህ ችግሮች ካልተፈቱ ወደ ብልጽግና፣ ሰላም እና መረጋጋት የሚደረገው ጉዞ ዘላቂነት አይኖረውም። ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ የሚያቃውሰው የግለሰብ ጤናን ብቻ አይደለም። ኃይልን ያዳክማል፤ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ጨምሮ ውሳኔ መስጠት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነትን ያዛባል፤ ግጭቶችን ያመጣል” የሚል ነው። ይህ ስም ማጥፋት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ በግልጽ ከተቃጡ የአሳብ ጦርነቶች አንዱ ነው።
በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ አካላት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተለያዩ ስም ማጥፋቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል። አንዳንዶቹ በዓላትን በማብዛት ለብሔራዊ ድኅነት ተጠያቂ ያደርጓታል፤ ሌሎች ለቅዱሳን ዝክር፣ ለሙታን ተዝካር ሀብት ንብረት በማባከን ይወቅሷታል፤ እነዚህ ደግሞ ጾም በማብዛት ሰዎች ጤናቸው እና የማሰብ ችሎታቸው እንዲቀንስ እንዳደረገች እየከሰሷት ይገኛሉ። ቤተ ክርስቲያን ግን ከእነዚህ ሁሉ ክሶች ነፃ ናት። ሆድን የፈጠረ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ምግብ እንደሚስፈልገው፣ እንዳዘጋጀለትም ታምናለች፣ ታውቃለች፤ ታስተምርማለች። ምግብ መብላትንም አትቃወምም። ነገር ግን “ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን” በሚለው ክርስቲያናዊ አስተምህሮዋ ልጆቿ ለመኖር እንዲመገቡ እንጂ ለመብላት እንዲኖሩ አትፈቅድም። እንዲህ ያለው መፈክር ለመብል ብቻ ለተፈጠርን ለሚመስላቸው ነው። ምግብ ለሰው ልጅ ኑሮ አስፈላጊ ቢሆንም ሰው የተፈጠረው ከመብልና ከመጠጥ ላለፈ ዓላማ መሆኑን ዕለት ዕለት ትሰብካለች። የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ሳይንስ ስለደገፈው እውነት፣ ስላልደገፈው ደግሞ ሐሰት የሚባል አለመሆኑን መረዳት ይገባል። ተመራማሪዎች ጾም አስፈላጊ ስለመሆኑ፣ የሚጾሙ ሰዎች ከማይጾሙ ሰዎች ይልቅ የተረጋጉ፣ የልብና የስኳር መጠናቸውን በመጠበቅ የተሻለ ጤና ያላቸው ስለመሆናቸውና ረጅም ዕድሜ የሚኖሩ እንደሆኑ በጥናት ማረጋገጣቸውን እየመሰከሩ ባለበት ወቅት ሥልጣንን መከታ አድርጎ ጥላቻን መዝራት ተገቢ አለመሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን። የሰሞነኛ ክስ ምንጩ ሰበብ እየፈለጉ ኦርቶዶክሳውያንን እና ለሆዳቸው አለመፈጠራቸውን የሚያምኑትን ማሸማቀቅ ነው።
ምኞታቸውን በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ ያካፈሉት ባለሥልጣን ከልጥፉ ጋር አንድ ጥናት ያያያዙ ቢሆንም ጥናቱ እርሳቸው ስለሚሉት ጉዳይ የሚጠቅሰው ነገር የለም። ጥናቱ የተሠራው በራሳቸው እና በሌሎች ሁለት ግለሰቦች የተደረገው ጥናት “Smallholder milk market participation, dietary diversity and nutritional status among young children in Ethiopia” የሚል፣ ትኩረቱም በወተት ተጠቃሚዎች ላይ ነው። እርሳቸው ያለ ዐውዱ ቢጠቅሱትም ከተባለው ጉዳይ ጋር ፈጽሞ ግንኙነት የለውም። ደግሞስ ጾም የሚጾሙ በአብዛኛው ከዐሥር ዐመት በላይ የሆኑ ሰዎች ናቸው። ሕፃናት ከእንስሳት ተዋጽዖ አይከለከሉም። የተመጣጠነ ምግብ መመገብም በሃይማኖት የተከለከለ አይደለም። ስለሆነም አቅርቦቱ በሌለበት፣ ብዙዎቹ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ እየገፉ የሚበሉት አትተው በሚሰቃዩበት አገር የተመጣጠነ ምግብ የማይመገቡት በሃይማኖቱ እንሌመገቡ ስለተከለከሉ ነው የሚል አሳብ ማቅረብ ሃይማኖቱን መጥላት፤ ሕዝብንም መናቅ ነው። ባለሥልጣኑ ሃይማኖትን ለመንቀፍና ቤተ ክርስቲያንን ለመውቀስ ብቻ የራስን አሳብ ያለ ማስረጃና ማረጋገጫ እንደ ተጨባጭ እውነት ማቅረባቸው በእጅጉ የሚያስነቅፍ ነው።
በቅዱሳን መጻሕፍት ብዙ ቅዱሳን ያለ ምግብ ወይም መናኛ ምግብ በመመገብ አገርንም ቤተ ክርስቲያንንም በሰላም ሲመሩ ኖረዋል። እንዲያውም ክርስትና ከድሎትና ከምቾት ጋር ስምም አይደለም። ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ ሐዋርያውያን አበው፣ ዐቃብያነ እምነት፣ ቅዱሳን ሊቃውንት፣ ቅዱሳን ሰማዕታት እና ቅዱሳን ጻድቃን አልጫን ዐለም በቅድስና ሕይወታቸው ያጣፈጡት የላመ የጣመ እየበሉ አይደለም። በብሉይ ኪዳንም በ፳፯ አገሮች ላይ የተሾመው ነቢዩ ዳንኤል ይህን የመሪነት ሥራውን ያከናውን የነበረው “ሐሰተኛ ምሁራን” እንደሚሉት የተመጣጠነ ምግብ እየተመገበ ሳይሆን የንጉሡ ምግብ እንዳያረክሰው በማሰብ ቆሎ እየቆረጠመ ነበር። ለዐሥር ቀን ቆሎ እየቀመሱ የሰነበቱት ሠለስቱ ደቂቅ ንጉሡ እንዲመገቡ ካዘዘው ይመገቡ ከነበሩት አምሮባቸውም፣ በአእምሮ ልቀውም መገኘታቸው ጤና የሚጠበቀው በምግብ ሳይሆን ምግብን በፈጠረ እግዚአብሔር መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው።
ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገዳመ ቆሮንቶስ ከቆመበት ሳያርፍ፣ ከዘረጋበት ሳያጥፍ ለአርባ ቀናት መጾሙ፣ ስንጾምም እንዴት መጾም እንዳለብን ማስተማሩ ጾም ለሰው ልጆች አስፈላጊ መሆኑን መግለጹ ነው። በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ የጾም አስፈላጊነት ክርክር የማይነሣበት ዶግማ ነው። የሰይጣንን ፈተና ድል ለመንሣትም ዋና መሣሪያችን መሆኑን ሁልጊዜ ስለ ምግብ እንድናስብ በማድረግ፣ በመብል ሊጥለን የሚፈልግ ዲያብሎስ የመብል ፈተና ሲያቀርብለት “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም፤ ተብሎ ተጽፏል” (ማቴ. ፬፡፬) በማለት አሳፍሮ አሳይቶናል። ስለሆነም ስለ ምግብና ስለ ሆድ ማሰብ ሞት ነው። እንዲያውም ሆድ በሞላ ቁጥር አእምሮ የማሰብ አቅሙ እየቀነሰ ይሔዳል። አብዛኛዎቹ የዐለም ፈጠራዎች ችግርና ማጣት የወለዳቸው ናቸው። ሰው ሁሉም ነገር ከተሟላለት የማሰብም ሆነ የመሥራት ፍላጎት አይኖረውም።
የኢትዮጵያ አብዛኛው ሕዝብ ባለሥልጣናቱ እንደሚያወሩት የተመጣጣነ ምግብ የሚያውቅ፣ በቀን ሦስት ጊዜ የሚመገብ አይደለም። ነገር ግን ከሌሎች ጋር ተሳስቦና ተግባብቶ የመኖር ችግር የለበትም። የማሰብም ሆነ ውሳኔ የመስጠት ጉድለት የለበትም። እንዲያውም በተቃራኒው መርጠው የሚመገቡትና በተመጣጠነ ምግብ ሰበብ መብልን ሥራቸው ያደረጉ ሹማምንት የሚሰጡት ውሳኔ ነው አገር ሲያጠፋ የሚታየው። የሚመሩትን ሕዝብ ማወቅ፣ ያለበትንም የኑሮ ደረጃ መገንዘብ ብዙ ከመሳት ይጠብቃል። የአገር ዕድገት በመሪዎች ሀብትና ቅንጡ አኗኗር አይመዘንም። በኢትዮጵያ የተመጣጠነ ምግብ ያለው ትምህርት ቤት ከመምህራን አፍ፣ በቴሌቪዥን መስኮት ከዝግጅት አቅራቢዎች እና በዐደባባይ ከባለሥልጣናት ንግግር ብቻ ነው። በገጠሩ የሚኖረው ማኅበረሰብ ባለማግኘት፣ ያለውም ቢሆን ከመብል ጋር ያለው አስተሳሰብ ከመኖር ጋር ብቻ የተያያዘ ስለሆነ ስለ ተመጣጠነ ምግብ ጉዳዩ አድርጎ አያስብም፤ አይበላምም። ይህ የተሠራበት እሴት በሕይወቱ ላይ ያመጣበት ችግር የለም። ጾሙንም እንደ ጫና ሳይሆን እንደ በረከት የሚቆጥረው ተረድቶት ነው። ቤተ ክርስቲያን ያለ ጥናት እንደሚናገሩት አካላት የተመጣጣነ ምግብ መመገብን አትከለክልም። ማግበስበስን ግን ትጸየፋለች።
ይህን የምታስተምረው ደግሞ እንደ እንግዳ ደራሽ፣ እንደ ውኃ ፈሳሽ መሠረት የሌለው ሳይሆን ከአምላኳ የተቀበለችው፣ ከሐዋርያት የተረከበችው ነው። ጌታችን በወንጌል “ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ” (ዮሐ. ፮፡፳፯) በማለት ሰው ሊሠራ የሚገባው አላፊ ለሆነው ዐለም ምግብ ብቻ ሳይሆን የዘላለም ሕይወቱን እያሰበ እንዲኖር ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “መብል ለሆድ ነው፤ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል” (፩ኛ ቆሮ. ፰፡፰) በማለት ሆድም መብልም እንደሚጠፉ ነግሮናል። አብዝቶ መብላት መጠጣት ወደ ጥጋብና እግዚአብሔርን ወደ መርሳት ያደርሳል። “ይሹሩ ወፈረ፣ ረገጠ፤ ወፈረ፣ ደነደነ፣ ሰባ፤ የፈጠረውንም እግዚአብሔር ተወ፤ የመድኀኒቱንም አምላክ ናቀ” (ዘዳ. ፴፪፡፲፭) የሚለው የመጽሐፍ ቃል የሚያስረዳን ይህኑ ነው። ስለሆነም ስለ ሥጋ ማሰብ፣ ስለ መብልና መጠጥ ብቻ ማስብ “ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፣ ሊዘፍኑ ተነሡ” (፩ኛ ቆሮ. ፲፡፯) ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔርን መርሳትና ሞት ነው።