ባይተዋርነት እስከ መቼ? ክፍል ሁለት

ባይተዋርነት እስከ መቼ? ክፍል ሁለት

ባይተዋርነት እስከ መቼ? ክፍል ሁለት

በክፍል አንድ ጽሑፋችን ኦርቶዶክሳውያን በሀገራችን ባይተዋር ያደረጉንን ጥቂት ምክንያቶች ለማየት ሞክረናል፡፡ በዛሬው ጽሑፋችን ደግሞ ከዚህ ባይተዋርነት የመውጫ መንገዶችን ለመጠቆም እንሞክራን፡፡
1. ለሰማያዊ ክብር፣ ለዘላለማዊ ሕይወት የሚያበቃ መንፈሳዊ ዝግጅት ይኑረን፡- እንደ ቃሉ የምንኖር እምነተ ብርቱዎች እና ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በአግባቡ የምንካፈል መሆን አለብን፡፡ ይህ መንፈሳዊ ዝግጅት እንደ ጥንቶቹ ጽኑ ክርስቲያኖች በአሕዛብ ፊት ያለ ፍርሃት “እኛ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” የምንል የዐደባባይ ምስክሮቹ እንድንሆን ያበረታናል፡፡ “ልንሔድ ከክርስቶስ ጋር ልንኖር እንናፍቃለን” ለማለት ያበቃናል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጸመውን በደል ለመቃወም እና ፍትሕ ርትዕ ለመጠየቅ ብሎም ለማስፈን እንድንችል፣ የፍርሃትን መንፈስ ገድለን የኃይልና የሥልጣንን መንፈስ እንድንለብስ ያደርገናል፡፡
2. መከራን በአኮቴት እንቀበለው እንጂ አንልመደው፤
እንደ አንድ ክርስቲያን እንዴት ባለ አኗኗር እንኖር ዘንድ እንዲገባን መመሪያችን ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡ ቅዱሱን መጽሐፍ በሕይወታቸው የኖሩትን ቅዱሳን ሕይወት ደግሞ እንደ ወደብ ማኅቶት ከሩቅ እየተመለከትነው ወደ እዚያ እንቀዝፋለን፡፡ ይህን በራስ ፍላጎት ክብርን ፍለጋ ራስን ዝቅ በማድረግ ትሕትና እና ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም የመኖርን ጥበብ በረከት እያገኘንበት ልንቀጥል የምንችለው ግን የእውነት መንገድ በስፍራው እስካለ ድረስ ነው፡፡ ስለዚህ የተወረወረብንን ጦር፣ የተወነጨፈብንን ቀስት አድራሻ መለየት ግድ ይለናል፡፡ “የግል ሕይወቴን ሊፈታተን የመጣ መከራ ነው ወይስ የማምነውን እምነት ዝክረ ስም ለማጥፋት የተነቀነቀ ጦር?” ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ “የሚምዘገዘገው ጦር ዒላማ የሆንኩት እኔ እንደ አንድ ክርስቲያን በእምነቴ እየተፈተንኩበት ነው ወይስ መጭው ትውልድ እንደ ክርስቲያን እንዳይኖር የክርስትናን ዘር ለማጥፋት የታለመ ነው?” የሚለውን መመለስ ይገባናል።
ከላይ ላነሣነው ጥያቄ የምንሰጠው መልስ መከራው በአኮቴት የሚቀበሉት ነው ወይስ ጋሻ አንሥተው ሊመክቱት የሚገባ ነው የሚለውን ውሳኔ ለመስጠት ይረዳናል፡፡ ለክብር በአኮቴት የምንቀበለው መከራ ህልውናን ለሚፈታተን የበለጠ አሣር አሳልፎ እንዳይሰጠን ማስተዋል የተገባ ነው፡፡ እንደ ቀላል በሆደ ሰፊነት የምናልፋቸው ጥቃቶች ሌላ ጥቃት እየወለዱ ሰፊ መቃብር ውስጥ እየከተቱን እንደሆነ የሚታይ ነገር ነው፡፡
አንዱን ፍርሃት እና ታካችነት ተደራርበው የሰፈሩበት ሰው የከጓደኛው ጋር በተኛበት ሌሊት ጅብ ይመጣና እግሩን መብላት ይጀምራል፡፡ ጓደኛው ‹‹አረ ምንድን ነው የመጣብን?›› ብሎ እንዲነቃ ሲቀሰቅሰው፡፡ “ዝም በል ጅብ የእኔን እግር እየበላ ነው፤” ብሎ እየመጣ ያለውን መከራ ረስቶ እንዲያንቀላፋ መከረው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ምክር ራስን የማዳኛውን ጊዜ ቆርጥሞ የሚበላ ከፍርሃት እና የአጥቂህን አልጠግብ ባይነት ካለማወቅ የሚወለድ ከንቱ ምክር ነው፡፡
ኦርቶዶክሳውያን እየሆነብን ያለውን መከራ ለምደነዋል፤ ወይም በኦርቶዶክሳውያን ሕይወት ላይ የተቃጣው ዱላ ዳር ሀገር ባሉት ወገኖቻችን ትከሻ ላይ ብቻ የሚበርድ መስሎናልና በምን ግዴ ቸል ብለነዋል፡፡ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ተዘንግቶ፣ አንዱ በእምነት ለሚመስለው ወንድሙ መቆምን ትቶ ነገዳዊ ውግንናን መሰባሰቢያ ማንነታችን አድርገነዋል፡፡ ሰዎኛው የዘውግ ፖለቲካ ከአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ሴራ ጋር ተጋምዷል፡፡ ለዘመናት የተሠራንበት የክርስትና ሥሪት ነገዳዊ ዘውገኝነትን መቋቋም አቅቶት ወደ ፍርስራሽነት ከተቀየረ አዲሱ ትውልድ በክርስትና መርሕ እና እሴቶች ታንፆ የማደግ ዕድሉም አብሮ ይፈራርሳል፡፡ ይህም የኢትዮጵያችን እስትንፋስ ሆኖ የኖረውን የክርስትና ሐረግ የሚበጠስ ነው፡፡
3. የኦርቶዶክሳዊነት ጋሻ ለመሆን ዝግጁ የሆነ ሥነ ልቡና ያስፈልጋል፡፡ በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል እግዚአብሔርን በማምለክ የኖሩ አበው እና እማት ልጆች ነን፡፡ ገና በክርስትና የጧት ዘመናት ከሕገ ኦሪት በጃንደረባው ቅዱስ ባኮስ በኩል ‹‹የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?›› በማለት የመንፈስ ቅዱስን ምሪት ጠይቃ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ በማለት ጥምቀትን የተቀበለች ሀገር ዜጎች ነን፡፡ ክርስትናን በመቀበል እና ብሔራዊ ሃይማኖት አድርገን በማወጅ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ነን፡፡ ዛሬ ይህ ሁሉ በኢትዮጵያ ምድር እንኳን በእውን ሲተገበር በታሪክ ዓምድ ላይ ተጽፎ እንዲቀመጥ የተፈለገ አይመስልም፡፡ ይህን የጠላት ሐሳብ ለመዋጋት የተዘጋጀ ኦርቶዶክሳዊ መሆን ይጠበቅብናል፡፡
4. ዓለምን በንቃት መከታተል፤ የመልክዐ ምድራዊ ፖለቲካ እና ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተጽእኖ የሚገመግም የሁነት ትንተና የሚሠራ ክፍል (ዲፓርትመንት) እንዲኖር ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡ ይህ ክፍል ሁሉን አቀፍ ዓቅምና ቁርጠኝነቱ ያላቸው የቤተ ክርስቲያኗ ልጆች የሚሳተፉበት፣ አስፈላጊው የሰው ኃይልና ሀብት የተሟላለት ሊሆን ይገባል፡፡ በአዎንታዊ ዕድሎች ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ትልእኮ ስኬት መጠቀም የሚቻልበትን፣ አሉታዊ ለውጦችን የተጽእኖ አድማስ ማዳከም የሚቻልበትን ምክረ ሐሳቦች በጥናት ተመሥርቶ ያቀርባል፡፡
5. ዓለም አቀፍ ትኩረት ለማግኘት መሥራት፡- ኦርቶዶክሳውያንን ዒላማ ያደረገ እና የተራዘመ ጥቃት መኖሩን ማሳወቅ፤ በክርስትናችን ምክንያት ለጥቃት መጋለጣችንን በኦርቶዶክሰዊያን ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ይመለከተዋል ለሚባል ተቋም በማማረጃ አስደግፎ ማሳየት ተገቢ ነው፡፡