፲፪ኛው የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የአቋም መግለጫ

በኢ/ኦ/ተ/ቤ የሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ የዓለም አቀፍ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት ፲፪ኛው ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ከግንቦት 26-27 ቀን 2015 ዓ.ም ተከናውኖ
በቀረቡ ሪፖርቶች፣ ጥናታዊ ሰነዶች፣ ከሁሉም አካባቢዎች ከቀረቡ የውይይት ግብዓቶች በመነሳት ባለ አስራ አንድ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።

1.  በ12ኛው ጠቅላላ ጉባኤ የቀረበውን ሪፖርትና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ተቀብለን አጽድቀናል ለትግበራው በጋራ እንሰራለን፡፡
2.  ከጠቅላይ ቤተክህነት ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ ሀገር አቀፍ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እስከ አጥቢያ ሰ/ት/ቤት የቀረበውን የአደረጃጀት መዋቅር በጥልቀት ገምግመናል፡፡በጉባኤው የተሰጡ ማስተካከያዎችን በማካተት ወደ ስራ እንዲገባ ወስነናል፡፡
3.  የሥርዓተ ትምህርት መጻሕፍትን ለማሳተም የበጀት እጥረት እንዳለ ተገንዝበናል፡፡ይህንን ከቅዱስ ሲኖዶስ እስከ ሀገረ ስብከት ያሉ የቤተክርስቲያን መሪዎች በመገንዘብ ለሕትመቱ ተዘዋዋሪ በጀት/Revolving budget/ እንዲፈቀድና የተዘጋጁ መጻሕፍት ወደ ሕትመት እንዲገቡ በየደረጃው ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ እንዲቀርብና ክትትል እንዲደረግ በአጽንዖት እንጠይቃለን፡፡
4.  ሀገሪቱ ላይ በሚከሰቱ የተለያዩ አለመግባባቶች ምክንያት ያለ እዳዋ እዳ የተሸከመችው ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን በአቢያተ ክርስቲያኗ ላይ የሚደርሰው መቃጠልና መዘረፍ በምእመናን እንዲሁም በሰንበት ት/ቤት ወጣቶቻችን ላይ የሚደርስ የህይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደልና መሳደድ እንዲቆም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እንጠይቃለን፡፡
5.  በተለያ ምክንያት የቤተ ክርስቲያንን መምህራንና አገልጋዮችን ማሰር እንዲቆም የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ እንጠይቃለን፡፡
6.  የቤተክርስቲያናችን አንድነት ተጠብቆ ምዕመናን ከመደናገር ወጥተው ሥርዓተ አምልኮ በነጻነት መፈጸም ይችሉ ዘንድ ይቅርታና ሰላምን ሲያስተምሩ የኖሩ የትግራይ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳትና የአስተዳደር አካላት ለቤተክርስቲያ አንድነትና ለምዕመናን ሲሉ ወደ ውይይትና ይቅርታ እንዲመለሱና ቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ በልጅነት መንፈስ እየጠየቅን ቅዱስ ሲኖዶስና በአንጻራዊ ሰላም ውስጥ ያለው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር በትግራይ በተፈጠረው ጦርነት ለተፈጠረው ችግር ተገቢውን ድጋፍ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ እንጠይቃለን፡፡
7.  በቃለ አዋዲ የተደነገገው የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ አደረጃጀት ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን በቀር እየተተገበረ አለመሆኑ በቤተክርስቲያን አስተዳደራዊ ሂደት ላይ ክፍተት እንደፈጠረ በጉባኤው በጥልቀት ተነስቷል፡፡ስለሆነም ከወረዳ ቤተክህነት እስከ ጠቅላይ ቤተክህነት ድረስ በቃለ አዋዲው መሰረት የካህናት፣የምዕመናን እና የሰንበት ት/ቤት አባላት ተሳትፎ እንዲከበር በታላቅ አጽንዖት እንጠይቃለን፡፡
8.  ሥርዓተ አምልኮ ለመፈጸም፣ልጆች ወልዶ ለማሳደግና ተተኪ ትውልድ ለማፍራት ሀገር ያስፈልጋል፡፡በሀገር ውስጥም ሰላም ከሌለ ምንም ማከናወን አይቻልምና በመላው ሀገሪቱ በተቃርኖ የሚገኙ አካላት በሚያርጉት ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት ንጹሀን ዜጎች ሕጻናት፣ሴቶችና ካህናት ላይ የሚደርስ እንግልትና ጉዳት እየከፋ መምጣቱን በመገንዘብ ልዩነታቸውን በውይይትና በድርድር ብቻ እንዲፈቱ እንጠይቃለን፡፡
9.  ከሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮች በፍጹም ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን የሚመጥኑ ሆነው አላገኘናቸውም፡፡በመሆኑም ሲመቱ ሕገ ቤተክርስቲያንን፣ፍትሐነገሥትንና ቃለ አዋዲን ባከበረና ባከበረ መልኩ ብቻ እንዲደረግ በልጅነት መንፈስ እንጠይቃለን፡፡
10.  በቤተክርስቲያናችን የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አካላት ተጠንተው የሚቀርቡ የመፍትሔ ሀሳቦችን ቅዱስ ሲኖዶስ በምክረ ሃሳብነት እንዲቀበላቸውና በማዳበር እንዲተገበሩ አቅጣጫ እንዲሰጥ ከጠቅላይ ቤተክህነት ጀምሮ ያሉ የቤተ ክርስቲያን መዋቅር አካላት የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ያለምንም መሸራረፍ ተግባራዊ እንዲያደርግ በአጽንዖት እናሳስባለን፡፡
11.  በቤተክርስቲያናችን ውስጥ የሚስተዋሉ የአስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ሁሉ በመሳተፍና እንደ ቤተክርስቲያን ተተኪ ልጅነታችን የበኩላችንን ኃላፊነት በባለቤትነት መንፈስ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ባለዉ መዋቅር ትኩረት ሰጥተን የምንሠራ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ግንቦት 27 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ